በመላኩ ብርሃኑ

አቶ ፃዲቁ ጴጥሮስ ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገለ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በ1996 ዓ.ም የሚሰራበት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት የጭሮ ቅርንጫፍ ወኪል ሆኖ በሚያገለግልበት ወቅት ወደአንድ ወረዳ ለስራ ሲሄድ የመኪና በር ጉልበቱን ይመታዋል፡፡ የጭሮ ሆስፒታል ለተሻለ ህክምና ለጥቁር አንበሳ ሪፈር ቢጽፍለትም የመጓጓዥና የህክምናው ወጪ ለመሸፈን አቅም ስላልነበረው ችላ ብሎ ተወው፡፡ በ2001 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ስራ ላይ እያለ በመውደቁ ያ ያደፈጠ የጉልበት ህመሙ ተቀስቅሶበት 2002 ዓ.ም ሙሉውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ማሳለፉን ይናገራል፡፡ “ከጭሮ እየተመላለስኩ መታከሜ፣ ለህመሜ የሚታዘዝልኝ የምርመራና የመድሃኒት ዋጋ የባልደረቦቼ እርዳታም ተጨምሮበት ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎኝ ነበር። በመጨረሻ እግሬ በዘላቂነት አልዘረጋ ብሎ በመቅረቱ የህክምና ቦርዱ ቀላል ስራ ላይ ብቻ እንድመደብ ሲወሰንልኝ ለህክምና ማስረጃው መክፈል የነበረብኝን 300 ብር ለማግኘት እንኳን ተቸግሬ ነበር፡፡” ይላል።

helath-hosጋዜጠኛ ፃድቁ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረውን የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት በደስታ ተቀብሎታል፡፡ “ያኔ የጤና መድን ሽፋን ቢኖረኝ ኖሮ ህክምና ቀደም ብዬ እጀምር ስለነበር ለዛሬው አካል ጉዳት አልዳረግም ነበር” ነው የሚለው፡፡ “ይህ እኮ ዘመናዊነት ነው፡፡ ዛሬ ትንሽ ብር አዋጥተህ ነገ ከባድ ህመም ሲገጥም ያልሠቀቀን መታከም የምትችለው እንዲህ ዓይነት የጤና ዋስትና ሲኖርህ ነው፡፡ እንኳን ለራሴ ለባለቤቴና ለልጆቼ የሚተርፍ ዕድል ስለሆነ ተግባራዊ እስኪሆን ጓጉቻለሁ።በተለይ ጡረታ ስወጣም ጭምር የዕድሉ ተጠቃሚ እንደምሆን በመረዳቴ ደስ ብሎኛል። ያሣለፍኩትን መከራ የማውቀው እኔ ነኝ፡፡” ይላል።

በዚሁ ድርጅት በስልክ ኦፕሬተርነት ላለፉት 22 ዓመታት ያገለገሉት የወ/ሮ አባይነሽ በየነ አስተያየት ግን ከዚህ የተለየ ነው። በበኩሌ ገንዘቡ ባይቆረጥብኝ ደስተኛ ነኝ” ይላሉ።ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ያቀርባሉ። አንደኛው የጤና መድን ሽፋኑ ከባድ የጤና ችግሮችን አያካትትም ተብሎ ሲወራ መስማታቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመንግስት ሆስፒታሎች ከወረፋውና መጉላላቱ ባሻገር የሚያረካ አገልግሎት አይሰጡኝም የሚል ስጋታቸው ነው፡፡ “ለመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ስለማህበራዊ ጤና መድን ገለፃ ሲደረግ በአጋጣሚ አልተገኘሁም ነበር የሚሉት ወይዘሮ አባይነሽ “ጓደኞቼ የነገሩኝ ከወር ደመወዜ 3 በመቶ እንደሚቆረጥና የመድን ሽፋኑ ከባድ ህመምን እንደማያካትት ብቻ ነው።እንደዚህ ከሆነ ደመወዜ መቆረጡን እቃወማለሁ” ብለዋል።

ይህ ዘጋቢ ከሳምንት በኋላ ሲያነጋግራቸው ግን ሃሳባቸውን ቀይረው ነበር። “በርግጥ እኔ ራሴ ታማሚ ነኝ። በነርቭ ህመም ሳቢያ እግሬ ላይ በደረሰው ጉዳት 1997 እና 1998 ሙሉውን ጊዜ ህክምና ላይ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ከኪሴ ባወጣሁት ገንዘብ፣የመስሪያ ቤቴ ሰራተኞች ተረባርበው ባደረጉልኝ እርዳታና መስሪያ ቤቴ በከፈለለኝ ግማሽ ዋጋ ነው የካቲት 12 እና ራስ ደስታ ሆስፒታሎች ተኝቼ መታከም የቻልኩት፡፡ አሁንም ሙሉ ጤንነቴ ስላልተስተካከለ ሆስፒታል እመላለሳለሁ።የጤና መድህን ስርዓቱን ጠቀሜታ አስመልክቶ በመስሪያ ቤቴ በድጋሚ በተደረገ ገለጻ የሰማሁት ነገር አስደስቶኛል።ለእንደኔ አይነት አነስተኛ ገቢ ያለው ሰው በየወሩ ጥቂት አዋጥቶ ከትንሽ ህመም እስከቀዶ ህክምና የሚደርስ የጤና አገልግሎት ማግኘት መቻል እድል ነው።” ነበር ያሉት።ወይዘሮ አባይነሽ አሁንም የመንግስት ሆስፒታሎች አገልግሎት ጥራት መሻሻል እንደሚገባው ግን አስተያየታቸውን ሳይሰነዝሩ አለለፉም።

