የብልት ያለመቆም ችግር

የብልት ያለመቆም ችግር አለ የምንለዉ የወንድ ብልት ለግብረ ስጋ ግንኙነት ሲዘጋጅ አልቆም ሲል ወይም የተወሰነ ቢቆምም ምንም ጥንካሬ የሌለዉ ከሆነ ነዉ፡፡ ይህ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ከቀጠለ በወንድየዉ ላይ ጭንቀትን፣በራስ ያለመተማመንንና የግብረስጋ ግንኙነት ችግሮችን ሊያመጣ ይችላል፡፡

PEMenየወንዶች ብልት ያለመቆም ችግርን ለህክምና ባለሙያዎ ማወያየት የሚከብድ ቢመስልም ለብልት ያለመቆም ችግር መንስኤ የሆኑና ቢታከሙት ችግሩን ሊያቃልል የሚችሉ እንደ የልብና የስኳር ህመም ያሉ የውስጥ ደዌ ችገሮች ስላሉ ምንም ሳያፍሩ የህክምና ባለሙያዎን ማወያየት ይመከራል፡፡ ችግሩን ያመጡትን ነገሮችን በመታከም ለዉጥ ከሌለዉ ደግሞ ሌሎች ስንፈተ ወሲብን ሊያክሙ የሚችሉ መድሃኒቶች ስላሉ ባለሙያዎትን ማማከርን አይርሱ፡፡

የወንድ ብልት ያለመቆም ችግር ምልክቶች
• የብልት አልቆም ማለት
• የብልት ቆሞ ያለመቆየት/ ቶሎ መልፈስፈስ
• የግብረ ስጋ ግንኙነት ፍላጎት መቀነስ

የህክምና ባለሙያዎትን ማማከር ያለቦት መቼ ነዉ?
• የብልት ያለመቆም ችግር ወይም ሌሎች የወሲብ ችግሮች እርስዎንና አጋርዎን ካስጨነቅዎ
• ከብልት ያለመቆም ችግር ጋር ተያያዥ ሊሆኑ የሚችሉ እንደ የስኳር፣ የልብ ህመም ወይም ሌሎች የጤና ችግሮች ካለዎ
• ከስንፈተ ወሲብ ጋር የሚገናኙ የማይመስሉ ሌሎች የህመም ምልክቶች ከስንፈተ ወሲብ ጋር አብሮ ካለዎ

ለብልት ያለመቆም ችግር ምክንያቶች ምንድን ናቸዉ?
ለወንዶች የወሲብ ስሜት መነቃቃት አእምሮ፣ ሆርሞኖች፣ ነርቮች፣ ጡንቻዎች፣ የደም ስሮችና ስሜት (emotions) የሚሳተፉ ሲሆን ይህ ሂደት እጅግ ውስብስብ ነዉ፡፡ የብልት ያለመቆም ችግር ከእነዚህ በአንዱ ወይም በሌለኛዉ ላይ ችግር በሚከሰትበት ወቅት ሊመጣ ይችላል፡፡ ጭንቀትና የስነ አዕምሮ ችግሮች ችግሩን ሊባብሱት ይችላሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳዮች የብልት ያለመቆም ችግርን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡

የብልት ያለመቆም ችግርን ሊያመጡ የሚችሉ አካላዊ ችግሮች
• የልብ ህመም
• የደም ስሮች መዘጋት ( atherosclerosis)
• የደም ግፊት መጨመር (የደም ብዛት)
• የኮሌስትሮል መጨመር
• የስኳር ህመም
• ዉፍረት
• የፓርኪንሰንስ ህመም
• መልትፕል ስኬሎሮሲስ
• የወንዶች ሆርሞን (ቴስቴስትሮን) መጠን መቀነስ
• በወንዶች ብልት ዉስጥ ጠባሳ መፈጠር
• ለህክምና የሚታዘዙ መድሃኒቶች
• መጠጥ (አልኮሆል)ና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆች
• የፕሮስቴት ዕጢ ማበጥ ወይም የፕሮስቴት ዕጢ ህክምና
• በዳሌ አካባቢ ወይም በህብለሰረሰር ላይ በሚደረግ ቀዶጥገና ወቅት የሚደርስ አደጋ

