ገብረህይወት ካህሳይ አዳማ

ዘመናዊ ህክምና ባልተስፋፋበት ዘመን ዳማ ከሴ፣ ድንገተኛ፣ ቀበሪቾ፣ ፌጦ፣ ግዛዋ፣ የኮሶ ቅጠልና ሌሎችም ዕፅዋቶች የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲታደጉ ኖረዋል። አሁንም እየታደጉ ነው። ለወደፊቱም ተፈላጊነታቸው እንደሚቀጥል አያጠራጥርም።

እማማ አዳነች ነፍሳቸውን ይማረውና ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት ብቸኛ የሰፈራችን የባህል ሐኪም ነበሩ። ትኩሳት ያንገበገበው፣ የሆድ ቁርጠት ያጣደፈው፣ ምች የመታውና ድንገተኛ ህመም ያጋጠመው የመንደሩ ህፃን ከቻለ በእግሩ ካቃተው ደግሞ በእናቱ ታዝሎ ወደ ቤታቸው ይወሰዳል። ከተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎች የሚዘጋጀው ጎምዛዛ አረንጓዴ ጭማቂ በብርጭቆ አሊያም በስኒ ከተጋተ በኋላ ነፍስ ይዘራል።

የታመመውን በመፈወስ በወቅቱ የተሳካ ጊዜ ያሳለፉት እማማ አዳነች እንደ ስማቸው ብዙዎችን ያዳኑና በስራቸው ሰፊ ማህበራዊ ተቀባይነት ያተረፉ የባህል መድሐኒት አዋቂ ነበሩ። ዳሩ ግን ምን ይደረጋል? እውቀታቸውን ለሌሎች ሰያካፍሉ ህይወታቸው አለፈ።

አሁን በምንኖርባት ምድር የሰው ልጆች በአኗኗራቸው፣ በአመጋገባቸው፣ በአየር ንብረት መለዋወጥና በተለያዩ ክስተቶች መልካቸውንና ባህሪያቸውን በሚቀያይሩ በርካታ በሽታዎች ለህመምና ለሞት ይጋለጣሉ። ይህንኑ ችግር ለመጋፈጥ ደግሞ ባህላዊ፣ ተደጋጋፊ ወይም አማራጭ የህክምና አገልግሎት ግድ የሚልበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከአፍሪካውያን 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የባህል መድሐኒት ተጠቃሚ ነው። 100 ሚሊዮን አውሮፓውያን ለባህል መድሐኒት ቅድሚያ ይሰጣሉ። 80 ሚሊዮን የሚጠጋ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የዚሁ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑን ያመለክታል። ለመሆኑ የባህል መድሐኒት ስንል ምን ማለታችን ነው?።

የባህል መድሐኒት ህክምና ማለት በህብረተሰቡ ሰፊ ተባይነት ባላቸው ሰዎች በእውቀት፣ በጥበብና በሙያ ላይ ተመስርቶ ከእፅዋት፣ ከእንሰሳትና ከመአድን እየተዘጋጀ ለህሙማን በፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ነው።

የባህል መድሐኒት ህክምና የባህል ሐኪሙ በሚኖርበት ሀገር ህብረተሰቡ የተቀበለውን ማንኛውንም ሐይማኖታዊ ወይም ማህበራዊ ዘዴዎችን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ አገልግሎት ጭምር እንደሚያካትት የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የብዝሃ ህይወት (Bio Diversity) ሃብት ባለቤት ናት። ብዛት ያላቸው የመድሐኒት እፅዋቶችን (Herbal Medicine) እንዳላትም ይነገራል። ይሁን እንጂ በህግ ማዕቀፍ ተደግፎ የሚፈለገውን ያህል ጠቀሜታ አልሰጠም።

አፄ ዮሐንስ ለባህል ህክምና መስፋፋት ጥብቅ ፍላጎት እንደነበራቸው ይነገራል፣ አፄ ሚኒሊክ የባህል ህክምና የሚጠሉ ባይሆንም ለዘመናዊ ህክምና የበለጠ ፍቅር እንደነበራቸው መረጃዎቸ ይጠቁማሉ። አፄ ኃይለስላሴ ይነስም ይብዛም በባህል መድሐኒት ላይ የመጀመሪያውን ህጋዊ አዋጅ እንዲወጣ አድርገዋል።

