የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈፃሚዎች በተለያዩ አዕምሮአዊ የጤና ችግሮች የተጠቁ ናቸው (የስነ ልቦና ባለሙያ)
ህጉ በአስገድዶ ደፋሪዎች ላይ ያስቀመጠው ቅጣት ለወንጀሉ ተመጣጣኝ አይደለም (የህግ ባለሙያ)

f4ca78dfbacfacf4e74c447526c2b68d_Mአየር ጤና አካባቢ ከሚገኘው ት/ቤቷ ወጥታ ወደ ቤቷ ለመሄድ በተሳፈረችበት ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ በነበሩ አምስት ወንዶች ታፍና ተወስዳ በደረሰባት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ህይወቷ ያለፈው የአስራ አምስት ዓመቷ ታዳጊ ሃና ላላንጎ ጉዳይ ከተማችንን ሲንጣት ሰንብቷል፡፡ ታዳጊዋ ታፍና ከተወሰደችበት መስከረም 21 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት የቡድን አስገድዶ መድፈር ጥቃታ ተፈፅሞባት፣ ጦር ኃይሎች ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን አካባቢ ተጥላ መገኘቷ መገቡ ይታወሳል፡፡

የህክምና እርዳታ አግኝታ ህይወቷ እንዲተርፍ የተደረገው ሙከራም የተፈፀመባት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እጅግ ከባድ በመሆኑና በስለት በመወጋቷ ሳቢያ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይሄ ክፉ ዜና ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ድርጊቱም በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ በታዳጊዋ ላይ ይህንን አሰቃቂ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ አምስት ወጣቶችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው፣ ጉዳያቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎታ በዝግ እየታየ ይገኛል፡፡

የሟቿን ታዳጊ ጉዳይ መነሻ በማድረግ ለአስገድዶ መድፈር ወንጀል የሚያነሳሱ አፈንጋጭ የወሲብ ባህሪያትን ምንነትና የሚያስከትሏቸውን የጤና ቀውሶች እንዲሁም ለወንጀሉ የተቀመጠውን ቅጣት አስመልክቶ ከባለሙያዎች ያገኘነውን ማብራሪያና መረጃ የአዲስ አድማስ
ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡

አስገድዶ መድፈር ከስነ ልቦና
ቀውስ አንፃር
መደበኛ ከሆኑትና ከተለመዱት ወሲባዊ ድርጊቶች በተለየ መንገድ ወሲብን የመከወን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች፣ ለአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርይ የተጋለጡ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ከእነዚህም መካከል አስገድዶ መድፈር፣ የቡድን ተራክቦ፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ሌሎች ወሲብን ሲፈፅሙ በማየት መርካት፣ ግለ ወሲብና በሰዎች  ስቃይ እርካታን ማግኘት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአስገድዶ መድፈርና በቡድን የሚደረጉ ተራክቦዎች በአብዛኛው የሚፈፀሙት በአልኮልና በተለያዩ የአደንዛዥ እፆች ራስን ስቶ አዕምሮ በአግባቡ እንዳያስብ በማድረግ ነው ይላሉ – ባለሙያዎች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርያት አመላካች የሆኑ ድርጊቶች በአገራችን እየተለመዱ መምጣታቸውን የጠቆሙት የሥነ ልቦና ባለሙያው ዶክተር አንተነህ ተስፋው፤ በተለይ ዕድሜያቸው ከ16-25 ዓመት በሚሆናቸው ወጣቶች ላይ ድርጊቱ በስፋት እየታየ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል፡

