የፋሲካ አመጋገባችን እንዴት ነው?

የፋሲካ አመጋገባችን እንዴት ነው?

የፋሲካ አመጋገባችን እንዴት ነውተልባ የጨጓራን መላጥ ይከላከላል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው በዓላት አንዱ በሆነው የፋሲካ በዓል ዋዜማ ላይ እንገኛለን፡፡ በዓሉ ከአምሣ አምስት ቀናት ፆም በኋላ የሚከበር በአል እንደ መሆኑ አከባበሩም ከሌሎቹ በዓላት ለየት ባለ መልኩ ነው፡፡ አንጀታችን ለሁለት ወራት ገደማ በቅባትና በሥጋ ላይ ማዕቀብ ጥሎ እንደመክረሙ፣ በዕለተ ፋሲካ ድንገተኛ ለውጥ ሲደረግበት ሊቆጣ ወይም ተግባሩን ለመፈፀም ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳም በደስታ ልናከብረው ያሰብነውን በዓል በጭንቀትና በህመም ልናሣልፈው እንችላለን፡፡

ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በበዓላት ሰሞን ወደተለያዩ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ለህክምና ከሚመጡ ታካሚዎች መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚወስዱት ከበዓል አመጋገብ ጋር በተያያዝ በሚከሰቱ የአንጀትና የጨጓራ ችግሮች ጉዳት የደረሰባቸው ህሙማንና ከአልኮል መጠጥ ጋር በተገናኙ የተለያዩ ችግሮች ሣቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የምግብ አለመፈጨት ችግር በተለያዩ ጊዜያትና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚከሰት ችግር ቢሆንም በበዓላት ሰሞን ችግሩ ሰፋ ብሎ ይታያል፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ምህረት ተስፋው ሲናገሩ፤ “በበዓላት ቀናት አመጋገባችን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በመሆኑና ቅባትና በርበሬ የበዛባቸዉን ምግቦች አብዝተን የምንመገብ ስለሆነ እንዲሁም በአንድ ጊዜ በርካታ ምግቦችን ስለምንመገብ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አልኮልና ቡና አብዝቶ መጠጣት፣ ጭንቀት፣ የጣፊያ መቆጣትና በሆድ ዕቃ ውስጥ የአየር መከማቸት፣ የምግብ አለመፈጨት ችግርን ከሚያስከትሉ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የምግብ አለመፈጨት ችግር መኖሩን ከሚጠቁሙ ምልክቶች መካከል የሆድ መነፋት፣ የሆድ ህመም፣ ቃር፣ የአየር መብዛት፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣ ጨጓራ አካባቢ የሚሰማ የህመም ስሜትና፣ ግሣት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እኒህም በታማሚው ላይ ጭንቀትና ከባድ የህመም ስሜትን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ በበዓላት ወቅት የሚኖረንን የአመጋገብ ባህርይ ተከትሎ የሚከሰተውን የምግብ አለመፈጨት ችግር ለመፍታት ዋንኛ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ጉዳዮች ዶ/ር ምህረት እንዲህ ይዘረዝሯቸዋል፡፡ “በተለይ እንዲህ እንደ አሁኑ አንጀታችን ከሥጋና ከቅባት ምግቦች ለወራት ታቅቦ ከቆየ በኋላ፣ ሣናለማምደው በድንገት ቅባትና በርበሬ የበዛባቸውን ምግቦች ስንመገብ ህመሙ በቀላሉ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ስለዚህም ቅባት የበዛባቸዉን ምግቦች በተቻለ መጠን መቀነስ፣ በአንድ ጊዜ ብዙ አለመመገብ፣ ቀበቶን አጥብቆ አለማሰር የምግብ መፍጨት ሥርዓቱ የተስተካከለና ጤናማ እንዲሆን ያግዛል፡፡ “የምግብ አለመፈጨት ችግርን ያግዛሉ ተብለው በህክምናው ዘርፍ ከሚታመንባቸው መድሃኒቶች ይልቅ ከላይ በዝርዝር የተገለፁት ነገሮች ችግሩ እንዳይከሰት፣ ከተከሰተም ለከፋ ችግር እንዳይዳርግ ሊከላከሉ የሚችሉ ናቸውና አዘውትረን ልንጠቀምባቸው ይገባል” ዶክተር ምህረት ይመክራሉ፡፡ በፆም ፍቺ ወቅት ቅባት ነክ ምግቦችን ከመመገባቸው ወቅት አንዳንድ ሰዎች ተልባ ወይንም አብሽ ይጠጣሉ፡፡ ይህም ጨጓራቸው የሚሰጠውን ምግብ በአግባቡ ለመፍጨት እንዲችል ለማዘጋጀት እንደሚረዳቸውም ይናገራሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክተው ዶክተር ምህረት ሲናገሩ፤ “ነገሩ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የተለመደና ተዘውትሮ የሚፈፀም ጉዳይ ነው፡፡

በህክምናው ረገድም ጠቀሜታ ያለው ነገር እንደሆነም ይታመናል፡፡ በተለይ ተልባ በውስጡ የሚዝለገለግ ነገር ስላለውና ይህ ዝልግልግ ነገር በጨጓራው ውስጠኛው ክፍል ገብቶ መላጥ እንዳያስከትል ይከላከላል” ብለዋል፡፡ ሌላው ከበዓላት ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የጤና እክል ደግሞ አልኮል አብዝቶ በመጠጣት የሚፈጠር ችግር ሲሆን እንደ ፋሲካ ባሉ ታላላቅ በዓላት የአልኮል መጠጥ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የተለመደ በመሆኑ አልኮል በጨጓራ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ የማቅለሽለሽ ስሜት እንደሚፈጥር ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡ ጉበት አልኮሉን ለማብላላት በሚያካሂደው እንቅስቃሴ የደም ስኳሩ መጠን ስለሚቀንስ በግለሰቡ ላይ የድካም ስሜት እንዲፈጠርና ሰውነቱ እንዲዝል ያደርገዋል፡፡

አልኮል አብዝተው የጠጡ ሰዎች ራስ ምታት፣ አፍ መድረቅ፣ ድካም፣ ትኩሣት፣ ማስመለስና ተቅማጥ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች ውሃ አብዝተው በመጠጣት ናርኮቲክ መድሃኒቶችን በመውሰድና በቂ እረፍት በማድረግ ችግራቸውን ሊያስወግዱ እንደሚችሉ ዶ/ር ምህረት ይገልፃሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ብዙ መጠጥ ጠጥተው ይህ አይነት ችግር ሲገጥማቸው ከህክምናው ይልቅ ተለምዶአዊ በሆነው ዘዴ ችግራቸውን ለማስወገድ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም የቲማቲም ጭማቂ መጠጣት፣ የሽሮ ፍትፍት መመገብና ውሃ አብዝቶ መጠጣት በህክምናው ዘርፍም የሚደገፍ ሲሆን ችግሩን ለማስወገድ ይረዳል እየተባለ የሚወሰደው ተጨማሪ የአልኮል መጠጥ ችግሩን ከማባባስ የዘለለ መፍትሔ እንደሌለው ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡ መጪውን በዓል በሠላም፣ በጤናና በደስታ እናከብረው ዘንድ ጤናችንን ከሚያጓድሉ ችግሮች መጠበቅ ግድ ይለናል፡፡ መልካም በዓል ይሁንልን!!

source- Addis Admas

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.