ዋናው ጤና

ይህን ያዉቁ ኖራል?…

በእያንዳንዱ የወር አበባ ዑደት ወቅት እድሜያቸዉ በሀያዋቹ ወይም በሰላሳዋቹ መጀመሪያ የሆኑ ጤናማ የፍቅር ጉዋደኛሞች የወሊድ መከላከያን የማይወስዱ ከሆነ ጽንስ የሚረገዝበት የሀያ ፐርሰንት(20%) እድል አለ፡፡ ጽንስ መቁዋጠር የሚቻለዉ በእንቁላል ማኩረት ሂደት ወይም ኦቩሌሽን( ovulation) በሚካሄድበት ወቅት ብቻ መሆኑን ስናስብ ይህ አሀዝ የሚያስደምም እንድመታን ይፈጥርብናል፡፡ሆኖም ግን የወንድ የዘር ፍሬ ከሴት እንቁላል ለበለጠ ጊዜ ከሶስት እስከ ስድስት ቀናት የመቆየት እና የማጸነስ ብቃት አለዉ፡፡ይህም ማለት ምንም እንኩዋን የግብረ ስጋ ግንኙነት የተደረገዉ እንቁላል ማኩረት ከመጀመሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ቢሆንም በዛ ያሉ የወንድ የዘር ፍሬዎች ልክ የሴት እንቁላሎች መኩረት ሲጀምሩ ማስጸነስ ይችላሉ ማለት ነዉ፡፡ሁሌም መታሰብ ያለበት ነገር ህጻን ልጅን ለመፍጠር አንድ የወንድ የዘር ፍሬ ብቻ እንደሚበቃ ነዉ! የእንቁላል ማኩረት ሂደቱ ካበቃ በሁዋላ ጽንስ መቁዋጠር የሚቻልበት የጊዜ ቆይታ የሚቀጥለዉ የወር አበባ ዑደት እስከሚመጣ ድረስ ይዘጋል፡፡እኛም እስኪ ወደ ርእሳችን እንመለስ እና እንቁላል ማኩረት ሂደት ወይም ኦቩሌሽን(ovulation) እና የዘር ማፍራት(Fertility) ምን ማለት እንደሆኑ እንመልከት ፡

ንቁላል ማኩረት ሂደት ወይም ኦቩሌሽን(ovulation) –

የሴት እንቁላሎች ከማኩረቻዉ ወይም ኦቫሪ( ovary) የሚወጡበት እና ከአስራ ሁለት እስከ ሀያአራት ሰአታት የሚቆይ በእያንዳንዱ ወር የሚፈጠር የሴት እንቁላሎች ዘር ማፍራት የሚችሉበት የእድል መስኮት ነዉ፡፡

የዘር ማፍራት (Fertility) –

በእንቁላል ማኩረቻዉ(ovulation)  ወቅት የተኮረተዉ የሴት እንቁላል ከወንድ የዘር ፍሬ ጋር በመዋሀድ ጽንስን መቁዋጠር የሚቻልበት ሂደት የዘር ማፍራት(Fertility) ብለን እንጠራዋለን፡፡

የእንቁላል ማኩረት ሂደት(ovulation) የሚከሰትበትን ወቅት እና ጊዜን ማወቅ ዘርን ለማፍራት በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ ትልቅ ሚናን ይጫወታል፡፡ከታች የተዘረዘሩትን ዘዴዋች ከተከተልን የእንቁላል መኩረቻዉን ወቅት ለመገመት ይረዱናል፡፡

