ድንገት የሚያፋቅረን ማግኔት የት ይገኛል?

ሊሊ ሞገስ
(ይህ ጽሁፍ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 77 ላይ ታትሞ የወጣ)

ሁልጊዜ የሚስማማቸውን የፍቅር ሰው ለማግኘት ከራሳቸው ጋር የሚመክሩና ከተፈጥሮ ጋር የሚሟገቱ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በቅፅበት እይታም የሚመለከቱትን ሰው ‹‹ምነው የእኔ ቢያደርገው በሚል የምኞት መንሰፍሰፍ ላጤነታቸውን የሚኮንኑም ጥቂት አይደሉም፡፡ ግን ሊስማማን የሚችለውን ሰው አይተን ብቻ እንዴት መምረጥ እንችላለን? የሚለው ሃሳብ ፈጥኖ የሚታሰብ አይሆንላቸውም፡፡ የሚስማማን ሰው በቅፅበት መለየት በእርግጥም መታደል ነው፡፡

magneticattractionጓደኛን መምረጥ በህይወታችን ውስጥ ከምንወስዳቸው ውሳኔዎች ሁሉ በእጅጉ የጠነከረ ነው፡፡ የእኔ ብለን ከልባችን የምናስበውን ሰው ለማግኘት ያለንን ጉጉት ከግብ ለማድረስ ስንል የምናፈሰው ነዋይ አንዳንድ የጥንድ አፈላላጊ ድርጅቶችን እና ዓለም አቀፍ የመረጃ ልውውጥ አገልግሎቶችን በቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እያንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል፡፡

ይሁንና ይህ ብቻ እርካታ አልሰጠንም፡፡ ለምሳሌ ዓለም አቀፍ (internet) የመረጃ ልውውጥ አገልግሎቶች በመጠቀም ጓደኛ ለማፈላለግ የሚንቀሳቀሱ 900 ሰዎች ላይ በ2005 እ.ኤ.አ ጥናት ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህም ጥናት መሰረት ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት የሚፈልጉትን ሰው አላገኙም፡፡ የሚስማማንን ሰው ለመምረጥ የምንጠቀምባቸው ዘይቤዎች ገና በጨለማ ውስጥ ያሉ ይመስላል፡፡

ጓደኛን ለመምረጥ የምንጠቀምበት ዘዴ ከምንም በላይ ውስብስብ ነው፡፡ ለመምረጥ የምንጠቀምባቸው መንገዶችም በሁለት አይነት መልኩ ይገለፃሉ፡፡ ልቦናችን/ህሊናችን እያወቀው ለመምረጥ የምንጠቀምባቸው ዘይቤዎች እና ሳናስበው ወይም ከህሊናችን/ከዕውቅናችን ውጪ ሆነን የምንጠቀምባቸው ዘይቤዎች ናቸው፡፡ ህሊናችን እያወቀው… የምንጠቀምባቸው ዘይቤዎች በጣም ጥቂቱ ክፍል ሲሆን የተቀረው ይህ ነው ብለን መግለፅ የማንችለው ማግኔታዊ ባህሪ የተነሳ የሚፈጠር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ፍቅር በቃላት ሊገለፅ የማይችል ድንቅ ኬሚስትሪ ነው የሚል ድምዳሜ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል፡፡

እያወቅን እንድንመርጥ የሚያስችሉ ጉዳዮች
በወንዶች ዓይን የሚገቡ ሴቶች ልጅ እግር የሆኑ እና በሳል የሆኑ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ቀጭን ወገብ ያላቸው፣ ሞላ ያሉ፡፡ ስስ ከንፈር እና ለስለስ ያለ የፊት ገፅታ ያላቸው ሴቶች ወንዶችን ይማርካሉ፡፡ ሴቶች ደግሞ ጀግና የሆኑ ወንዶች ይማርኳቸዋል፡፡ጡንቺስት የሆነ፣ ሰፋ ያሉ ትከሻ ያለው፣ ጥርት ያለ የቆዳ መልክ ያለው እና ጎልቶ የሚታይ የወንድነት ባህሪ ያለው፣ ወንዳወንድ የፊት ገፅታ የተላበሱ ወንዶች እንደሚማርኳቸው የቅርብ ጊዜ ጥናት አሳይቷል፡፡