ከቴክኖሎጂው እድገትና ወሲባዊ ፊልሞች እንደ አሸን ከመፍላታቸው ጋር ተያይዞ አስገድዶ መድፈር፣ የቡድን ወሲብና ግብረሰዶማዊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ መምጣታቸውንም ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርያት አንዱ የሆነው አስገድዶ መድፈር የአዕምሮአዊ ጤና ቀውስ ውጤት ነው፡፡ ለአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርያት አጋላጭ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋንኞቹ፡-
ከአስተዳደግ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ስነልቦናዊ ችግሮች
አዕምሮ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች
የሆርሞኖችና ኬሚካሎች መዛባት
የኒውሮኖች ጉዳት ናቸው፡፡
ከአስተዳደግ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የስነ ልቦና ችግሮች
ችግሩ በአብዛኛው ከአስተዳደጋችን ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው፡፡ ለራስ የሚሰጥ አነስተኛ ግምትና በልጅነት ዕድሜ ለወሲባዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆን ለአፈንጋጭ የወሲብ ባህርይ ሊዳርግ ይችላል፡፡
አዕምሮ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች
በአዕምሮአችን ላይ በበሽታም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች አካላዊ ጉዳቶች ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ጉዳቶች ደግሞ የአዕምሮአችንን የወሲብ ክፍል ሊጎዱትና በዚያም ሳቢያ በወሲባዊ ባህርያችን ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ለአፈንጋጭ የወሲብ ባህርይ ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡
የሆርሞኖችና የአዕምሮ ኬሚካሎች መጠን መዛባት
አንድሮጅንና ኤስትሮጅን የተባሉት በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙት ሆርሞኖች ወሲባዊ ፍላጐትና ስሜታችንን ለመቆጣጠር የማረዱን ናቸው፡፡ የእነዚህ ሆርሞኖች መዛባት በወሲባዊ ባህርያችን ላይ የሚያስከትሉት ተፅእኖ ቀላል አይደለም፡፡
የኒውሮኖች ጉዳት
የአዕምሮ ሴሎች እርስ በርስ እንዲተሳሰሩና መልእክት እንዲለዋወጡ የሚያደርጉ የአዕምሮአችን መረቦች በተለያየ ምክንያት ጉዳት በሚደርስባቸው ጊዜ አፈንጋጭ ለሆነ ወሲባዊ ባህርይ ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡
በአጠቃላይ ለአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርይ ልንጋለጥ የምንችለው በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ሲሆን ችግሩ በወቅቱ ታውቆ የባለሙያ እገዛ ካላገኘ በጊዜ ብዛት አፈንጋጭ የወሲብ ባህርይው ሙሉ በሙሉ የግለሰቡን አዕምሮ በመግዛት በራስ መተማመን የሌለውና ወሲባዊ እሳቤውን ለመቆጣጠር የማይችል ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የችግሩ ተጠቂ የሆነ ሰው ለራሱ ያለው ግምት እጅግ አነስተኛ ስለሚሆን ራሱን ከማህበረሰቡ ያገላል፡፡ ራሱን ለማጥፋትም ይፈልጋል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት የችግሩ ተጠቂዎች የስነልቡና ባለሙያዎች ጋር ወይንም የስነ አዕምሮ ሐኪሞች ዘንድ በመሄድ ለችግራቸው መፍትሄ መሻት ይኖርባቸዋል፡፡
የአስገድዶ መድፈር ድርጊት የተፈፀመባት (የተፈፀመበት) ሰው ብቻ ሳይሆን የፈፀመው ግለሰብም ጭምር የህክምና እርዳታ ሊያገኝ የሚችልበት መንገድ መመቻቸት ይኖርበታል ያሉት የስነልቡና ባለሙያው ዶክተር አንተነህ፤ ይህ አሰራር በሌሎች አገራት የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አስገድዶ መድፈርና ህጋዊ ተጠያቂነቱ
በ15 ዓመቷ ታዳጊ ወጣት ላይ የተፈፀመው የቡድን አስገድዶ መድፈር ወንጀል ያስቆጣቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የድርጊቱ ፈፃሚዎች በአፋጣኝ ተይዘው ለድርጊታቸው ተመጣጣኝ የሆነና ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል (መቀጣጫ የሚሆን) ፍርድ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ሰንብተዋል፡፡ የወንጀሉ ፈፃሚዎች በሞት እንዲቀጡ አሊያም የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲወሰንባቸው የጠየቁም በርካቶች ናቸው፡፡ ለመሆኑ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ለዚህ መሰሉ ድርጊት የሚሰጠው የቅጣት ውሳኔ እምን ድረስ ነው? የህግ ባለሙያው አቶ ዳዊት ታዬ ለዚህ ማብራሪያ አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ፤ የአስገድዶ መድፈርን ወንጀል እስከ አስር አመት ሊደርስ በሚችል ቅጣት የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጐ አስቀምጦታል፡፡
ድርጊቱ የተፈፀመው አስራ አምስት ዓመት ባልሞላት ሴት ልጅ ላይና በብዙ ሰዎች ተባባሪነት ከሆነ ቅጣቱ እስከ አስራ አምስት አመት ሊደርስ እንደሚችል ይገልፃል፡፡ ድርጊቱ ሞትን የሚያስከትል ሲሆን ደግሞ ቅጣቱ ከፍ ሊል ይችላል፡፡ ሆኖም በአስገድዶ መድፈር ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ የቅጣት ህጐች ደፋሪዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያላቸው ናቸው ብሎ ለመናገር እንደማያስችሉ አቶ ዳዊት ይናገራሉ፡፡

“ህጉ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀመ ሰው ወንጀሉን የፈፀመባትን ሴት ያገባ እንደሆነ ክሱ ቀሪ ሊሆን እንደሚችል ያስቀምጣል፤ ይህም የድርጊቱ ፈፃሚዎች ጋብቻ በመፈፀም ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስለሚያስቡ ድርጊቱን ከመፈፀም ወደ ኋላ አይሉም፤ ምክንያቱም ወንጀሉን በጋብቻው ካስቀሩ በኋላ ጋብቻውን ደግሞ በቀላሉ ሊተውት ይችላሉና” ሲሉ አስረድተዋል አቶ ዳዊት፡፡
ተጎጂውን ለአካል ጉዳት፣ ለስነ ልቦና ቀውስና ባስ ሲልም ለህልፈት የሚዳርገውን ይህን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከልና ከነአካቴውም ለማጥፋት የሁሉንም የጋራ ህብረትና ጥረት ይጠይቃል፡፡
ጉዳዩ ጊዜ የሚሰጥና ለነገ በይደር የሚተው አይደለም፡፡ ግለሰቦች፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ማህበረሰብ፣ ፖሊስ (መንግስት)፣ መምህራንና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንዲሁም የፆታ እኩልነት ተሟጋቾች ዛሬውኑ አገራዊ እንቅስቃሴ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ ነገ በሃና ላይ ከተፈፀመው ጥቃት የከፋ በሌሎች ላይ ላለመፈፀሙ ምንም ማረጋገጫ እንደሌለን መዘንጋት የለብንም እሳቱን ለማጥፋት ከመረባረብ ቃጠሎ እንዳይነሳ መከላከል የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.