የወንዶች የጤና ችግሮች

prostate cancerወንዶችና ሴቶችን ለየብቻ ፆታ ለይተው የሚያጠቁና ለሞት የሚዳርጉ በርካታ የበሽታ አይነቶች የመኖራቸውን ያህል በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚከሰቱ ሆነው በአንደኛው ፆታ ላይ በርክተው የሚታዩ የበሽታ አይነቶችም አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 በአሜሪካ ሳይንቲስቶች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ሴቶች እንደ ማይግሪን (ራስ ምታት) ሪህና አስም በመሳሰሉ ከፍተኛ የስቃይ ስሜትን በሚያስከትሉ የጤና ችግሮች ከወንዶች በበለጠ የሚጠቁ ሲሆን ወንዶች ደግሞ ለሞት በሚዳርጉ የበሽታ አይነቶች ይጠቃሉ፡፡ ለዛሬው ወንዶችን ብቻ ለይተው ከሚያጠቁ የበሽታ አይነቶች መካከል ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡፡

1. የታይሮይድ ሆርሞን

በአንገት አካባቢ በሚገኝ አነስተኛ እጢ ውስጥ የሚገኝ ሆርሞን ሲሆን ሆርሞኑ አጠቃላይ የሰውነታችንን የሃይል አጠቃቀም የሚቆጣጠር ነው፡፡ ይህ ሆርሞን ከመጠን በላይ በሚሆን ጊዜ ለእንቅልፍ ማጣት፣ ለልብ ድካምና ለልብ ምት፣ ለክብደት መቀነስ ያጋልጣል፡፡
ሆርሞኑ ከመጠን ባነሰ ጊዜ ወይም ሰውነታችን ከሚያስፈልገው መጠን በታች በሆነ ጊዜ ለስንፈተ ወሲብ፣ ለብልት መወጠር አለመቻል፣ ለዝቅተኛ የወሲብ ፍላጐትና ዘር የመርጨት ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህ ችግር ወንዶችን ብቻ በተናጠል የሚያጠቃ የጤና ችግር ነው፡፡

2.ፕሮስቴት ካንሰር

ይህ በሽታ ገዳይ ከሆኑና ወንዶችን ከሚያጠቁ በሽታዎች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ሲሆን በወንዶች የመራቢያ አካል በተለይም በዘር ፍሬዎቻቸው እና ፈሳሽ በሚመነጭባቸው አካላት ውስጥ አላስፈላጊ ህዋሳት ያለ ገደብ ሲራቡ የሚፈጠር የጤና ችግር ነው፡፡ በሽታው በዘር የመተላለፍ እድል ያለው ሲሆን ብዙው ጊዜ እድሜያቸው ከአርባ አመት በላይ በሆናቸው ወንዶች ላይ ጐልቶ ይታያል፡፡

የፕሮስቴት ካንሰር በመጀመሪያዎች የመፈጠሪያ ጊዜው በቴስቶስቴሮን (የወንድ ሆርሞን) አማካኝነት ይነሳና ቀስ በቀስ እድገቱን እየቀጠለ ይሄዳል፡፡
እስከዛሬ በተደረጉ ጥናቶች፤ የበሽታውን መንስኤ ለማወቅ አልተቻለም። ነገር ግን የእድሜ መግፋት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል መጠጣትና አጫሽነት ካንሰሩን እንደሚያባብሱት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት ያወጣቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በዓለማችን ከስድስት ወንዶች አንዱ በዚህ በሽታ የመጠቃት እድል ገጥሟቸዋል፡፡ በላይኛው የታፋ አካባቢ ከፍተኛ የህመምና የማቃጠል ስሜት መኖር፣ ቶሎ ቶሎ መሽናትና ሽንት መጣሁ መጣሁ የሚል ስሜት መኖር ለዚህ በሽታ መከሰት ምልክቶች ናቸው፡፡

3. የዘር ፍሬ ካንሰር

እድሜያቸው ከ15-35 ያሉ ወጣቶችን በስፋት የሚያጠቃና በወንዶች የዘር ፍሬ ላይ የሚከሰት የካንሰር አይነት ነው፡፡ የዘር ፍሬ ካንሰር ዛሬ በአለም አቀፍ ደረጃ የበርካታ ወጣት ወንዶች የጤና ችግር እየሆነ ነው። ወንዶች የዘር ፍሬዎቻቸውን በየጊዜው በመዳሰስ እብጠትና ጠጠር ያለ ነገር መኖሩን መመርመርና ጥርጣሬ የሚያሳድር ነገር ከገጠማቸው በአፋጣኝ ወደ ህክምና ባለሙያ ጋ መሄድ እንደሚገባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

4. የጉበት ካንሰር (ሄፓቶሴሉላር ካርሴኖማ)

ይህ በሽታ በሁለቱም ፆታዎች ላይ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም ወንዶች በዚህ በሽታ የመጠቃት እድላቸው ከሴቶች በሁለት እጥፍ የበለጠ ነው፡፡ በሽታው ሒፓቶቶሳይት በተባለው የጉበት ህዋስ ላይ ተከስቶ ካደገ በኋላ ቀስ በቀስ አጠቃላይ ጉበትና መላው ሰውነት ላይ እያደገ በመሄድ፣ ለከፍተኛ የጤና ችግርና ለሞት የሚያጋልጥ በሽታ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ብዙ አልኮል በየጊዜው የሚጠቀሙ ሰዎች በጉበት ህብረህዋሳቸው ላይ ቁስለትና ጠባሳ እንዲፈጠር በማድረግ ለጉበት በሽታ ይጋለጣሉ። በሽታው በገዳይነቱ የታወቀና በየዓመቱ በርካቶችን ለህልፈት የሚዳርግ በወንዶች ላይ ጐልቶ የሚታይ በሽታ ነው፡፡

5. ከፍተኛ የደም ግፊት

ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በከፍተኛ የደም ግፊት ይጠቃሉ፡፡ የወንዳ ወንድነት ሆርሞን መጠን በደም ውስጥ ከፍተኛ ሲሆን የደም ግፊት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሥራ አካባቢ ውጥረት፣ የእንቅልፍ እጦትና ጭንቀት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በደም ግፊት በሽታ የበለጠ እንዲጠቁ ያደርጋቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ወንዶች ከሴቶች ይበልጥ በልብ በሽታ፣ በኮሌስትሮል፣ በደም ቧንቧ ችግሮች፣ በመተንፈሻ አካላት ካንሰርና መሰል የጤና ችግሮች እንደሚጠቁ በአሜሪካ ሳይካትሪስት ማህበር የተደረገና ባለፈው ዓመት ይፋ የሆነ ጥናት አመላክቷል፡፡ በአጠቃላይ ሴቶች እጅግ ስቃይ በሚያስከትሉ ህመሞች ወንዶች ደግሞ ለሞት በሚዳርጉ የበሽታ አይነቶች እንደሚጠቁም ጥናቱ አመልክቷል፡፡

 ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.