የድርጅቱ የሠው ሃብት ስራ አመራርና ልማት ማስተባበሪያ ሃላፊ አቶ ታዬ ቸርነት በአንድ መስሪያ ቤት የሚሰሩ ሰዎች በማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓቱ ላይ ያላቸውን የተለያየ አመለካከት አንስተው ሲናገሩ “የግንዛቤ ማነስ የፈጠረው ችግር ነው” ይላሉ፡፡ “መረጃውን በሚገባ ማዳረስና የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓትን ጠቀሜታ በተመለከተ በተከታታይ ግንዛቤ መፍጠር ከተቻለ ፕሮግራሙን ደግፎ ለተግባራዊነቱ የሚተጋ እንጂ የሚቃወም ሰራተኛ እንደማይገኝ እርግጠኛ ነኝ” ይላሉ በሙሉ ልብ።

የ ‘ሃምሳ ሎሚ’ ዘመኖች
አቶ ታዬ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር መንግስት ለሰራተኞቹ የህክምና ወጪ የሚሸፍነው ተኝተው ሲታከሙ ለዚያውም ግማሽ ዋጋ ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ በተረፈ ማንኛውም ሰራተኛ ህመም ሲገጥመው ከኪሱ በመክፈል፣ ጉዳቱ የባሰ ከሆነና አቅም ከሌለው ደግሞ ከስራ ባልደረቦቹ እርዳታ በማሰባሰብ ይታከም እንደነበር ይናገራሉ።ይህ የእርዳታ አሰባሰብ ልምድ በሰራተኛው ዘንድ ‘ሃምሳ ሎሚ’ የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። “ሃምሳ ሎሚ እርዳታውን በሚያደርገው ሰራተኛ ላይ በወጪ መደራረብ ከሚፈጥረው ምሬትና እርዳታውን በሚቀበለው ሰራተኛ ላይ ከሚያሳድረው የተረጂነት የስነልቡና ጫና ባሻገር ሌሎች ችግሮችም ያስከትላል።ለምሳሌ ‘ቲፎዞ’ (ብዙ ጓደኞች) ያሉት ሰው ብዙ እርዳታ ሲሰበሰብለት ባይተዋሩ ደግሞ ዘወር ብሎ የሚያየውም አያገኝም።በዚህ ሳቢያ በአንድ መስሪያ ቤት ሰራተኞች መካከል የግንኙነት መሻከርን የሚያስከትል ቂም እና ጥላቻ ይከሰታል፡፡ የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓቱ ሁሉም በአቅሙ እያዋጣ በእኩልነት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ስለሚያደርግ ይህን ሁሉ ችግር ይፈታዋል” ይላሉ።

አቶ ታዬ ለረጅም ዘመን የሰሩበት የሰው ሃይል አስተዳደር ሰራተኛው በህመም ጊዜ የሚደርስበትን ችግር በቅርበት እንዲገነዘቡ እንዳስቻላቸው ይገልጻሉ። “ብዙ ጊዜ ሰራተኛው ህመም ሲገጥመው ደመወዝ እስኪደርስ ይጠብቃል አለያም በሞዴል 6 ከደመወዝ ላይ ቅድሚያ ብድር ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በሽታው በጊዜ መታከም ሲገባው እንዲቆይበትና ለበለጠ ጉዳት እንዲጋለጥ ያደርገዋል፡፡ወደህክምና የሄደ ሰውም እንደ ኤም አር አይ፣ ሲቲ ስካን ወይም ከበድ ያለ የላቦራቷሪ ምርመራና መድሃኒት ሲታዘዝለት መጪውን መሸፈን ስለሚያቅተው አንድም ህክምናውን ያቋርጣል አለያም እርዳታ ይጠይቃል፡፡አንዳንዴም ዛሬ የታዘዘላቸውን መድሃኒት ከ2 ና 3 ሳምንት በኋላ ደመወዝ እስኪደርስ ጠብቀው የሚገዙ ሰራተኞች አሉ።ብዙው ሰራተኛ ደመወዙ አነስተኛ ስለሆነ የቤተሰቡ አባላት ሲታመሙበት የሚያሳክመው በአብዛኛው ከባልደረቦቹ በሚሰበሰብ እርዳታ ነው። የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት ተግባራዊ መሆኑ ሰራተኞችም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በታመሙ ጊዜ ያለምንም መሳቀቅ ወደህክምና ተቋም በመሄድ አገልግሎት እንዲያገኙ ስለሚያስችል ችግሮቹን በሙሉ ያስወግዳል” ብለዋል።

ማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት
“ከእያንዳንዱ እንደአቅሙ፣ለእያንዳንዱ እንደአስፈላጊነቱ”

የጤና መድህን አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ ወይም ክፍያ ግለሰቦች ወይም ቤተሰቦች የጤና መታወክ ባጋጠማቸው ጊዜ ከልታሰበ ከፍተኛ የህክምና ወጪ የሚጠበቁበትና በገንዘብ እጦት ምክንያት በቂ ህክምና ያለማግኘት ስጋትን የሚያስወግድ ስልት ነው።የጤና መድህን ደመወዝተኛ ያልሆኑና መደበኛ ባልሆነ ገቢ የሚተዳደሩትን የህብረተሰብ ክፍሎች በሚያቅፈው ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እና በመንግስት ወይም በግል ድርጅቶች ተቀጥሮ ደመወዝ ተከፋይ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል በሚያቅፈው ማህበራዊ የጤና መድህን ተለይቶ በሁለት ይከፈላል።

የማህበራዊ የጤና መድህን በመደበኛው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ ዜጎችን የሚያቅፍና ትርፍን መሰረት ያላደረገ የመድህን ስርዓት ሲሆን በዚህ የመድህን ስርዓት ሰራተኞችና አሰራዎች በየወሩ የሚያዋጡት ገንዘብ ወደ አንድ ቋት ተሰብስቦ በመግባት የህክምና አገልግሎት የሚፈልጉ ሰራተኞችን የህክምና ወጪ ይሸፍናል።የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት በባህሪው ጤነኛው ታማሚውን፣ የተሻለ ገቢ ያለው አነስተኛ ገቢ ያለውን የሚደግፍበት ስርዓት ነው፡፡ በስርዓቱ መሰረት ሁሉም አባል ከደመወዙ 3 በመቶ የሚያዋጣ ሲሆን ከአሰሪውም 3 በመቶ ጭማሪ ይደረግለታል።አገልግሎቱ ግን ሁሉም አባል ያዋጣውን ገንዘብ ብዛት መሠረት ሳያደርግ እንደ ህመሙ ሁኔታ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት ፍትሃዊ የጤና መድህን ነው። “የማህበራዊ ጤና መድህንን ‘ከእያንዳንዱ እንደአቅሙ ለእያንዳንዱ እንደአስፈላጊነቱ’ በሚል አጭር ቃል ልንገልጸው እንችላለን” ትላለች በባሌ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ሄልዝ ሁለተኛ ዲግሪዋን በመስራት ላይ የምትገኘውና በጤና መድህን ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ለመስራት የምትንቀሳቀሰው ሲስተር መሰረት አሻግሬ። ይህን አባባሏን በምሳሌ ስታስረዳም “ ደመወዙ 3 ሺህ ብር የሆነ ሰው በወር 90 ብር ቢያዋጣ ደመወዙ 500 ብር የሆነ ሰው የሚያዋጣው ደግሞ 15 ብር ይሆናል።ሁለቱም የህክምና አገልግሎት ፈልገው ሲሄዱ ግን ባዋጡት መጠን ሳይሆን በህመማቸው ሁኔታ እኩል በፍትሃዊነት ይስተናገዳሉ።በዚህ ሂደት ባለ 3ሺህ ብር ደመወዝተኛው ባለ 5መቶ ብር ደመወዝተኛውን ደግፎታል ማለት እንችላለን። ለዚህም ነው ስርዓቱ አባላት እርስ በርስ የሚደጋገፉበትና የሚደጓጎሙበት ስልት ነው የሚባለው” ትላለች።

የጤና መድህን በኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው?

