ጤና ይስጥልኝ፤ እንደምን ከረማችሁ? ከአንባቢነት እና ተከታታይነት አሳልፎ ወደ ተሳታፊነት እንዳመራ ያስገደደኝ ችግሬ ‹‹የጡቴ እባጭ›› የስፐርም ክምችት ይሆን እንዴ? ከሚለው ችግር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የዛን አይነት እባጭ ከወጣብኝ ቀን ጀምሮ እስካሁን (አሁን 24 ዓመቴ ነው) ድረስ ሊጠፋ አልቻለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስነካካው ያሳምመኛል፡፡ አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ ስነካካው የወሲብ ስሜት ይቀሰቅስብኛል፡፡

(ከማንኛውም ሱስ ማለትም ሲጋራ፣ ሐሽሽ፣ ጫት፣ መጠጥ ነፃ ነኝ ሌላም ምንም አይነት የምጠቀመው መድሃኒት የለኝም)

opentalkmagazine_breast_pain_302917246ይህን ችግሬ ያዋየሁት የምወደው ጓደኛዬ እባጭ ለማጥፋት ስፖርት ስራ አለኝ፡፡ ግን ደግሞ እስፖርት አዘውትሬ ብሰራም ምንም ለውጥ ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ችግሩ ከወሲብ ጋር ይቆራኝ እንደሆነ ብዬ ብዙ ጊዜ ብሞክረውም ለጊዜው ትንሽ ከመቀነስ አልፎ ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊያመጣልኝ አልቻለም፡፡ ባለፈው ለልጁ ስታማክሩት ለትንሽ ጊዜ ጠብቀው እና ሊጠፋ ይችላል ወይም በቀላል ኦፕራሲዮን አስወግደው ብላችሁት ነበር፡፡ እኔ ግን ራሱ ይጠፋል ብዬ ብጠብቀውም እነሆ ከ12 ዓመቴ ጀምሮ የወጣብኝን እባጭ እስካሁን ድረስ ሊጠፋ ባለመቻሉ መጠበቁ ተስፋ አስቆርጦኛል፡፡ በኦፕራሲዮን እንዳላስወግደው ደግሞ ከፍርሃት እና ገንዘብ ማጣት ደምሮ ሊሆንልኝ አልቻለም፡፡

ሌላው ደግሞ ከ1 ዓመት በላይ አብራኝ የቆየችው ፍቅረኛዬ ሁሌ እንደጨቀጨቀችኝ ነች፡፡ ለምን አታጠፋውም? ትለኛለች አሁን አሁን እማ ብሶባት ወሬዋ ሁሉ ስለወጣብኝ እባጭ ሁኗል፣ በዚሁ ምክንያት ከልቤ የማፈቅራት ፍቅረኛዬ እንዳላጣት እየሰጋሁኝ ነው፡፡ እናም እባካችሁ ከእናንተ ሌላ እርዳታ የምጠይቀው ከጓደኛዬ ሌላ የማዋየው የለኝም እና ከዚህ ሌላ መፍትሄ ያለ እንደሆነ ጠቁሙኝ፡፡ መቸም ምላሽ እንደማትነፍጉኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በተረፈ ቸሩን ይግጠማችሁ ፍቱን ለሆነ መፍትሄያችሁ በጉጉት እየጠበቅኩኝ ነኝ ሰላም ሁኑልኝ፡፡ ደብሊው ኤ

የዶ/ር ዓብይ ዓይናለም፦ ውድ ወዳጃችን W.A በቅድሚያ ስለጥያቄህ አመሰግናለሁ፡፡

የጡትህ እባጭ ከ12ኛው ዓመት የዕድገት ዘመንህ ጀምሮ የወጣ በመሆኑ ከዕድገት (ጉርምስና) ጋር የተዛመደ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ በዚህ የዕድሜ እርከን ላይ የሚጀምር የጡት ማበጥ (በወንድ ላይ) በጉርምስና የዕድሜ ዘመን ከሚኖረው መጠኑ የጨመረ የሆርሞን ምርት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተለይም ፆታዊ ሆርሞኖች (sex hogmones) ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ እነዚህ እብጠቶች ከዕድገት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በመሆናቸው ፍፁም ጤናማ ናቸው፡፡ አብዛኞቹም በራሳቸው በጊዜ ሂደት የሚቀንሱ አሊያም የሚጠፉ ናቸው፡፡ የወንድ ልጅ ጡት አድጎ (አብጦ) ማየት የተለመደ ባለመሆኑ ግን በእይታ (ውጫዊ ገፅታ) ላይ የሚፈጥሩት አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛነቱ ግን አያጠያይቅም፡፡ በተለይም እብጠቱ ለውጫዊ ገፅታ ትኩረት በሚሰጥበት የወጣትነት ዕድሜ ላይ መሆኑ ይበልጥ አስጨናቂ አድርጎታል፡፡ በአንፃራዊነት አረጋውያን (በዕድሜ የገፉ ወንዶች) በአብዛኛው ይህን መሰል የጡት ማበጥ የሚያጋጥማቸው ቢሆንም ትኩረት አይሰጡትም፡፡ ከዚህም የጡት እብጠቱ ችግር ከእይታ (ግንዛቤ) ጋር የተቆራኘ መሆኑን መገንዘብ ይችላል፡፡

ውድ W.A የጡት እባጩን ከጠላኸው ማስወገድ መብትህ ነው፡፡ ብዙም የሚያሰጋ አደጋ የሌለበት ውጤታማ የኦፕራሲዮን ህክምና አለ፡፡ በተለይ እዚህ አዲስ አበባ መትተህ የምትታከም ከሆነ አማራጩ ሰፊ ነው፡፡ የመንግስት ሆስፒታሎች ካሉባቸው የስራ ጫናና ለዚህ መሰል ችግሮች ከሚሰጠው አነስተኛ ቦታ አንፃር ህክምናውን ለማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንብህ እንኳን መሰል ህክምና የሚሰጥ የተደራጀ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ማዕከል አለ፡፡ የዚህ ህክምና ዋነኛ ችግር ውድነቱ ነው፡፡ በግል የጤና ተቋማት አገልግሎቱ የሚሰጥበት ዋጋ ለብዙዎቻችን ከባድ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ እንዲሁም በራሱ ለሚያልፍ ችግር ያን ያህል ወጪ ማውጣቱ አስፈላጊ ነውን የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡ ምናልባት አንተ ከ12ኛ ዓመት የዕድሜ ዘመንህ ጀምሮ ለ12 ዓመታት ያህል እብጠቱ አብሮህ ስለቆየ በራሱ የመጥፋት እድሉ አነስተኛ ነው ብለህ ታስብ ይሆናል፡፡ ቢሆንም ግን 24ኛ ዓመት የዕድገት ዘመን የወጣትነት ጊዜ አጋማሽ እንጂ መጨረሻ ባለመሆኑ ጥቂት ዓመታት ብትታገሰው እብጠቱ የመቀነስ ወይንም የመጥፋት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ መጠበቁ ከሰለቸህና አቅም ካለህ በኦፕራሲዮን ማስወጣቱ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ ህክምናው የጎላ የጤና እክል የሚያስከትል ወይም አደጋ የሌለው ነው፡፡ ከሁለቱ ውጪ ሌላ አማራጭ ግን ለጊዜው የለም፡፡

Source- zehabesha.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.