እንቁላል ማኩረት ሂደት(ovulation) መገመቻ መንገዶች

 • የቀን መቁጠሪያን መመልከት ፡  

Ovulation-to-implantationለተወሰኑ ወራት የወር አባባን በቀን መቁጠሪያ በመከታተል የማኩረት ሂደቱ ሊከሰት የሚችልበትን ወቅት መገመት ይቻላል፡፡ በአብዛኛዉ ጊዜ የእንቁላል ማኩረት ሂደት ወይም ኦቩሌሽን (ovulation) የወር አበባ ዑደት ማጋመሻ ወቅት ላይ ይከሰታል፡፡ስለሆነም የወር አበባ ዑደቱ የሚቆይበት ጊዜ ከታወቀ፤አብዛኛዉን ጊዜ የወር አበባ ዑደት (ከመጀመሪያዉ የወር አበባ ቀን እስከ ቀጣዩ የወር አበባ ድረስ) ሀያ ስምንት ቀናት ያክል ይረዝማል፡፡ነገር ግን ልክ እንደማንኛዉም የእርግዝና ክስተት ቁርጥ ያለ የቀናት ርዝመት አይጠበቅም፡፡አንዳንዴ ከወራት ወራት የሚለያይ ሲሆን ከ ሀያሶስት እስከ ሰላሳ አምሰት ቀናትም ሊቆይ ይችላል፡፡የማኩረት ሂደቱ የሚከሰትበትን ቀን ለመገመት እንደ የእንቁላል ማኩረት ሂደት መጠቆሚያ (ኦቩሌሽን ፕሪዲክተር) ovulation predictor የመሳሰሉ መገልገያዋችን በመጠቀም ሊያዉቁ ይችላሉ፡፡ምናልባት የወር አበባዉ የሚቆይበት ጊዜ በየወሩ የተለያየ ከሆነ፤የማኩረት ሂደቱ የሚከሰትበትን ቀን ለመገመት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ማንበብ እጅግ አስፈላጊ ነዉ፡፡

 • የሰዉነት ስሜትን በማዳመጥ ፡

ሀያ ፐርሰንት (20%) የሚሆኑት ሴቶች የማኩረት ሂደቱ ሊከሰት ሲል ሰዉነታቸዉ የተለየ ስሜት ይፈጠርበታል፡፡ስሜቶቹም እንደዉጋት ያለ ወይም ተደጋጋሚ የሆነ በታችኛዉ የሆድ እቃ ክፍል ላይ ሆኖ እንቁላል በሚኮረትበት አካባቢ ብቻ የመቆንጠጥ ስሜት ይፈጠራል፡፡ይህም ስሜት ሚቴልሽሜርዝ( mittelschmerz) በጀርመንኛ ትርጉሙ “መካከለኛ ህመም” ተብሎ ይጠራል፡፡ስሜቱ የእንቁላል መዳበር ወይም መኮረት ዉጤት ነዉ ተብሎ ይታመናል፡፡ እነዚህን ስሜቶች በንቃት በመከታተል እና መልእክታቸዉን በመረዳት የማኩረት ሂደቱ እየተከሰተ መሆኑን ማወቅ ይቻላል፡፡

