ሄፕታይተስ ቢ ድምፅ አልባው ገዳይ በሽታ

ሄፕታይተስ ቢ ድምፅ አልባው ገዳይ በሽታ

“ዕድሜዬ 27 ዓመት ነበር፤ ወቅቱ ገና ትዳር የመሠረትኩበት ጊዜ ሲሆን ጥሩ ጤንነት እንዳለኝ ይሰማኝ ነበር። በአካባቢዬ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ በርካታ ኃላፊነቶች የነበሩኝ ከመሆኑም ሌላ ሰብዓዊ ሥራዬም ብዙ ውጥረት ያስከትልብኝ ነበር። ሄፕታይተስ ቢ ጉበቴን እየጎዳው እንዳለ አላወቅኩም ነበር።”—ዱክ ዩን

በት ከደም ውስጥ መርዛማ ነገሮችን የሚያጣራ ከመሆኑም ባሻገር ቢያንስ ቢያንስ 500 የሚሆኑ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ያከናውናል። ሄፕታይተስ ወይም የጉበት ብግነት የአንድን ሰው ጤንነት በእጅጉ ሊጎዳ የሚችለው በዚህ ምክንያት ነው። ሄፕታይተስ አልኮል አብዝቶ በመጠጣት ወይም መርዛማ ለሆኑ ነገሮች በመጋለጥ ሳቢያ ሊመጣ ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ለሄፕታይተስ መንስኤ የሚሆኑት ቫይረሶች ናቸው። ሳይንቲስቶች ሄፕታይተስ አምጪ የሆኑ አምስት ቫይረሶችን መለየት የቻሉ ሲሆን ቢያንስ ሌሎች ሦስት ዓይነት ቫይረሶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምናሉ።—ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።

ከአምስቱ ቫይረሶች አንዱ የሆነው ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ በየዓመቱ ቢያንስ 600,000 ሰዎችን ይገድላል፤ ይህም በወባ ምክንያት ከሚሞቱ ሰዎች ጋር ይተካከላል። ከሁለት ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ማለትም ከዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት በሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን አብዛኞቹ በወራት ጊዜ ውስጥ ከበሽታው ድነዋል። ይሁን እንጂ 350 ሚሊዮን በሚሆኑት ሰዎች ላይ በሽታው ሥር ሰዶባቸዋል። እነዚህ ሰዎች በቀሪ ሕይወት ዘመናቸው የበሽታው ምልክት ይኑራቸውም አይኑራቸው በሽታውን ወደ ሌሎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ።*

ሥር የሰደደ የሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ገና ከጅምሩ ተገቢውን ሕክምና ካገኙ በጉበታቸው ላይ የሚደርሰውን ከባድ ጉዳት ማስቀረት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ለዚሁ ተብሎ በሚደረግ ልዩ የደም ምርመራ ካልሆነ በስተቀር ሊታወቅ ስለማይችል አብዛኞቹ ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ እንኳ አያውቁም። በተለምዶ የሚደረገው የጉበት ምርመራ እንኳ የበሽታውን ምልክት ላያሳይ ይችላል። በመሆኑም ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ አለምንም ማስጠንቀቂያ ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ ድምጽ አልባ ገዳይ በሽታ ሊሆን ይችላል። በአንድ ሰው ላይ ግልጽ የሆኑ የሕመም ምልክቶች የሚታዩት በቫይረሱ ከተያዘ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ሊሆን ይችላል። በዚህ ወቅት ግን ሕመሙ ተባብሶ ስሮሲስ የተባለ የጉበት በሽታ ወይም ካንሰር ወደ መሆን ደረጃ ሊደርስ ይችላል። እነዚህ በሽታዎች የሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ከሚገኝባቸው አራት ሰዎች መካከል የአንዱን ሕይወት ያጠፋሉ።

“ሄፕታይተስ  ቫይረስ የያዘኝ እንዴት ነው?”