በጤና መድህን ስትራተጂው ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የሕዝብ ቁጥር በየዓመቱ በ2.7 ዕድገት እያሳየ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የጤና አገልግሎት ፍላጎትም በዚያው ልክ ጨምሯል፡፡ይህም ለጤና የሚወጣውን ወጪ ከፍ ያደርገዋል።እንደስትራተጂው በ2004/05 (እ.ኤ.አ) ከመንግስት አጠቃላይ ወጪ ውስጥ 5.1 በመቶ የነበረው የጤና ወጪ በ2 ዓመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ በ2006/07 ወደ 11.6 በመቶ አድጓል፡፡እ.ኤ.አ. ከ8 ዓመታት በፊት በ2004/05 የተሰበሰበው ብሔራዊ የጤና መረጃ የሀገሪቱ አጠቃላይ የጤና ወጪ 4.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያመለክታል። የግለሰቦች የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪም በዚሁ ጊዜ ከ 5.6 ዶላር ወደ 7.14 ዶላር ከፍ ብሏል፡፡ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ ያለው የጤና ፋይናንስ ከፍተኛ ጉድለት ያሳያል። ይህን ለማሟላት ግን መንግስት ብቻውን አቅም አይኖረውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የጤና ወጪ 40 በመቶ የሚሸፈነው ከውጭ በሚገኝ እርዳታ ነው፡፡ ይህን የፋይናንስ ጉድለት በመሙላት የፈውስ ህክምና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የሃገሪቱን የጤና ወጪ በጊዜ ሂደት ከእርዳታ ጥገኝነት ነጻ በማድረግ ዘለቄታዊ የሆነ የፋይናንስ ስርዓትን ለመመስረት ከፋይናንስ ምንጮች አንዱ የሆነውን የጤና መድህን ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ይሆናል።

ሌላው የዚህ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊነት የሚመነጨው የኢትዮጵያ ህዝብ የጤንነት ሁኔታ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር ነው።በኢትዮጵያ ሀገራዊ የጤና አገልግሎት ሽፋን ወደ 95 በመቶ የተጠጋ ቢሆንም የህዝቡ ወደጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት የመምጣት ልምድ ግን አናሳ ነው።የአለም ጤና ድርጅት ዝቅተኛ መስፈርት አንድ ሰው በዓመት ከ2.5 እስከ 3 ጊዜ የጤና ተቋማትን መጎብኘት እንዳለበት ያመለክታል።በኢትዮጵያ ግን በ3 ዓመት አንዴም ወደጤና አገልግሎት መስጫ ጣቢያ የሚሄድ ሰው ጥቂት ነው።በዚህ ሳቢያ በሃገሪቱ የህዝቡ አማካይ የዕድሜ ጣሪያ አነስተኛ እንዲሆንና (በ2005 48 ዓመት ነበር) ትርጉም ባለው መልኩ ቢቀንስም የእናቶችና የህፃናት ሞት መጠን አሁንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል። የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ተስፋይ “የህዝቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን ምክንያቱ የአቅም ማነስ ችግር ነው” ይላሉ።ስለሆነም የጤና መድህን ስርዓቱን በመዘርጋት በቀጥታ ከኪስ የሚከፈለውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ከተቻለ የህዝቡ የጤና አገለግሎት ማግኘት ፍላጎትና ወደጤና ተቋማት የመሄድ ልምድም ይጨምራል።በውጤቱም ጤናው የተጠበቀ አምራች ማህበረሰብ መፍጠር ይቻላል ነው የሚሉት።

“እስካሁን ምን ተጎዳንና ? አሁንስ ምን ልናገኝ?”

ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀና በአንድ የግል ኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ በአስተዳደር ኦፌሰርነት የሚሰራና የጤና መድህን ስርዓቱን የተመለከተ መረጃ እንደሌለው የሚናገረው ወጣት “የመንግስት ጤና ተቋማት ክፍያ ዝቅተኛ እንደውም ነጻ ነው ለማለት የተጠጋ በመሆኑ በእኔ በኩል ሰራተኛውም ይሁን አሰሪዎች ለጤና መድን ገንዘብ ማዋጣታቸው ጠቀሜታው አይታየኝም” ይላል። “በአሁኑ ወቅት ማንኛውም ዜጋ የትኛውም የመንግስት ጤና ጣቢያ ወይም ሆስፒታል ከሄደ በአነስተኛ ዋጋ ይታከማል።አገልግሎቱ አመርቂ አለመሆኑን ብስማማበትም እዚያ መታከም ለሚፈልግ ክፍያው ኪስ እንደማይጎዳ አውቃለሁ።መንግስት በጤና መድን የሚሰበሰብውን ገንዘብ ለጤና ተቋማት የሚያደርገውን ድጎማ ለማስቀረት ሊጠቀምበት ካልሆነ በቀር የተለየ ጥቅም ያመጣል ብዬ አልገምትም” ይላል። በጤና መድን ስትራተጂው ላይ ግን ይህ ሃሳብ የተሳሳተ ስለመሆኑ የሚያስረዱ ማብራሪያዎች ተቀምጠዋል።

