ዓይን ያለው ሁሉን ይመለከታል

Preventing-blindnessዓይን ያለው ሁሉን ይመለከታል። ዓይን በአፈጣጠሩ ትንሽ ቢሆንም ከርቀት አሻግሮ ማየት ይችላል። ዘፋኙስ «አሁን አየ አይኔ» አይደል ያለው። ዓይን ለማየት ብቻ ሣይሆን በራሱም ውበት ነው። ስለ ዓይን ገጣሚዎች ግጥም ገጥመዋል፤ ዘፋኞችም ዘፍነዋል ፤ ስንቶቹ በዓይናቸው ውበት ስንቶቹን በፍቅር አማ ለዋል።

ዓይን በተፈጥሮው ጉዳትን መቋቋም የማይችል በመሆኑ ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል «ዓይንና ወዳጅ ትንሽ ይበቃቸዋል» አይደል ተረቱስ የሚለው። እድሜ ለቴክኖሎጂ አሁን አሁን የዓይን ችግር ያለባቸው ሰዎች ሕክምናውን በቀላሉ ለማግኘት የሚቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው። ዓይን በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ላይ ሊወድቅ ይችላል። እንደ ጉዳቱም አስከፊነት አንዳንዱ ታክሞ ሲድን የባሰበት ደግሞ የዓይን ብርሃኑን እስከ መነጠቅ ይደርሳል።

በሀገራችንም ሆነ በሌላው ሀገር ኅብረተሰቡን ለዓይነ ስውርነት እየዳረገ ካለው ሕመም ውስጥ አንዱ የዓይን መስታወት ጠባሳ ነው። ይህ የዓይን መስታወት ጠባሳ ብርሃን ሙሉ በሙሉ እስካልተቋረጠ ድረስ ለችግሩ መፍትሄ አለው። ሕመሙም በሕክምና የሚድን ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች ግንዛቤው ስለማይኖራቸውና የማይድን ስለሚመስላቸው ወደ ሕክምና ሄደው የተነጠቁትን የዓይን ብርሃን ለማስ መለስ ጥረት ሲያደርጉ አይስተዋሉም።

የዓይን መስታወት ነቀላና ተከላን በተመለከተ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የዓይን ሕክምና ኃላፊ እና በዓይን መስታወት ዙሪያ ሰብ ስፔሻላይዝ የሆኑት ዶክተር ኤልያስ ኃይሉን አነጋግረናቸዋል።

የዓይን መስታወት ነቀላና ተከላ የሚከናወነው በዋናነት ከሞተ ሰው በሚለገስ የዓይን መስታወት አማካኝነት ነው። በሰለጠኑት አገራት ሕክምናው መሰጠት የጀመረው ከ100 ዓመታት በፊት ነው። በእኛም ሀገር ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት ይኸው ሕክምና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ተጀምሯል። አሁን ደግሞ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በመቀሌ ፣በጐንደር እንዲሁም በሃዋሳ በሚገኙና በሙያው በሰለጠኑ የሕክምና ባለሙያዎች ይህ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ እየተሰጠ እንደሆነ ዶክተር ኤልያስ ይገልፃሉ።

የዓይን መስታወት ወይንም ብሌን በዓይናችን የፊት ለፊት ክፍል ላይ የሚገኘው በጣም ንጹሕና ብርሃንን የሚያሳልፈው ክፍል ነው። ይህ የዓይናችን ክፍል በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ዓይነት ሥራዎችን ስለሚያከናውን ነው። የመጀመሪያው ተግባሩ በዓይናችን የውስጥ ክፍል አደጋ እንዳይደርስበት ሽፋን ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ ሁለተኛውና ዋነኛው ደግሞ ከርቀት ወደ ዓይናችን የሚመጣውን ማንኛውንም ብርሃን በማጠፍና ብርሃን መቀበያው ላይ ሬቲና የተባለው የዓይናችን ክፍል ላይ እንዲደርስ የሚያደርግ ነው።

