የማሀፀን ጫፍ ነቀርሳ ማለት ምን ማለት ነው?

Cervical Cancer
የማህፀን ነቀርሳ የሚያድገው ቀስ በቀስ ከብዙ አመታት በኋላ ሲሆን በመጀመሪያ ወደ ቅድመ ነቀርሳነት ካደገ በኋላ በመቀጠልም ወደ ነቀርሳ በሽታነት ይቀየራል። ወደ ቅድመ ነቀርሳነት ያደጉ ኢፒቴሊያል የተባሉ ሴሎች ነቀርሳ እንዲፈጠር ምክንይት ይሆናሉ። እነዚህ ወደ ቅድመ ነቀርሳነት ያደጉት ሴሎች በራሳቸው የነቀርሳ ሴሎች አይደሉም ነገር ግን ህክምና ሳይደረግላቸው ከቀረ ወደ ነቀርሳነት ሊለወጡ የሚችሉ ሴሎች ናቸው።እያከታተሉ በየ3 እና 5 ዓመታት የሚደረጉ የማህፀን ምርመራዎች ትክክለኛ ያልሆነ የሴሎች ለውጥ እንዳለና እንደሌለ ያሳያሉ። ትክክለኛ ያልሆነ የሴሎች እድገት ከታየ ደጋግሞ በመመርመር ወደ ነቀርሳነት ሳይቀየሩ ቶሎ ህክምና ሊደረግላቸው ይገባል።የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ መከሰቻ ምክንያቶች ምንድናቸው?የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ ያመጣሉ ተብለው የሚታመኑ ህዋሶችና ድርጊቶች፣1.  ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (Human papilloma virus)

2.  ማጨስ እና

3.  ሌሎች ምክንያቶች

የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ ብዙ መረጃዎች እንደሚሉት ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (Human papilloma virus) የተባለው ህዋስ ለዚህ በሽታ መከሰቻ በዋነኛነት የሚጠቀስ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም አጫሽነትም በዚሁ በሽታ የመጠቃት እድልን ከፍ እንደሚያደርግም መረጃዎቹ ይገልፃሉ።

የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ ተላላፊ በሽታ ባለመሆኑ ከአንዱ ወደሌላው የሚተላለፍ በሽታ አይደለም። በመሆኑም ከቤተሰብ አባል አንዱ በዚህ በሽታ ቢያዝ ይተላለፋል ወይም ደግሞ በዚህ በሽታ የመያዝ እድል ከፍተኛ ነው (ይጨምራል)  ማለት አይቻልም።

የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ሊከሰት የሚችል በሽታ ሲሆን ነገር ግን ብዙን ጊዜ በ40ዎቹ እና በ50ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን ሴቶች የሚያጠቃ በሽታ ነው።

ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (Human papilloma virus)

ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (Human papilloma virus) በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት በቆዳ ንኪኪ ምክንያት ከታማሚው ወደ ጤነኛው ሰው ይተላለፋል። በአብዛኛው የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ሴቶች በተወሰነ መልኩ በሕይወታቸው ውስጥ የዚህ ቫይረስ ተሸካሚዎች ናቸው። ምንም እንኳ በሕይወት ዘመናቸው ከአንድ የፍቅር ጓደኛ ጋር ብቻ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚፈፅሙ ሴቶች ቢሆኑም የዚህ ቫይረስ ተጠቂ መሆን የተለመደ ነው። ኮዶም ተጠቃሚዎች ቢሆኑም ኮንዶሙ በበቂ ሁኔታ ከዚህ ቫይረስ የሚከላከል አይደለም።

ቫይረሱ በማህፀን ውስጥ አለ ማለት በማህፀን ጫፍ ነቀርሳ ተይዘዋል ማለት አይደለም እንዲያውም ብዙዎቹ ቫይረሱ እንዳለባቸው ምንም ምልክት ስለማያሳቸው በዚህ ቫይረስ እንደ ተያዙ ሳያውቁ በሰውነታቸው በሽታ ተከላካይ አማከኝነት ከሰውነታቸው ያስወግዳሉ። ነገር ግን ጥቂት ሴቶች በሰውነታቸው በሽታ ተከላካይ አማከኝነት  ይህን ቫይረስ ለማስወገድ አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥማቸዋል በተለይ እነዚህ ሴቶች የሚያጨሱ ከሆነ ለማህፀን ጫፍ ነቀርሳ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው።

ከመቶ በላይ የሚሆኑ ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረሶች (Human papilloma virus) አሉ ብዙዎቹ ምንም አይነት በሽታ የሚያስከትሉ አይደሉም። ጥቂቶቹ አነስተኛ ጥቃት የሚያስከትሉና ለአባላዘር በሽታ መንስኤዎች ናቸው።

ነገር ግን የሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (Human papilloma virus) መተላለፊያ ምልክት የሴቶቹ ወይም የወንድ ፍቅረኛቸው ከፍቅር ጓደኛቸው ውጭ መሄድ የሚያመለክት እዳይደለና ይህ ቫይረስ በጣም የተለመደና ኮንዶም መጠቀምም ሙሉ በሙሉ የሚከላከለው አለመሆኑን መረዳት አለብን። በእርግጥ ብዙን ጊዜ መቼና ከየት ቫይረሱ እንደ ያዛቸው ባለመታወቁ አንድ ሰው ቫይረሱ ኖሮበት ለረጅም ጊዜ እንዳለበት ሳያውቅ ሊኖር ሰለሚችል እራስንም ሆነ የፍቅር ጓደኛቸውን መውቀሱ ምንም የሚጠቅም አይደለም።