 • የሰዉነት የሙቀት መጠንን በመለካት

ይህም ሲባል የሰዉነትን የመነሻ ሙቀትን በመለካት ማለት ነዉ፡፡የሰዉነት የመነሻ ሙቀትን ለየት ባለ የሰዉነት ሙቀት መለኪያ ወይም ቤዛል ቦዲ ቴርሞሜትርን(ቢ.ቢ.ቲ.) (Basal Body Thermometer) በመጠቀም ይለካል፡፡የሰዉነት የመነሻ ሙቀትን ለማግኘት ልክ ከእንቅልፋችን ስንነሳ ይህም ቢያንስ ቢያንስ ከሶስት እስከ አምስት ሰአታትን በእንቅልፍ ካሳለፍን በሁዋላ ቢሆን ይመከራል፡፡በሴቶች ይህ የሰዉነት መነሻ ሙቀት በእያንዳነዱ የወር አበባ ዑደት ወቅት ይቀያየራል፡፡ይህም ሊሆን የቻለዉ በወር አበባ ዑደት ሂደት የሆርሞን (hormone) ተለዋዋጭነት ስለሚስተዋል ነዉ፡፡በመጀመሪያዉ የዑደቱ አጋማሽ ኤስትሮጅን(estrogen) በመጠን በመብዛት የበላይነቱን ይወስዳል፡፡ነገርግን በሁለተኛዉ የዑደቱ አጋማሽ የእንቁላል ማኩረት ሂደት ወይም ኦቩሌሽን( ovulation) ተካሂዶ ስለሚያበቃ የፕሮጅስትሮን(progesterone) መጠን በከፍተኛ መጠን ይጨምራል፡፡ፕሮጅሰትሮን(progesterone)  የሴቶችን የሰዉነት ሙቀት እንዲጨምር ምክነያት ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለዉ ፕሮጅሰትሮን(progesterone) ማህጸንን ለለማ እና ከሌላ ሴት ለተገኘ የለማ እንቁላል ስለሚያዘጋጅ ነዉ፡፡ከዚህም እንደምንረዳዉ  በመጀመሪያዉ የወር አበባ ዑደት አጋማሽ የሚኖረዉ የሴቶች የሰዉነት ሙቀት ከሁለተኛዉ የዑደቱ አጋማሽ ከእንቁላል ማኩረት ሂደት ወይም ኦቩሌሽን( ovulation) በሁዋላ ካለዉ የሰዉነት ሙቀት ያነሰ እንደሚሆን ነዉ፡፡ትንሽ ግራ ያጋባል አይደል? በተሸለ መልኩ ለመግለጽ የሴቶች የሰዉነት የመነሻ ሙቀት የእንቁላል ማኩረት ሂደት ወይም ኦቩሌሽን( ovulation) ሊከሰት ሲል መጠኑ ትንሽ ይሆንና ከተከሰተ በሁዋላ ደግሞ በፍጥነት እና በአስገራሚ ሁኔታ ከግማሽ ዲግሪ በላይ ይጨምራል፡፡የሆነዉ ሆኖ ግን የሰዉነትን የመነሻ ሙቀትን ለአንድ ወር ብቻ መከታተል ሴቶች መቼ እንቁላል ማኩረት እንደሚጀመሩ አይነግረንም ነገር ግን እንቁላል ማኩረቱ ተከስቶ እንደነበር መረጃ ይሰጣል፡፡ስለሆነም ሴቶች ለተወሰኑ ወራት የሰዉነትን የመነሻ ሙቀታቸዉን መከታተል ከቻሉ በወር አበባ ዑደታቸዉ ላይ የሚታየዉን መደጋገም በመመርኮዝ ለወደፊት የእንቁላል ማኩረቱ መቼ እንደሚጀምር በመገመት ዘርን ለመተካት የሚያደርጉትን ጥረት ማሳካት ይችላሉ፡፡