የዓይን መስታወት ወደ ጐን ርዝመቱ ከ11-12 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ሲሆን፤ ቁመቱ ደግሞ ከ10-11 ሚሊ ሜትር ርዝማኔ አለው። የዓይን መስታወት የዓይን ኳሱን አንድ አምስተኛ ክፍል የያዘ ነው። ዓይን በአግባቡ እንዲያይ ከተፈለገ የዓይን መስታወት ጥራቱ መጠበቅ ይኖርበታል፤ አለበለዚያ ግን ብርሃን በአግባቡ ወደ ዓይናችን መግባት ስለማይችል የዓይናችን ብርሃን የማየት ችሎታ በጣም ያሽቆለቁላል ብሎም ማየት እስከ አለመቻል ያደርሳል ሲሉ ዶክተር ኤልያስ ያስረዳሉ።

እ. ኤ . አ በ2006 እና 2007 በሀገራችን በተደረገው የዓይነ ስውርነት መንስኤ ጥናት ከዓይን ሞራና ከመነፅር ችግሮች ቀጥሎ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ለዓይነ ስውርነት ምክንያት የሆነው የዓይን መስታወት ጠባሳ እንደሆነ ነው ዶክተር ኤልያስ የተናገሩት።
የዓይን መስታወት ጠባሳ በሁለት ዓይነት ይከፈላል ሲሉ ዶክተር ኤልያስ ይገልፃሉ። አንደኛው በትራኮማ አማካኝነት የሚከሰት ሲሆን፤ ሌላኛው ከትራኮማ ውጪ በሌላ ምክንያቶች የሚከሰት ነው። የሁለቱ ምክንያቶች በአንድ ላይ ተዳምረው ከ15 እስከ 19 ከመቶ ለሚሆነው የዓይነ ስውርነት ምክንያት እንደሆነም ያመለክታሉ። ወደ 300 ሺ የሚሆኑ ዓይነ ስውራን በዚህ ችግር ላይ ሊኖሩ እንደሚችሉ በመስኩ የተደረገውን ጥናት ጠቅሰው ያስረዳሉ።

የዓይን መስታወት ከዓይናችን ፊት ለፊት በመገኘቱ ለብዙ አደጋ የተጋለጠ ነው። ዓይንን ለአደጋ ከሚያጋልጡት መካከል አንዱ በተፈጥሮ የሚከሰት ሲሆን፤ ይህ የሚሆነው ሽሉ በማሕፀን ውስጥ በሚኖርበት ጊዜ እናቲቱ በቂጥኝ፤ በጨብጥ፤ በሳምባ በሽታ እና በመሳሰሉት በሽታዎች ከተጠቃች ሕፃኑ ሲወለድ የዓይን መስታወት ጉዳት ደርሶበት የመወለድ እድል ይኖረዋል።

ሌላው የዓይን መስታወትን የሚያጠቃው ደግሞ ኢንፌክሽኖች ናቸው። እነዚህ ኢንፌክሽኖች ከቫይረስ ‘ ክላሚዲያ’ ከሚባሉትና ትራኮማ ከሚመደቡበት የትራኮማ ክፍሎች ከጀርም ወይም ከባክቴሪያ ሊመጡ ይችላሉ።

እንደ ዶክተር ኤልያስ ‘ ኢንኮሲያኪያሲስ’ አንዱ ለዓይነ ስውርነት መከሰት በምዕራብ አፍሪካ የታወቀ ነው በእኛም ሀገር በሰሜን ምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ወደ ኢሉባቦርና ጐንደር ‘ኢንኮሲያኪያሲስ’ የጉዳት ደረጃው ለዓይነ ስውርነት የሚዳርገው አይደለም። ሆኖም ግን በዓይን መስታወት ላይ ትንሽ ጠባሳን ያስከትላል ይላሉ።

ዓይን ሰበቡ ብዙ ነው የዓይን ጠባሳን የሚያስ ከትሉት እነዚህ ብቻ አይደሉም። በሰውነታችን ውስጥ በሚፈጠሩት የኬሚካል ውህደት አማካኝነትም ማለትም በተፈጥሮ የሚገኙት ኢንዛይሞች ቁጥራቸው ሲጐድል የሚወለደው ሕፃን የዓይን መስታወቱ ጥጥ መስሎ ይወለዳል። ከቁስ አካል ጋር መጋጨት፣ ከባድ ቦክስ፣ ኬሚካሎች ወዘተ በዓይን ላይ በቀላሉ ጉዳት የሚያደርሱ ናቸው።

