‹‹ቫይረሱ በደሜ ውስጥ መኖሩን እየነገርኳቸው”

‹‹ቫይረሱ በደሜ ውስጥ መኖሩን እየነገርኳቸው ደንገጥ እንኳን ሳይሉ ካለ ኮንዶም ወሲብ መፈጸም እንደሚፈልጉ የገለጹልኝ ብዙ ናቸው፡፡hivtransmissionኮንዶምማ የማይታሰብ ነገር ነው ይላሉ፡፡ በእንቢታቸው ጸንተውና ደብድበውኝ ካለኮንዶም የፈለጉትን የፈጸሙ አሉ፤›› ያለችን የሃያ ሰባት ዓመቷ ሴተኛ አዳሪ ነች፡፡

የፊቷ ጥራት፣ አለባበሷ፣ እርጋታና ፈገግታዋ እንክብካቤ በበዛበት ቤተሰብ ውስጥ በምቾት ማደጓን እንዲገምቱ የግድ ይላል፡፡ የእሷ ሕይወት እውነታ ግን ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው፡፡ የተወለደችው አዲግራት ከተማ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ የመጣችው በሕፃንነቷ ነው፡፡ የአሥራ ሁለት ዓመት ታዳጊ ሳለች በአክስቷ ባል ተደፍራለች፡፡ የባለቤቷን ኃጢአት በመሸፈን ትዳሯን ከመፍረስ ለመታደግ በወሰነችው አክስቷ ምክንያት ሰባት ዓመታትን ከልጅነት ጓደኛዋ ቤት ውስጥ ባልበረታ ሰውነቷ የቤት ሠራተኛ ሆና አሳልፋለች፡፡ በዕድሜም ሆነ በአካል የልጃቸው እኩያ ብትሆንም የጓደኛዋ ወላጆች እንደ ቤት ሠራተኛ፣ እንደ አገልጋይ እንጂ እንደ ልጅ ሊያስጠጓት አልወደዱም፡፡ እሷ ግን ‹‹የምሔድበት ባልነበረኝ ወቅት ያስጠጉኝ በመሆናቸው እነሱን የምወቅስበት አንደበት የለኝም፤›› ትላለች፡፡ 

ነፍስ ካወቀች ለመጀመርያ ጊዜ በሕይወትዋ አንዳች የብርሃን ጭላንጭል አየች፡፡ በጣም የሚወዳትና ከነበረችበት አስቸጋሪ ሕይወት ሊያወጣት የሚችል አንድ ሰው አገኘች፡፡ ዛሬ በሕይወት የሌለው የሁለት ልጆቿ አባት ታክሲ ነበረችው፡፡ ዕለት በዕለት ያገኘውን ገንዘብ በሙሉ ለባለቤቱ የሚያስረክብ ትሁትና ለጋስ ነበር፡፡ እሷም የሚሰጣትን ለነገ ሳትል ለቤተሰቡ በሚያስፈልጉ ነገሮች ላይ በማዋል ይህ ነው የሚባል ጥሪት ማፍራትን አንድም ቀን አስባው አታውቅም፡፡ 

ስለ ባለቤቷ ብዙ መናገር አልቻለችም፡፡ አቀረቀረች፡፡ እንባዋ ዱብ ዱብ እያለ ፊቷ በእንባ ይታጠብ ጀመር፡፡ ባለቤቷን ስታስብ በአንድ በኩል ቅንነቱ፣ በሌላ በኩል ‹‹ጥፋቱ›› አንድ ላይ ወደ አእምሮዋ መጣ፡፡ ‹‹ኖሮ አንዲት ጥያቄ ብጠይቀው እላለሁኝ ሁሌ፡፡ እቆጫለሁ ግን ደግሞ ልወቅሰው አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ኖሮ እንዲህ ነው ያላልኩትን በሕይወት የሌለ ሰው ዛሬ እንዲህ አጥፍቷል ማለት ከባድ ነው፡፡››