ለቫይረሱ የተዳረጉ ሴቶች የህመሙን ምልክት ሲያዩ ወዲያው ወደ ህክምና ባለመሄዳቸውና ለከፋ ችግር በመጋለጣቸው አንዳንድ ጊዜ የበደለኝነት ስሜትም ይሰማቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በምንም ምክንያት ቢሆን እራስን እና የፍቅር ጓደኛን ከመውቀስ እነዲሁም የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማቸው ከመጨነቅ መራቅ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የማይቀይሯቸው ነገሮች ላይ እየተጨነቁ ሌላ ችግር ከማምጣት ለበሽታቸው ትኩረት ሰጥተው ሊቆጣጠሩት በሚችሉበት ነገሮች ላይ መፍትሄ ማፈላለጉ የተሻለ ስለሆነ ነው።

የመጀመሪያው የሴል ለውጥ (እድገት) ምንም እንኳ ህክምና ለማድረግ ቀላል ቢሆንም የህመም ስሜት ስለማይሰማቸውና የምርመራ ውጤትም አብዛኛውን ጊዜ ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ ስለሚያሳይ በቶሎ ላይደረስበት ይችላል።

ነገር ግን ከ20 ሴቶች አንዷ የሴል ለውጥ (እድገት) ሊኖርባት ስለሚችል ይህ ቫይረስ የተገኘባቸው ሁሉ ምርመራውን መከታተልና ህክምና ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሴቶች የቫይረሱን ምርመራ ከ25-44 የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉት በየ3 አመቱ ከ45-60 የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉት በየ5 አመቱ ምርመራውን በትክክል መከታተል መደበኛ ያልሆኑ ሴሎች አመራረትን አግኝተው በጊዜው ተገቢውን ህክምና ለማድረግ እና የመሀፀን ጫፍ ነቀርሳን ለመከላከል ይረዳቸዋል።

ከልጅነት እድሚያቸው ጀምረው የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ሴቶች እና ከተለያዩ ሰዎች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ሴቶች በማህፀን ጫፍ ነቀርሳ ለመጠቃት ከፍተኛ የሆነ እድል ስለሚኖራቸው በእንደዚህ አይነት አስጊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ፈጥነው ወደ ህክምና መሄድ ይጠቅማቸዋል።

እንዴት አድርገን ለማህፀን ጫፍ ነቀርሳ መጋለጥን ልንቀንስ እንችላለን?

·         ትክክለኛውን የቫይረሱን ምርመራ ማድረግ እና በጊዜው ያለው ችግር ላይ መድረስ ይህ ምርመራም ከ25-44 የእድሜ ክልል ውስጥ ለሆኑት በየ3 አመቱ ከ45-60 የእድሜ ክልል ውስጥ ለሆኑት በየ5 አመቱ ምርመራ ማድረግ፣

·         መጀመሪያ ምንም የግብረ ስጋ ግንኙነት ከማድረግ በፊት የቫይረሱን ክትባት መከተብ፣

ስለዚህ ወጣት ልጃገረዶች ሁሉ ይህን ክትባት መከተብ ብሎም ትክክለኛውን ምርመራ መከታተል መቀጠሉ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ክትባቱ ለስንት ጊዜ ከቫይረሱ የመከላከል አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል በውል የታወቀ ነገር ስለሌለና ሁሉም የቫይረስ አይነቶችም ቢሆኑ በዚህ ክትባት ባለመከልከላቸው ምርመራውን መከታተል የግድ ይላል።

ያለአግባብ ደም የሚፈስ ከሆነ፣ ከማህፀን የሚወጣ ፈሳሽ ካለ፣ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ህመም ካለ እና ከግንኙነት በኋላ መድማት ካለ ወይም ሴት ካረገዘች በኋላ ደም የሚፈሳት ከሆነ ቶሎ ወደ ህክምና ማዕከል መሄድ ይኖርባታል።

ማጨስ

ማጨስ በማህፀን ጫፍ ነቀርሳ እንዲጠቁ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ስላለው የሚያጨሱ ሰዎች የሲጋራው ኒኮቲን ወይም ንጥረ ነገር በማህፀናቸው ፍሳሽ ውስጥ ስለሚቀር በብዛት በማህፀን ፍሳሽ ውስጥ የሚከማቸው ኒኮቲን ወይም ንጥረ ነገር ማህፀን በሽታ አምጪ ተዋሲያኖችን እንዳይከላከል ያደርጋል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ማህፀን የበሽታ መከላከያ ዘዴው ስለተጎዳበት የሂማን ፓፒሎማ ቫይረሱን ከማህፀናቸው እንዳያስወግዱ በማድረግ ቫይረሱ ጥቃት እንዲያደርስና መደበኛ ያልሆኑ የማህፀን ጫፍ ሴል እንዲመረቱ ምክንያት ይሆናል።

ሌሎች ለማህፀን ጫፍ ነቀርሳ የሚዳርጉን ነገሮች

ትልቁ ለማህፀን ጫፍ ነቀርሳ የሚያጋልጠን ነገር በየጊዜው ትክክለኛ የሆነ ምርመራ አለማድረግ ነው። ምክንያቱም የማሀፀን ጫፍ ሴል ሁልጊዜ ስለሚቀየር የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርገው የማያውቁ ቢሆኑም እንኳ በትክክል ምርመራውን መከታተሉ ጠቃሚ ነው።

ይህን ደግሞ ማድረግ ያለባቸው የማሀፀን ምርመራን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በማድረግ ሲሆን በየጊዜው ለቫይረሱ የሚያደርጉት ምርመራ በወቅቱ የማሀፀን ጫፍ ሴሎች ለውጥ ያሳያቸዋል።

ከአይሪሽ ካንሰር ሶሳይቲ ከፃፈው መፃፍ ላይ የተገኘ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here