 • ስለ ህጽናገት ወይም ሰርቪክስ( cervix ) በደንብ መረዳት፡ 


የእንቁላል ማኩረት ሂደት ወይም ኦቩሌሽን( ovulation) ሙሉ በሙሉ የተደበቀ ሂደት አይደለም፡፡የሴቶች ሰዉነት የሆርሞን (hormone) ለዉጥን ሲገነዘብ፤ ይህም ለዉጥ እንቁላል ከማኩረቻዉ ኦቫሪ(Ovary) ሊረጭ መሆኑን ስለሚገልጽ ሰዉነት ራሱን በዛ ላሉ የወንድ የዘር ፍሬዎች በማዘጋጀት የሴት እንቁላል እንዲለማ አመቺ የሆነን እድል ይፈጥርለታል፡፡አንዱ የእንቁላል ማኩራት ሂደት ሊከሰት እንደሚችል የምናዉቅበት ምልክት የራሱ የህጽናጋት አቀማመጥ ነዉ፡፡በወር አበባ ዑደቱ መጀመሪያ፤ ህጽናጋት ማለትም አንገት የመሰለ በማህጸን እና በሴት ብልት መካከል የሚገኝ እና በወሊድ ጊዜ ተለጥጦ የህጻኑን ጭንቅላት ማሳለፍ የሚችል መተላለፊያ፤ ዝቅ ያለ፣ጠንካራ እና የተዘጋ ሆኖ ይገኛል፡፡ነገርግን የእንቁላል ማኩረት ሂደቱ ሲቃረብ ወደሗላ ይመለሳል፣በመጠኑም ቢሆን ይላላል እናም የወንድ የዘር ፍሬን ለማሳለፍ በትንሹ ይከፈታል፡፡አንዳንድ ሴቶች እነዚህን ምልክቶች በቀላሉ መገንዘብ ይችላሉ፤ሆኖም ሌሎቹ ደግሞ ይህን ለመገንዘብ ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡የዚህ አምድ አላማ ሁሉም ሴቶች ሰዉነታቸዉ የሚያስተላልፈዉን መልእክት በመረዳት የእንቁላል ማኩረት ሂደቱን እንዲገነዘቡ እና ዋናዉጤና ስለሆነ! ጤንነታቸዉንም እንዲጠብቁ ማድረግ ነዉ፡፡ ስለሆነም የህጽናገትን ሁኔታ አንድ ወይም ሁለት ጣቶችን በመጠቀም በየእለቱ መከታተል እና ማረጋገጥ የተረዱትንም በመመዝገብ የእንቁላል ማኩራት ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ መገንዘብ ይቻላል፡፡ሌላኛዉ የህጽናገት ምልክት ደግሞ የህጽናገትን ፈሳሽ ሁኔታ፣የመጠን መጨመር እና ተከታተይነትን በመከታተል ነዉ፡፡የህጽናገትን ፈሳሽ በሴቶች የሚከሰት ሲፈስም የዉሰጥ ልብስን እንዲጣበቅ የሚያደርገዉ ፈሳሽ ሲሆን ዋነኛ አገልግሎቱም የወንድ የዘር ፍሬን ወደ ኦቪየም(ovum) ተሸክሞ መዉሰድ ነዉ፡፡

የወር አበባ እንዳበቃ፤እነደሚገመተዉም የተለዩ ክስተቶች አይጠበቁም በተለይም ምንም አይነት የህጽናገትን ፈሳሽ አይኖርም፡፡ሆኖም የወር አበባ ዑደት ሂደቱን ሲቀጥል የህጽናገት ፈሳሽ መጠን ሲጨምር ይስተዋላል፤አብዛኛዉን ጊዜ ነጭ ደመናማ መልክ ሲኖረዉ በጣቶች መካከከል ለመለጠጥ ከሞክሩ የሚበጠስ ነዉ፡፡ወደ እንቁላል ማኩረት ሂደት ሲቃረቡ የህጽናገትን ፈሳሽ መጠኑ ይጨምራል ነገር ግን የቀጠነ፣የጠራ እና ልክ እንደ የምግብ እንቁላል ነጩ ክፍል የማሙዋለጭ ባህሪን ያሳያል፡፡በእነዚህ ጊዜያቶች ፈሳሹን በጣቶች መካከከል ለመለጠጥ ከሞክሩ እስከተወሰኑ ሴንቲ ሜትሮች ርዝመት ወዳለዉ ግማድ ይወጠርና ይበጠሳል፡፡በመጸዳጃ ክፍል ዉስጥ ሊያደርጉት የሚችሉት መዝናኛም ሊሆን ይችላል አየደል? በዛዉም ሊመጣ ያለን የእንቁላል ማኩረት ሂደትን መገመቻ ከሆኑት አንዱን ይተገብራሉ ማለት ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ ፍተሻ መጸዳጃ ክፍልዎን ተወት አድርገዉ ወደ መኝታ ክፍልዎ ትኩረቶትን እና ጊዜዋትን እንዲያዉሉ ሁነኛ ጠቁዋሚዋ ነዉ! የእንቁላል ማኩረቱ ሂደት ከተከሰተ በሁዋላ ምናልባት ምንም አይነት ምልክት ላያዩ ወይም ወፈር ያለ ፍሳሽ ሊጎለብት ይችላል፡፡በአንድ ማስታወሻ መዝገብ ላይ ማስቀመጥ ከተቻለ ፤የህጽናገትን ፈሳሽ ከህጽናገት አቀማመጥ እና ከሰዉነት የመነሻ ሙቀት ጋር በማገናዘብ የእንቁላል ማኩረቱ ሂደቱ የሚከሰትበትን ቀን ለመገመት እጅግ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ የህጽናገትን ፈሳሽ በነዚህ ጊዚያቶች በተደጋገሚ ስለሚከሰት እርስዋ የፈለጉትን አላማ ለማሳካት በቂ ጊዜን ይሰጥዋታል፡፡