በአጠቃላይ እነዚህ የወንድ ገፅታዎች ጥሩ የወሲብ ብርታት እና ጥሩ ዘረመል ያለውን ወንድ ያመለክታሉ፡፡ በተጨማሪም ሴቶች ሀብት ባላቸው ወንዶች ወይም ሃብትን ለማምጣት ብቃት ባላቸው ወንዶች ይማረካሉ፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እውቀት/የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ተጓዳኝ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ውበት፣ አዕምሮ እና ሀብት አለማቀፋዊ ነገሮች ናቸው ማለት ነው፡፡

በምንም የኑሮ መመዘኛ ከማንመጣጠናቸው ሰዎች ጋር (Supermate) በፍቅር ልንወድቅ አንችልም፡፡ በመካከለኛ ኑሮ የሚኖር አንድ ሰው ከአቅም በላይ ከሆነ ሰው ጋር ለመገናኘት እቅዱ ቢኖረው መግቢያ መውጪያው ይጠፋበታል፡፡ ምክንያቱም ከእንደነዚህ አይነት ሰዎች ጋር ጓደኝነት መመስረት ለጥቂት ሰዎች ካልሆነ በስተቀር ለአብዛኞቹ አስቸጋሪ ነውና፡፡ በምርጫ መሀል የፍቅር ጣልቃ ገብነት መኖር ጥቅ እዚህ ላይ ነው፡፡ በጥንዶች መሀል የፍቅር መኖር ጥቅሙ በተጠናከረ ኃይል ልጁን ለማሳደግ ብቻ አይደለም ከማንመጣጠን ሰዎች ጋር ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን ከማባከን ለመቆጠብም ጭምር እጂ፡፡ ስለዚህ ሰዎች በውበት፣ በጭንቅላት ብስለት እና በአኗኗር ዘይቤ ከራሳቸው ጋር ተመሳሳይ ከሆኑ ሰዎች ጋር በፍቅር ለመውደቅ ያዘነብላሉ፡፡

ሳናውቅ ፍቅረኛን የምንመርጥባቸው

እስካሁን የተመለከትናቸው ሰዎች ውጫዊ ኑሮአችንን በመመልከት ተማርከው የሚሆናቸውን ሰው ለመምረጥ የሚያስወስኗቸውን ነገሮች ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከላይ እንደተገለፀው በገሃድ የሚታይ ባይሆንም ወሳኝ የሆነ መጠቆሚያ ነው፡፡
ስለዘረመል እና የጓደኝነት ምርጫን አመላክቶ በተካሄደው ጥናት መሰረት በተገኘው አመርቂ ውጤት እያንዳንዳችን ለአንድ የተወሰነ የዘረመል ስብስብን ላካተተ ሰው ፍላጎታችን እንደሚያርፍ አሳይቷል፡፡ ይኸውም MHC (histocompatability complex) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በሽታ አምጪ ህዋሶችን በመከላከል ረገድ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ሁለት ጥንዶች ውስጥ ያለው የMHC አይነት የተለያየ ከሆነ የሚወልዷቸው ልጆ ጤናማዎች እና በሽታን የመከላከል ብቃታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ሰዎችን የመምረጥ ዝንባሌያችን የሚጨምረውም ከዚሁ ልዩነት በመነሳት ሲሆን በአጋጣሚ የሚጣመሩ ጥንዶች ተመሳሳይ የሆነ MHC የሚኖራቸው ሁኔታ ዝቅተኛ ነው፡፡

የተለያዩ MHC ያላቸው ሰዎች እንዴት ነው ሊገናኙ የሚችሉት? ይህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ግልፅ ባይሆንም ሽታ ወሳኝ የሆነ የመጠቆሚያ መሳሪያ ነው፡፡ ሰዎች ጓደኞቻቸውን በማሽተት ለይተው ይመርጣሉ፡፡ ጥናትም እንደሚያሳየው የተለያዩ MHC ያላቸው ሰዎች በለበሱት ልብስ ሽታ እርስ በርስ ይሳሳባሉ፡፡ ይህንን ነው የፍቅር ኬሚስትሪ ብለን የምጠራው፡፡