በሰነዱ ላይ እንደተብራራው የመንግስት የጤና ወጪ መጨመርና ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣት ለጤና መድህን ስርዓቱ መጀመር አንድ ምክንያት ቢሆንም የስርዓቱ መጀመር ግን የመንግስትን ወጪ ያስቀረዋል ማለት አይደለም፡፡ የጤና መድህን ከአጠቃላይ የጤና ክብካቤ ገንዘብ ማግኛ ስልት አንዱ ሆኖ የሚቀጥል እንጂ ብቸኛው ባለመሆኑ አሁንም የጤናው ዘርፍ ወጪ የሚሸፈንበት መንገድ ከመንግስት ወጪ፣ከውጪ እርዳታ(ቢያንስ እስከሚቀጥሉት አስር ዓመታት)፣ከግል ድርጅቶች፣ከግለሰቦችና ከሌሎች ምንጮች የሚገኝ ገቢ ሆኖ ይዘልቃል፡፡ ይህ ስርዓት መንግስት ለጤናው ዘርፍ የሚመድበውን ወጪ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያደርገዋል እንጂ እንዲያቋርጥ እድል አይሰጠውም ። “ሌላው ቀርቶ ይህንን ለማስተባበር የተቋቋመው የጤና መድህን ኤጀንሲ የቢሮ ኪራይና የአስተዳደር ወጪዎች የሚሸፈኑት በመንግስት ባጀት እንጂ ዜጎች በሚያዋጡት ገንዘብ አይደለም” ይላሉ የኤጀንሲው ሃላፊዎች።

የአስተዳደር ኦፌሰሩ በአስተያየቱ ያነሳው የመንግስት ጤና ተቋማት ዋጋ ዝቅተኝነት “እስካሁን ምን ተጎዳንና ገንዘብ እናዋጣለን” የሚል አንደምታ አለው። የጤና መድን ስትራተጂው ግን የመንግስት የጤና ተቋማት ወጪ አሁን ባለው መልኩ እንደማይቀጥል ነው የሚያብራራው፡፡

“አሁን ያለው የጤና አገልግሎት ክፍያ አገልግሎቱን ለማቅረብ ከማያስፈልገው ወጪ ጋር ሲነፃፀር በጣም አንስተኛ ስለሆነ በሂደት አገልግሎቱን ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ወጪ በሚያንፀባረቅ መልኩ የዋጋ ክለሳ መደረጉ የማይቀር ነው…. የአገልግሎት ጥራት ከተሻሻለ በኋላም ቢሆን የአገልግሎት ክፍያን መጨመር የጤና አገልግሎት ፈላጊዎችን ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ጫና በመፍጠር የሚፈልጉትን የጤና አገልግሎት በቀላሉ እንዳያገኙ እንቅፋት መፍጠሩ አይቀሬ ነው” ይላል።

በዚህ ስሌት የመንግስት ጤና ተቋማት አሁን በሚሰጡት የአገልግሎት ክፍያ የማይቀጥሉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዋጋ ክለሳ ሲደረግ “በምን አቅሜ እታከማለሁ” የሚል ስጋት እንዳይፈጠር ከወዲሁ የጤና መድን ስርዓቱ ከዋጋ ክለሳው ጋር በተጓዳኝ እንዲመሰረትና እንዲስፋፋ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።

በጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአስተኝቶ ማከም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ እንደሚናገሩት በአሁኑ ወቅት የመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጡት የህክምና አገልግሎት ወጪ ተገልጋዮች ከማከፍሉት የገንዘብ መጠን ጋር የማይገናኝ ነው፡፡ “ካርድ ማውጫው ሁለት ብር ለካርድ ህትመት የሚወጣውን ገንዘብ እንኳን አይሸፍንም” ይላሉ። ታማሚዎች ለህክምናው ተመጣጣኝ የሆነውን ዋጋ ከኪሳቸው አውጥተው ይክፈሉ ከተባለ የሕክምና ዋጋ ከባድ እንደሚሆን ነው ዶክተር ብርሀኔ የሚናገሩት።

ከላይ አስተያየቱን እንደሰጠው የአስተዳደር ሃላፊው ሁሉ ብዙዎች የመንግስት የጤና ተቋማት የአገልግሎት ጥራት ብዙ ጉድለቶች እንዳሉበት ሲናገሩ ይደመጣሉ። “የጤና መድህን ስርዓቱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ተገልጋዮች ለሚያዋጡት ገንዘብ የሚመጥናቸውን አገልግሎት ያገኙ ዘንድ መዋጮው ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ በፊት ይህ ክፍተት መስተካከል ይገባዋል” የሚሉ አስተያተቶችም ይሰነዘራሉ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ተስፋይ ግን “የአገልግሎት ጥራት በጊዜ ሂደት የሚመጣ ነው” የሚሉት ። “በኢትዮጵያ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የግል ህክምና ተቋማትም ከፍተኛ የጥራትና የብቃት ችግር አለባቸው።ይህ ጥራት እስኪመጣ እንጠብቅ ካልን ዜጎች በህመምና በህክምና እጦት እየተጎዱ እንዲቀጥሉ መፍቀዳችን ነው። ስርዓቱን ዘርግተን የማያቋርጥ የጥራት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በጊዜ ሂደት ሁሉም የሚረካበት አገልግሎት እንዲፈጠር ማድረግ ቀላሉ አማራጭ ነው” ብለዋል።

“መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በሚፈልገው መልኩ ለማቅረብ ትልቁ ችግር ገንዘብ ነው፡፡ በዚህ ሣቢያ የጤና ጣቢያዎችም ሆኑ ሆስፒታሎች ተገቢ የህክምና አገልግሎት ለመስጠጥ የሚያስችላቸው የህክምና መሳሪያም ይሁን የመድሃኒት ግብዓት ከፍላጎቱ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ማግኘት አይችሉም፡፡ የጤና መድህን ስርዓቱ ከተገልጋዮች የሚሰበሰበውን ገንዘብ ከሌሎች ምንጮች ከሚገኝ ገቢ ጋር አቀናጅቶ የጤና አገልግሎቱን በጥራት ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ ለማደራጀት ያውለዋል፡፡ የጤና መድህን መጀመር ለጤናው ዘርፍ ተጨማሪ ገንዘብ ለማስገኘት ያስችላል የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡” ይላሉ ዋና ዳይሬክተሯ።

የጤና መድህን ጤነኛው በሚከፍለው ገንዘብ ህመምተኛው ሕክምና ማግኘት የሚችልበት የመደጓጎም ሂደት ነው የሚሉት ዶ/ር ብርሃኔ የጎረቤት ሀገር ሱዳንን ልምድ ዋቢ በማድረግ “በሃገራችን የጤና መድህን ጉዳት አለው ከተባለ እስከዛሬ አለመጀመሩ ነው” ይላሉ፡፡
“ሱዳን የጤና መድህን ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች 15 ዓመት ሆኗታል፡፡በዚያች ሀገር ዋጋቸው ከባድ የሆነ መድሃኒቶችን ጨምሮ ህክምና ክፍያው አነስተኛ ነው።ምክንያቱም የዘረጉት ሲስተም የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ ግዢ ሲያደርጉ እንኳን ከአምራቾች ጋር በዋጋ የመደራደር ብቃት ፈጥሮላቸዋል።የጤና መድህን ስርዓት በኢትዮጵያ መጀመሩ የአፈፃፀም ችግር ሊያገጥም ቢችልም ያሉትን የጤና ፋይናንስ ችግሮችም ይሁን የመንግስትና የተገልጋይ የወጪ ጫናዎችን ለማቃለል መሰረታዊ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

የተገልጋይ ስጋቶች

በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የሪከርድና ማህደር አገልግሎት ክፍል ሰራተኛ የሆነችው ወይዘሮ ዘነበች አካሉ (ስሟ ለዚህ ፅሁፍ የተለወጠ) ከሶስት ዓመታት በፊት በገጠማት የጉበት ህመም ሳቢያ ለህክምና ወደ ራስ ደስታ ሆስፒታል ሄደ እንደነበር ትናገራለች፡፡ በዚህ ሆስፒታል አገልግሎቱን ለማግኘት በወረፋ የገጠማት ውጣ ውረድ ሳያንስ በህክምና መሳሪያ እጦት ምርመራዋን በውጭ እንድታደርግ በመታዘዟ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጓን ትናገራለች። ከዚያ በኋላም አልጋ የለም ተብላ ብዙ እንደተጉላላች ነው የገለጸችው።ይህ በራሷ ደርሶ ያየችው ችግር በመንግስት የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ዕምነት እንዳያድርባት እንዳደረጋት ነው ወይዘሮ ዘነበች የምትናገረው፡፡ መስሪያ ቤቷ የጤና መድህንን በተመለከተ ገለጻ ሲያደርግ በጉዳዩ ላይ ያላትን ሃሳብ ማንሳቷንም ትገልጻለች። “የመንግስት ሆስፒታል አገልግሎት አሠጣጥ ጥራት መጀመሪያ መሻሻል ካልቻለና የጤና መድህን ስርዓቱ የግል ሆስፒታሎችንም ካላካተተ ገንዘቡ ከደመወዛችን ቢቆረጥም ተጠቃሚ አያደርገንም” የሚል ሃሳብ አላት።

