«የወገብ ሕመም ስላለ ብቻ ህክምናን ከሴራጂም መጀመሩ ጥፋት እንጂ ፈውስ አይኖረውም» አምባሳደር ዶክተር ዘነበ ገድሌ

back_seeknesየማናውቀው ወይም አውቀን ልብ ባላልነው ምክንያት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን ጉዳት ይደርስባቸዋል። ጉዳት ከሚደርስባቸው የሰውነት ክፍሎች መካከል ደግሞ ጭንቅላት፤ ህብለ ሰረሰር (ስፓይናል ኮርድ)ና ነርቮች ተጠቃሾቹ ናቸው። እነዚህ ህመሞች ደግሞ በራሳቸው ብቻ ሳይሆን በርካታ የጤና ችግሮችን አስከትለው መምጣታቸው ይነገራል። ሆኖም ብዙዎቻችን ምልክቶቻቸውን እያየን እንኳን ለጤና ችግሮቹ ትኩረት አንሰጥም። 

የጭንቅላት፤ የህብለ ሰረሰርና የነርቭ ህመሞች በእንግሊዝኛ አጠራራቸው «ኒውሮሎጂ»ና «ኒውሮ ሰርጀሪ» ይባላሉ። እነዚህ ህመሞች ትኩረታቸውን የሚያደርጉት ደግሞ ጭንቅላት፤ ህብለ ሰረሰርና ነርቭ ላይ ነው። ህመሞቹ በርካታ በመሆናቸው ዘርዘር አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል።


እኛም ይህንን የኅብረተሰብ ችግር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያመራነው የነርቭ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ወደሆኑት አምባሳደር ዶክተር ዘነበ ገድሌ ነው። 
ዶክተር ዘነበ በክሪስማስ የነርቭ፣ የጭንቅላትና ህብለሰረሰር ቀዶ ሕክምና ሆስፒታል የአጥንትና የነርቭ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሲሆኑ፤ በሙያው ረዘም ላለ ዓመታት አገልግለዋል አሁንም በማገልገል ላይ ናቸው ዶክተር ዘነበ የሚጥል በሽታ (ኢፒሊፕሲ) አምባሳደርም ናቸው። ዶክተር ዘነበ ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያም ዝግጅት ክፍሉ የላቀ ምስጋና ያቀርባል።

አዲስ ዘመን፡- የአጥንት ህክምና (ኒው ሮሎጂ) ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ዘነበ፡- ኒውሮሎጂ ማለት «ኒውሮ» ነርቭ ከሚለው የመጣ ነው። ይህ የጤና ዘርፍ የሚያተኩረው የጭንቅላትን፤ ህብለሰረሰርንና ነርቮችን በማጥቃት ወይም ህመምን በማስከተል የሚመጣ ነው። ይህም በተፈጥሮ፤ በአደጋ የሚከሰቱ ችግሮችን በቀዶ ህክምና መፍትሄ የሚሰጥ የህክምና ዘርፍ ነው።

አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሮ ያልተስተካከሉ የአንጎል፤ የህብለ ሰረሰር ችግር ሊኖራቸው ይችላል። ተዛብቶም መፈጠር አለ። በተፈጥሮ ሲባልም ተፈጥሮ ሂደቱን ሳይጨርስ መወለድ ይሆናል ለምሳሌ ሕፃናት ትልቅ ጭንቅላትን ይዘው መወለድ አንዱና ዋነኛው ነው። ይህ በአገራችንም የተለመደና ብዙዎችን የሚያሰቃይ ነው። በህክምና በውስጡ የተጠራቀመውን ፈሳሽ አውጥቶ ማከም ይቻላል። በእዚህ ደግሞ መጠኑንም መቀነስ ይቻላል። ሆኖም በወቅቱ መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን፡- ተያያዥ የሆኑትን የአጥንት ህብለሰረሰርና የነርቭ በሽታዎች በስንት ልንከፍላቸው እንችላለን?

