ከሞት ጋር የሚደረግ ትንቅንቅ

የውጭ አገር ህክምና ማግኘት ከሚገባቸው ህሙማን መካከል የሚሳካላቸው ከ5 በመቶ በታች ናቸው 

           የገጠመውን የደም ካንሰር በሽታ በአገር ውስጥ ህክምና ለማዳን ባለመቻሉ፣ ወደ ውጭ አገር ሄዶ መታከም እንደሚስፈልገው የሚገልፀው የህክምና ማስረጃ እስኪሰጠው ድረስ ህመሙ ተስፋ አስቆራጭ አልሆነበትም ነበር፡፡ 

blood cancerየጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሃኪሞች ቦርዱ ፈርሞ በሰጠው ማስረጃ ላይ ህክምናውን በሁለት ወራት ውስጥ ማግኘት ካልቻለ በህይወት የመቆየት እጣ ፈንታው አጠያያቂ እንደሆነ በግልፅ ሰፍሯል፡፡ ሁኔታው እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ በቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን በአሁኑ ኢትዮ-ቴሌኮም ውስጥ ለአራት አመታት ሲሰራ ቆይቶ ድርጅቱ ባደረገው የአሰራር ለውጥ ሳቢያ ከስራቸው ከተፈናቀሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከስራው ከተፈናቀለ ወዲህ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው በሙያው በግል እየተሯሯጠ በሚያገኛት የዕለት ገቢ ነው፡፡ ገቢው ባለቤቱንና ሁለት ህፃናት ልጆቹን እንዳቅሙ ለማስተዳደር አስችሎታል፡፡ አልፎ አልፎ የሚሰማው ከባድ የህመም ስሜት እንዲህ እንዳሁኑ ዛሬ አልጋ ላይ ሳያውለው በፊት ሥራውን ለማስተጓጎልና ከቤት ለማዋል ሲታገለው እንደምንም እያሸነፈው ወደ ሥራው ይሄድ ነበር፡፡ የህመም ስሜቱን ለማስታገስና ስቃዩን ለመቋቋም የተለያዩ ማስታገሻ መድሃኒቶችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ቀስ በቀስ ህመሙ እየባሰበት ስቃዩ እረፍት እየነሳው ሲሄድ ወደ ሃኪም ቤት ለመሄድ ተገደደ፡፡ ህመሙ ከበድ ያለ በመሆኑ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄዶ መታየት እንዳለበት በተነገረው መሰረትም ወደ ሆስፒታሉ ሄዶ ምርመራ አደረገ፡፡ የምርመራው ውጤትም በሽታው ሥር የሰደደና በአገር ውስጥ ህክምና ሊድን የማይችል የደም ካንሰር ህመም መሆኑ ተነገረው፡፡ በሁለት ወራት ውስጥ ህክምናውን ማግኘት ካልቻለ ህይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅም የሆስፒታሉ የህክምና ቦርድ አረጋገጠለት፡፡ ለዚህ ህክምና ከ120 ሺህ ዶላር በላይ ያስፈልገዋል ተባለ፡፡ ፋሲል ይህንን መርዶ ከሰማ ቀን ጀምሮ እንቅልፍ ይሉ ነገር በአይኑ እንዳልዞረ አጫውቶኛል፡፡ አሁን በቀን አምስት መቶ ብር እየከፈለ ለእርዳታ ማሰባሰቢያነት በሚጠቀምበት ሚኒባስ መኪና ውስጥ ተኝቶ ለሞት የቀሩትን ቀናት ይቆጥራል፡፡ ከመኪና ኪራይ፣ ከእርዳታ ጠያቂቁው ሰው ዕለታዊ ክፍያና ከልዩ ልዩ ወጪዎች የሚተርፈውን ጥቂት ገንዘብ ለመድሃኒቶች መግዣና ለዕለት ወጪው እንደሚያውለውና ወደ ውጭ አገር ሄዶ የመታከም ተስፋው እንደጨለመም ነግሮኛል፡፡ ወደ ውጭ አገር ሄዶ አለመታከሙ ከሚፈጥርበት ስጋት ይልቅ ለሞት የቀሩትን ቀናት መቁጠር ይበልጥ እንደሚያስጨንቀውም አልደበቀኝም፡፡ 


የፋሲልን አይነት እጣ ፈንታ ገጥሟቸው በመኖርና ባለመኖር፣… በህይወትና በሞት፣ ለመኖር በመጓጓትና ለሞት በሚደረግ ጉዞ ሰቀቀን ውስጥ ሆነው ለወገኖቻቸው የድረሱልን ጥያቄ የሚያስተጋቡ ወገኖች እየተበራከቱ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ለውጭ አገር ህክምና ገንዘብ ለማግኘትና ለከፋ ህመምና ስቃይ ከዳረጋቸው ህመም ለመገላገል እጅግ በመጓጓት፣ የወገኖቻቸውን እርዳታና ድጋፍ ፍለጋ ደጅ መጥናታቸው በከተማችን የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ 