የብልት ያለመቀም ችግር የሚያመጡ ስነልቦናዊ ምክንያቶች፡-
አዕምሮ ተከታታይነት ያለዉ አካላዊ ሁነቶችን በማነሳሳት ለብልት መቆምና ወሲባዊ ደስታዎችን በማምጣት ከፍተኛዉን ሚና ይጫወታል፡፡ ለወሲባዊ ስሜቶች ችግርና ለብልት ያለመቆም ችግርን የሚያባበሱ የተለያዩ አዕምሮአዊ ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህም ዉስጥ፡-
• ድብርት፣መረበሽ ወይም ሌሎች የስነአዕምሮ ችግሮች
• ጭንቀት
• በጭንቀት ምክንያት የግንኙነት ችግሮች፣ የሰዉ ከሰዉ ተግባቦት ችግር ወይም ሌሎች ነገሮች

ለብልት ያለመቆም ችግር የሚያጋልጡ ነገሮች
ዕድሜዎ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ብልት ለመቆም ረዘም ያለ ሰዓት የሚወስድ ሲሆን ከቆመም በኃላ በጣም ጠንካራ ላይሆን ይችላል፡፡ ዕድሜ እየጨመረ በሚመጣበት ወቅት የብልት ያለመቆም ችግር የሚከሰተዉ ከእድሜ መጨመር ጋር አብረዉ የሚመጡ የጤና ችግሮችና የሚወስዷቸዉ መድሃኒቶች ስላሉ ነዉ፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች
• የውስጥ ደዌ ችግሮች፡- ስኳርና የልብ ችግሮች
• ሲጋራ ማጨስ
• ዉፍረት፡- በተለይ በጣም መወፈር
• የተወሰኑ መድሃኒቶች፡- ለድብርት፣ ለአለርጂዎች የሚሰጡ መድሃኒቶች፣ ለካንሰርና ለደም ግፊት ህክምና የሚሰጡ መድሃኒቶች
• አደጋ፡- በተለይ ለብልት መቆም የሚረዳዉ ነርቭ ላይ አደጋ ሲደርስ
• ስነልቦናዊ ችግሮች፡- ጭንቀት፣ድብርት
• አደንዛዥ ዕፅና አልኮሆል የሚጠቀሙ፡- በተለይ ረዘም ላለ ጊዜ ለተጠቀሙ
ለረጅም ጊዜ ብስክሌት የሚያሽከረክሩ፡- ይህ ነርቮችን ስለሚጫንና ወደ ብልት በሚሄደዉ የደም ዝዉዉር ላይ ግዜያዊ ጭነት ስለሚያመጣ ግዜያዊ የብልት ያለመቆም ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡

ለብልት ያለመቆም ችግር ጊዜ ሊደረጉ የሚችሉ ምርመራዎች፡-
• አካላዊ ምርመራ፡- በብልትዎ፣ በዘር ፍሬዎና በነረቮች ላይ ምርመራ ማድረግ
• የደም ምርመራዎች
• የሽንት ምርመራ
• የአልትራሳዉንድ ምርመራ
• በእንቅልፍ ሰዓት የብልት መቆም ምርመራ፡-
• ስነልቦናዊ ምርመራዎች

ለብልት ያለመቆም ችግር የሚደረጉ ህክምናዎች
መጀመሪያ የሚደረገዉ ለሌላ ህመም እየወሰዱ ያለ መድሃኒት ካለ ለብልትዎ ያለመቆም ችግር ምክንያት መሆን ያለመሆኑን ማረጋገጥ