ዶክተር ዘነበ፡- ችግሮቹን በሦስት ልንከፍላቸው እንችላለን። ከወገብ ወደ እግር የሚሄድ ህመም አንዱ ነው። ይህ ህመም ሲጀምር የወገብ ብቻ ሆኖ ይጀምራል። ከዛም ወደ እግር እየወረደ ይሄዳል፤ ወደ እግር እንዲሄድ የሆነው ደግሞ ወደ እግር የሚሄደው ነርቭ ጫና ስለሚበዛበት ነው፤ ይህንን ደግሞ ቀላል ብለን ልንወስደው እንችላለን። በተለይም ህመሙ እንደተፈጠረ ህክምና ከተወሰደ ህመምተኛው ወዲያውኑ ወደ ነበረበት ይመለሳል። ሆኖም ጫናው እየቀጠለ በሄደ መጠን የሚደርሰው ጉዳትም እያየለ ይመጣል።

ሁለተኛው ደግሞ መደንዘዝ ነው። ይህ የሚከሰተው የመጀመሪያው የህመም ደረጃ እየተባባሰና እየከፋ ሲሄድ ነው። የመደንዘዝ ስሜቱ ምንም ህመም ላይኖረው ይችላል። እንዲያውም ህመምተኛው ድንዝዝ ሲለው የተሻለው ሊመስለው ይችላል። ሆኖም መደንዘዝ ከባድ ደረጃ መድረሱን አመልካች ነው። አሁንም ህክምና ካልተወሰደበት አቅም ወደ ማሳጣት ደረጃ ያደርሳል። አቅም አጣ ማለት ደግሞ ሦስተኛውና የተባባሰው ደረጃ ላይ ደረሰ ማለት ነው። እነዚህ ሁሉ ምልክቶች ሲታዩ በተለይም የመጀመሪያው ደረጃ ላይ ህክምና ወስዶ በቀላሉ ወደ ጤናው ይመለሳል። መዘግየት ግን ከፍተኛ ጥፋትን ያስከትላል።

ከሌሎች የሰውነት ክፍሎቻችን ይልቅ በእነዚህ የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ የሚከሰቱ ችግሮች በቶሎ እልባትን ቢያገኙ መልካም ነው። በነርቭ ላይ ያሉ ጉዳቶች ቂመኞች ናቸው። ችግራቸውንም በቶሎ ማስወገድ ከተቻለ ቶሎ ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ። ለችግሮቹ ጊዜ በተሰጠ ቁጥር እነርሱም ስር ስለሚሰዱ ውጤቱን ለማየት ብዙ ትዕግስት ይጠይቃል፡፡ የሚያረካ ውጤትም ላይገኝባቸው ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህ የአንጎል፤ የህብለ ሰረሰርና የነርቭ ችግሮች ደረጃቸው ይህ ከሆነ መንስኤዎቻቸው ምንድን ናቸው?

ዶክተር ዘነበ፡- ይህ የሙያ ዘርፍ በርካታ የህመም ዓይነቶችን ያጠቃልላል። ሆኖም በተፈጥሮ ይከሰታሉ የተባሉት የህመም ዓይነቶች መንስኤዎች በሙሉ የሚከሰቱት ሽሉ በማህፀን ውስጥ እንዳለ ጀምሮ ነው። የጀርባ ህመምም ቢሆን የጀርባ አጥንት ወይም አከርካሪ በተፈጥሮ አምስት መሆን ያለበት ሲሆን፤ አንዳንድ ጊዜ አራት ሌላ ጊዜ ደግሞ ስድስት ሊሆን ይችላል። ከእዚህም ባሻገር በተፈጥሮ መገጣጠም የሚገባቸው አካላት ሳይገጥሙ ክፍተት ይኖራቸዋል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ አንድ ሰው እያደገ በሚሄድበት ወቅት የጀርባ ህመም እንዲኖረው ምክንያት ይሆናሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜም ህመሞች በጉርምስና ዕድሜ ይከሰታል። ሆኖም በተለይ ለጀርባ ህመም መከሰት ዋና መንስኤ ተብለው የሚወሰዱት ያለ አግባብ ክብደት ያላቸውን እቃዎች ማንሳት፤ መውደቅ፣ የአከርካሪንና የዲስክን ሥራ በማበላሸት ነርቭ ላይ ጫና ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ጎምበስ ቀና ብለው እቃ የሚያነሱ ሰዎች፤ በብዛት የሚቀመጡ ፀሐፊዎችና ሌሎችም በዲስካቸው ላይ ጫና ስለሚኖር ለእዚህ ህመም የተጋለጡ ናቸው እነዚህ እንግዲህ ለህመሞቹ እንደ ምክንያት የሚጠቀሱም ናቸው።