“ለመጀመሪያ ጊዜ የሕመም ምልክት የታየብኝ በ30 ዓመቴ ነበር” ይላል ዱክ ዩን። “በወቅቱ ተቅማጥ ይዞኝ ስለነበረ የምዕራባውያን ሕክምና ወደሚሰጥ አንድ ሐኪም ሄድኩ፤ ሆኖም የሰጠኝ ሕክምና የሕመሙን ምልክት ለጊዜው የሚያስወግድ ብቻ ነበር። ከዚያም የእስያውያን የባሕል ሐኪም ዘንድ ሄድኩ፤ እሱም ለአንጀትና ለሆድ የሚሆን መድኃኒት ሰጠኝ። ሁለቱም ሐኪሞች ሄፕታይተስ ይኖርብኝ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ምርመራ አላደረጉም። ተቅማጡ ሊቆምልኝ ስላልቻለ የምዕራባውያን ሕክምና ወደሚሰጠው ሐኪም ተመልሼ ሄድኩ።* እሱም ሆዴን በስተቀኝ በኩል ቀስ ብሎ መታ መታ ሲያደርግ ሕመም ተሰማኝ። የደም ምርመራውም ጥርጣሬው ትክክል መሆኑን አረጋገጠ፤ በደሜ ውስጥ የሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ነበር። በዚህ ጊዜ እጅግ ተደናገጥኩ! ደም ወስጄም ሆነ የፆታ ብልግና ፈጽሜ አላውቅም ነበር።”

ዱክ ዩን፣ ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ እንዳለበት ካወቀ በኋላ ሚስቱ፣ ወላጆቹ እንዲሁም ወንድሞቹና እህቶቹ የደም ምርመራ ተደረገላቸውና በሁሉም ደም ውስጥ ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስን የሚከላከሉ ፀረ እንግዳ አካላት (አንቲቦዲስ) መኖራቸው ታወቀ። ይሁን እንጂ በሽታ ተከላካይ ሕዋሶቻቸው ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ ከሰውነታቸው ውስጥ አስወግደውት ነበር። ዱክ ዩን፣ ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ የተያዘው ከአንዳቸው ተጋብቶበት ይሆን? ወይስ ሁሉም በበሽታው ለመያዛቸው ምክንያት የሆነው ነገር አንድ ይሆን? ይህን በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። እንዲያውም 35 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች በቫይረሱ የተያዙት እንዴት እንደሆነ በውል አይታወቅም። ሆኖም ሄፕታይተስ ቢ በዘር፣ ተራ በሆነ ንክኪም ሆነ ምግብ አብሮ በመብላት እንደማይተላለፍ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ከዚህ ይልቅ ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ የሚጋባው በቫይረሱ ከተያዘው ሰው የወጣው ደም አሊያም ሌላ ፈሳሽ (ለምሳሌ ከወንድ ወይም ከሴት ብልት የሚወጣ ፈሳሽ) ወይም ደግሞ ምራቅ በቆሰለ ሰውነት ወይም የአካል ሽፋን በኩል ወደ ሌላ ግለሰብ የደም ሥር በሚገባበት ጊዜ ነው።

በተለይ የሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ምርመራ በብዛት በሌለባቸው አሊያም ጨርሶ በማይደረግባቸው አገሮች ቫይረሱ ያለበትን ደም በመውሰዳቸው ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለበሽታው ይዳረጋሉ። ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ከአንዱ ወደ ሌላ የመተላለፍ አቅሙ ኤድስ አምጪ ከሆነው ከኤች አይ ቪ ቫይረስ 100 እጥፍ ይበልጣል። በምላጭ ጫፍ ላይ ያለ የደም ቅንጣት እንኳ ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ሊያስተላልፍ የሚችል ሲሆን የደረቀ የደም ጠብታ ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ቫይረሱን የማስተላለፍ አቅም ይኖረዋል።*

ሁኔታውን በሚገባ መረዳት

“የምሠራበት ኩባንያ ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ እንዳለብኝ ሲያውቅ ከአብዛኞቹ ባልደረቦቼ ተገልዬ በአንዲት ትንሽ ቢሮ ውስጥ እንድሠራ አደረገኝ” በማለት ዱክ ዩን ተናግሯል። በብዙ አካባቢዎች እንዲህ ማድረግ የተለመደ ሲሆን ይህም ቫይረሱ ስለሚተላለፍበት መንገድ ትክክለኛ ግንዛቤ ከማጣት የመጣ ሊሆን ይችላል። በቂ እውቀት አላቸው የሚባሉ ሰዎች እንኳ ሄፕታይተስ ቢን ከሄፕታይተስ ኤ ጋር ሊያማቱት ይችላሉ። ሄፕታይተስ ኤ በቀላሉ የሚተላለፍ ሲሆን ለሞት የመዳረግ አቅሙ ግን አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፍ በመሆኑ ጨዋ የሆኑ ሰዎች እንኳ በጥርጣሬ ዓይን ሊታዩ ይችላሉ።