 • የእንቁላል ማኩረት ሂደትን መጠቆሚያ መሳሪያዋችን በመግዛት መጠቀም

የህጽናገትን ፈሳሽን በጣቶች መንካት ጥሩ ስሜትን አይሰጦትም? እንግዲያዉስ ለዚህ መፍትሄ ስላለ ለመፈተሽ በእጅዋ የመንካት ግዴታ የለቦትም! የእንቁላል ማኩረት ሂደቱን መጠቆሚያ መሳሪያዋች( Ovulation predictor kits (OPKs)) የእንቁላል ማኩራት ሂደቱ የሚከሰትበትን ቀን ከ 12 እስከ 24 ሰዐታት ቀደም ብሎ እንዲያዉቁት ይረዳዋታል፡፡ይህንንም ለማድረግ መሳሪያዉ የሉቴናይዚንግ ሆርሞንን( luteinizing hormone(LH)) መጠን ይከታተላል፡፡የሉቴናይዚንግ ሆርሞንን( luteinizing hormone(LH)) የእንቁላል ማኩራቱ ሂደት ከመከሰቱ በፊት ከሚፈጠሩት ሆርሞኖች (hormones) ዉስጥ በመጠኑ ከፍተኛዉን ደረጃ የሚይዝ ሆርሞን (hormone) ነዉ፡፡ከእርስዎ የሚጠበቀዉ መጠቆሚያ መሳሪያዉ ላይ በመሽናት የመሳሪያዉ አመልካች  የእንቁላል ማኩራቱ ሂደቱ እንደሚከሰት አልያም እንደማይከሰት እሰኪነግሮት መጠበቅ ነዉ፡፡

