c1f74303d2e9fe86004dc43cc969e023_M በህገወጥ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና አገልግሎት ላይ ያተኮረ የህዝብ ንቅናቄ መድረክ በደሴ፣ በአላማጣና በሽሬ ከተሞች ባለፈው ግንቦት ወር ተካሂዷል፡፡ 
የህዝብ ንቅናቄ መድረኩ በተለይ በህገወጥ የምግብና መድሃኒት ንግድ ምንነትና የሚያስከትለው ችግር ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በሰፊው ምክክር ለማድረግና ህብረተሰቡን የቁጥጥሩ ባለቤት ለማድረግ ታልሞ የተካሄደ መድረክ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፤ ከህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ዝውውር ጋር በተያያዘ በጣም ተጋላጭ በሆኑና በተመረጡ ቦታዎች ላይ የህዝብ ንቅናቄ መድረክ ያካሂዳል፣ በቅርቡም በሶስት ከተሞች ላይ የተከናወኑት መድረኮች የዚህ እንቅስቃሴ አካል ናቸው፡፡ 

በውይይት መድረኮቹ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎትና ግብአት ከየት ወዴት፣ ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድና የጤና አገልግሎት ቁጥጥር ነባራዊ ሁኔታ፣ የምግብና የመድሃኒት ህገወጥ ዝውውር አጠቃቀምና ጤና አገልግሎት ክልላዊ ገጽታ፣ ህገወጥ የምግብ፣ የመድሃኒትና ጤና አገልግሎት እንቅስቃሴን በጋራ ለማስወገድ ቀጣይ አቅጣጫ (የጋራ ዕቅድ) የሚሉ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን ለተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየትም በቂ ጊዜ ተሰጥቶ በርካታ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ 

በጋራ ምክክር መድረኩ ትኩረት አግኝተው ከተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ “ህገወጥ የምግብ፣ መድሃኒት ንግድና የጤና አገልግሎት ቁጥጥር ስራዎች ነባራዊ ሁኔታ” በሚል በባለስልጣን መ/ቤቱ የኢንስፔክሽንና ቅኝት ዳይሬክቶሬት የቀረበው ገለፃ ሲሆን አላማውም በሀገራችን በምግብ፣ በመድኃኒትና በጤና አገልግሎት ዙሪያ ያለውን ህገወጥ እንቅስቃሴ በማስቃኘት በቀጣይ ህገወጥ እንቅስቃሴን በመከላከሉ ስራ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትና ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ለማነቃቃት ነው፡፡ 

አግባባዊ የምግብ ንግድ ስራ 
ማንኛውም ምግብ ባለስልጣኑ ወይም የክልል ጤና ጤና ተቆጣጣሪ አካል ሳይፈቅድ መመረት፣ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት፣ መላክ፣ መዘጋጀት፣ መከማቸት፣ መከፋፈል፣ መጓጓዝ ወይም ለሽያጭ ወይም ለህብረተሰቡ ሊቀርብ አይችልም፡፡ 

ማንኛውም ምግብ ጥራቱና ደህንነቱ ተጠብቆ መመረት፣ መታሸግ፣ ገላጭ ጽሑፍ መለጠፍ፣ መከማቸት፣ መጓጓዝና መሸጥ አለበት፡፡ 
በማንኛውም ምግብ ላይ መጠኑን ወይም ክብደቱን ለመጨመር፣ መልኩን ለማሳመር ወይም ለሌላ ተመሳሳይ ዓላማ ሲባል የሰውን ጤና ሊጐዳ ወይም የምግቡን ጥራትና ደህንነት ሊያጓድል የሚችል ባእድ ነገር መጨመር ወይም መቀላቀል የተከለከለ ነው፡፡ 

ማንኛውም ለህብረተሰቡ ሽያጭ አገልግሎት የሚውል የታሸገ ምግብ በአማርኛ ወይም እንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፈ ገላጭ ጽሑፍ ሊኖረው ይገባል፡፡ 