ስለ ሁኔታው ትክክለኛ ግንዛቤ አለማግኘትና ጥርጣሬ ከባድ ችግሮች ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለምሳሌ በብዙ አካባቢዎች ሰዎች በደማቸው ውስጥ የሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ያለባቸውን ሕሙማን ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ሁሉንም ያገላሉ። ጎረቤቶች ልጆቻቸው አብረዋቸው እንዲጫወቱ አይፈቅዱም፣ ትምህርት ቤቶች አይቀበሏቸውም፣ አሠሪዎችም ሊቀጥሯቸው ፈቃደኛ አይሆኑም። ሰዎች እንዲህ ያለውን መገለል ስለሚፈሩ የሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ምርመራ ከማድረግ ወይም ሕመሙ እንዳለባቸው ከመናገር ወደኋላ ይላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ እውነታውን ከማሳወቅ ይልቅ የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን ጤንነት አደጋ ይጥላሉ። በዚህ ምክንያት ይህ ቀሳፊ በሽታ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል።

የእረፍት አስፈላጊነት

ዱክ ዩን እንዲህ ብሏል፦ “ሐኪሜ ሙሉ በሙሉ እረፍት እንዳደርግ ነግሮኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ከሁለት ወር በኋላ ወደ ሥራ ተመለስኩ። በደም ምርመራም ሆነ በሲቲ ስካን ምንም ዓይነት የስሮሲስ ምልክት ስላልታየብኝ ደህና የሆንኩ መሰለኝ።” ከሦስት ዓመት በኋላ የሚሠራበት ኩባንያ ወደ ትልቅ ከተማ ስላዛወረው ኑሮው ይበልጥ ውጥረት የበዛበት ሆነ። የተለያዩ ወጪዎችን ለመሸፈንና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሲል ተግቶ መሥራት ነበረበት።

በወራት ጊዜ ውስጥ በዱክ ደም ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን በጣም ስላሻቀበ ከፍተኛ ድካም ይሰማው ጀመር። ዱክ እንዲህ ብሏል፦ “ሥራዬን ለመተው ተገደድኩ። አሁን ሳስበው ያን ያህል በሥራ መድከሜ ይቆጨኛል። ቀድሞውኑ የሥራ ጫናዬን ብቀንስ ኖሮ ይህን ያህል አልታመምም ነበር፤ በጉበቴም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አይደርስም ነበር።” ዱክ ዩን በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት አግኝቷል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሥራውንም ሆነ ወጪውን ቀንሷል። ከዚህም በላይ መላ ቤተሰቡ ትብብር አድርጎለታል፤ ሚስቱ አንዳንድ ቀዳዳዎችን ለመድፈን የሚያስችላትን አነስተኛ ሥራ መሥራት ጀምራለች።

ከሄፕታይተስ  ጋር መኖር

የዱክ ዩን የጤንነት ችግር እየተባባሰ መሄዱን አቁሟል፤ ይሁን እንጂ ጉበቱ ደም አላስተላልፍ እያለ በማስቸገሩ ምክንያት የደም ግፊቱ ከፍ ይላል። ከ11 ዓመት በኋላ በምግብ መውረጃ ቧንቧው ላይ ያለው የደም ሥር ፈንድቶ ብዙ ደም ከጉሮሮው በመፍሰሱ ሆስፒታል ገብቶ ለአንድ ሳምንት ለመተኛት ተገዶ ነበር። ከአራት ዓመት በኋላ የአእምሮ ችግር አጋጠመው። ጉበቱ ሙሉ በሙሉ ሊያጣራው ስላልቻለ አሞንያ የተባለው ንጥረ ነገር በአንጎሉ ውስጥ ተከማችቶ ነበር። ይሁን እንጂ በተደረገለት ሕክምና በጥቂት ቀናት ውስጥ ችግሩ ሊወገድለት ችሏል።

