ወጣትነት፣ስርዐተ ጾታ እና ተዋልዶ፣ ጤና

ወጣትነት፣ስርዐተ ጾታ እና ተዋልዶ፣ ጤና

Planned Parenthood
Planned Parenthood

ሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ለስኬት የሚያበቁ አዲስ እዉቀት የመቅሰምን ክህሎት ይጠይቃሉ። የእኛ የወጣቶች የትምህርት አለም ስኬት የበለጠ የሚፈተነው ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስንሳተፍ ነው። ይሁን እንጅ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምንገባ ወጣቶች ሁሉ ይሳካልናል ማለት አይደለም። የከፍተኛ ትምህርት እድልን አግኝተን ከቤተሰቦቻችን እና ከመኖርያ አካባቢያችን ርቀን ወደ ትምህርት ተቋማቱ በምንሄድበት ጊዜ የቤተሰብ ናፍቆት እና  ከአካባቢዉ ጋር ቶሎ ያለመላመድ የመሳሰሉ ሁኔታወች በመጠኑም ቢሆን የመጀመርያ ችግሮቻችን ናቸው። የመማር ክህሎቶቻችን የሚፈታተኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግዳሮቶችም ብዙ ናቸዉ። በዚህ ላይ ደግሞ ወጣትነት የራሱ የሆነ አካላዊ፣ አእምሮአዊ እና ስሜታዊ ለዉጦች የሚንጸባረቁበት፣ ስሜቶቻችንን ወደ ተግባር ለመለወጥ ዉስጣዊ ግፊታችን የሚያይልበት ወቅት በመሆኑ ጊዜያዊ ስሜቶቻችን የተነሳንለትን አላማ  በአግባቡ እንዳናሳካ  መሰናክል ሊሆኑብን ይችላሉ።

በዚህ ወቅት የወደፊት ህይወታችንንና  ግባችንን መሰረት በጥንቃቄና በብልህነት ካላስቀመጥነው በስተቀር የነገው ማንነታችን በዛሬዉ በተንኮታኮተ መሰረታችን  እውን የማድረግ ተስፋችን ቅዠት ሆኖ ሊቀርብን ይችላል።

ይህን ከህይወት ዘመናችን በጣም አስደሳች የሆነ የወጣትነት ጊዜያችን በአግባቡ ልናሳልፈዉና የወደፊት የህይወት አቅጣጫችንን ልናስተካክልበት ይገባናል። በአንጻሩ ችኩልተኝነት እና የስሜት ተለዋዋጭነት ፣ በትምህርት ሁኔታወች ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እና የአቻ ግፊት እጅግ የሚጨምርበት ጊዜ ነው። እነዚህ ነገሮ ች ደግሞ  የእኛን ራእይ የሚያደበዝዙ ነገሮች ናቸው። ስለዚህም እኛ ወጣቶች ስለሚከተሉት ነገሮች አጥጋቢ እዉቀት ካለን እና ያወቅነውን ነገር በተግባር መፈጸም ከቻልን ካሰብንበት አላማ እና ግብ መድረስ የማያስችለን አንዳች ነገር ይኖራል ብየ አላስብም።

1 የአካዳሚክ/የትምህርት ስኬት እና እንቅፋቶችን ለይቶ ማወቅ

2 ስለ ወጣቶች ስርአተ ጾታ እና የተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ማወቅ

በዚህ ጽሁፌ ዉስጥ ስለ ወጣቶች ስርአተ ጾታ እና የተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያስጨብታል ብየ ያሰብኩትን ከተለያዩ ምንጮች በማሰባሰብ አቅርቤያለሁ። ምንም እንኳ ጽሁፌ ስለ ወጣቶች ይሁን እንጅ የማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል ይመለከታል። በዚህ የከፍተኛ ት/ት ተቋማት ተማሪወች ድህረ ገጽ ላይ አብዛኛው ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ወጣት ተማሪወች ስለሆንን ይበልጥ ትኩረት ለእኛ ለወጣት ተማሪወች ይሁን በሚል እሳቤ ነው የጽሁፌ ርእስ ስለ ወጣቶች ያደረግኩት።