ሌላኛዉ አማራጭ ደግሞ የምራቅ ምርመራ ነው፤ይህም ምርመራ ምራቅ ዉስጥ የሚገኝ የኢስትሮጅንን(estrogen) ከፍተኛ መጠንን የእንቁላል ማኩራቱ ሂደቱ ሲቃረብ ለመለካት ይጠቅመናል፡፡ የእንቁላል ማኩረቱ ሂደቱ ሲከሰት ፤ በመመርመሪያዉ የእይታ ክፍል ስንመለከት የብዕራር ተክል ቅጠል ወይም በዝናብ ወቅት መስታወቶች ላይ የሚታዩትን እርጥበቶች የሚመስል መልክ ያሳየናል፡፡ሁሉም ሴቶች ይህን መሰሉን ምልክት ላያዩ ይችላሉ ፤ነገር ግን እነዚህ መመርመሪያ መሳሪያዎች ከላይ ከተጠቀሱት እላያቸዉ ላይ በመሽናት ከምንጠቀማቸዉ መሳሪያዋች በዋጋቸዉ ርካሽ ሲሆኑ በድጋሚም ለመጠቀምም ያስችላሉ፡፡ከጠቀስናቸዉ መሳሪያዋችም በተጨማሪም በሴቶች ላብ ዉስጥ በወሩ የተለያዩ ጊዜያት የሚቀያየሩት እና የሚገኙት የተለያዩ ጨዎችን (ክሎራይድ( chloride )፣ሶዲየም (sodium)፣ፓታሺየም (potassium)) ይፈትሻሉ፡፡ይህ የጨዎች መቀያየር የክሎራይድ አዮን ሰርጅ( chloride ion surge) በመባል ይታወቃል፡፡እነዚህ የጨዋች መጠን ለዉጦች ከኢስትሮጅንን(estrogen) እና ከሉቴናይዚንግ ሆርሞን( luteinizing hormone(LH)) ቀድመዉ ስለሚከሰቱ የእንቁላል ማኩራቱ ሂደቱ ከመከሰቱ ከአራት ቀናት በፊት ይጠቁማል፡፡ይህም ከመጠቆሚያ መሳሪያዋች( Ovulation predictor kits (OPKs)) የእንቁላል ማኩራት ሂደቱ የሚከሰትበትን ቀን ከ 12 እስከ 24 ሰዐታት አስቀድሞ ከሚታወቅበት ጋር ሲወዳደር የላቀ አገልግሎትን ይሰጣል፡፡በዘመናዊዎቹ መሳሪያዋች የተሳካ ምርመራን ለማድረግ መነሻ የአዮን (ion) መጠንን ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነዉ፡፡ይህንም ተግባር ለማከናወን በአሁኑ ወቅት ገበያ ላይ የሚገኝ፤ መነሻ የአዮን (ion) መጠንን ለማወቅ በትንሹ ለተከታታይ ስድስት ሰዐታት በእጅ ላይ መታሰር ያለበት መሳሪያ አለ፡፡ምንም አይነት የእንቁላል ማኩረት ሂደቱን መጠቆሚያ መሳሪያዋች ( Ovulation predictor kits (OPKs)) የእንቁላል ማኩራት ሂደቱ የሚከሰትበትን እርግጠኛ ቀን እና መቼ ጽንስ ሊቋጠር እንደሚቻል አይነግረንም፡፡እናም የትኛዉንም መሳሪያ ወይም መንገድ ቢመርጡ ትእግስት እና በተደጋጋሚ የሚደረጉ ሙከራዋች ቁልፍ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ለሁሉም ግን በሻማ ያሸበረቀ እራትን ፣ በሳምንቱ መጨረሻ ከፍቅረኛዋት ጋር የሚዝናኑበትን እቅድ ወይም እርስዋንና የፍቅር አጋርዋን ዘር ለማፍራት የሚያስችል ሁኔታን ማዘጋጀትን አይዘንጉ፡፡ሙከራቹህም የተሳካና የምትደሰቱበትም ይሁንላቹ! ሙከራቹሁም መሳካት አለመሳካቱን ለማወቅ እና ለመገንዘብ ይህን አምድ ማንበብዋን አያቋርጡ!

11578745_m

የዘር መፍራት ወይም የእርግዝና ምልክቶች

ጽንስ እንደተቋጠረ የሚያመላክቱ የመጀመሪያዋቹ ምልክቶች:

አርግዛለሁን?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ ምልክቶችን በአመክሮ መከታተል ያስፈልጋል፡፡ለምሳሌ ያክል ላላ ያሉ ጡቶች፣ድካም እና ለማስታወክ የሚገፋፋ ህመም ስሜትን መጥቀስ ይቻላል እነዚህም ምልክቶች ጽንስ ከተቋጠረ በጥቂት ሳምንታቶች ዉስጥ ይታያሉ፡፡ከዚህ በታች ለመጥቀስ የተሞከሩት ምልክቶች የተለመዱ የእርግዝና የመጀመሪያዋቹ ምልክቶች ናቸዉ፡፡

 • ላላ ያለ፣ያበጠ ጡት

በጡቶቾ ላይ የዉጋት ወይም ህመም ስሜት የመጀመሪያዎቹ የ እርግዝና ምልክቶች ናቸዉ፡፡ለዚህ መከሰት የኢስትሮጅንን(estrogen) እና የፕሮጅስትሮን( progesterone ) ጥምረት ከፍተኛዉን ሚና ይጫወታል፡፡የሆነዉ ይሁን እንጂ ህመሙ ጥቅም አዘልም ነዉ፤ማለትም ሰዉነት ጡት ለማጥባት እንዲችል ስለሚያዘጋጅ ነዉ፡፡