አሁን ዱክ ዩን 54 ዓመት ሆኖታል። በሽታው ከባሰበት የሚኖሩት አማራጮች በጣም ውስን ናቸው። ፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ ሊያስወግዱለት አይችሉም። ከዚህም ሌላ መድኃኒቶቹ አስከፊ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። የመጨረሻው አማራጭ ጉበቱን ማስቀየር ቢሆንም ጉበት የሚለግሳቸው ሰው ለማግኘት እየተጠባበቁ ያሉት ሕመምተኞች ቁጥር ከለጋሾቹ ቁጥር በእጅጉ ይበልጣል። “በየትኛውም ጊዜ ሊፈነዳ እንደሚችል ቦምብ ሆኛለሁ” ይላል ዱክ ዩን። “ይሁን እንጂ ይህን እያሰቡ መቆዘም የሚፈይደው ነገር የለም። አሁንም በሕይወት አለሁ፤ የማርፍበት ቤትም ሆነ በጣም ግሩም የሆነ ቤተሰብ አለኝ። እንዲያውም በአንዳንድ መንገዶች ያለሁበት ሁኔታ ያልታሰበ በረከት አስገኝቶልኛል። ከቤተሰቤ ጋር የማሳልፈው እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን የማጠናበት ተጨማሪ ጊዜ አግኝቻለሁ። ይህም አለጊዜዬ እሞታለሁ በሚል ፍርሃት እንዳልዋጥና ምንም ዓይነት ሕመም የማይኖርበትን ሕይወት በጉጉት እንድጠባበቅ አድርጎኛል።”*

ዱክ ዩን ይህን የመሰለ አዎንታዊ አመለካከት መያዙ መላ ቤተሰቡ ደስታ የሰፈነበት ሕይወት እንዲመራ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን እሱም ሆነ ባለቤቱ እንዲሁም ሦስት ልጆቹ በሙሉ ጊዜ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ይካፈላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

የአንድ ሰው በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ቫይረሱን በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ከሰውነት ማስወገድ ካልቻሉ በሽታው ሥር እንደ ሰደደ ይቆጠራል።

ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም።

በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ደም በሚፈስበት ጊዜ አንድ እጅ በረኪናን በ10 እጅ ውኃ በመበጥበጥ ጓንት አድርጎ የፈሰሰውን ደም ወዲያውኑ በሚገባ ማጽዳት ያስፈልጋል።

መጽሐፍ ቅዱስ በሽታ ስለማይኖርበት ዓለም የሚሰጠውን ተስፋ በሚመለከት ራእይ 21:3, 4ን እንዲሁምትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ቶሎ ሕክምና መውሰድ ጉዳቱ እንዳይባባስ ሊረዳ ይችላል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሰዎች ያገሉኛል የሚለው ፍራቻ ብዙዎች የሄፕታይተስ  ቫይረስ ምርመራ ከማድረግም ሆነቫይረሱ እንዳለባቸው ከመናገር ወደኋላ እንዲሉ ያደርጋቸዋል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የትኛው ዓይነት ሄፕታይተስ ነው?

  ሄፕታይተስ የሚያመጡ አምስት ዓይነት ቫይረሶች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን በስፋት የታወቁት ሄፕታይተስ ኤ፣ ቢ እና ሲ የሚባሉት ሦስቱ የቫይረስ ዓይነቶች ናቸው። ሌሎች ቫይረሶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ሁሉም ዓይነት የሄፕታይተስ በሽታዎች እንደ ኢንፍሉዌንዛ ያለ የሕመም ምልክቶችን የሚያስከትሉ ሲሆኑ ዓይንን ቢጫ ሊያደርጉ ወይም ላያደርጉ ይችላሉ። ብዙ ሰዎች በተለይም ደግሞ ትናንሽ ልጆች ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት አይታይባቸውም። በሽታው ሄፕታይተስ ቢ ወይም ሄፕታይተስ ሲ በሚሆንበት ጊዜ የሕመም ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት ጉበት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ሊሆን ይችላል።