መልካም ንባብ

የተዋልዶ ጤና

የተዋልዶ ጤና ማለት ከተዋልዶ ጤና ጋር ተያይዞ የተሟላ የአካል፣ የስሜት፣ የአእምሮ፣ እንዲሁም የማህበራዊ ጤንነት ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የበሽታ አለመኖር ወይም የመራብያ አካላት ተገቢውን የተግባር ሂደት መተግበር መቻልን ያካትታል። ከዚህ በተቃራኒ ሁኔታ የሚገኙ ነገሮች የተዋልዶ ጤና  ችግሮች ናቸው።

 ወሲባዊ ጤንነት

ወሲባዊ ጤንነት ማለት ሃላፊነት የሚሰማው፣ እርካታ ያለው፣ ጥንቃቄ የተሞላበት ማለትም ከበሽታ፣ ከጉዳት፣ ከጥቃት፣ ከአካል ጉድለት፣ ከአላስፈላጊ የህመም ስሜት ወይም ከሞት አደጋ ነጻ የሆነ ወሲባዊ ህይወት የሚገኝበት ማለት ነው።

ለወጣቶች የተዋልዶ ጤና ትኩረት መስጠት ለምን አስፈለገ?

        አብዛኞች ወጣቶች በወጣትነት የእድሜ ክልል ዉስጥ እያለን ለተለያዩ ችግሮች በተለያዩ ምክንያቶች እንጋለጣለን። ለእነዚህ ችግሮች በዋናነት የሚከተሉት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።

 • ስለ ስርአተ ጾታእና ተዋልዶ ያሉን መረጃወች ዉስን መሆን
 • የተፈጥሮ ሆርሞኖች በከፍተኛ መጠን በሰዉነታችን ዉስጥ እየተመረቱ ስለሚሰራጩ እና በባህርያችን እና በጸባያችን ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩ
 • የተለያዩ ነገሮችን የማወቅ፣ አዲስ ነገርን የመፈለግ ሁኔታችን ስለሚጨምር
 • የህይወት አቅጣጫችን የሚቀይሩ ብዙ ዉሳኔወችን የምናሳልፍበት ወቅት በመሆኑ
 • ማህበረሰቡ፣ አቻ ጓደኞቻችን እና የምንኖርበት አካባቢ ተጽእኖ ስለሚያደርጉብን እና ሌሎች መሰል ምክንያቶች ናቸዉ።

በወጣትነት ወቅት የሚከሰቱ ስሜታዊ እና ማህበራዊ ለውጦች

     በወጣትነት ወቅት ከሚከሰቱ አካላዊ ለውጦች በተጨማሪ ሌሎች የማህበራዊና ስሜታዊ ለዉጦች በእኛ ስሜት እና  ባህሪ ላይ አሉታዊና አወንታዊ ተጸእኖ አላቸው። ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ከአሉታዊ ለውጦች መካከል የሚመደቡ ናቸዉ።

 • ራሳችን ስለመቻል ማሰብና  ለራሳችን መወሰንን መሞከር ወይም መጀመር
 • ስለ  ወሲብ፣ አደንዛዥ እጾች፣ አልኮልና የሚያነቃቁ ነገሮችን የማወቅ እንዲሁም የመሞከር ጉጉታችን መጨመር
 • የአቻ ጓደኞቻችን ምክር ከቤተሰቦቻችን ምክር አስበልጠን መዉሰድ
 • ስለ አለባበሳችን፣ አነጋገራችን፣ ራሳችን መጠበቅ እና  መጨነቅ መጀመር፣ እንዲሁም ስለዉበታችን መጠንቀቅ
 • ፈጣን የሆነ የባህሪ መቀያየር መኖር (ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ መደበር፣ መደሰት፣ መጨነቅ ወዘተ)
 • የማህበረሰቡን ደንብ፣ ፈቃድና ህጎችን መጣስና በቤተሰብ፣ በአስተማሪና በአዋቂወች የተከለከሉ ተግባራትን ለመፈጸም መሞከር
 • በአካላዊ፣ ማህበራዊና ስሜታዊ ለዉጦች ምክንያት የሚፈጠሩ ፍላጎቶችን ጥቅምና ጉዳት የማመዛዘን እና የመረዳት ችሎታ አለመኖር