እንደ ወይዘሮ ዘነበች ዓይነት ስጋት ያላቸው ብዙ ለአገልግሎት ጥራት ትኩረት የሚሰጡ ተገልጋዮች ላይ የመክፈል አቅምና ፍላጎት ላይ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን የጤና መድህን ስትራተጂው ያብራራል። በውጤቱም “ታካሚዎች የጤና አገልግሎት ለማግኘት የሚጠበቀው ጊዜ ቢያጥር የመድሃኒት አቅርቦት ቢሻሻልና ሌሎችም የአገልግሎት ጥራቶች ተግባራዊ ቢደረጉ ካለው ከፍያ እጥፍ ከፍለውም ቢሆን ለመታከም ፍላጎት ያላቸው መሆኑን አረጋግጠዋል” ይላል፡፡ ተገልጋዮች ለጥራት የሚሰጡትን ትኩረት አጉልቶ ከሚያሳየው ከዚህ የጥናት ውጤት በተጨማሪ በማህበራዊ ጤና መድህን ማስፈፀሚያ ደንቡ ላይ እንደሰፈረው የጤና ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ስለመስጠታቸውና የጥራት ደረጃዎችን ስለማሟላታቸው በየጊዜው ግምገማ ይደረግባቸዋል።በገቡት ውል መሰረት በተተመነው ዋጋ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለተጠቃሚዎች መስጠት ካልቻሉም ወንጀልና በፍትሃብሔር ተጠያቂ ይሆናሉ። የጤና መድህን ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር መንግስቱ በቀለ እንደሚናገሩትም የጤና መድህን ስርዓቱ የመንግስትን ብቻ ሳይሆን መስፈርቱን የሚያሟሉ የግል ጤና ተቋማትንም ያሳትፋል። እንደዶክተር መንግስቱ ገለጻ የመንግስትም ይሁን የግሉ የጤና ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት የተሟላና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ግዴታዎች ተቀምጠዋል። “ህብረተሰቡ ለማህበራዊ ጤና መድህን የፋይናንስ ምንጭ በመሆኑ የስርዓቱ ባለቤት ነው። በጤና ተቋማት በሚያገኘው አገልግሎት ካልረካና ችግሮች ካየ ለሚቋቋሙ ቅሬታ ሰሚ አካላት በባለቤትነት ስሜት ችግሩን በማሳወቅ አሰራሩ እንዲስተካከልና እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይገባዋል።” ብለዋል።

በጤና መድን የሚሸፈኑና የማይሸፈኑ አገልግሎቶች

በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት በቅርቡ ተግባራዊ በሚሆነው የጤና መድን ስርዓት ዙሪያ የተካሄዱ ውይይቶች ካስተናገዷቸው ጥያቄዎች ዋናው “ገንዘባችንን አዋጥተን የምናገኘው የጤና አገልግሎት የሚያካትታቸው የህክምና ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?” የሚለው እንደሆነ ውይይቱን የመሩት ሃላፊዎች ይናገራሉ። “በብዙዎች ዘንድ የጤና መድህን ሽፋኑ ከጥቃቅን ህመሞች አይዘልም የሚል የተሳሳተ መረጃ መኖሩን ተገንዝበናል።ይህ ከግንዛቤ እጥረት የተከሰተ በመሆኑ የጤና መድህን ማስፈጸሚያ ደንቡ ላይ ላይ የተዘረዘሩትን በማብራራት የመረጃ እጥረቱን መቅረፍ ተችሏል” ብለዋል።

ዶክተር መንግስቱ እንደሚያብራሩት የጤና አገልግሎት ፓኬጁ ሁሉንም የቤተሰብ ጤና አገልግሎቶች፣ በመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ፓኬጅ ውስጥ የተካተቱትን የፈውስ ህክምናዎች እና ለህይወት አስጊ የሆኑ ህመሞችን በተመላላሽም ይሁን በማስተኛት ማከምን ያካትታል ይላሉ፡፡ ለምሳሌም ቀዶ ህክምና፣ደም ግፊት፣ በልዩ ልዩ ምክንያት የሚመጡ የልብ ህመሞች፣የስኳር በሽታ፣የዓዕምሮ ጤና፣ድንገተኛ በሽታዎች፣ካንሰር፣የድንገተኛ የኩላሊት ስራ ማቆምና ይህን ለማከም የሚታዘዝ የኩላሊት አጠባ (ዴያሌሲስ) ትኩረት የተሰጣቸውና በመድን ስርዓቱ የሚሸፈኑ የጤና ችግሮች ናቸው። ተገልጋዩ በሚያዋጣው ገንዘብ ሊሸፈኑ የማይችሉና ብዙ ወጪ የሚጠይቁ እንደ ጥርስ መትከል፣የዓይን መነጽር፣ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና፣የመሳሰሉት ለህይወት አስጊ ያልሆኑ ችግሮችን ለማከም የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች በጤና መድን ፓኬጅ እንደማይካተቱ ነው የሚያብራሩት። በሌላ ህግና አሰራር የህክምና ወጪያቸው መሸፈን የሚችሉ የስራ ላይ እና የትራፊክ አደጋ፣ወይም እንደቤተሰብ ምጣኔና ክትባት ያሉ በነጻ የሚሰጡ ህክምናዎችን እንዲሁም ወጪያቸው ከፍተኛ የሆኑ የውጭ ሃገር ህክምናዎችንና የአካል ማዛወር (ንቅለተከላ) ህክምና በዚህ የጤና መድን ስርዓት የማይሸፈኑ መሆናቸውንም ዶክተር መንግስቱ ይናገራሉ።
“ከዚህ ውጪ ማንኛውም ተገልጋይ በህክምና ባለሙያዎች የታዘዙ እንደሲቲ ስካን፣ኤም አር አይ፣አልትራ ሳውንድ፣ኤከስሬይ እና መሰል የምርመራ አገልግሎቶችንና ከምርመራ በኋላ በሃኪም የታዘዙና በኤጀንሲው የመድሃኒቶች ዝርዝር የተካተቱ መድሃኒቶችን ሁሉ ያለክፍያ የማግኘት መብትም ይኖረዋል።” ነው ያሉት።