በኬሚካሎች አማካኝነት ዓይን ላይ ጉዳት ሲደርስ ጉዳት የደረሰበት ሰው ወደ ሕክምና እስከሚሄድ ድረስ ዓይኑን በደንብ አድርጐ በውሃ መታጠብ አለበት። ምክንያቱም የህመሙን ስሜትና የሚደርሰውን ጉዳት በመጠኑም ቢሆን ስለሚቀንሰው ነው።

ጨረርና ከፍተኛ ሙቀት በዓይን ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የዓይን መስታወትን ለማበላሸት የራሳቸው የሆነ ድርሻ ስላላቸው ለእንዲህ ዓይነት ነገሮች ላለመጋለጥ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ። እነዚህ ነገሮች ቀላልና ትንሽ ቢሆኑም የሚያስከትሉት አደጋ ግን በጣም አስከፊ ነው።

የዓይን መስታወት ጉዳት እንዳይደርስበት መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ አስመልክቶ ዶክተር ኤልያስ ሲገልፁ፤ በዓይን ላይ የሚደርሱ ህመሞች የተለያዩ ቢሆኑም አስቀድሞ ወደ ሕክምና በመሄድና የዓይን ምርመራ በማድረግ የዓይንን ጤንነት አስቀድሞ መጠበቁ ወሳኝነት አለው። አክለውም የህመም ስሜት ከተሰማ ሕመሙ ሳይባባስ እና ወደ ዓይነ ስውርነት ደረጃ ሳይደርስ ከወዲሁ መቆጣጠር ይቻላል። በተለይ ደግሞ በኢንፌክሽን አማካኝነት የሚከሰቱትን ፊታችንን በቀን ሁለት ጊዜ በሳሙና መታጠብ አንዱ መፍትሔ ነው።

በፋብሪካ ውስጥ ከኬሚካል ጋር በተያያዘ የሚሰሩና በብየዳ ሥራ ላይ ያሉ ሰዎች ጉግል መነፅር በማድረግ ዓይናቸውን ከአደጋ መታደግ እንዳለባቸው ነው የገለፁት።
በተፈጥሮ ምክንያት የዓይን መስታወቱ ከተጐዳ እና የደም ስር ካልያዙ ጠባሳ ቢኖረውም በቀላሉ በመስታወት ንቅላ ተከላ መስተካከል እንደሚቻል ተጠቅሷል።
የዓይን መስታወት ነቀላና ተከላ እንዴት እንደ ሚከናወን ዶክተር ኤልያስ ሲያብራሩ «የዓይን መስታወት ነቀላና ተከላው በሀገራችን የሚከናወነው በቀዶ ህክምና ነው። በሌሎች በሰለጠኑና ቴክኖሎጂው ባላቸው ሀገሮች የተጐዳውን አካል ብቻ በማውጣት ወይም ጨረር በመጠቀም ህክምናው ይከናወናል።»

የዓይን መስታወት ነቀላና ተከላ ሲባል መስታወቱን ብቻ በክቡ በ7 ነጥብ 5 ወይም 8 ሚሊሜትር ለመስፊያ ቦታ ትቶ ተቆርጦ ይወጣና በዛው ልክ የተዘጋጀው ሌላ መስታወት ይተከላል ማለት ነው።

የዓይን መስታወቱ ነቀላና ተከላ ከተካሄደ በኋላ ህክምናውን ያገኙ ሰዎች ለዓይናቸው ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ባለሙያው ይናገራሉ። ንቅለ ተከላው ከተካሄደ በኋላ ስፌቱ በጣም ቀጭን በሆነ ክር ውሃ በማያሳልፍ መልኩ በጥንቃቄ ከዓይን ጋር ተመሳስሎ ይሰፋል፡፡ መስታወቱ በተፈጥሮው ምንም የደም ስር ስለሌለው ከዓይናችን ጋር ለመዋሀድ ዓመታት ይፈጃል። ሕክምናው የተደረገለት ሰው ምንም ሳይዘናጋ ሐኪም ባዘዘው መሠረት ቢያንስ ለዓመታት የሐኪም ክትትል ማድረግ አለበት።
በተለይ ደግሞ ዓይናቸውን እንዳያሹት በማለት አጥብቀው አሳስበዋል። ከሕክምናው በኋላ ዓይኑ እየዳነ ሲመጣ ክሮቹ ቀስ በቀስ እንዲወጡ ይደረጋል።