በወጣትነት ጊዜ በሴቶች እና በወንዶች ላይ የሚታዩ እውነታወች

          በወጣትነትጊዜ የሚከሰቱ አካላዊ፣ ስሜታዊ እና ማህበራዊ ለዉጦች ሁሉ ተፈጥሮአዊ ወይም የማይቀየሩ ናቸዉ። እነዚህ ተፈጥሮአዊ የሆኑ የለዉጥ ሂደቶች እንደየሰዉ የአመጋገብ እና የአኗኗር ሁኔታ ከአንዱ ወጣት ወደ አንዱ ወጣት ይለያያሉ።ከዚህ ከጥሎ የተዘረዘሩት ከልጅነት ወደ ወጣትነት የእድሜ  ክልል ስንገባ  የሚያጋጥሙን እዉነታወች ናቸው። እነዚህን እዉነታወች ማወቅ በወጣትነት ጊዜያችን ከሚያጋጥመን የመደናገጥ ስሜት እንድናለን።

 • ወንዶች ብልታቸው በቆመ ቁጥር በግዴታ የዘር ፈሳሽ ማፍሰስ ወይም ወሲ ብ መፈጸም አይኖርባቸውም
 • አንድ ወንድ ወጣት የዘር ፈሳሹን በተደጋጋሚ ቢያፈስም በሰዉነቱ ዉስጥ የሚገኘውን የዘር ፈሳሹን የሚያመርተው አካል በቀጣይነት ስለሚያመርት መጠኑ አይቀንስም ወይም ከምንጩ አያልቅም። ይህ ማለት ግን የዘር ፈሳሽን ያላግባብ ማፍሰስ አለበት ማለት አይደለም።
 • በአንድ ወጣት የዘር ማምረቻ  ዉስጥ ከተገቢው መጠን በላይ የወንድ የዘር ፍሬ ፈሳሽ አይጠራቀምም። የግብረ ስጋ  ግንኙነት ሳይደረግ ለብዙ ጊዜ ቢቆይም የጤና ችግር አይፈጥርም።
 • አንድ ወንድ በእንቅልፍ ልብ ዉስጥ ሆኖ የዘር ፈሳሽ የመፍሰስ ሁኔታ  ሊያጋጥመው ይችላል።ሆኖም ግለሰቡ ወሲብ ፈጽሟል ማለት አይደለም።
 • አንድ ወንድ የዘር ፍሬ  ፈሳሽ  በሚያፈስበት ጊዜ 500 ሚሊዮን የሚሆኑዘሮችን ይረጫል። ከነዚህ መሃል አንዱ የዘር ፍሬ ብቻ ከሴቷ የዘር ፍሬ ጋር ሲገናኝ እርግዝና  ሊፈጥር ይችላል።
 • ከሆርሞኖች ዉጭ የወንድን ብልት ሊያሳድግ የሚችል ነገር የለም። ለምሳሌ በተደጋጋሚ ወሲብ መፈጸም የወንድን ብልት አያሳድግም።
 • የአንዲት ወጣት ሴት ልጅ የሁለቱ ጡቶቿ መጠን ሊለያይ ይችላል።
 • ከሆርሞኖች ዉጭ ጡት ሊያሳድግ የሚችል ነገር የለም።የተለያዩ  ነገሮችን በመሞከር ለምሳሌ  የጡት ጫፍን በነፍሳት በማስነከስ ጡት ሊያድግ አይችልም። እንዲያዉም የጡት ጤንነትን ይጎዳል።
 • የሴት ልጅ ጡት በፊት ከነበረበት ቦታ ዝቅ ሲል ወሲብ ፈጽማለች ወይም ወልዳለች  ማለት ሳይሆን በመሬት ስበት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
 • አንዳንድ ጊዜ  መጠኑ ያልበዛ  ከጡት ጫፍ የሚወጣ ፈሳሽ ሊኖር  ይችላል።
 • ሴቶች በጡቶቻቸው አካባቢ መጠነኛ ጸጉር ሊኖር ይችላል ይህም መልካም ነው።
 • ወጣትም ሆኑ አዋቂ ሴቶች የጡት መያዣ በመጠቀም ጡት እንዳይወድቅ እና  ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ ይችላሉ። ይህም ለጡት ጤንነት ጠቃሚ ነው።
 •  የሴት ልጅ የጡት ወተት መመረት ወይም መዘጋጀት በጡት መጠን አይወሰንም።
 • ከሴት ብልት ዉስጥ የሚመነጭ ፈሳሽ በተለያዩ  ወርሃዊ ኡደቶች ወቅት ወይም ሴቷ የወሲብ ፍላጎቷ በሚነሳሳበት ወቅት ሊለያይ ይችላል። መጠኑም ይጨምራል።እንዲሁም በዉፍረት መጠን ሊለያይ ይችላል።
 • የወጣቶች አካላዊ ለውጥ መኖር፣ ወሲባዊ ፍላጎቶች መጨመር እና  ለወሲብ ብቁ መሆን ብቻ ከወሲብ ጋር ተያይዘዉ የሚከሰቱ ችግሮችን አስቀድመዉ የመገንዘብእና  የመጠንቀቅ አቅም ይኖራል ማለት አይደለም።