በተፈጥሮ የሚከሰቱ እንደ ጭንቅላት ግዝፈት ዓይነት ችግሮችም ሽሉ ሆድ ውስጥ እያለ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ በሚፈጠር የምግብ ማነስ፤ በተለይም የፎሊክ አሲድ እጥረት፤ በእርግዝና ወቅት የተለያዩ መድኃኒቶችን ያለባለሙያ ትዕዛዝ መጠቀም፤ ለእዚህ ዓይነቱ ችግር ያጋልጣል በመሆኑም የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት መድኃኒቶችን ከመጠቀም መቆጠብ ያስፈልጋል። በከፍተኛ ሁኔታ የጭንቅላት ላይ አደጋዎችም ለችግሮቹ መንስኤ ናቸው። ለምሳሌ የመኪና አደጋ በሚያስከትለው ችግር ሳቢያ ብዙዎች አንገታቸውና አከርካሪያቸው ይሰበራል። በእዚህ ምክንያት ሰውነታቸው ያለመታዘዝ (ፓራላይዝ) የመሆን እጣ ይገጥማቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- የተለየ የመከሰቻ የእድሜ ክልልስ አለው?

ዶክተር ዘነበ፡- አዎ በተለይም ከአደጋ ጋር በተያያዘ ለጭንቅላት፤ ህብለ ሰረሰርና ለነርቭ ችግር የሚጋለጡ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ 20 እስከ 40 ያሉት ናቸው። ይህም በጥናት ተረጋግጧል። ሌላው እድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የአንጎል ውስጥ ደም ስሮች እየተዘጉ ይሄዳሉ፤ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ የምንመገባቸው ቅባት የሚበዛባቸው ምግቦች ፤ በደንብ የህክምና ክትትል ያላገኙ የጤና ችግሮች የአንጎል ደምስር እንዲበጠስ ያደርጋሉ፤ እነዚህ ደግሞ በብዛት የሚታዩት ዕድሜያቸው ገፋ ባሉ ሰዎች ላይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የእነዚህ በሽታዎች ምልክትስ ምን ይመስላል?


ዶክተር ዘነበ፡- ምልክቶቹ እንደየሰው ቢለያዩም ዋናው ግን የእጅ መዛል (መደንዘዝ)፤ የምላስ መያዝ፤ግማሽ ሰውነት መድከምና መሰል ሁኔታዎች እንደ ምልክት ሊያዙ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ ምልክቶች በአንዴ ላይታዩም የሚችሉበት አጋጣሚ አለ።

አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ምልክቶች ታይተውበት የመጣ ህመምተኛ ምን ዓይነት ህክምና ወይም ምርመራ ነው የሚደረግለት?

