ልብ ያልተባለው የልብ ህመም!

ልብ ያልተባለው የልብ ህመም!ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የልብ ህመሞች በጉሮሮ ህመም ሳቢያ የሚከሰቱ ናቸው ልብ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራውን ካቆመ ደም ወደ አንጐላችን መድረስ አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ አንጐላችን ኦክስጅን እንዳያገኝ ያደርገዋል፡፡ የሰው ልጅ አንጐል ለ15 ሰኮንዶች ያህል ኦክስጅን ካላገኘ ህሊናን መሳት ይከተላል፡፡ አንጐላችን ከ10 ደቂቃ በላይ ኦክስጅን ካላገኘ ሞት ይከተላል፡፡ በዚህ መሠረታዊ የሰውነታችን አካል ላይ የሚደርስ ችግር በቀላሉ መፍትሔ ለማግኘት የሚችል ባለመሆኑ ለከፍተኛ አደጋና ሞት ያጋልጠናል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በልብ ህመም የተያዘ ሰው የቱንም ያህል ዘመናዊ ህክምና ቢያገኝም ህመሙን ሙሉ በሙሉ ማዳንና ወደቀድሞው ሁኔታ መመለስ አይቻልም፡፡ ይህ መሠረታዊ የሆነው የአካላችን ክፍል ምንም የህመም ምልክት ሳያሳየንና ጤነኛ መስሎን በድንገት በሚፈጥረው ችግር ህይወታችን ለአደጋ ይጋለጣል፡፡

ድንገተኛ ስለሆነው የልብ ህመም መንስኤዎች፣ ምልክቶችና ህክምናዎች አስመልክቶ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር ታረቀኝ ተስፋዬ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ የልብ ህመም በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት የሚታይና ለበርካቶች ድንገተኛ ሞት መንስኤ ሆኗል። አብዛኛዎቹ የልብ ህሙማን በሽታው እንዳለባቸው እንኳን ሳያውቁ በድንገት በሚፈጠር ችግር ህይወታቸው ሲያልፍ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህም ህብረተሰቡ ጤናውን ለመጠበቅና ያሉበትን የጤና ችግሮች አስቀድሞ በማወቅ ህክምናና ጥንቃቄ የማድረግ ልምድ እንደሌለው አመላካች ነው” የሚሉት ዶ/ር ታረቀኝ፤ የልብ ህመም ዓይነቶችን እንዲህ ይዘረዝሯቸዋል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት የልብ ህመም የሰለጠኑት አገራት የጤና ችግር እንደሆነ ይታሰብ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ችግሩ የድሃ አገራትም ዋንኛ አሳሳቢ ችግር መሆኑ አልቀረም፡፡ በሰለጠኑት አገራት ህዝቦች ላይ በስፋት የሚታየው የልብ በሽታ ከሚፈለገው በላይ ቅባት ያላቸውን ምግቦች በመመገብ የሚከሰተው የልብ ህመም ሲሆን ይህ ችግር ዛሬ ዛሬ እንደአገራችን ባሉ የድሃ አገራትም የሚከሰት ሆኗል፡፡ በአገራችን ከቅባት ምግቦች ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የልብ ህመም ከገጠር ይልቅ በከተማ የሚኖሩ ህዝቦችን ያጠቃል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም የከተሜው ህዝብ የሰለጠኑት አገራትን የአኗኗር ዘይቤ የሚከተል በመሆኑና በአመጋገብ ባህሉ ላይ ለቅባትና ለጣፋጭ ምግቦች ቅድሚያ ስለሚሰጥ እንደሆነም ዶ/ር ታረቀኝ ይገልፃሉ፡፡ ሌላው በአገራችን በስፋት የሚታየው የልብ ህመም በምች አማካኝነት የሚከሰተው ወይም በጉሮሮ ህመም ሳቢያ የሚፈጠረው የልብ ህመም ሲሆን ይህም ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የልብ ህመም መንስኤ ነው፡፡ ዶ/ር ታረቀኝ እንደሚገልፁት፤ በርካታ የልብ ህመም አይነቶች በአገራችን የሚታዩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት በስፋት የሚከሰቱና በጣም የተለመዱ ናቸው፡፡