የመጀመርያ ልጇ ሰባት ዓመቱ፣ ሁለተኛዋ ደግሞ ሦስት ዓመቷ ነው፡፡ ባለቤቷ ከአራት ዓመታት በፊት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ ደርሶ በነበረ የመኪና አደጋ ሕይወቱ ሲያልፍ እሷ የሁለት ወር ነፍሰጡር ነበረች፡፡ ባለቤቷ በሕይወት እያለ ታክሲዋ የራሱ እንደሆነች ነግሯታል፡፡ የሚገኘውን ገቢም ይጠቀሙበት የነበሩት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ሞቱን ተከትሎ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወላጆቹ “የእኛ ንብረት ነው” በማለት ታክሲውን ወሰዱ፡፡ የባለቤቷ ድንገተኛ ሞት ድንጋጤ ሳይለቃት መጠለያ ማግኘቷ፣ መልበስና ጐርሳ ማደሯም ወዲያው ከጥያቄ ውስጥ ወደቀ፡፡ ይህም ሳይበቃ ሌላ ፈተና ገጠማት፡፡ ታመመች፡፡ ሰባተኛ ወሯ ላይ ስትመረመር የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደሟ ውስጥ መኖሩ ተነገራት፡፡

‹‹የመጀመርያ ልጄን እርጉዝ ሆኜ ተመርምሬ ነጻ መሆኔን አውቄ ነበር፤›› በማለት ከባለቤቷ ውጭ ግንኙነት ፈጽማ እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡ የተደላደለው ኑሮዋ በአንድ ጀምበር በየአቅጣጫው ይፍረከረክ ያዘ፡፡ ይኖሩበት ከነበረው ደህና ቤት ወጥታ እዚያው ግቢ ካለች ሌላ ጠባብ ቤት ገባች፡፡ በዚያው ግቢ ተከራይታ ትኖር የነበረች ሌላ ሴተኛ አዳሪ ምክርን ያለማቅማማት በመቀበል ሁለተኛ ልጇን ወልዳ አርባ ቀን ሳይሞላት፤ ጡቷ እየፈሰሰ ገላዋን ሸጣ ለማደር አደባባይ ወጣች፡፡ በአንድ ዓመት የመጠጥ ቤት ቆይታዋ የባሏ ውሽማ ከነበረች ሴተኛ አዳሪ ጋር በአጋጣሚ ተገናኘች፡፡ 

‹‹ፎቶግራፉን አይታ አረጋገጠችልኝ፡፡ ከዚያች ዕለት በኋላ ያን መጠጥ ቤት ጥዬ በመውጣት መንገድ ላይ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ነገሮችን መለስ ብዬ ስመለከት በመጨረሻዎቹ ጊዜያት ባለቤቴ ካለ ሰዓቱ በጊዜ መግባት፣ መሸት ሲል ደግሞ ሌሊት ለመሥራት የተነጋገርኳቸው ሰዎች አሉ፣ ጫት አደርሳለሁ እያለ ያመሽ ያድር ጀምሮ ነበር፡፡››

ምንም እንኳ ዛሬ ላይ በወር ለልጆቿ ትምህርት ቤት የሚከፈለውን 480 ብር ለመሸፈን ቢያስችላትም ገላን ሸጦ ማደር ከሌሎች ሴተኛ አዳሪዎች በተለየ መልኩ ከብዷታል፡፡ በጠዋት ለልጆቿ ትምህርት ቤት መድረስ ስላለባት ደንበኞቿ ወደሚፈልጉት ቦታ ርቃ መሔድ አትችልም፡፡ ከገንዘብ ባሻገር ለሷ አካባቢም ድርድር የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ ጠዋት አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ከቤት ደርሳ ልጆቿን ማለባበስ፣ ቁርስ ማብላት፣ ምሳ መቋጠርና ትምህርት ቤት ማድረስ አለባት፡፡ አመሻሽ ላይ ለማግስቱ የሚሆን ምግብ ማዘጋጀት፣ ልጆቿን ማጣጠብና ራት ማብላትም ይጠበቅባታል፡፡ 

‹‹የተከራየሁበት ቤት ባለቤቶች ቤታቸው ጠባብ በመሆኑ ሠራተኛቸው እኔ ጋ እንድታድር ጠይቄያቸው እሺ አሉ፡፡ ሌሊት ልጆቼን እየጠበቀች አብራ ታድርልኛለች፡፡›› ወጣቷ ዕረፍት ከማጣቷና ከመንገላታቷ ይበልጥ ችግር የሆነባት አንዳች ነገር አለ፡፡ በዚህም ታዝናለች፣ ታለቅሳለች፣ ትፀፀታለች፣ ፈጣሪዋን ታማርራለች፤ ሌሎችንም ትወቅሳለች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ ይህ ችግር እንቅልፍ ከማጣቷ፣ ከመንገላታቷ ሁሉ የከፋ ነው፡፡ የሕመም ስሜት እየተሰማት ሰውነቷ እየተንቀጠቀጠ ረዥም ሰዓት በብርድ መቆምን፣ ታማ በላብ ተዘፍቃ ከተኛችበት አልጋ ተነሥታ መውጣትንም ተቋቁማዋለች፡፡ የልጆቿን ለምንድን ነው እቤት የማታድሪው? ቀን ቀን የማትሠሪው? ጥያቄም ችላዋለች፡፡