ዶክተር ዘነበ፡- በተለይም ቅፅበታዊ በሆነ መልኩ ከሆነ የተከሰተው የደም ስር ችግር መሆኑ ጥርጥር የለውም። እናም አንጎል እንዲጠና ይሆናል፤ ለእዚህ ጥናት ደግሞ እንደ ሲቲ ስካን፤ ኤም አር አይ እና መሰል የዘመኑ ቴክኖሎጂ የወለዳቸው መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ሆኖም ቀስ በቀስ ሰውነቱ እየደነዘዘ ምላሱ እየተያዘ የመጣ ከሆነ ግን የአንጎል ላይ የሚበቅሉ እጢዎች ናቸው ተብሎ ስለሚገመት ተዛማጅ የሆኑ ምርመራዎችና ህክምና ይሰጣል ይህም ሙሉ በሙሉ በአገሪቱ መስጠት የሚቻልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- ኅብረተሰቡ «የወገብ ህመም፤ የነርቭ እንዲሁም የሰውነት መደንዘዝ ገጥሞኛል» በማለት በየአካባቢው ያሉ ሴራጂም መታሻዎችን ይጠቀማል። ይህ ሙሉ በሙሉ ከሕመም ያድናል? ወይስ ጊዜያዊ ማስታገሻ ብቻ ነው?

ዶክተር ዘነበ፡- አዎ ይህ ጥያቄ በጣም ጥሩና ወቅታዊ ነው፤ በየጊዜው የምንሰማውና የምናያቸው ነገሮች አሉ። እዚህ ላይ የሚያስፈልገው እውነቱን መናገር ነው። ምክንያቱም ብዙዎች ጠቃሚ እየመሰላቸው ራሳቸውን ለተለያዩ ችግሮች ብሎም በቀላሉ ሊድን የሚችል በሽታቸውን እያባባሱ ስለሚገኙ። እኔ ይህን የሴራጂም ጉዳይ ሁልጊዜ የማመሳስለው ከወጥ መሥራት ጋር ነው። ወጥ ውስጥ ሽንኩርትን ጨምሮ የተለያዩ ማጣፈጫዎች እንደሚያስፈልጉት ሁሉ እዚህ ህክምና ላይም የሚያስፈልጉና መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች አሉ። ለወጡም ሆነ ለህክምናው የሚያስፈልጉ ነገሮች መኖራቸው ባይካድም አሁን እያስቸገረ ያለው የቅደም ተከተል ጉዳይ ነው። ወጡ ሲሠራ አንዱ ነገር እንኳን ቢዛነፍ ወይም መቅደም ያለበት ቀርቶ መዘግየት የሚችለው ቢቀድም ጥሩ ወጥ ሊሆን አይችልም። ሴራጅምም እንደዛው ነው። «ህክምናው ያስፈልጋል?» አዎ ያስፈልጋል ሆኖም «መቼና እንዴት» የሚለው ግን ከፍተኛ ትኩረት ይሻል።

ሴራጂም በሚያስፈልግበት ጊዜም ቢሆን ቅደም ተከተልን መጠበቅ ያስፈልጋል። ሆኖም ቅደም ተከተሎቹ እየተዛነፉ በመሆናቸው ችግሮች እየተፈጠሩ ነው። በመሰረቱ ኦፕሬሽን ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ህመሞች ላይ ሴራጂም መጠቀም በጥብቅ የተከለከለ ነው። ስለዚህ መጀመሪያ ሰውየው ለመታሸት ከመሄዱ በፊት «የእኔ ችግር የቱ ነው ብሎ መለየት ያስፈልገዋል። ግን ወገቤን አመመኝ ስላለ ብቻ ህክምናውን ከሴራጂም መጀመሩ ጥፋት እንጂ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።

የጡንቻ ችግር ከሆነ ሴራጂም ከህክምናው አንዱ በመሆኑ ሊያስፈልግ ይችላል። ምክንያቱም ማሽኑ ጡንቻዎችን የማፍታታት ጠቀሜታ ስላለው ነው። ሆኖም ከእዚህ ያለፈ ጠቀሜታ ስለሌለው እዚህ ላይ ሊያበቃ ይገባል «ኦፕሬሽን ያስፈልገዋል» የተባለን ሰው ሴራጂም ማሳሸት ግን ማጥፋት፣ ማበላሸትና የከፋ ጉዳትን ማምጣት ነው። በመሆኑም መቅደም ያለበት ነገር «ይህ ሰው ህምሙ ምን ዓይነት ነው? ደረጃውስ? ምንዓይነት ህክምና ነው የሚያስፈልገው?» የሚለውን ማጣራት ያስፈልጋል።

