የሴት ኮንዶም

ኤች አይቪ ኤድስን ጨምሮ ሌሎች ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳቢያ የሚተላለፉ በሽታዎችና ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችል የሴት ኮንዶም በዲኬቲ ኢትዮጵያ ወደ አገራችን አስመጥቶ ለገበያ ከቀረበ ቆየት ብሏል፡፡ ኮንዶሙን ሁልጊዜና በአግባቡ ከተጠቀሙበት በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችንም ሆነ ያልተፈለገ እርግዝናን የመካላከል አቅሙ አስተማማኝ እንደሆነም የጤና ባለሙያዎችን ይናገራሉ፡፡ ዲኬቲ ኢትዮጵያ ኮንዶሙን በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች እንዲጠቀሙበት በማድረግ አበረታች ውጤት አስገኝቷል ሲባል ሰማሁና ጉዳዩን ከራሳቸው ከተጠቃሚዎቹ አንደበት ለመስማት ወደ ስፍራው ተጓዝኩ፡፡

Female comdumበአዲሱ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ሳቢያ ምስቅልቅሉ ከወጣው የመርካቶው ሰባተኛ መንደር የደረስኩት ባለፈው ማክሰኞ አመሻሹ ላይ ነበር፡፡ ስፍራው በወሲብ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በስፋት የሚገኙበት በመሆኑ በቂ መረጃዎችን እንደማገኝ እምነት ነበረኝ፡፡ ከአዲስ ከተማ የመሰናዶ ት/ቤት ፊት ለፊት የሚገኙት ቅያሶች በሙሉ ወደ እነዚሁ አካባቢዎች የሚያደርሱ በመሆናቸው አንዱን መንገድ ይዤ ቁልቁል ወረድኩ፡፡
በቆርቆሮና በጣውላ እርስ በርስ ተዛዝለው የተሰሩና በሮቻቸው አጫጭር የሆኑትን የሴተኛ አዳሪዎቹን ቤቶች እያለፍኩ ወደመሀል ዘለቅሁ፡፡ የቀድሞው ቀበሌ 12 በርካታ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች የሚገኙበት አካባቢ ነው፡፡

ሴቶቹ ከተለያዩ የአገራችን ክልሎች የመጡ መሆናቸውንና በወሲብ ንግድ ለዓመታት ተሰማርተው እንደቆዩ ነገሩኝ፡፡ ስለኤችአይቪ/ ኤድስና ጥንቃቄ በጎደለው ወሲብ ሳቢያ ስለሚከሰቱ በሽታዎች በቂ ግንዛቤም አላቸው፡፡ ኮንዶምን ሁልግዜ የመጠቀም ፍላጎት ቢኖራቸውም አብዛኛውን ጊዜ ያለኮንዶም ወሲብ ለመፈጸም የሚፈልጉ አንዳንድ ግድየለሽ ደንበኞቻቸው ያለፍላጐታቸው ከኮንዶም ውጭ ወሲብ እንዲፈፅሙ እንደሚይስገድዷቸው አጫወቱኝ፡፡ “ብዙውን ጊዜ በኃይል እየተጠቀሙ ያለኮንዶም ወሲብ ለመፈጸም የሚፈልጉ ወንዶችን ጮኸን እናስይዛቸዋል፡፡ እርስ በርሳችን በመረዳዳት ሴቲቱን አስገድዶ ያለኮንዶም ሊገናኝ የሚፈልገውን ወንድ በፖሊስ እናሲዛለን፡፡ አንዳንዴ ግን ወንዶች ያለኮንዶም ወሲብ ለመፈፀም የሚያቀርቡልን ማባበያ እያታለለን እኛም በፍቃደኝነት እንፈፅማለን፡፡ አንዳንዱ ወንድ ደግሞ ተስማምተን በኮንዶም ወሲብ ማድረግ ከጀመርን በኋላ ያጠለቀውን ኮንዶም አውልቆ በመጣል ያለኮንዶም ይገናኛል፡፡ ምን ታደርጊዋለሽ፡፡ ህይወት እንዲህ ናት!”
ሴቶቹ ህይወታቸው ስቃይና ሐዘን የተሞላበት እንደሆነና ራሳቸውን እንደ ሰዉ ቆጥረው ተስፋ ለማድረግ እንደማይችሉ ነገሩኝ፡፡ በቅር/ጀ ወደ አገራችን መጥቶ ገበያ ላይ ስለወሰው የሴቶች ኮንዶም ያውቁ እንደሆነ ጠየቅኋቸው፡፡