በአፍ የሚዋጡ መድሃኒቶች
• ሲልደንፊል (ቪያግራ)
• ታደልፊል (ሲያሊስ)
• ቫርድንፊል

እነዚህ መድሃኒቶች የሚሰሩት ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሲሆን የብልትዎን ጡንቻዎች በማላላትና ወደ ብልት የሚሄደዉን ደም በመጨመር ወሲባዊ መነቃቃት በሚፈጠርበት ወቅት ብልትዎ እንዲቆም ያደርጋሉ፡፡እነዚህን መድሃኒቶች ከመዉሰድዎ በፊት የጤና ባለሙያዎትን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች የሚከተሉት ነገሮች ካሉ ላይሰሩ ይችላሉ ወይም ለጤና አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡-
• ናይትሬት ያላቸዉን መድሃኒቶች እየወሰዱ ከሆነ (ናይትሮግላይሴሪን)
• ለደም ማቅጠኛ የሚሰጡ መድሃኒቶችን እየወሰዱ ከሆነ፣ አልፋ ብሎከርስ የሚባሉና ለፕሮስቴት ህክምና እየወሰዱ ከሆነ፣ የደም ግፊት መቀነሻ መድሃኒቶችን እየወሰዱ ከሆነ
• የልብ ችግር ወይም ድካም ካለዎት
• የደም ግፊት በጣም መቀነስ ካለዎት ወይም በህክምና ያልተቆጣጠረ የደም ብዛት ካለዎት
• በስትሮክ ከዚህ በፊት ታመሁ ከሆነ
• በቁጥጥር ስር ያልዋለ የስኳር ህመም ካለዎት

ሌሎች መድሃኒቶች (በኢትዮጵያ ውስጥ ላይገኝ ይችላል)
• እራስን በራስ የሚወጉ አልፕሮስታዲል
• በብልት የሚገቡ አልፕሮስታዲል
• የወንዶች ሆርሞንን(ቴስቴስትሮን) መተካት

ከመድሃኒቶች አልሰራ ካሉ ወይም በተለያ ምክንያት መድሃኒቶችን መጠቀም የማቻል ከሆነ ሀኪምዎ የሚከተሉትን ሊያዝሎት ይችላል
• ፔኒስ ፓምፕ
• ፔኒስ ኢምፕላንትስ
• የደም ስር ቀዶጥገናዎች

ስነልቦናዊ ምክሮች
የብልት ያለመቆም ችግርዎ ከጭንቀት፣መረበሽ ወይም ድብርት ጋር የተገናኘ ከሆነ የስነዓዕምሮ ባለሙያዎችን ወይም የስነልቦና ባለሙያዎችን ማማከር ያስልጋል፡፡ የብልት ያለመቆም ችግር የመጣዉ አካላዊ በሆነ ችግር ቢሆን እንኳ ጭንቀትና የግንኙነት ችግር ማምጣቱ ስለማይቀር እነዚህን ባለሙያዎች ማማከር ይጠቅማል፡፡
የኑሮ ዘይቤ ለዉጥ ማድረግ
• ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ማቛረጥ
• ክብደትን መቀነስ
• የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ/ማዘዉተር
• አደንዛዥ ዕፅ ወይም አልኮሆል በመዉሰድ እየተቸገሩ ከሆነ ህክምና ማግኘት
• የግንኙነት ችግሮች ካለቦት መፍትሄ መፈለግ

ተጨማሪ ምክሮች
• ችግሩ ለረጅም ጊዜ ያለ/የሚቀጥል ነዉ ብሎ ያለመዉሰድ
• የትዳር ወይም የፍቅር አጋረዎን በመፍትሄዉም ይሁን በችግርዎ ዉስጥ አጋር ማድረግ
• ጭንቀትን፣መረበሽንም ይሁን ማንኛዉንም የስነአዕምሮ ችግሮች ችላ ብሎ ያለማለፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.