ካንሰር – የታዳጊ ሀገራት ሌላኛው ፈተና

በሀገራችን ስለካንሰር በሽታ ያለው ግንዛቤም ሆነ መረጃ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። የካንሰር በሽታ እጅግ ውስብስብ እና በቀላሉ ሊታወቅ የማይችል በመሆኑ ሳይታወቅ በርካቶችን ለህልፈተ ህይወት እየዳረገ ነው። ከበሽታ ድብቅ ባህሪይ የተነሳም ብዙ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት አይደለም። በሽታውን ለመከላከልም ሆነ ለማከም ያለውን እንቅስቃሴ እንኳን ብናይ በሀገራችን የካንሰር ህክምና እየተሰጠ ያለው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ብቻ ነው። በሀገራችን ስላለው የበሽታው ስርጭትም ቢሆን በቂ የሆነ መረጃ እጥረት መኖሩን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያ ደግሞ ከታዳጊ ሀገራት ተርታ የተሰለፈች እንደመሆኗ በርካቶች በዚህ በሽታ እየተጠቁ ይገኛሉ።

የአለም የካንሰር ቀን በየአመቱ ጥር 27 ቀን (February 4) በአለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል። የዘንድሮውም “ስለ ካሰር የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን እናስወገድ” (Debunk the myth on cancer) በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

different types of cancerኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት እያደረሱ ያሉት የጡት ካንሰር ሰርቪካል ካንሰር እና የማህፀን ጫፍ ካንሰር መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይኸውም በእነዚህ የካንሰር አይነቶች ከሚጎዱ ሰዎች ውስጥ 64 በመቶዎቹ ሴቶች ሲሆኑ፣ 16 በመቶዎቹ ደግሞ ወንዶች ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ካንሰር በሀገራችን የገዳይነት ሚና ከሚጫወቱ በሽታዎች ቀዳሚው እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል። ለዚህ ችግር ከሚያጋልጡ ነገሮች መካከልም ትንባሆ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ በሂፒታይተስ ቢ እና ሲ መጠቃት፣ የአካባቢ መበከል እና የመሳሰሉት እንደ ምክንያት ተቀምጠዋል።

ለካንሰር ምክንያት የሆኑት ነገሮች እጅግ ውስብስብና ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት። ሆኖም ግን ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች ቀጥታ የሰውን ልጅ ጂን (ዘረመል) በማጥቃት ለካንሰር በሽታ ይዳርጋሉ። የካንሰር በሽታ ከ90 በመቶ እስከ 95 በመቶ የሚሆነው በአካባቢያዊ ተጽዕኖዎች የሚከሰት ሲሆን፣ ከ5 በመቶ እስከ 10 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በዘር የሚከሰት ነው። አካባቢዊ ምክንያት ከሚከሰተው ውስጥም ትምባሆ ከ25 እስከ 30 በመቶ ካንሰር የማስያዝ ድርሻ ሲኖረው፣ የአመጋገብ ችግር እና ውፍረት ከ30 እስከ 35 በመቶ ድርሻን ይይዛሉ። ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ በሽታዎች መጠቃት (Infections) ከ15 እስከ 20 በመቶ፣ ጭንቀት፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ሌሎች ደግሞ 10 በመቶውን ይይዛሉ። ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በዘር የሚተላለፍ ነው።

በዓለም ላይ በካንሰር ምክንያት ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል 18 በመቶ አካባቢ የሚሆነው የሚከሰተው ከኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ ሲሆን ከ30 እስከ 35 በመቶው ደግሞ ከአመጋገብ፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግንና ከውፍረት ጋር በተያያዘ ነው። በኢንፌክሽን በሚከሰት የካንሰር ሞት ውስጥም በአፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር ተመዝግቧል። ይኸውም 25 በመቶ ሲሆን፣ 10 በመቶው ደግሞ ባደጉት ሀገራት ይከሰታል።

በአሁኑ ወቅት ከሁለት መቶ በላይ የተለያዩ የካንሰር አይነቶች የሰውን ልጅ በማጥቃት ላይ መሆናቸውን ሳይንቲስቶቹ ይናገራሉ። የካንሰር በሽታ በበርካታ አይነቶች የሚከፋፈል ቢሆንም በአለም አቀፍ ደረጃ የከፋ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙትና የበርካቶች ሴቶች ህይወት የሚያልፍባቸው የማህፀን ጫፍ ካንሰር እና የጡት ካንሰር ናቸው። በእነዚህ በሽታዎች የተያዙ ሰዎችም ከመዳን ይልቅ ህይወታቸው ያልፋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በማህፃን ጫፍ ካንሰር ከተያዙ ሴቶች ውስጥ 45 በመቶዎቹ በሽታውን ለ5 ዓመታት የመቋቋም አቅም ሲኖራቸው በጡት ካንሰር ከተያዙት ደግሞ 89 በመቶዎቹ ለ5 ዓመታት በሽታውን ይቋቋማሉ።

የማህፀን ጫፍ ካንሰር በሽታ እንደሌሎቹ የካንሰር አይነቶች ምልክቶቹ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አይታዩም። ሆኖም ግን ከረጅም ጊዜ በኋላ በመገጣጠሚያ አካባቢ የሚሰማ ህመም፣ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት እንዲሁም የምግብ ፍላጎት ማነስ ምልክቶቹ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ምልክቶች በድንገት የሚከሰቱ፣ በተደጋጋሚ ወይም በየቀኑ የሚታዩ እንዲሁም ከወትሮው የተለየ አስቸጋሪ ስሜትን የሚፈጥሩ ናቸው።