ከላይ የተዘረዘሩት እዉነታወች ሁሉም በማንኛውም ሰው ላይ ላይከሰቱ ወይም ሊከሰቱ ይችላሉ።

ጾታዊ ጥቃት(gender based violence)

       በአጭሩ ጾታዊ ጥቃት ማለት አንድን ግለሰብ ሴት ወይም ወንድ በመሆናቸው ማለትም ጾታን ብቻ መሰረት በማድረግ በግለሰቦች ስነ ልቦናዊና አካላዊ ጤንነት፣እድገት እና  ማንነት ላይ አሉታዊ ጉዳት የሚያደርሱ ማናቸውንም ተግባራት መፈጸምን ያካትታል።

ስለ ጾታዊ ጥቃቶች ስናነሳ ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን መገንዘብ ግድ ይላል።እነዚህም

ሰብአዊ መብት፣ ሃይል እና የመብት ጥሰት ናቸው።

1 ሰብአዊ መብት ስንል ሰወች ሰው በመሆናቸው ብቻ  ሊያገኙት የሚገባ መብት ሲሆን እነዚህ መብቶች ከሃገር ሃገር አይለያዩም።

2  ሃይል ሲባል ሰወችን በማስገደድ አንድ ነገር ያለፍላጎታቸው ተገደው እንዲያደርጉ ማድረግ የሚያስችል ገንዘብ፣ ስልጣን፣  መሳርያ፣ ጉልበት፣ እዉቀት ወዘተ የሚያጠቃልል ነው።

3 ጾታዊ ጥቃት የሰባዊ መብቶ ች ጥሰት ሲሆን ይህም ሃይልን በመጠቀም ያለግለሰቦች ስምምነት የሚፈጸም ነው።

ጥቃት በሁለት ጾታወች የሃይል አለመመጣጠን ሊፈጸም የሚችል ሲሆን ይህም በወንዶች እና  በሴቶች  አንዳንዴም በወንዶች መካከል (ለምሳሌ ግብረ ሰዶም)፣ ወይም በሴቶች መካከል ሊፈጸም ይችላል።

ጾታዊ ጥቃት አካላዊ (መደብደብ፣ በትህምርት ቤት እና  በቤት ዉስጥ የሚፈጸም ጥቃት፣ ቅሚያ ወዘተ)፣ ወሲባዊ (ለጾታዊ ጥቃት ማግባባት፣ ወሲባዊ ትንኮሳ፣ መድፈር ወዘተ)፣ ስነ ልቦናዊ (ዘለፋ፣ የቅጽል ስም መስጠት፣ ማስፈራራት፣ ማንቋሸሽ ወዘተ)፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ (የስራ ጫና) ሊሆን ይችላል።

ጥቃት የሚፈጸምበት ቦታ እና ፈጻሚወች

1 በተቋማት ዉስጥ

በአንዳንድ መምህራን፣ በአስተዳደር ሰራተኞች፣በተቋሙ ዉስጥ ለኮንስትራክሽን እና ለተለያዩ  ስራወች የተሰማሩ ግለሰቦች፣ ወንድ ተማሪወች፣ ሴት ተማሪወች፣የትምህርትቤት ዘበኞች….