ሄፕታይተስ  ቫይረስ

  ሄፕታይተስ ኤ ቫይረስ በበሽታው በተያዘ ሰው ዓይነ ምድር ውስጥ ይገኛል። ቫይረሱ በጨዋማም ሆነ ጨዋማ ባልሆነ ውኃ እንዲሁም በበረዶ ውስጥ ሳይሞት ሊቆይ ይችላል። አንድ ሰው በሚከተሉት መንገዶች ለሄፕታይተስ ኤ ቫይረስ ሊጋለጥ ይችላል፦

 በሰው ዓይነ ምድር ከተበከለ የውኃ አካል የተገኘን ዓሣና ሌሎች የባሕር ምግቦች ሳያበስሉ መብላት ወይም የተበከለ ውኃ መጠጣት

 በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የሚደረግ አካላዊ ንክኪ ወይም አብሮ መብላትና መጠጣት አሊያም የመመገቢያ ዕቃዎችን በጋራ መጠቀም

 መጸዳጃ ቤት ከገቡ በኋላ፣ በበሽታው የተያዘ ሕፃን ሽንት ጨርቅ ከለወጡ በኋላ ወይም ምግብ ከማዘጋጀት በፊት እጅን በደንብ አለመታጠብ

 ሄፕታይተስ ኤ አጣዳፊ ሕመም የሚያስከትል ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ሥር አይሰድም። አብዛኛውን ጊዜ ሰውነታችን በራሱ በሳምንታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ ቫይረሱን ያስወግደዋል። እረፍት ከማድረግና ጥሩ ምግብ ከመመገብ ሌላ ይህ ነው የሚባል የተለየ ሕክምና የለውም። ጉበት ሙሉ በሙሉ እንደዳነ በሐኪም ከመረጋገጡ በፊት አልኮል መጠጣትና ጉበት ላይ ጫና ያመጣሉ የሚባሉ እንደአሲታሚኖፊን ያሉ መድኃኒቶችን መውሰድ ተገቢ አይደለም። ሄፕታይተስ ኤ ቫይረስ አንድ ጊዜ የያዘው ሰው ተመልሶ በዚሁ ቫይረስ አይያዝ ይሆናል እንጂ ሌላ ዓይነት የሄፕታይተስ በሽታዎች ሊይዙት ይችላሉ። ሄፕታይተስ ኤን በክትባት መከላከል ይቻላል።

ሄፕታይተስ  ቫይረስ

  ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ በበሽታው በተያዙ ሰዎች ደም እንዲሁም ከብልታቸው በሚወጡ ፈሳሾች ውስጥ ይገኛል። እንደነዚህ ያሉት ፈሳሾች ቫይረሱን የመከላከል አቅም በሌለው ሰው ሰውነት ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ ቫይረሱ ይዛመታል። ቫይረሱ በሚከተሉት መንገዶች ሊተላለፍ ይችላል፦

 በወሊድ ወቅት (በቫይረሱ ከተያዘች እናት ወደ ልጅ)

 በተገቢው መንገድ ከጀርም ያልጸዳ የሕክምና፣ የጥርስ፣ የንቅሳት ወይም ሰውነትን ለመብሳት የሚያገለግል ሌላ መሣሪያ

 መድኃኒት ለመስጠት የሚያገለግል መርፌን፣ ምላጭን፣ የጥፍር መሞረጃን ወይም መቁረጫን፣ የጥርስ ብሩሽን ወይም በቆሰለ የአካል ክፍል በኩል የደም ቅንጣትን ሊያስተላልፍ የሚችል ማንኛውንም ሌላ መሣሪያ በጋራ መጠቀም

 የፆታ ግንኙነት

  ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ በትናንሽ ነፍሳት ወይም በሳል፣ እጅ በመጨባበጥ፣ በመተቃቀፍ፣ ጉንጭ ላይ በመሳሳም፣ ጡት በማጥባት ወይም አብሮ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም እንደ ሹካ ያሉ ሌሎች የመመገቢያ መሣሪያዎችን በጋራ በመጠቀም እንደማይተላለፍ የጤና ባለሙያዎች ያምናሉ። አብዛኛውን ጊዜ አዋቂ የሆኑ ሰዎች ሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ተይዘው ከዳኑ በኋላ ሰውነታቸው ዳግመኛ በዚህ በሽታ እንዳይያዙ የሚያደርግ የመከላከያ አቅም ያዳብራል። ትናንሽ ልጆች ሥር በሰደደ ኢንፌክሽን የመያዛቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። ተገቢው ሕክምና ካልተደረገ በስተቀር ሥር የሰደደ የሄፕታይተስ ቢ በሽታ ጉበት ሥራውን እንዲያቆም በማድረግ ለሞት ሊዳርግ ይችላል። ሄፕታይተስ ቢን በክትባት መከላከል ይቻላል።