እይታው ምን ያህል አስተማማኝ ነው ለሚለው ጥያቄ የተሰጠው መልስ የዓይን መስታወት ነቀላና ተከላ እስካሁን የተዋጣላቸው ከሚባሉ የቀዶ ሕክምና አንዱ ነው። የሆኖ ሆኖ ቀዶ ህክምና የተደረገለት ሰው በተፈ ጥሮው ሊያየው ከሚችለው እይታ ጋር እኩል ይሆናል ተብሎ ለማሰብ ያስቸግራል ምክንያቱም ከዓይን ጠባሳው ባሻገር የዓይን ሞራ የብርሃን መቀበያ ችግሮች አስቀ ድመው ህመምተኛው ካለበት እይታውን ሊቀንሰው ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሕመምተኛው ሌላ የከፋ ችግር ከሌለበት ካለማየት ወደ ማየት ይሸጋገራል ሲሉ ያስረዳሉ። የዓይን መስታወት ከሌላ ሰው ላይ ተነቅሎ የሚተከል ቢሆንም በሚተከልለት ሰው ላይ የሚያ ስከትለው ችግር እንደሌለ ነው የተናገሩት።
« የዓይን መስታወት የሚወሰደው ሕይወቱ ካለፈ ሰው ነው ይህ የዓይን መስታወት ለሌላ ሰው ከመተካቱ በፊት መስታወቱ ምርመራ ይደረግበታል። ንፁህና ምንም አይነት ችግር ከሌለበት በዓይን ባንክ እንዲቀመጥ ይደረጋል።
«ከዚህ ባሻገር ከዓይን መስታወቱ ጀርባ ያሉ በጣም ልዩ የሆኑ ‘ ኢንዶቴልያል ‘ ተብለው የሚጠሩና የዓይን የማየትን መጠን የሚያረጋግጡ ሴሎችን ቁጥራቸው በተለየ ማሽን ይቆጠራሉ። ከተቆጠሩ በኋላ ንፅህናቸው ከተረጋገጠ ለአገልግሎት ይውላሉ፡፡ እነዚህ ሴሎች ግን እድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተዳከሙ ስለሚሄዱ የወጣቶች ዓይን መስታወት ቢሆን ይመረጣል።

ከቀዶ ህክምና በኋላ ሕክምናው የተደረገለት ሰው የሚያጋጥም ምንም ችግር የለም። እንደ ማንኛውም ጤነኛ ሰው ያያል፤ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችንም ማድረግ ይችላል። መስታወቱም የጊዜ ገደብ የለውም ማድረግ የሚገባው ነገር ቢኖር ግጭቶች እንዳይከሰቱ ጠንቀቅነው » ብለዋል።

የማንኛውም ሰው የዓይን መስታወት ለሁሉም ሰው አገልግሎት ይሰጣል፤ በዕድሜ ምክንያት የሚኖር ልዩነት የለም። የትልቁ ሰው ለትንሹ ይሆናል የትንሹም እንዲሁ ለአዋቂዎች ይሆናል።

የዓይን መስታወት ነቀላውና ተከላው ለማካሄድ ታካሚው የሚከፍለው ገንዘብ አለ ፤ክፍያው ግን ለዓይን መስታወቱ አይደለም። «የዓይን መስታወት ዋጋም ሆነ ተመን የለውም» ይላሉ ዶክተር ኤልያስ። የዓይን መስታወቱ የሚቀመጥበት ፈሳሽ ኬሚካል ከውጭ ሀገር የሚመጣ ስለሆነ ለነዚህ ነገሮችና ለሌሎች ተጓዳኝ ሥራ ማስኬጂያ ታካሚው ከ5 ሺ 600 እስከ 7 ሺ ብር ለዓይን ባንኩ ይክፈላል። በተጨማሪም እንደ ማንኛውም ታካሚ ከሆስፒታሉ ለሚያገኘው አገልግሎት እንደሚከፍል ነው የተገለፀው።