ሁሉም ሴቶች ስለ ኮንዶሙ ያውቃሉ፡፡ ሞክረውታልም፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ስል ጥያቄዬን ቀጠልኩ፡፡
“በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተሽ በራስሽ ፍላጎትና አማራጭ መጓዝ አትችይም፡፡ ደንበኛሽ ገንዘቡን እስከከፈለ ድረስ እሱ በሚፈልገው መንገድ ማስተናገድ አለብሽ፡፡ ይህንን ስታደርጊ ታዲያ ራስሽን ለበሽታና ለሞት አጋልጠሸ አይደለም፡፡ የሴት ኮንዶም በመምጣቱ ሁላችንም ደስተኞች ነን፤ ምክንያቱም በእኛ ስራ ኮንዶም መጠቀም የደንበኛሽን በጎ ፍቃደኝነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ ወንዱ በወሲብ ላይ እያለን ኮንዶሙን በማውለቅ ያለኮንዶም ሊገናኘን ስለሚችል ይህ ኮንዶም ከእነዚህ ችግሮች ይታደገናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በስካር ኃይል ያለኮንዶም ሊያወጡን ከሚፈልጉ ወንዶች ይጠብቀናል፡፡ አንዳንድ ወንዶች ገንዘባቸውን ከፍለው ለወሲብ ዝግጁ መሆን ሲያቅታቸው ኮንዶሙን አውልቀው ያለ ኮንዶም ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሴት ኮንዶሙን አጥልቀን ዝግጁ ከሆንን ያለ ችግር እናስተናግዳቸዋለን፡፡ ኮንዶሙ እነዚህ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ሁሉ ጉዳቶችም አሉት፡፡ የሴት ኮንዶሙ ለስምንት ሰዓታት በማህፀን ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል ብለው ነገረውናል፡፡ ስለዚህ ኮንዶሙን ቀደም ብለን አጥልቀን ደንበኞቻችንን እንጠብቃለን፡፡ ደንበኞቻችን በአብዛኛው ደስተኞች አይደሉም፤ አንዳንዶቹ አስተማማኝ አይደለም በማለት ኮንዶም አጥልቀው ይገናኙናል፤ በዚህ ጊዜ ህመም ይሰማናል፡፡ ድርቀት ስለሚፈጠርም ምቾት ያለው ወሲብ አንፈፅምም፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ ሲቀመጥና በተለይ ብዙ ስንቆም ምቾት ይነሳናል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሴት ኮንዶሞችን የምንጠቀመው በበዓላት ዋዜማና ግርግር በሚበዛባቸው ጊዜያት ነው፡፡” ከሴቶቹ ጋር ስለሴት ኮንዶም ያደረግሁትን ቆይታ ካጠናቀቅሁ በኋላ ስለ ሴት ኮንዶም ምንነት ጠቀሜታና የጎንዮሽ ጉዳት እንዲያብራሩልኝ የማህፀን ፅንስ ስፔሻሊስት ዶክተር የኔነህ ታምራትን አነጋገርኳቸው፡፡

የሴቶች ኮንዶም በተለያዩ የዓለማችን አገራት በስፋት በጥቅም ላይ የሚውሉ ቢሆንም በአገራችን እምብዛም የማይታወቅና ከጥቂት ጊዜያት በፊት እንደገባ የገለፁልኝ ዶክተሩ፤ ህብረተሰቡ ስለሴት ኮንዶም ምንነትና አጠቃቀም እምብዛም ባለማወቁ በአግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም ብለዋል፡፡

የሴት ኮንዶሞች በተለያዩ አይነትና ብራንድ በዓለም ገበያ ላይ የሚገኙ ሲሆን  Femidom, Fc femeal condom, Reality, Dominiquie femy, Protectiv care, 7C2, 7C የተባሉት ይገኙበታል፡፡ በአገራችን ገበያ ላይ የሚገኙት 7C2 የተባሉት ኮንዶሞች ናቸው፡፡ የሴት  ኮንዶም ላቴክስ ከሚባልና ከጎማ ተክል ከሚመነጭ ፈሻሽ የሚሰራ ሲሆን በአግባቡና ሁልጊዜ ከተጠቀሙበት ያልተፈለገ እርግዝናንም ሆነ ኤችአይቪ/ ኤድስን ጨምሮ ሌሎች በግብረስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ያስችላሉ፡፡የሴት ኮንዶሞች በመጀመሪያ አካባቢ ለአጠቃቀም  ምቹ አለመሆን፣ ምቾት አለመሰማት አይነት ችግሮች እንዳሏቸው ባይካድም ሲለመዱ ግን ይህ አይነቱ ስሜት እንደሚጠፋም ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡ የሴት ኮንዶም ከተጠቀመች ሴት ጋር ወሲብ ለመፈፀም የሚዘጋጅ ወንድ ኮንዶም ማድረግ ይጠበቅበታል ወይ ለሚለው ጥያቄም ዶክተሩ ሲመልሲ ይህ እጅግ አደገኛና ሁለቱንም የወሲብ ተጓዳኞች ችግር ላይ የሚጥል ነገር ነው፤ ሴቷ ኮንዶሙን ከተጠቀመች ወንዱ መጠቀም አይኖርበትም፡፡ ሁለቱም ከተጠቀሙ ግን ድርቀት በመፍጠር ኮንዶሙ የመቀደድና የመላጥ ችግር ያስከትላል፤ ይህም በሽታ በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው እንዲተላለፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.