 • ድካም ፡

በእርግዝና የመጀመሪያዋቹ ወቅቶች ከፍተኛ የሆነ የሰዉነት ሀይል ለጽንሱ ድጋፍ የሚሆን ሁኔታን ማለትም ፕላሴንታን ( placenta) ለማመቻቸት ይዉላል፡፡ይህም ከሰዉነቶ የሚወሰደዉ ሀይል ድካምን ይፈጥራል፡፡

 • መድማት እና የጡንቻዋች መኮማተር ፡

ጽንስ ከተቋጠረ በሗላ ከአምስት እስከ አስር ቀናት ባሉት ጊዜያት ዉሰጥ የወር አበባ ከመታየቱ በፊት የሚከሰት ቀለል ያለ የደም መድማት አንዳንድ ጊዜ ሽል ወይም ኢምብሪዮ(embryo) እራሱን ከህጽናጋት ግድ ግዳ ጋር እንዳጣበቀ ያመላክታል፡፡አንዳንድ ሴቶች ልክ እንደ ወር አበባ ሲከሰት እንደሚስተዋለዉ መኮማተር ስሜት ካረገዙ ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ የሆድ እቃ መኮማተር ያጋጥማቸዋል፡፡ለማጠቃለል ያክል የተወሰኑት ሴቶች ብቻ ሽል ወይም ኢምብሪዮ(embryo)  ከህጽናጋት ግድ ግዳ ጋር በመጣበቁ ምክንያት የሚከሰተዉ ቀለል ያለ መድማት እና የሆድ እቃ መኮማተር ያጋጥማቸዋል፡፡ነገር ግን እርግዝናዉ ተከስቶም እነዚህን ምልክቶች ማየት የማይችሉ ሴቶች ይኖራሉ፡፡

 • ለማስታወክ የሚገፋፋ ህመም እና ከፍተኛ የሆነ የማሽተት ስሜት ፡

ሆድ እቃዎ አካባቢ የሚሰማ የህመም ስሜት በተለምዶ የማለዳ ህመም ወይም ሞርኒነግ ሲክነስ ( morning sickness) እርግዝና ከተከሰተ ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ በየትኛዉም የቀኑ ጊዜ ይከሰታል፡፡ለዚህ ክስተት ዋነኛዉ ምክንየት ከፍተኛ የሆነ የፕሮጅስትሮን( progesterone) መጠን ነዉ፡፡ከዚህም በተጨማሪ ከተለምዶ የበለጠ የተነቃቃ የማሽተት ስሜት ይከሰታል፤ይህም ቀድሞ እንብዛም የነበሩት ሽታዋች እንዲጠነክሩ እና የመረበሽ ስሜት እንዲፈጠር ስለሚየደርግ ለማስመለስ በቅርቦ ወደሚያጋጥሞት የመጸዳጃ ክፍል እንዲከንፋ ያደርጎታል!

 • ምግብን መጥላት እና መጎምጀት ፡  

ከጥቂቶች በቀር ሁሉም እርጉዝ ሴቶች የሚያዩት ወይም የሚያሸቱት ምግብ ያስጎመጃቸዋል፤አብዛኞቹ ደግሞ ቢያንስ አንድ የምግብ አይነት የመጥላት ባህሪ በሆርሞኖች (hormone) ምክንያት ያጋጥማቸዋል፡፡እነዚህ ሁኔታዋች ግን ሙሉ በሙሉ አሉታዊ ተጽኖ የላቸዉም፡፡እንዲያዉም ለእርግዝና ከማይመከሩት እንደ ቡና እና አልኮል (alcohol) ሲያርቆት ጠቃሚ ወደ ሆኑት እንደ አይስ ክሬም (ice cream) የመሳሰሉ ምግቦች እንዲያዘነብሉ ይረዳዎታል፡፡ መቼም አይስ ክሬም (ice cream) የሚለዉን ሲያነቡ፤የምር ነዉ? የሚል ጥያቄ ተፈጥሮቦት ይሆናል! አዎን አይስ ክሬም (ice cream)፤ በካልሲየም (calcium ) የዳበረ ስለሆነ በጣም ጠቃሚ ነዉ፡፡