በ1948 የወጣው የአፄ ኃይለስላሴ አዋጅ የባህላዊ ህክምና ተግባራዊ የሚሆነው ታካሚው ለአደጋና ለጉዳት በማያጋልጥ መልኩ ሐኪሙ በሚኖርበት አካባቢ ለሚገኝ ማህበረሰብ የሚሰጥ አገልግሎት መሆኑን ቢደነግግም ለሙያው የሚሰጠው ድጋፍና ጥበቃ የለውም።

የባህል መድሐኒት በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ በሽታን በመፈወስ በጤና ክብካቤ አገልግሎት ላይ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር ለተለመዱ መድሐኒቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማሰቀረት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አያጠያይቅም። ቻይና የባህል ህክምና አገልግሎትን በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል በዓመት በአማካይ 83 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታገኛለች። የደቡብ ኮርያ የዘርፉ ገቢም ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል።

ኢትዮጵያ የዘርፉን ጠቀሜታ በመገንዘብ ፖሊሲ በመቅረፅና 2002 አዋጅ በማውጣትና አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳ መመሪያ በማዘጋጀት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆንዋን የኢትዮጵያ የምግብ የመድሐኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ገልጿል።

በባለስልጣኑ የሜዲኰሌጋል ዳይሬክተር ወይዘሮ አብረኽት ግደይ እንደሚሉት የአገራችን የባህል መድሐኒት አገልግሎት በህግ ማዕቀፍ እንዲመራ በየክልሉ እውነተኛ የባህል መድሐኒት ሊቃውንቶችንና የባህል መድሐኒት እፅዋቶችን የመለየትና የመመዝገብ ስራ ተጀምሯል።

ለእውነተኛ የእውቀቱና የጥበቡ ሊቃውንቶች ህጋዊ ፈቃድ በመስጠት ጥራቱን፣ ደህንነቱንና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የባህል መድሐኒት በስፋት ወደ ገበያ እንዲገባ ለማድረግ በአንፃሩ ደግሞ በባህል መድሐኒት ስም በየመንገዱ ጎጂ መድሐኒቶችን የሚቸበችቡ አጭበርባሪዎችን ለመቆጣጠር የተሟላ መመሪያ ተዘጋጅቷል።

በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ምርምር ማዕከል የባህላዊና ዘመናዊ መድሐኒት ቅመማ ረዳት ተመራማሪ ክርስትና ሃይሌ በበኩላቸው ማዕከላቸው በተለያዩ የባህል መድሐኒት ዕፅዋቶች ላይ ፈዋሽነታቸውና መጠናቸውን ለመወሰን የሚያስችሉ ምርምሮች በማካሔድ ላይ ነው።

በኢትዮጵያ የምግብ የመድሐኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን የፖሊሲ አማካሪ አቶ ዳዊት ዲካሶ እንደሚሉት ከሆነ በባህል መድሐኒት ዕፅዋቶች ላይ የሚካሔደው ምርምር ብዙም የተወሳሰበ አይደለም። ”አስፈላጊው ነገር የባህል መድሐኒት ዕፅዋቶችን ከሳይንሳዊ አሰራር ጋር በማዋሃድ መርዛማነታቸውን ማስተካከልና ታካሚው የሚወስደው መጠን በመለየት በስፋት ወደ ገበያ እንዲገቡ ማድረግ ነው” ብለዋል።

መንግስት ለዘርፉ ተገቢ ትኩረት በመስጠቱ በባህል መድሐኒት ዙርያ ለመሳተፍ በርካታ ባለሃብቶች ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አቶ ዳዊት ጠቁመው በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ ላይ የባህል መድሃኒት እያቀነባበሩ ለገበያ የሚያቀርቡ ሁለት ትላልቅ ፋብሪካዎች እንደሚገነቡ አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፋርማሲዮቲካል ኬሚስትሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር የፋርማሲ ትምህርት ቤት ዲንና የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ፕሬዘዳንት ዶክተር አርአያ ሐይመተ በሰጡት አስተያየት የባህል መድሐኒት ሲነሳ በአንድ በኩል የባህል መድሃኒት ዕፅዋትን በሌላ በኩል ደግሞ የባህል መድሐኒት ሊቃውንትን መልሶ ማልማት ያስፈልጋል።