ብዙ ፍቅሮች ታስቦባቸው የተካሄዱ ሳይሆን በተለያየ አጋጣሚ የሚፈጠሩ ናቸው ይላል ሳይንስ፡፡ ድንገተኛ ፍቅር ወይም በድንገት በተፈጠረ አጋጣሚ የተነሳ ወደ ፍቅር፣ ወደ ግንኙነት አልያም ወደ ጋብቻ ሊያመራ ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ተፈጥሯዊ ከሆነ ስሪታችን ጋር የሚሄድ ነው፡፡ እንደተመራማሪዎች ገለፃ ከሆነ በድንገት በሚደረጉ የስሜት መሳሳቦ የተነሳ ልጆች ሊወለዱ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ እንስሳት ላይም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ በአይጦች ላይ፣ በዓሣዎች ላይ፣ በጥንቸሎች ላይ፣ እንዲሁም በዝንጀሮዎች ላይ የተደረገው ጥናት ያሳየው ድንገተኛ መዋደድና በአጋጣሚ ወደዘር መቀላቀል የማዘንበል ሁኔታ የታየ ክስተት ሲሆን ይህም በሰውነታችን ውስጥ ካለው ተፈጥሯዊ ማግኔት ጋር የተገናኘ ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡

አንድ ሰው አጠገቡ ካሉ ተቃራኒ ፆታዎች ጋር ላይፋቀር ይችላል፣ ለሌላ ሰው ቆንጆ የሆነች ሴት ለዚህ ሰው ቆንጆ ላትሆን ትችላለች፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በውስጣችን ያለው የፍቅር ማግኔት ከመከፈቱና መዘጋቱ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የፍቅር ማግኔት ሜጀር ሂስቶኮምፓቲቢሊቲ ኮምፕሌክስ በመባል የሚጠራ ሲሆን በአጭር መጠሪያውም ‹‹MHC›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህ የ‹‹MHC›› ዘርም ‹‹HLA›› በመባል የሚጠራውን ማለትም (Human Leukocyte Antigen›› የተባለና በነጭ የደም ሴል ላይ የሚገኝን ፕሮቲን ያስገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ፕሮቲን ዋና ስራ በሽታ መከላከል ይሁን እንጂ በተለይ አፍንጫችን ውስጥ የሚገኘውን ልዩ የጠረን መለያ ክፍል ባህሪ የመቅረፅ አቅም አለው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

በአፍንጫችን ውስጥ ቬሮሞናሳል በመባል የሚጠራ የሽታ ወይም የጠረን ማዕከል ያለ ሲሆን ይህም የጠረን ማጣሪያ ቦታ አንድን ተቃራኒ ፆታ ሳቢ ወይም የማይስብ መሆንና አለመሆኑን የምንለይበት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ምግብ ጥሩ መሆን አለመሆኑን ወይም ጤናማ መሆን አለመሆኑን የምንለይበት ትልቁ መንገድ ጠረኑ ነው የሚሉት ባለሙያዎች አንድም ሰው የአንድን ተቃራኒ ፆታ መስህብነት የሚያረጋግጠው በጠረን ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ ልዩ የፍቅር ጠረኞችን የሚሸከሙ ኬሚካሎች በልዩ ስማቸው ‹‹ፌርሞንስ›› በመባል ይጠራሉ፡፡

በዚህ ዙሪያ ባለሙያዎች የተለያዩ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ ከዚህም አንፃር አንዲት ሴት ለፍቅርም ሆነ ለወሲብ የበለጠ የምትሳበው ከእሷ ጋር የሚመሳሰል ዘር ካለው ጋር ሳይሆን ከእሷ ዘር ጋር የማይመሳሰለውን ነው፡፡ አንድ ወንድም በተመሳሳይ መልኩ አንዲትን ሴት ውብ አድርጎ እንዲመለከታት የሚያደርገው ወይም እንዲሳብባት የሚያደርገው ከእሱ የሰውነት ዝርያ ማለትም (MHC Gene) ጋር የማይመሳሰለውን ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ሰው ሴት/ወንድ ከእሱ ጋር የማይመሳሰል ዘር ከያዘ ሰው ጋር በድንገት ሳያስበው በፍቅር ሊወድቅ፤ ወደ ወሲብ ውሳኔ ውስጥ ሊያመራ፤ ወደ ጋብቻ ሊቀጥል አልያም ልጅ የመውለድ አጋጣሚንም ሊፈጥር ይችላል፡፡
በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት ከሆነ በአጋጣሚ ተመሳሳይ ዝርያ ካለው ወንድ ጋር የፀነሰች ሴት ሳታውቀው ፅንሱን ታስወርደዋለች፡፡ ሰውነቷ ፅንሱን አይቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ተመሳሳይ ዘር ካለው ወንድ የተፀነሰ በመሆኑ፡፡ እንዲሁም በሰው ሰራሽ የአረባብ ዘዴ የተፈጠሩ ሽሎችም ከተመሳሳይ ‹‹MHC gene›› ካላቸው የወንድና የሴት ዝርያ የተፀነሱ ከሆኑ ወደ ፅንስነት ማደግ አይችሉም ወይም በራሳቸው ይመክናሉ፡፡ ይህንንም ሆን ብለው ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው ስፐርምና ዕንቁላሎች እንዲዋኻዱ ተደርገው ውጤቱን በተመለከቱ ተመራማሪዎች ታይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ሴቶች የወንዶችን ቲሸርት ተሰጥቷቸው እንዲያሸቱና የየትኛው ቲሸርት ባለቤት የሆነ ወንድ የበለጠ እንደሚማርካቸው በተደረገው ጥናትም ሁሉም ማለት ይቻላል የሚማረኩበት ወንድ ከእነሱ የተለየ ዝርያ ያለውን ነው፡፡