ማን ስንት ያዋጣል?

በዚህ የጤና መድህን ስርዓት ውስጥ ይታቀፋሉ ተብለው የተለዩት ዜጎች ቁጥር ከነቤተሰባቸው 7 ሚሊዮን ይደርሳል። ይህ ስርዓት ፋይናንሱን የሚያገኘው ከሰራተኛው ደመወዝ 3 በመቶና አሰሪው ከሚያዋጣው 3 በመቶ ድምር ሲሆን ለጡረተኞች ደግሞ 1 በመቶ ከጡረታ ገቢያቸው እንዲሁም 1 በመቶ ከመንግስት ከሚደረግላቸው መዋጮ ጋር ተዳምሮ ከሚገባው ገንዘብ ነው። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ተስፋይ እንደሚገልጹት የሚሰበሰበው ገንዘብ መጠን ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር ሲታሰብ በጣም ጥቂት ነው። የመንግስትና የሌሎች አካላት ድጎማ ታክሎበት የሚገኘውን ገንዘብ በፍትሃዊነት ጥቅም ላይ ያውላል።የመድን ስርዓቱ ባህሪ አንድ ሰው ሁሌም ይታመማል ተብሎ ስለማይገመት ጤነኛ በሆነበት ጊዜ የሚያዋጣውን ገንዘብ ህመም ላይ ያሉት እንዲታከሙበት እያደረገ ሁሉም አባላት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል አሰራር ይከተላል” ብለዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙት 123 የመንግስት ሆስፒታሎች ለጤና መድን አባላቱ አገልግሎት እንዲሰጡ መታቀዱን የሚናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ኤጀንሲው ከመደበኛው ክፍለኢኮኖሚ ውጪ ያሉትንና ቋሚ ገቢ የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችም በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ስርዓት አቅፎ በቤተሰብ መዋጮ እና ከክፍያ ነጻ በሆነ አሰራር የጤና መድህን ስርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው መዋጮ መቼ እንደሚጀመር ኤጀንሲው ይፋ የሚያደርግ መሆኑን ሃላፊዎቹ ጠቁመዋል።ነገር ግን ሁሉም ተቋማት የሰራተኞቻቸውን ፎርም በመሙላት እስከጥር 30 2006 ድረስ ወደኤጀንሲው እንዲልኩ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።

(ይህ ጽሁፍ የፌዴራል ጤና ዋስትና ኤጀንሲ ባዘጋጀው የ2006 ዓ.ም የጤና ዘገባ ውድድር 1ኛ በመውጣት የተሸለመ ዘገባ ነው)

 

*  ጋዜጠኛ  መላኩ ብርሃኑ – በጤናና በአካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚጽፍ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ነው።ለሁለት ዓመታት አሸናፊ ከሆነበት የኢትዮጵያ አካባቢ ጋዜጠኞች ማህበር ‘Environment reporting grant ’ ባሻገር የአለምአቀፉ ጋዜጠኞች ማህበር ICFJ ባዘጋጀው የ2013 ዓለምአቀፍ የክትባት ተኮር ዘገባ ውድድር ላይ  ‘ቀናት የሚታደጓቸው እድሜ ልኮች’ በሚል ርዕስ ያቀረበው ዘገባ ከ200 ተወዳዳሪ ጽሁፎች መካከል  ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት ተሸልሟል። በ2014 የአፍሪካ ሚዲያ ኢኒሺየቲቭ AMI ለአፍሪካ ቻሌንጅ ሪፖርት ውድድር ከመረጣቸው የ15 አፍሪካ ሃገራት የመጨረሻ ዙር እጩ አሸናፊ ጋዜጠኞች መካከልም  አንዱ ነው። እ.ኤ.አ በ2013 እና 14 ብቻ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ፓኖስ ኢትዮጵያ እና የጤና መድህን ኤጀንሲ ባዘጋጁት ሃገር አቀፍ ጤና ነክ ዘገባዎች ውድድር ላይ በመሳተፍ ሁሉንም አንደኛ በመውጣት ሽልማት ተቀብሏል።

—–///—-

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.