በየአካባቢው፣ በየመኖሪያ ቤቱ ይህን ዓይነት ሥራ የሚሰሩ አካላት ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል። በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤም መቀየር አለበት። ምክንያቱም «ጎረቤቴ በእዚህ ነው የዳነው» ብሎ ብቻ ህመም ስለተሰማ ወደ ሴራጅም መሄድ ፈፅሞ የተሳሳተ ነው። መጀመሪያ ያለብንን ችግር ብሎም የህመማችንን ደረጃ እንለይ።

አዲስ ዘመን፡- ሰዎች በተለይም በዲስክ መንሸራተት ጉዳይ በጣም ይሰቃያሉ። ህክምናው እንዳለም አያውቁም። እውን ህክምናው ፈዋሽ ነው?

ዶክተር ዘነበ፡- ይህ አመለካከት እጅግ የተዛባ ነው «ዲስክ መንሸራተት መፍትሔ አለው፤ የተንሸራተተው ነገርም ወደ ቦታው እንዲመለስ ማድረግ ይቻላል። አንድ ሴንቲ ሜትር በሆነች ቀዳዳ አማካይነት የተንሸራተተውን ዲስክ በማውጣት ሰውየውን ከህመም ውጪ ማድረግ ይቻላል። ህክምና ከሚሰጥባቸው ችግሮች ውስጥ እንደውም በጣም ቀላሉ የዲስክ መንሸራተት ነው። ሆኖም ሰዎች ዲስካቸውን አንሸራተው ህመማቸውን ተሸክመው 10 ዓመትና ከዛ በላይ ይቆያሉ። ከእነዚህ ይልቅ ህመማቸውን በቶሎ ይዘው የመጡ ደግሞ ከሚባለው በላይ ውጤታማ ይሆናሉ።

አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ያለው የጭንቅላት፤ ህብለሰረሰርና ነርቨ (ኒውሮሎጂ) ህክምና ምን ደረጃ ላይ ነው? ብሎም የኢትዮጵያ ነርቭ ቀዶ ህክምና ማኅበርስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት አንፃር ሚናው ምን ይመስላል?

ዶክተር ዘነበ፡- ይህ የሙያ ዘርፍ ሥራ የጀመረው በኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች የዛሬ 22 ዓመት ነው። ነገር ግን እስከ ቅርብ ጊዜ አይታወቅም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ከሌላው የጤና ዘርፍ ጋር ሲነፃፀር በጣም መሣሪያዎችን የሚጠይቅ መሆኑ ነው። በአሁኑ ወቅት የሲቲ ስካን፤ኤም አር አይና መሰል የመመርመሪያ መሣሪያዎች ወደ አገር ውስጥ መግባት ህክምናው እንዲታወቅ አድርጎታል። የእነዚህ መሣሪያዎች እንደ ልብ አለመገኘት ደግሞ ብዙኃኑን ለችግር ሲያጋልጥ ጥቂት ገንዘብ ያላቸው ሰዎችም ቢሆን በከፍተኛ ችግር ከአገር ውጭ ወጥተው ታክመው የሚድኑበት ሁኔታ ነበር። እነዚህ ነገሮች ሳይኖሩም ቢሆን አንዳንድ ህክምናዎች ይሰጡ ነበር መሣሪያው ከመጣ በኋላ ግን የተሻለ ህክምና መስጠት ተችሏል። ብዙ ታካሚዎች አገልግሎቱን እያገኙ ነው።