እንደተመራማሪዎቹ ገለፃም ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የተቃራኒ ፆታ ሰዎ ዝርያ ከእነሱ ጋር የተለየ መሆኑን የሚወስኑት ሳያውቁት ቢሆንም ይህን መሰል ከእውቅናቸው ውጭ የሆነ ውሳኔ እንዲፈጠር የሚያደርገው የአፍንጫቸው ልዩ የዝርያ ማጣሪያ ጣቢያ ሲሆን ውሳኔውን ሳያውቁት የሚያስተላልፈውም ደግሞ ውስጠኛው አዕምሯቸው ነው፡፡ ሰውነታችን ይህን የሚያደርገው ይላሉ ሳይንቲስቶች የተለያየ ዝርያ ያላቸው ተቃራኒ ፆታዎች የሚፀንሷቸው ልጆች የሰውነት በሽ መከላከያ አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሳቢያ ረጅም ዕድሜ ስለሚኖሩ ሲሆን ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው ወላጆች ግን የሚወልዱት ልጅ የሚኖረው የበሽታ መከላከያ አቅም ደካማ ስለሚሆን ዕድሜው ስለሚያጥር ነው ይላሉ፡፡

መጥፎ ፍቅር የሚፈጥሩ አጋጣሚዎች

በአጠቃላይ ተፈጥሯዊ በሆነ የስሜት ምላሻችሁ የምትወስኑትን ውሳኔ ተቀበሉት፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው የሚከሰቱ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የእርግዝና መቆጣጠሪያ እየተጠቀሙ ያሉ ሴቶች የወንድ ምርጫቸው ከራሳቸው MHC ጋር ተመሳሳይነት ያለውን ነው፡፡ ስለዚህ መድሃኒት እየጠተቀሙ ያሉ ሴቶች በዘረመሉ ረገድ የማይስማማቸውን ወንዶች የመምረጥ አደጋ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ የእርግዝና መከላከያ መድሃኒት ከመውሰዳቸው በፊት የጠረን መረጃ ቢጠቀሙ ከሁሉ የበለጠ ተመራጭነት አለው፡፡
ሁለተኛ ምሳሌ ደግሞ ከሴቶች የወር አበባ ወቅት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የመማረክ ወይም ያለመማረክ ሁኔታ ከወር አበባ ዑደት ጋር ሊለዋወጥ ይችላል ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ ወንዶች የሴቶች ሽታ ማራኪ የሚሆንላቸው የማህፀን እንቁላላቸው ዝግጁ በሆነበት ወቅት ነው፡፡ የፍቅር ስሜት ውስጥ የሚገቡትም በዚህ ወቅት ነው ይባላል፡፡

በተጨማሪም ወሲብ መፈፀም ጓደኛችሁን የምትመርጡበት መንገድን ሊያወሳስበው ይችላል፡፡ ወሲብ ከፈፀምን በኋላ አዕምሮአችን ኦክሲቶሲን የተባለ ሆርሞን ያመነጫል፡፡ ይህም ሆርሞን ሞ ያለ የጓደኝነትን ስሜት የሚፈጥር ፍቅር እንዲኖረን እና ልጅ የማሳደግ ጥሩ መንፈስ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ ከተቃራኒ ፆታ ጋር፡፡

ይህ ማለት እንግዲህ በጥድፊያ የሚፈፀም ወሲብ ሙሉ በሙሉ ለእናንተ ከማሆን ሰው ጋር በፍቅር እንድትወድቁ ከፍተኛ ግፊት ውስጥ ሊያስገባችሁ ይችላል፡፡ ይህም ማለት ተፈጥሯዊውን ‹‹MHC›› ዘራችሁ እንድትወስኑ ያሳስታችኋል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.