ዩኒቨርሲቲው የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግርን ለመቀነስ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/ 2004 (ዋኢማ) -ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግር ተጋላጭነት ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከተባበሩት መንግስታት የሕፃናት አድን ድርጅት /ዩኒሴፍ/ እና ከተባበሩት መንግሥታት የሥነ-ሕዝብ ድርጅት ጋር በጥምረት እየሰራ ይገኛል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ኦልጂራ  ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የተማሪዎችን የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግር ተጋላጭነት ለመቀነስ ተማሪዎችን ያሳተፈ ተግባር እየተከናወነ ነው።

የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግርን በተማሪዎች እርስ በርስ እንዲፈታ ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ፣ በሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በጭሮ ኮሌጅ ተማሪዎች የሥነ-ተዋልዶ ጤና እና የአቻ ግፊት የአሰልጣኞች ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

አቶ ለሜሳ እንዳሉት የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግር ተጋላጭነት ለመቀነስ ተማሪዎች በሚያደርጉት ውይይት ችግሮቹን ለመፍታት ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አካላት ጋር በጋራ ይሰራሉ።

እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስና የሥነ-ተዋልዶ ጤና የመረጃ ማዕከል በመክፈት ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በገንዘብ ችግር ምክንያት ለሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግር ተጋላጭ የሚሆኑ ሴት ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል። በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዘንድ የሥነ-ተዋልዶ ጤና የመብት ጥያቄ እንዲሆን ለማድረግ በዓመት ለ3 ሺህ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

በዓመት ሁለት ጊዜ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲና በሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነፃ የኤችአይቪ/ኤድስ ምክርና ምርመራ የሚካሄድ መሆኑን አቶ ለሜሳ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የግብርና ኢኮኖሚክስ ተማሪ ማህሌት ሙሉጌታ በበኩሏ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስና በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ተከታታይ ስልጠና ለተማሪዎች የሚሰጥ መሆኑን ተናግራለች።

የሚሰጠው ስልጠና ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከዩኒቨርሲቲው ውጭ የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመከላከል እንዲችሉ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሴቶች በራሳቸው እንዲተማመኑ አቅም ይፈጥርላቸዋል ብላለች።

የሦስተኛ ዓመት የሥርዓተ ፆታ ተማሪና የዩኒቨርሲቲው የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት ተማሪ ሰለሞን ለገሰ እንዳለው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችን ለመቀነስ በተማሪዎች መካከል የእርስ በርስ ስልጠና ይካሄዳል።

በተማሪዎች መካከል የሚደረገው የእርስ በርስ ስልጠና ትኩረት የሚያደርገው በአቻ ግፊት ተፅዕኖና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ከመሆኑ ባሻገር ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ሳምንታት የሚቆይ የወጣቶች ውይይት እንዳለም ጠቁሟል።

በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የሲቪል ምህንድስና እና የከተማ ልማት ተማሪ ናርዶስ ታመነ በበኩሏ በግቢው ውስጥ ነፃ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራና በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረት ያደረገ የተማሪዎች ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ገልጻለች።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን የአቻ ተፅዕኖ ለመከላከል የዩኒቨርሲቲው የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ክበብ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በርካታ ተማሪዎችን የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመቋቋም መቻላቸውን አስረድታለች።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችን ለመቀነስ በሚያከናውነው ተግባር በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሞዴል መሆኑን በቅቷል።

ዩኒቨርሲቲው ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት አድን ድርጅት /ዩኒሴፍ/ እና ከተባበሩት መንግሥታት የሥነ-ሕዝብ ድርጅት ጋር በጥምረት የሚያካሂደው ፕሮጀክት ዋና ዓላማ የተማሪዎችን የሥነ-ተዋልዶ ጤና ማሻሻል ነው።

ፕሮጀክቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2008 የተጀመረ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግርን እንዲከላከሉ ትኩረት የሚያደርግ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.