የባህል መድሐኒት ሊቃውንቶች ቁጥር በዕድሜ መግፋት ምክንያት እውቀታቸውን ለልጆቻቸው ሳያወርሱ በሞት ተመናምነዋል። ሙሉ በሙሉ ሳናጣቸው ተገቢው ድጋፍና ክብካቤ በመስጠት እውቀታቸው ተመዝግቦ ለትውልድ እንዲተላለፍ መደረግ አለበት። የባህል መድሐኒት ዕፅዋቶች ከደን መመንጠር ጋር ተያይዞ በመጠንም ሆነ በዓይነት በእጅጉ ተመናምኗል። ዶክተር አርአያ እንደሚሉት የባህል መድሐኒት ዕፅዋቶች ጨርሰው ሳይጠፉ ያሉትን መጠበቅና መንከባከብ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች መልሶ ማባዛት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው።

ለዚሁ ጉዳይ ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ግንባር ፈጥረው ሊረባረቡ እንደሚገባ ዶክተር አርአያ ይመክራሉ።

የባህል መድሐኒት ህክምና ህጋዊ እውቅና አግኝቶ በህጋዊ ማዕቀፍ ቁጥጥር ወደ ገበያ እንዲገባ ለማድረግ በተዘጋጀው መመሪያ ዙርያ ለመወያየት በቢሾፍቱ ከተማ ሰሞኑን በተዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ ከተሰባሰቡት ተመራማሪዎች ባሻገር አንዲት ታዋቂ የባህል ህክምና ባለሙያ ልምዳቸውን ለማካፈል በተጋባዥነት ተገኝተው ነበር።

የባህል ሐኪሟ ወይዘሮ አበበች ሽፈራው ይባላሉ። ባለፉት 35 ዓመታት በየአድባራቱና በየገዳማቱ በመዞር ከአገራችን አራቱ ማእዘናት ያሰባሰቡዋቸው ከ300 በላይ የባህል መድሐኒት ዕፅዋቶችን በቢሾፍቱ ከተማ በአንድ ማዕከል እንዲባዙ አድርገዋል። የመድሐኒት ዕፅዋቶቹን አጠቃቀም የሚያብራሩና የሚያስረዱ በርካታ መፃህፍትም በእጃቸው አስገብተዋል።

በማዕከሉ የተሰበሰቡት የአገር ሃብቶች ለአደጋ እንዳይጋለጡ የብረታብረትና ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ የመጠበቁንና የመንከባከቡን ሃላፊነት ወስዶ ከሐኪም አበበች ሽፈራው ጋር አብሮ እየሰራ ነው። ወይዘሮ አበበች ተቋሙ ላደረገላቸው ድጋፍ ከምስጋናና ከአድናቆት በላይም እንደሆነ ይናገራሉ።

መንግስት በአሁኑ ወቅት ለባህል መድሐኒት ህክምና የሰጠው ትኩረት እንዳስደሰታቸውና ለእውነተኞቹ የባህል ሊቃውንት መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን የገለጡት ወይዘሮ አበበች ሙያውን፣ እውቀቱንና ጥበቡን ሳይበርዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የበኩላቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

” ከሁሉም በላይ ግን በዕድሜ መግፋት ምክንያት እየተመናመኑ የመጡት ሊቃውንቶችና የባህል ህክምና ዕፅዋቶችን መንግስት እንደቅርስና መዓድን ሁሉ ተገቢ ጥበቃ ካደረገላቸው ከወርቅና ከቡና ያልተናነሰ ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን አልጠራጠርም” ብለዋል።

የባህል መድሐኒት ህክምና የወርቅና የቡና ያክል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከሰጠ አሊያም ቻይናና ኮርያ የተጓዙበትን መንገድ ማሳካት ከተቻለ

”አረንጓዴ ወርቅ” የሚል ስያሜ ቢሰጠው የተጋነነ አይሆንም።

የመድሐኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የመድሐኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች መግዣ በጀት ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል። የተወሰነውን በባህል ህክምና መድሐኒት መሸፈን ብንችል እንኳን ከጤናው በተጓዳኝ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውንም ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል የሚል እምነት አለኝ። አዎን! የመድሐኒት እዕዋቶችን ”አረንጓዴ ወርቅ” ሆነው እንዲያገለግሉን ልንጠብቃቸው፣ ልንከባከባቸውና መልሰን ልናባዛቸው ይገባል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.