በዘር አማካኝነት የሚከሰት የልብ ህመም፡፡ ወይንም ከውልደት ጀምሮ የሚፈጠር የልብ ህመም ይህ አይነቱ የልብ ህመም ችግሩ ካለባቸው እናትና አባት የሚወለዱ ልጆች ላይ ይስተዋላል። የልብ ህመም ችግር ያለባቸው ወላጆች በተለይም ወላጅ አባት በሽታውን ወደ ልጁ ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ ከውልደት ጀምሮ የልብ ህመም የሚኖራቸው ህፃናት ችግሩ በእናታቸው ማህፀን ውስጥ ሳሉ የደረሰባቸው ሊሆንም ይችላል፡፡ በእርግዝና የመጀመርያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ በሚወሰዱ መድሃኒቶችና በጨረር ህክምና ሳቢያ በጽንሱ ላይ በሚፈጠር ችግር ህፃናት ከልብ ህመም ጋር ሊወለዱ ይችላሉ፡፡ በቶንሲል ወይም በጉሮሮ ህመም ሳቢያ የሚከሰት የልብ በሽታ ለዚህ በሽታ ዋንኛው መንስኤ ስትሬፕቶኮከስ የሚባለው ባክቴሪያ ሲሆን እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ህፃናት ላይ በስፋት ይታያል፡፡ ባክቴሪያው ወደ ሰው አካል ውስጥ ከገባ በኋላ በቅድሚያ በጉሮሮ አካባቢ ህመምን ይፈጥራል – ታማሚው የህክምና እርዳታ አግኝቶ ከህመሙ ካልተፈወሰ ባክቴሪያው የልብ በሽታን ሊያስከትልበት ይችላል፡፡

በሀገራችን ውስጥ ከሚታየው የልብ ህመም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚከሰተው በጉሮሮ ህመም ሳቢያ ነው፡፡ የልብ ምት መዛባትና የልብ የደም ቧንቧ መጥበብ ልባችን በተለያዩ ምክንያቶች ተግባሩን በአግባቡ ለመከወን ሲቸገር ወይንም ሥራውን በትክክለኛው ሁኔታ መሥራት ሲያቅተው የልብ ምት መዛባት ይፈጠራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የልብ የደም ቧንቧ ጥበት በሚከሰትበት ጊዜ ልባችን ወደተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች የሚያሰራጨው ደም በአግባቡ ሊደርስ ስለማይችል፣ ለከፍተኛ ጉዳትና ለሞት ይዳረጋል፡፡ የልብ ደም ቧንቧ ጥበት በአብዛኛው የሚከሰተው የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ነገሮችን አብዝቶ በመመገብ ሲሆን በአገራችን ከቶንሲል ህመምና ከደም ግፊት ቀጥሎ በሶስተኛነት ደረጃ ለልብ ህመም መፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በደም ግፊት፣ በስኳር ህመም ሳቢያ የሚከሰት የልብ ህመም በደም ግፊት ሳቢያ የሚከሰተው የልብ ህመም በአገራችን በስፋት የሚታይና ብዙዎችን ለጉዳት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ በቁጥጥር ሥር ያልዋለ የደም ግፊት፣ በልብ ጡንቻዎች ላይ ጫናን በመፍጠር ልብ በአግባቡ ሥራውን እንዳያከናውን ያደርገዋል፡፡ የደም ግፊት ለልብ ተጨማሪ ጫናን በመስጠት ልብ ከአቅሙ በላይ ሸክም እንዲሸከም ያደርገዋል፡፡ ይህም ተጨማሪ ሸክምም፣ ልብ ጡንቻ እንዲያወጣ ያደርገዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ልብ የተሸከመው ሸክም ከአቅሙ በላይ ስለሚሆንበት እየደከመና ሥራውን በአግባቡ መሥራት እየተሳነው ይሄዳል፡፡ የስኳር ህመም የልብ በሽታን ከሚያስከትሉ በሽታዎች አንዱ ነው፡፡