በህይወት በመኖርና ባለመኖር ከባድ ፈተና ውስጥ ወድቀው ከህመም ስቃያቸው ጋር እየታገሉ ለመኖር በመጓጓት፣ በሰቀቀን ውስጥ ሆነው ለወገኖቻቸው የድረሱልኝ ጥሪያቸውን ከሚያስተጋቡት እጅግ በርካታ እርዳታ ጠያቂዎች መካከል ያሰቡት ተሳክቶላቸው፣ ለህክምናቸው የሚያስፈልጋቸውን ወጪ አሟልተው ከህመማቸው የሚፈወሱና ከስቃያቸው እፎይታን የሚያገኙት እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ እርዳታ ጠያቂ ህሙማን፤ በገንዘብ ማጣት ምክንያት በጊዜ መታከም ያልቻለ ህመማቸው ሥቃያቸውን እያበረታ፣ ወደ ሞት የሚያደርጉትን ጉዞ ሲያፋጥነው ማየቱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡


በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ፍቃዱ ተስፋዬ እንደሚናገሩት፤ በአገር ውስጥ ህክምና መዳን በማይችሉ የጤና ችግሮች ተይዘው የውጭ ህክምና ማግኘት ካለባቸው ህሙማን መካከል ህክምናውን አግኝተው ለፈውስ የሚበቁት ከ5 በመቶ በታች ናቸው፡፡ ባለሙያው እንደሚገልፁት፤ አብዛኛዎቹ ህሙማን ለህክምና የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ማሟላት ባለመቻላቸው ምክንያት ለከፋ ሥቃይና ሞት ይዳረጋሉ፡፡ በውጭ አገር ለሚደረገው ህክምና የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ገንዘቡን በእርዳታና መሰል ሁኔታዎች አሟልቶ ህክምናውን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን የሚጠቁሙት ዶክተሩ፤ ይህም ህሙማኑ በእርዳታ የሚያገኙትን ገንዘብ ለውጭ አገር ህክምናው ለማዋል ከማሰብ ይልቅ ለዕለት ተዕለት ኑሮአቸው መደጎሚያና ለሚያሰቃያቸው ህመም ማስታገሻ የሚሆኑ መድኃኒቶች መግዣ እንዲውል በማድረግ፣ ዕለተ ሞታቸውን ይጠባበቃሉ ብለዋል፡፡ በየቤታቸው የሚበሉትና የሚቀምሱት የሌላቸውና በአገር ውስጥ ህክምና ሊድኑ በማይችሉ ከባድ የጤና ችግሮች ለተያዙ ህሙማን፤ በመቶ ሺዎች ዶላር የሚያስወጣ ህክምና በውጪ አገር ማድረግ እንደሚስፈልጋቸው መንገር ለህሙማኑ ተረት ተረት እንደማጫወት ነው የሚሉት ዶክተሩ፣ ህሙማኑ ይህን ያህል ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበት አንዳችም ተስፋ የሌላቸው በመሆኑ፣ ከህመሙ በላይ የሚጎዳቸው “መቼ ይሆን የምሞተው” የሚለው ሃሳብና ጭንቀት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በስፋት ከሚታዩት የውጭ አገር ህክምና የገንዘብ እርዳታ ጠያቂዎች መካከል፣ ከ92 በመቶ በላይ የሚሆኑት ገንዘቡን አግኝተው በመታክም ከህመማቸው የመፈወስ እድል እንደሌላቸው ያመኑና በእርዳታ በሚያገኙት ገንዘብ ህይወታቸውን ለማቆየት የቆረጡ ናቸው ብለዋል፡፡ 


የልብ ህመም፣ የኩላሊት ድክመት (ከአገልግሎት ውጪ መሆን) ካንሰር፣ የአንጎል እጢና የአዕምሮ ህመሞች በአብዛኛው በአገር ውስጥ ህክምና ማዳን ባለመቻሉ የውጭ አገር ህክምናን የግድ የሚሉ የጤና እክሎች መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተሩ፤ እነዚህ የጤና ችግሮች በአሁኑ ጊዜ የበርካታ ኢትዮጵያዊያን ፈተናዎች እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡ “አሳሳቢው ጉዳይ በእነዚህ የጤና ችግሮች ተይዘው የወገኖቻቸውን የእርዳታ እጅ ከሚጠባበቁት ህሙማን መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡ 
እነዚህ ወጣቶች በህይወት የመኖርና ያለመኖር ፍጥጫና ጉጉት ውስጥ ሆነው፣ ከህመማቸው ለመዳን ብቻ ሳይሆን ለጥቂት ቀናት በህይወት ለመቆየት የወገኖቻቸውን የእርዳታ እጆች ጠባቂ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየን ነገ አገር ተረካቢ ይሆናሉ የምንላቸውን ወጣቶቻችንን በቀላሉ ሊድኑ በማይችሉ በሽታዎች እያጣናቸው መሆኑን ነው” ሲሉ ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡ 


ዛሬ ዛሬ በመዲናችን የተለያዩ አካባቢዎች በብዛት የሚታዩት የውጭ አገር ህክምና ፈላጊ የእርዳታ ጠያቂዎች፤ ለህክምናው አስፈላጊ የሆነውን ገንዘብ ከማግኘታቸው በፊት ህይወታቸው እንደሚያልፍና በእርዳታ የሚሰበሰበው ገንዘብ የህክምና ወጪውን ለመሸፈን የማይበቃ መሆኑን ባደረጉት ጥናት ማረጋገጣቸውን ዶክተር ፍቃዱ ይገልፃሉ፡፡ 

Source: .addisadmassnews

1 COMMENT

  1. በሰለጠነው ሀገርም የተሻለ የህክምና መሳሪያ ስላለ ነው እንጂ ሁሉንም አይነት የካንሰር በሽታ አክመው ማዳን አይችሉም ።እድሜ ማርዘም ነው የሚምክሩት፣የእዚም በካንሰር ሰዎች ይምታሉ፣

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.