ሴተኛ አዳሪዎች ከአረብ አገራት የከፋ በደልና እየተፈፀመባቸው ነው

መንግሥቱ አበበ

An hoping to survive. Looking for cheap sex

አንዲት ዝሙት አዳሪ ቤት ተሸንሽኖ አንድ ሜትር ተኩል በሆነ የማያፈናፍን ክፍል ትከራያለች፡፡ ኪራዩ በቀን ወይም በወር አይደለም በሰው ነው፡፡ አንድ ወንድ ሲገባ 5 ብር ትከፍላለች፡፡ ምንም ነገር ከውጭ መግዛት አትችልም፡፡ ለምሳሌ ቡና፣ ለስላሳ፣ ማስቲካ፣ ሲጋራ (የምታጨስ ከሆነ)፣ … መግዛት ብትፈልግ ከአከራዮቿ ነው መግዛት ያለባት፡፡ ከምትቆምበት በራፍ ዞር ካለች ‹ሰው መጥቶ የማገኘውን ብር አሳጣሽኝ› በማለት 5 ብር ያስከፍሏታል፡፡ ይህ ሁሉ በደል የሚፈጸመው እዚሁ በመዲናችን ባሉ ሰፈሮች ነው – ሾላ፣ ሰባተኛ፣ … ነገር ግን ይህኛው ሳያመንና ሳያስጨንቀን በየአረብ አገራቱ በእህቶቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍ፣ በደልና ጭቆና ያንገበግበናል … በማለት እንባ እየተናነቀው የተናገረው፣ ፅናት የማኅበራዊና ልማት ድርጅት ሊቀመንበር ብርሃኑ መለሰ ነው።

ብርሃኑ፣ የዲኬቲ ኢትዮጵያ የማህበራዊ ግብይት ኮንዶም ሻጭ (ያንግ ማርኬተርስ) ነው። ወጣቱ፤ ይህን አሳዛኝ ታሪክ ያጫወተን፣ ዲኬቲ ኢትዮጵያ፤ ጋዜጠኞች፣ የኮንዶም ሻጭ ወጣቶች ሕይወት ምን እንደሚመስል ግንዛቤ እንዲያገኙ በዚህ ሳምንት በፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ነው፡፡
ብርሃኑና የሌሎች ማህበራት ያንግ ማርኬተርስ ከዲኬቲ ጋር በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውንና ኮንዶም ሸጠው በሚያገኙት ገቢ ህይወታቸው መለወጡን  ተናግረዋል። ከአባሎቻቸው መካከል ባሳዩት ጥሩ የሥራ ብቃት ዲኬቲ በቋሚ ሠራተኝነት የቀጠራቸውና  በዩኒቨርሲቲና በኮሌጅ ደረጃ የሚማሩ አባላት እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ከዲኬቲ ጋር የሚሰሩ ወጣቶች በተለያዩ ክበባት የተደራጁ ሲሆን ኮንዶም በመሸጥ ኤች  አይቪን በመከላከል፣ የቤተሰብ ምጣኔ ግንዛቤ በመፍጠር፣ በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤ ላይ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ክበባት ውስጥ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ዲኬቲ የሚሰጣቸውን ኮንዶም እየሸጡ 75 በመቶውን ለራሳቸው ይወስዳሉ፣ ቀሪው 25 በመቶ ለድርጅቱ ሲሆን ለቤት ኪራይ፣ ለጽህፈት መሳሪያ፣ ለቢሮ ቁሳቁስ መግዣ ስለማይበቃቸው ዲኬቲ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡

ኮንዶም መሸጥ ብቻ ሳይሆን በየት/ቤቱ የአቻ ለአቻ ክበባት በመፍጠር ስለ ኤች አይ ቪና የአባማዘር በሽታዎች፣ ልቅ ወሲብ ስለሚያስከትለው ጉዳትና መታቀብ ስላለው ጥቅም፣ …. ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ስራቸው ብዙ መጥፎ ነገር እንዳጋጠማቸው የጠቀሱት ወጣቶቹ፤ በአባቷ የተደፈረች፣ ት/ቤት ሽንት ቤት ውስጥ የወለደች ልጅ፣ … ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የዲኬቲ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትና የኮንዶም አቅርቦት 50 በመቶ እንደሆነ የጠቀሱት የድርጅቱ አገር አቀፍ የችርቻሮ ሽያጭ ማናጀር አቶ ፋሲል ጉተማ፤ ኮንዶም ኤችአይቪ ከመከላከሉም በላይ በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች በመከላከል፣ አዳዲስ የኤችአይቪ በሽተኞች ቁጥር መቀነስ የጤና ግብአት እንደሆነና ከሚጠብቁት በላይ ውጤት ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡

ወደፊት ያንግ ማርኬተሮች ከኮንዶሙ ጋር የሚዋጥ የወሊድ መከላከያ፣ የኑትሪሽን ምርቶችና ለምለም (ኦአርኤስ) የተባለውን መድኃኒት ከኮንዶም ጋር እንዲሸጡ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው አቶ ፋሲል ገልጸዋል፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.