በቁጥጥር ሥር ያልዋለ የስኳር ህመም ከአስር ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የልብ ህመምን ያስከትላል። አንድ የስኳር ህመምተኛ ስኳሩን ቢቆጣጠርና ተገቢውን ህክምናና መድሃኒት በአግባቡ ቢወስድ የልብ ህመም መምጫ ጊዜውን ሊያራዝመው ይችላል፡፡ የስኳር ህመም ያለበት ሰው በልብ በሽታ መያዙ አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ውፍረት ለተለያዩ የጤና ችግሮች ከሚያጋልጡ ጉዳዮች ዋንኛው ነው፡፡ ከእነዚህ የጤና ችግሮች መካከልም የልብ በሽታ አንዱ ነው። ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለስኳር፣ ለደም ግፊት፣ ለኮሌስትሮል (የደም ቅባት መጠን መብዛት) በሽታዎችም ያጋልጣል፡፡ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለዕድሜ ለልብ በሽታ መጋለጥ ምክንያት ይሆናል፡፡ አንድ ከትክክለኛው የውፍረት መጠን በላይ ያለ ሰው ወይም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ይታይበታል ተብሎ የሚታሰብ ሰው ከሌላውና ጤናማ ክብደት ካለው ሰው በበለጠ ለልብ ህመም ይጋለጣል፡፡ ኤችአይቪ/ኤድስና የቲቢ በሽታዎች ኤችአይቪ ኤድስ እና የቲቢ በሽታዎች የልብ ህመምን ያስከትላሉ ከሚባሉ በሽታዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ኤችአይቪ ኤድስ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም በማዳከምና ጡንቻዎቻችንን በማጥቃት የልብ ህመም እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።

የቲቢ በሽታ ደግሞ የልብ መሸፈኛ የሆነውን አካል በማጥቃት ውሃ እንዲጠራቀምና ልብ በአግባቡ ሥራውን ለማከናወን እንዳይችል ያደርገዋል፡፡ ይህም የልብ ህመምን ያስከትላል፡፡ የልብ ህመም ምልክቶች አንድ ሰው በልብ ህመም መያዙን የሚያመለክቱ የተለያዩ ምልክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች እንዲየሰውየው በሽታን የመከላከል አቅምና የሰውነት መዳከም በግልጽ ሊታዩም ላይታዩም ይችላሉ፡፡ የልብ ህመም ያለባቸው ሰዎች በአብዛኛው ከሚያሳይዋቸው ምልክቶች መካከል:- የትንፋሽ ማጠር፣ የልብ ምት መፍጠን ተንጋሎ ለመተኛት (በጀርባ ለመተኛት) መቸገር የእግር ማበጥ የፊትለፊት ደረት ውጋት…ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች በአብዛኛው የልብ በሽተኞች ላይ ተደጋግመው የሚታዩ በመሆናቸው ምልክቶቹ በታዩ ጊዜ በአፋጣኝ ህክምና ማግኘት እንደሚገባም ዶ/ር ፍቅረማርያም ይናገራሉ፡፡ የልብ ህመም ሊድን የማይችል በሽታ እንደመሆኑ ተገቢው ህክምናና ክትትል ካልተደረገለትም በድንገት ለህልፈተ ህይወት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች ስለበሽታው ምንነትና ስለምልክቶቹ ባለማወቃቸው ምክንያት ህክምናም ሳያገኙ ህይወታቸው አደጋ ላይ ሲወድቅ ይስተዋላል፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድ ምልክቶቹ በታዩ ጊዜ ወደ ሐኪም ዘንድ በመሄድ ተገቢውን የህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የልብ ህመም በአገራችን በዘመናዊ መሣሪያዎች በታገዘ ሁኔታ ህክምና የሚደረግለት መሆኑን የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በአብዛኛው ህክምናው ውስብስብና እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን የሚጠይቅ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ለልብ ህሙማን ከሚደረጉት ህክምናዎች መካከል ፈሳሽን ከሰውነት ውስጥ የማስወገድ ህክምና፣ የደም ቧንቧና የጠበቡ የልብ በሮችን የማስፋት ህክምናዎች፣ የልብ ተከላና ዝውውር ህክምናዎች ጥቂቶቹ እንደሆኑም ዶክተሩ አክለው ገልፀዋል፡፡ ልብ ሣንላቸው ቀርተን ህይወታችንን ለከፋ አደጋዎች ከሚያጋልጡት ችግሮች መካከል አንዱ የሆነውን የልብ በሽታ ልብ ልንለውና ትኩረት ልንቸረው እንደሚገባንም ዶክተሩ አሳስበዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.