‹‹በቦርሳዬ የምይዘውን መድኃኒት እስከማሳየት፣ የልጆች እናት መሆኔንና ታሪኬን እስከመንገር የደረስኩባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ቫይረሱ በደሜ ውስጥ መኖሩን ለማሳመን፡፡ እሺ አይሉኝም አያምኑኝም፡፡ አንገቴ ላይ ሁለት ሦስት ቦታ የነከሰኝ ሰውም አለ፡፡ እስከዛሬ አንድ ሰው ብቻ ነው ጠዋት ላይ ‘እውነትሽን ነው ማታ የተናገርሽው?’ ብሎ የጠየቀኝና ቤቴ ድረስ በመሔድ ሕይወቴን ለማየት የሞከረው፡፡ ሕይወቴ በብዙ ፈተና የተወጠረ ነው፡፡››

ለብዙዎች የጎሕ መቅደድ ሁሌም ብራ፣ በጎውን ተስፋ ተመኝተው ከቤት የሚወጡበት ነው፡፡ ለእሷ ግን ንጋት በሐዘንና በፀፀት እያነባች ወደ ቤት የምትመለስበት ነው፡፡ ዘወትር ስለራሷ፣ ስለ ልጆቿም ታነባለች፡፡ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ መኖሩን እየነገረቻቸው አሻፈረን ብለው በኃይል ያለኮንዶም ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች ጥቂት አለመሆን ከጥልቅ ሐዘን ውስጥ ከቷታል፡፡ ‹‹ከቤቴ ጧት የምደርሰው በቫይረሱ መያዛቸውን እያሰብኩኝ በሐዘን እያነባሁ ነው ልጆቼን የሚያስተምርልኝ ባገኝ እኮ ፊቴን ወደዚህ ሥራ በጭራሽ አላዞርም ነበር፤›› በማለት ከማስገደድ ይልቅ ያለ ኮንዶም ግንኙነት ለመፈጸም ብትስማማ የሚሰጧትን ገንዘብ እጥፍ እንደሚያደርጉላት ቃል የሚገቡላት ጥቂት እንዳልሆኑ ትናገራለች፡፡ 

ቫይረሱ በደሟ ውስጥ መኖሩን እየተናገረችና በተለያየ መንገድ ለማሳመን እየሞከረች እሷ የዚህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟታል፡፡ ምን ያህል ሴተኛ አዳሪዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን በግልጽ ይናገራሉ? ‹‹አንገቴ በንክሻ እስኪቆስል ድረስ እየደበደበኝ የነበረውን ሰው ለማትረፍ ሞክሬያለሁ፡፡ ግን አልሆነልኝም፡፡ እዚህ ድረስ ገፍቶ የማይሔድ፣ ገንዘብ የሚያታልለው ሰው ቢኖርስ? ብዬ ሳስብ ያስፈራኛል ከቫይረሱ የሚተርፍ ያለ አይመስለኝም፡፡›› 

ቫይረሱ በደሟ ውስጥ መኖሩን እየነገረቻቸው ያለ ኮንዶም ወሲብ ለመፈጸም የሚያስገድዷት ወንዶች ምን ዓይነት እንደሆኑ ጠይቀናታል፡፡ የተማሩ፣ ውጭ አገር የሚመላለሱ፣ ወጣት፣ አዛውንት… የተለያዩ ወንዶች ቫይረሱ በደሟ ውስጥ መኖሩን ስትነግራቸው፣ ‹‹ውሸትሽን ነው›› ብለዋታል፡፡ በማስገደድም ይሁን በገንዘብ ሸንግለው የልባቸውን ለመፈጸም ሞክረዋል፡፡ የተሳካላቸውም አሉ፡፡  (ሪፖርተር)

1 COMMENT

  1. yele condom sex lanichim chimir betam adega alew , lemin drug resistace yehonu yeteleyayu virus ziriyawoch ke’anidu tamami wade lelaw tamami yitelalefalu betechemarim besex litelalefu yemichilu bizu beshita amichi tewasiyan yegubet beshitan chemiro ,,,silezih irasishinim iyetebekish wegenishinim tebiki E/her kanichi gar yihun !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.