Source- addisadmassnews
የምግቡ ስም 
በምግቡ ውስጥ ያለው ይዘት 
የምግቡ አምራች ድርጅት ስምና ሙሉ አድራሻ 
የምግቡ መለያ ቁጥር (Batch no)
ምግቡ የተመረተበትና የመጠቀሚያ ጊዜው የሚያበቃበት ቀን 
አግባባዊ የመድሃኒት ንግድ ስራ 
ማንኛውም መድኃኒት ደህንነቱ፣ ፈዋሽነቱና ጥራቱ ተገምግሞ በአስፈጻሚ አካሉ ሳይመዘገብ በጥቅም ላይ ሊውል አይችልም፣ 
ማንኛውም መድሃኒት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት፣ ለማምረትና ለህብረተሰቡ ሽያጭ ለማዋል መጀመሪያ በባለስልጣኑ በብሔራዊ የመድሃኒት መዘርዝር ውስጥ በመካተት ተመዝግቦ የገበያ ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡ 
የማንኛውም መድሃኒት ገላጭ ጽሑፍ፡- 
የመድሃኒቱ ሳይንሳዊ ስም 
በመድሃኒቱ ውስጥ ያለው ይዘት 
የመድሃኒቱ አምራች ድርጅት ስምና ሙሉ አድራሻ 
መድሃኒቱ የተመረተበትና አገልግሎት የሚያበቃበት ጊዜ 
በቀን መወሰድ ያለበት መጠንና የአወሳሰድ ሁኔታ…ሊያካትት ይገባል፡፡ 
አግባባዊ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ 
ማንኛውም የጤና ተቋም በሀገሪቱ የተቀመጠውን የጤና አገልግሎት ደረጃ ያሟላ መሆን አለበት 
ከሚመለከተው የጤና ተቆጣጣሪ አካል ህጋዊ እውቅና የተሰጠው መሆን ይኖርበታል 
ለሚሰጠው አገልግሎት የሚያስፈልጉ በቂ የህክምና መሳሪያዎች እንዲሁም ብቃታቸውና ሙያዊ ስነ ምግባራቸው የተረጋገጠ የጤና ባለሙያዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡ 
ባለስልጣን መ/ቤቱ ከላይ ከተገለፀው አግባባዊ አካሄድ በተቃራኒ የሚካሄዱ ህገወጥ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና አገልግሎቶችን ይቆጣጠራል፣ በአዋጅ (661/2002) በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት፣ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃም ይወስዳል፡፡ ለአብነት ያህል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከደንብና አግባብ ውጪ ሲሰሩ በነበሩ ላይ የተጣሉ ቅጣቶችን ማየት ይቻላል፡፡ 
ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ ምርቶች (ባለፉት 9 ወራት)
የምርት ዓይነት         ብዛት በቶን 
ምግብ             45 ቶን 
መድሃኒት            27 ቶን 
ኮስሞቲክስ         14 ቶን 
በቁጥጥር ወቅት የተገኙና ተገቢውን መስፈርት ሳያሟሉ ቀርተው የተወገዱ ምርቶች 
የምርት ዓይነት         የድርጅቶች ብዛት 
ምግብ             127 ድርጅቶች 
መድሀኒት             130 ድርጅቶች 
አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ድርጅቶች 
705 የምግብ አስመጭዎችና ጅምላ አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር ተካሂዶ 90 ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀታቸውን እንዲመልሱ ተደርጓል፡፡ 8 ድርጅቶች ላይ የእገዳ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡ 

በ321 መድሃኒት አስመጪና አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር ተካሂዶ በ24 ድርጅቶች ላይ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ስረዛ ድረስ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡ 

በህዝብ ንቅናቄ መድረኮቹ ላይ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎች፣ የክልል ተቆጣጣሪ አካላት፣ የፍትህ አካላት (የፍርድ ቤትና ፖሊስ ተወካዮች) የወጣትና ሴት አደረጃጀቶች፣ ከተለያዩ ሴክተር መ/ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች (ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ ከንግድ ቢሮ፣ ከንግድ አሰራርና ሸማቾች ጥበቃ ባስልጣን….) ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ መሰል የምክክር መድረኮች ችግሮችን በጋራ ነቅሶ ጠቃሚ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለመስጠት የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ የመላው ማህበረሰብ ችግር የሆነውንና ውስብስብ እየሆነ የመጣውን ህገወጥ የምግብና መድሃኒት ዝውውር ለመግታት፣ የህዝብ ንቅናቄ መድረኮችን ማዘጋጀት የግድ ይላል፡፡ የጤና ጠንቅ የሆነውንና በሁላችንም ህይወት መንገድ ላይ የቆመውን ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድና ዝውውር መግታት የሚቻለው ህብረተሰቡ የቁጥጥሩ ባለቤት መሆን ሲችል ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለስልጣን መ/ቤቱ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ብሎም የመላው ማህበረሰብን የተጠናከረ ድጋፍ ይሻል፡፡ 

ህብረተሰቡ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብና ጥራቱ፣ ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት በመጠቀም ጤናውን ሊጠብቅ ይገባል፡፡ እንዲሁም በምግብ፣ በመድሃኒትና በጤና አገልግሎቶች ላይ ማናቸውም ዓይነት ህገወጥ እንቅስቃሴ ሲገጥመው ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካልና ለፖሊስ በመጠቆም መተባበር አለበት፡፡ 

ህገወጥ የምግብና መድሃኒት ንግድና የጤና አገልግሎትን በጋራ እንቆጣጠር!!!
(የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ)

Source- addisadmassnews

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.