2 ከግቢ ዉጭ

በአንዳንድ መምህራን እና ወንድ ተማሪወች፣ የትምህርት ቤት ጥበቃወች፣ ከትምህርት ቤት ዉጭ ያሉ ወንዶች፣ ዘመዶች፣ ጓደኞች፣ጎረቤቶች፣ ገንዘብ ያላቸው ወንዶች(sugar daddies)…

በቤት ዉስጥ

በአባት እና  እናት፣ በእንጀራ አባት እና  እናት፣ በ ትላልቅ እህቶች እና  ወንድሞች፣ በሌሎች የቤተሰብ አባላት፣ ዘመዶች የቤት ሰራተኞች፣ ዘበኞች፣ ጎረቤቶች እና በአካባቢው ያሉ ወንዶች፣  ወዘተ ናቸው። ሴቶች በአብዛኛው በሚያዉቋቸው ግለሰቦች እና  ጓደኞች ተጠቂ ሲሆኑ ወንዶች በማያዉቁት ግለሰብ የመጠቃት እድላቸው ሰፊ እንደሆነ  የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ወሲባዊ ጥቃት

      ወሲባዊ ጥቃት ያልተፈለገ ወሲባዊ አስተያየቶች መስጠት፣ ለወሲባዊ ብዝበዛ ሰወችን ማጓጓዝ፣ከአንድ ሰው ጋር ወሲብ ለመፈጸም ሃይል መጠቀምን የሚያካትት ሲሆን ድርጊቱም በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታ እና በሌላም ቦታ ሊሆን ይችላል።

ወሲባዊ ብዝበዛ ወይም ጥቃት በሁለት መንገድ ሊፈጸም ይችላል።

1 አንድን ግለሰብ የወሲብ ጥቅም ለማግኘት በገንዘብ፣ በመጠለያ፣ በምግብ ወይም ሌሎች ቁሳቁሶች በማቅረብ ወሲብ ለመፈጸም የሚደረግ ጾታዊ ጥቃት ነው(sexual exploitation)።

2 በማስፈራራት፣ ስልጣንን በመጠቀም፣ ግሬድን እንደ ቅድመ  ሁኔታ በማስቀመጥ ወሲባዊ ግንኙነት በሃይል/ ያለፍላጎት መፈጸምን ያካትታል።

ጾታዊ ጥቃት ከጽንሰት እስከ ሞት ባለው የህይወት ዘመን ሊፈጸም ይችላል።

ከዉልደት በፊት፦ ጾታን ለይቶ ማስወረድ፣ ለምሳሌ በምርመራ ቀድሞ  ጾታን በመለየት ሴት ከሆነች ማስወረድ።

ሴት ወይም ወንድ ልጅ ለመዉለድ አስቀድሞ መዘጋጀት እና ማርገዝ….

በልጅነት፦ አካላዊ፣ ወሲባዊ ኣና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች መፈጸም፣ የሴት ልጅ ግርዛት….

በልጃገረድነት፦ ያለድሜ ጋብቻ፣  አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ስነ ልቦናዊ ጥቃት፣ ወሲባዊ ብዝበዛ፣ ጠለፋ….