በአጠቃላይ ሕክምናው እስከ 10 ሺ ብር ሊደርስ እንደሚችል ነው የጠቀሱትቀደም ሲል ሕክምናው በሀገር ውስጥ በማይሰጥበት ጊዜ ውጭ ሄዶ ለመታከም ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው። በውጭው ዓለም ለዚህ ህክምና ብቻ ከ10 ሺ -20 ሺ የአሜሪካን ዶላር ይከፍላሉ።

ሕክምናውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችሉ መሳሪያዎች አስፈላጊ እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም የህክምና መሳሪያዎቹ በበቂ ሁኔታ ስለመሟላታቸው ለተጠየቀው ጥያቄ የሕክምና ባለሙያው እንደመለሱት ህክምናው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከተጀመረ 6 ወራት ቢሆነውም ህክምናውን ለማድረግ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በለገሱት እርዳታ የተገኘ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ተሟልተዋል ባይባልም ህክምናውን ለማካሄድ በቂ ናቸው። የመስታወት መቁረጫ ምላጮች ግን እጥረት እንዳለ ነው የተናገሩት፤ ምላጩ አንዴ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ስለማያገለግል እንዲሁም በሀገራችን በገበያ ላይ ስለሌለ ውጭ ከሚኖሩ ጓደኞ ቻቸው እየጠየቁ አገልግሎቱን እየሰጡ መሆኑን ነው የገለፁት። ከሁሉም በላይ የሰዎችን ብርሃን ተመልሶ ማየቱ አስደሳች ነው ሲሉም ይናገራሉ።

የዓይን ብርሃንን መመለስ ቀላል አይደለም የችግሩን አስከፊነት በይበልጥ የሚያውቁት በችግሩ ውስጥ ያሉት ሰዎች ናቸው። እነዚህን ሰዎች ለመታደግ ሥራው ተጀምሯል። ስራውን በስፋት ለመስራትና በችግሩ ውስጥ ያሉትን ሁሉ ለማዳረስ አቅም ያላቸው ግለሰቦችም፣ ኮሌጁም፣ መንግሥትም አብሮ መሥራት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

የዓይን መስታወት ሕክምና በሀገራችን መሰጠት መጀመሩ ሰዎች ተመልሰው ብርሃናቸውን እንዲያገኙ እያደረገ ነው። በዓይን መስታወት ጠባሳ የተጠቁ ሰዎች ህክምናው በሀገሪቱ እየተሰጠ መሆኑን አውቀው ወደ ሕክምና ቢሄዱ መልካም ነው። ጅማሬውም የሚያበረታታና ተስፋ ሰጪ በመሆኑ መንግሥትም ለጋሽ ድርጅቶችም ለባለሙያዎቹ ድጋፍ ቢያደርጉላቸው ከአገራዊ ጥቅም ባሻገር ለህብረተሰቡ አገልግሎቱን በሰፊው ለማዳረስ ስለሚያስችል ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።

የዓይን ብርሃን አንዴ ከጠፋ በስጦታ የማይገኝ በመሆኑ ህብረተሰቡም ለዓይኑ የሚሰጠው ግምት ከምንም በላይ መሆን ይኖርበታል። ዓይን ተጐድቶ መዳን የማይችልበት ደረጃ ከደረሰ በምንም ህክምና ሊስተካከል ስለማይችል ከወዲሁ መታሰብ ይኖርበታል።

ባለሙያዎቹ ህክምናውን በሀገራችን በመጀመራቸው በውጭ ሀገር ሄዶ ህክምናውን ለማድረግ የሚወጣውን ገንዘብ፣ እንግልት አስቀርተዋልና ሊበረታቱ ይገባል።(ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ድረ¬ ገፅ ያገኘነው ነው።)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.