በማህፀን ጫፍ ካንሰር ከተያዙ ሴቶች 90 በመቶዎቹ በወቅቱ ህክምና ካገኙ መዳን እንደሚችሉ የሚገልፀው የአለም ጤና ድርጅት፣ አሳዛኙ ነገር ግን የበሽታው ምልክቶች ግልፅ ባለመሆናቸው እና ህክምናው የሚጀመረው ዘግይቶ በመሆኑ የብዙዎች ህይወት እያለፈ መሆኑን ይገልፃል። የካሰር በሽታ ምልክቶች ዘግይተው የሚስተዋሉ እና እንደየካንሰሩ አይነት የሚለያዩ ቢሆኑም የራሳቸው የሆነ መገለጫ አላቸው። ከምልክቶቹ መካልም ያልታሰበ ክብደት መቀነስ፣ ትኩሳት፣ ከሚገባው በላይ የሆነ ድካም፣ በቆዳ ላይ የሚመጣ ለውጥ እና የመሳሰሉት ናቸው።

የማህፃን ካንሰርን ወደ መከላከል ስንመጣ ደግሞ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት 30 በመቶ የሚሆነውን የማህጻን ጫፍ ካንሰር በምንመገበው ምግብ መከላከል እንችላለን። ለአብነት ያህልም ቀይ ሽንኩርት የማህጸን ጫፍ ካንሰርን በ60 በመቶ የመቀነስ አቅም አለው። በተጨማሪም በሳምንት ውስጥ ለአምስት እና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ቲማቲም የምትበላ አንዲት ሴት በማህጻን ጫፍ ካሰር የመያዝ እድሏ 60 በመቶ ይቀንሳል። አሳ እና የአሳ ውጤቶችም ቢሆን በማህጻን ጫፍ ካንሰር የመያዝ እድልን 30 በመቶ ይቀንሳል፣ እንደ የስነ ምግብ ጥናት ውጤት።

በ2002 (እ.ኤ.አ) ዓለም አቀፉ የካንሰር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው በየዓመቱ 608 አዳዲስ የካንሰር ተጠቂዎች ይመዘገባሉ። በኢትዮጵያ ምን ያህል ሰዎች በካንሰር በሽታ እንደተያዙ የሚያመለክት በቂ ዳታ እንደሌለ ነው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ያስቀመጠው። ያም ሆኖ ግን ይህ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በየዓመቱ 501 ሰዎች በካንሰር ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል። የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በኢትዮጵያ በ2002 (እ.ኤ.አ) ከ100ሺ ሰዎች 12 ሰዎች በካንሰር ይያዙ ነበር ያለ ሲሆን በ2005 (እ.ኤ.አ) ይህ ቁጥር በመቀነስ ከ100ሺ ሰዎች 9ኙ በበሽታው እንደሚያዙ አስቀምጧል።

በአዲስ አበባ በ2012 (እ.ኤ.አ) በተደረገ ጥናት ከታህሳስ 2012 እስከ ህዳር 2012 ድረስ 1ሺህ 995 ወይም 68.7 በመቶ ሴቶች እና 912 ወይም 31.3 በመቶ ወንዶች በካንሰር የተያዙ ናቸው። በዚህ ጥናት ላይ 65 በመቶዎቹ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲሁም ቀሪዎቹ ከ17 በግል የጤና ተቋማት የተውጣጡ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም 34 በመቶዎቹ የጡት ካንሰር፣ እንዲሁም 15.83 በመቶዎቹ የሰርቪካል ካንሰር ተጠቂዎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ሉኪሚያ (የደም ካንሰር) በተባለው የካንሰር አይነት የተያዙት 14.8 በመቶ ሲሆኑ፣ በኮለን እና ፕሮስቴት የካንሰር አይነት የተያዙት ደግሞ እያንዳንዳቸው 7 በመቶ ናቸው።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሴቶች በማህጸን ጫፍ እና በጡት ካንሰር ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰባቸው ሲሆን፣ በርካታ ወንዶች ደግሞ ካፕሲ ሳርኮማ እና ፕሮቴስት በተባሉ የካንሰር አይነቶች እየተጠቁ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በ2007 (እ.ኤ.አ.) ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ በካንሰር ምክንያት 7.9 ሚሊዮን ወይም የሰው ዘር 13 በመቶ ህይወታቸውን አጥተው እንደነበረ የሚያመለክተው የአለም ጤና ድርጅት ዘገባ፣ ይህ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ ክፋቱ በታዳጊ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መምጣቱን ይገልፃል። በ2012 እ.ኤ.አ በካንሰር ምክንያት ለሞት ከተዳረጉ ሰዎች መካል 64.9 በመቶ የሚሆኑት የተከሰቱት በታዳጊ ሀገራት ነው።

በአለም አቀፍ ደረጃ የካንሰር በሽታ ከልብ በሽታ ቀጥሎ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች አንዱ ነው። በዚህ በሽታ ምክንያትም በአሁኑ ወቅት በየአመቱ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ህይወት እንደሚያልፍ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ቁጥር ደግሞ በአስር አመታት ውስጥ በእጥፍ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ። የካንሰር በሽታም ልክ እንደሌሎች በሽታዎች ሁሉ በታዳጊ ሀገራት ላይ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚስተዋል ነው የተገለፀው።

ምንጭ— ሰንደቅ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.