ሄፕታይተስ  ቫይረስ

  ሄፕታይተስ ሲ ቫይረስ የሚተላለፍበት መንገድ ከሄፕታይተስ ቢ ቫይረስ ብዙም ያልተለየ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ የሚተላለፈው በተበከለ መርፌ ዕፆችን በመውሰድ ነው። ሄፕታይተስ ሲ ምንም ዓይነት መከላከያ ክትባት የለውም።*

የዓለም የጤና ድርጅት www.who.int በተባለ ድረ ገጹ ላይ ስለ ሄፕታይተስ ተጨማሪ መረጃ ይሰጣል።

የሄፕታይተስ  ቫይረስን ዑደት ማቆም

  ሄፕታይተስ ቢ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ቫይረስ ቢሆንም ሥር የሰደደ የሄፕታይተስ ቢ በሽታ ካለባቸው ሰዎች 78 በመቶ የሚሆኑት የሚኖሩት በእስያና በፓስፊክ ደሴቶች ነው። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ከሚኖሩት 10 ሰዎች መካከል አንዱ በደሙ ውስጥ ይህ ቫይረስ ይገኛል። በዚያ የሚገኙ አብዛኞቹ ሕሙማን በቫይረሱ የሚያዙት በወሊድ ጊዜ ከእናታቸው ስለሚተላለፍባቸው አሊያም ሕፃናት ሳሉ በበሽታው ከተያዙ ሌሎች ሕፃናት ደም ጋር ንክኪ ስለሚኖራቸው ነው። ለአራስ ልጆችና ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ሌሎች ሰዎች የሚሰጠው ክትባት ይህን ዑደት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ነው።* ክትባት በሚሰጥባቸው አገሮች የበሽታው ስርጭት በእጅጉ ቀንሷል።

የሄፕታይተስ ክትባት ከደም ክፍልፋዮች ሊዘጋጅ ይችላል። ስለዚህ ሁኔታ ይበልጥ ማወቅ የሚፈልጉ አንባቢያን በሰኔ 15, 2000 እና በጥቅምት 1, 1994 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የወጡትን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” የሚሉትን ዓምዶች መመልከት ይችላሉ። ከዚህም ሌላ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው “ከአምላክ ፍቅር አትውጡ” በተባለው መጽሐፍ ገጽ 215 ላይ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይቻላል።

Souce0 http://wol.jw.org/

1 COMMENT

 1. እንደምን አላችሁ:
  በእንግሊዘኛ ጽፌላችሁ ነበር
  ዋናው ጉዳይ ከሁለት አመት በፊት ታምሜ የተለያዩ ህክምና አርጌ ነበር:: ከ7 ወር በፊት ተመርምሬ ሄፓታየተስ ቢ እንዳለብኝ ተነገረኝ ከዛም ከህንድ አገር የባህል መዳኒት አስመጥቸ 1 ወር ከ2 ሳምንት እንደወሰድሁ ስመረመር በደሜ ውስጥ አለመኖሩ ተነገረኝ:: ተጠራጥሬ በ2ኛው ቀንም ደግሜ ተመረመርኩ የለም:: ከ2 ወር በኋላም ለላ ሆስፒታል ተመረመርኩ ነጋቲቭ ነኝ:: ነገርግን ህመሙ እየባሰብኝ ነው በተለይ የቀኝ የላየኛው ሆድ ህመም፡ እራስ ምታትና ሌሎችም::
  ቫይረሱ በደሜ ሳይገኝ ሰዉነቴ ውስጥ የመኖር እና ህመም የማምጣት እድል አለው?
  እስኪ አግዙኝ አደራ:: አድራሻዬ beletafand017@gmail.com
  አመሰግናለሁ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.