በጎልማሳነት፦  ወሲባዊ ብዝበዛ፣ ወሲባዊ ትንኮሳ፣ አስገድዶ መደፈር፣ ጠለፋ፣ ያለፍላጎት ማስረገዝ…

በእርጅና፦ የባል ወይም የሚስት ንብረት ለማግኘት አንድ ሰው ራሱን እንዲያጠፋ ማድረግ፣ አካላዊ፣ ወሲባዊ ኣና ስነ

ልቦናዊ ጥቃቶች

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዉስጥ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች

      በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዉስጥ በሴት ተማሪወች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች አይነታቸው ፈርጀ ብዙ ነው። እነዚህም የቃል እና የጽሁፍ ትንኮሳወች፣ ወሲባዊ ትንኮሳወች፣ አካላዊና  ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች ……..ሲሆኑ እነዚህም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዉስጥ የሚመደቡ ናቸው።

የሴት ተማሪወች ትምህርት መድገምና ማቋረጥ ተማሪወች እርስ በርስ እና ከተቀረው የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንዳንድ ጥናቶች ያመላክታሉ።

በሌላ በኩል በዩኒቨርስቲዎች አድሎአዊ አስተሳሰቦች እና ቅድሚያ ግምቶች በሴት ተማሪወች ላይ እንደሚሰጥ ተጠቁሟል። በአንድ ጥናት እንደተጠቆመዉ 8.2% የዩኒቨርስቲ ሴት ተማሪወች የዚህ አድሎአዊ አስተሳሰብ ተጠቂ መሆናቸው ተገልጿል።(ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር አለማየሁ 2003 ዓ.ም) እነዚህ አድሎአዊ አስተሳሰቦችም የሚከተሉት ናቸው።

 • እናንተ ሴቶች ከአንድ ሴሚስተር በኋላ ትባረራላችሁ/ትጫራላችሁ።
 • ኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ በጣም ይከብዳችኋል ወይም አትችሉትም።
 • እናንተ ምን አለባችሁ መምህሩን ጠብሳችሁ/ጓደኛ አድርጋችሁ ፈተና ማለፍ ትችላላችሁ።
 • ምን ታደርጉ ዩኒቨርስቲ ለእናንተ ምቹ ነው።

በአጠቃላይ ሴት ተማሪወች በዩኒቨርሲቲ የሚያጋጥሟቸዉ ጾታዊ ጥቃቶች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚከተሉት ናቸው።

 • ከአንዳንድ ነባር ተማሪወች የሚመጣ ተጽእኖ ሲሆን ይህም ሴት ተማሪወች ትምህርታቸው ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋል።
 • ለሴት ተማሪወች ያለው አመለካከት አድሎአዊ መሆንና የተሳሳቱ ቅድሚያ ግምቶች መኖራቸው።
 • ሴት ተማሪወች ዉጤታማ አይደሉም ብሎ ማሰብ። ይህ አስተሳሰብ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በሴት ተማሪወች ላይም መኖሩ።
 • አካላዊና  የቃል ትንኮሳወች፣ ጥቃቶች …. በወንድ ተማሪወች፣ በመምህራን፣ በአስተዳደር ሰራተኞችና በህብረተሰቡ መኖሩ።
 • ሴት ተማሪወች የምክር አገልግሎት የመጠቀም ልምድ አናሳ መሆን።
 • አስገድዶ መደፈር እና ወሲባዊ ብዝበዛወች ናቸው።

እነዚህን ጉዳዮች በሁለት ከፍለን ስናያቸው በመጀመርያደረጃ  በተቋሙ ዉስጥ የሚፈጸሙ እንደ አካላዊ የቃል ትንኮሳወች፣ በሴት ተማሪወች ትምህርት ብቃትና ዉጤታማነት ላይ አሉታዊ አስተያየቶች መኖራቸው ተጠቃሾች ናቸው። ይበልጥ ሴት ተማሪወች በአንዳንድ ስነ ምግባር በጎደላቸዉ መምህራን ግሬድን እንደ መሳርያ በመጠቀም ወሲባዊ ትንኮሳ እንደሚፈጸምባቸው ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ሴት ተማሪወች ከፍተኛ የስነልቦና ጫና እንደሚያድርባቸው በሚሰጡት አሉታዊ መልስ ዝቅተኛ ዉጤት ማምጣትና  ዛቻወችን፣ ማስፈራርያወችን በመፍራት ወሲባዊ ጥቃቶችን በመቀበል ለተዋልዶ  የጤና ችግሮችና ለኤች አይ ቪ ኤድስ መጋለጥን ያስከትላል።