በኒውሮሰርጀሪ ዘርፍ ብዙ ዓለም አቀፍ ማኅበራት አሉ። እነዚህ ማኅበራት ደግሞ ያደጉ አገራትን ችግሮች ፈትተው እርዳታን ለማድረግ ለማገዝ በማደግ ላይ ወዳሉት አገሮች ዞረዋል። ለመታገዝና ለመረዳት ደግሞ እኛም በማኅበር መደራጀት ነበረብን። በአሁኑ ወቅትም ማህበሩ ዓለም አቀፉን የኒውሮ ሰርጀሪ ማህበር አባልነት በመጠየቅ ተባባሪ አባል ሆኗል። የተለያዩ ውድ የህክምና መሣሪያዎችን በልገሳ መልክ አስገብቷል።
ከእዚህም ባሻገር ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር እ ኤ አ ከ 2006 ጀምሮ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል። በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ሦስት ስፔሻሊስቶች ሲኖሩ በስልጠና ላይ ደግሞ 17 የሚጠጉ ባለሙያዎች አሉ። በመሆኑም የሙያ ማህበሩ ትልቅ አስተዋጽኦን እያደረገ ነው። በቅርቡም 28 ዓለም አቀፍ ሙያተኞችን ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት ስልጠና እንዲሰጡ ተደርጓል። በቀጣይም ሰልጣኞች የተለያዩ አገሮችን ልምድ እንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮግራም ተፈራርመናል።

አዲስ ዘመን፡- ኅብረተሰቡ ከእነዚህ በሽታዎች እንዲርቅ ህክምና ያገኙ ሰዎችም ዳግም እንዳይከሰትባቸው ምን ማድረግ ይገባል?

ዶክተር ዘነበ፡- ዋናው ነገር ይህ የጤና ችግር ህክምና እንዳለው፣ በአገሪቱም ህክምናው እንደ ሚሰጥና ታክሞ መዳንም እንደሚቻል ማወቅ ነው። ሆኖም ልንከላከላቸው የምንችላቸው ነገሮች ላይ ኅብረተሰቡ ትኩረት ማድረግ አለበት፤ የእርግዝ ናሂደት ክትትልና ምክክር ሁሌም እንደሚነገረው በህክምና ተቋም መሆን አለበት። ይህ ከብዙ የጤና ችግሮች የምንድንበት ነው፤ ሌላው በጭንቅላት፤ በህብለ ሰረሰር ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ልንከላከል ይገባል፤ ክብደት ያለው ሥራ የሚሰሩ ሰዎችም ለራሳቸው መጠንቀቅ አለባቸው። ከመሬት ዕቃዎችን ማንሳት ካስፈለገ ጉልበትን አጥፎ መሬት ቁጭ ብሎ ማንሳት ያስፈልጋል። ወገብን አጥፎ ዕቃ ማንሳት ለችግር ያጋልጣል፤ ረጅም ሰዓት መቀመጥና መቆምም ችግር ያመጣል። በኮምፒዩተርና ተመሳሳይ ሁኔታ ሥራዎችን አቀርቅረው የሚሠሩ ሰዎችም በአከርካሪያቸው ላይ ችግር ስለሚከሰት ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ አንዳንድ የጤና ችግሮች ሲኖሩም እንደ ሴራጂም ያሉ ህክምናዎችን ከመጠቀም በፊት ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- ዶክተር የሚጨምሩት ነገር ካለ?

ዶክተር ዘነበ፡- አዎ አለ። ኅብረተሰቡ ለእዚህ ህክምና ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ነው። ማኅበራችን ደግሞ ይህንን ህክምና በማስተዋወቅ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስገባት ኃላፊነቱን ይወጣል። መገናኛ ብዙኃንም ይህንን ህመምና መፍትሔውን ለኅብረተሰቡ በማሳወቅ የራሳችሁን ኃላፊነት መወጣት አለባችሁ። 
ምንጭ- አዲስ ዘመን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.