 • በተደጋጋሚ ሽንት መሽናት ፡

ጽንስ ከተቋጠረ ከሁለት ወይም ከሶስት ሳምንታት በሗላ ሽንት በተደጋጋሚ የመሽናት ፍላጎቶ ሲጨምር ያስተዉላሉ፡፡ይህ ስሜት የተፈጠረዉ በእርግዝና ሆርሞን (hormone) ኤች.ሲ.ጂ( hCG) ምክንያት ሲሆን ይህም ሆርሞን (hormone) ወደ ኩላሊት የሚሄደዉን የደም ዝዉዉር በመጨመር የእርስዎን ከጊዜ በሁዋላ ደግሞ የጽንሱን ቆሻሻ ኩላሊቶች በተገቢ ሁኔታ እንዲያስወግዱ ይረዳቸዋል፡፡ ሌላኛዉ ምክንያት ደግሞ እያደገ የመጣዉ ማህጸን ወይም ዩትረስ( uterus ) በኩላሊት ላይ ጫናና በማሳደር ለሽንት መከማቻ ይዉል የነበረዉን ቦታ እንዲጠብ ያደርገዋል፡፡ስለሆነም በተደጋጋሚ ወደ መጸዳጃ ቤት እንዲያመሩ ያስገድድዋታል፡፡

 • በሆድ እቃ አካባቢ የሚከሰት የሆድ መነፋት ወይም ብሎቲንግ (Bloating) ፡

የጅንስ ሱሪዋትን ቁልፍ ለመቆለፍ እያስቸገሮት ነዉ? ይህ በሆድ እቃዎ አካባቢ የተፈጠረዉ ዉፍረት በፕሮጅስትሮን( progesterone) ሆርሞን (hormone) ምክንያት ይከሰታል፡፡ፕሮጅስትሮን( progesterone) የምግብ መፈጨት ሂደትን በማዘግየት ከምግቡ የሚወጡት ንጥረ ነገሮች በዝግታ ወደ ደም ዝዉዉር እንዲገቡና ጽንሱንም እንዲመግቡት ያደርጋል፡፡የምግብ መፈጨት ሂደት ሲዘገይ ሆድ እቃ አካባቢ መነፋት ወይም ብሎቲንግ (Bloating) ይከሰታል፡፡

ስለ እንቁላል ማኩረት እና የዘር ማፍራት በዚህ አምድ በሰፊዉ ለመቃኘት ተሞክሯል ሆኖም ግን ሁልጊዜም ቢሆን የተረዳነዉን መተግበር ከባለቤቱ ይጠበቃል፡፡ባጠቃላይ የዳሰስናቸዉ ሀሳቦች ሁሉም ሰዉ ሴትም ትሁን ወንድ ማወቅ ያለባቸዉ እና ለሰዉ ልጅ ዘር መቀጠል ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ሲሆኑ ለጤናማ ትዳር እና የፍቅር ግኑኝነቶችም አስፈላጊ ናቸዉ፡፡በመጨረሻም ለሁላችንም መልካም ጤናን ተመኘን፤ ምክንቱም ዋናዉጤና ነዉ እና !

References:

http://www.whattoexpect.com/preconception/fertility/five-ways-to-tell-you-are-ovulating.aspx

ዕሁፉን ያዘጋጀው፡ ኢሳያስ ዘነበ

ዕሁፉን የገመገመው፡ አዲስ አለማየሁ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.