በሁለተኛ ደረጃ ከተቋሙ ዉጭ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች በወንድ ተማሪወች፣ መምህራን እና ሌሎች ከዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ዉጭ ባሉ አካላት የሚፈጸም ሲሆን ይህም አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችን ይጨምራል። በአንዳንድ ዩኒቨርስቲወችም በገንዘብ እና በተለያዩ ስጦታወች በመደለል ወሲባዊ ብዝበዛ የሚፈጽሙ ግለሰቦች በተለይም(sugar daddies) መኖራቸው ይታወቃል። ይህንንም ተግባር ለመፈጸም ህገ ወጥ ደላሎች እንዲሁም መጥፎ  የሴት ጓደኞች በዋናነት ተባባሪ እንደሆኑና ይህም በሴት ተማሪወች ዉጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ተገልጿል።(ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር አለማየሁ 2003 ዓ.ም)

መፍትሄ ሃሳቦች

 • ሴት ተማሪዎች እነዚህ ከላይ የተገለጹት ችግሮች እንዳሉ ቀድሞ በመረዳት አስፈላጊዉን ጥንቃቄ እና የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸዉ ማወቅ።
 • ሴት ተማሪዎች መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ጓደኞች በመራቅ ትምህርታቸው ላይ ማተኮር።
 • ወሲባዊ ትንኮሳ በማንኛውም ተማሪ፣ መምህር ወይም የዩኒቨርስቲ አመራር ቢቀርብ ይህን ለመከላከል እና ጥፋተኛዉን ተጠያቂ የሚያደርግ መመርያ  በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ስለተዘጋጀ ወደ ዩኒቨርሲቲው ስርዓተ  ጾታ ቢሮ በመሄድ አስፈላጊውን እርምጃ  እንዲወሰድ ማድረግ። በተጨማሪም ለትምህርት ሚኒስቴር  ስርዓተ  ጾታ ዳይሬክቶሬት ማሳወቅ።
 • በዩኒቨርሲቲው የሚገኘውን የምክር አገልግሎት የመጠቀም ልምድ ማዳበር።
 • በራስ የመተማመንና(self confidence) ለራስ የሚሰጥን ግምት(self esteem) ማሳደግ።
 • ጭፈራ ቤቶች፣ አዝማሪ ቤቶች፣ የጫትና የሺሻ ቤቶች ለጾታዊ ጥቃት እንደሚያጋልጡ ማወቅና በተቻለ መጠን መጠንቀቅ።
 • ሴት ተማሪዎች የመብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው በአብዛኛው ለሚመለከተው አካል ቀርቦ የማመልከት ልምድ አናሳ መሆን በተለይ በቂ ማስረጃ ያለማግኘት ይስተዋላሉ። ነገር ግን ሴት ተማሪወች የሚፈጸምባቸውን ማንኛውም አይነት የመብት ጥሰቶች በዩኒቨርሲቲዉ ለሚገኘው የስርዓተ ጾታ ቢሮ ወይም ለህግ አገልግሎት ክፍል ማሳወቅ። በተጨማሪም በህገ መንግስቱ ላይ እነዚህ ጥቃቶች የመብት ጥሰት በመሆናቸው ጉዳዩን በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ ለፖሊስ በማመልከት አስፈላጊዉን ዳኝነት ማግኘት ይቻላል።
 • ለተጎጅዎች አስፈላጊውን የስነ ልቦና እና የጤና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ።

ለማጠቃለል ያህል እነዚህ ጥቃቶች የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት ሃገራችን የፈረመችዉን አለም አቀፍ ስምምነቶች እንዲሁም ህገ መንግስቱን እና የትምህርት ስልጠና ፖሊሲውን የሚቃረኑ በመሆናቸውና ሃገራችን ከድህነት ለመዉጣት በምታደርገው ጥረት እንቅፋት መሆናቸዉን ተገንዝበን በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት እና የየዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ችግሩን ለመቅረፍ መረባረብ እና የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል።

ምንጭ – ethiopiawinote

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.