የቂጥኝ ምልክቶች (Syphilis)

secondary_syphilisየቂጥኝ ምልክቶች በሶስት የበሽታው ደረጃዎች ላይ ተለያይተው ይቀመጣሉ፡፡ በበሽታው ከተለከፉ በኋላ ከ 9 – 90 ቀናት (በአማካይ 21 ቀናት) የሚሆን የመራቢያ ጊዜ ይኖራል፡፡ በዚህን ጊዜ ምንም አይነት ምልክት አይታይም፡፡ በእያንዳንዱ የበሽታው ደረጃ ላይ ልዩ ልዩ ምልክቶች ሊታዩ ወይም ይህ ነው የተባለ ምልክት ላይታይ ይችላል፡፡

ደረጃ 1 – መጀመሪያው (Primary Syphilis)

የመጀመሪያው የቂጥኝ ደረጃ የሚመጣው ከመራቢያው ጊዜ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ህመም የሌለው ነገር ግን በጣም የተበከለ Chancre (ሻንከር) የተባለ ቁስል በብልት አካባቢ አልፎ አልፎ ደግሞ በአፍ አካባቢ ይመሰረታል፡፡ ይህ የበሽታው ደረጃ ከሌሎቹ በጣም ተላላፊ ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ሰው ንክኪ በሚፈጥርበት ወቅት በበሽታው ሊበከል ይችላል፡፡ ቁስሎቹ ያለ ምንም ሕክምና ከሶስት እስከ ስድስት ሳምንት ውስጥ ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ 25% በሚሆኑት ጉዳዮች ላይ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ይሸጋገራሉ፡፡

ደረጃ 2 – ሁለተኛው (Secondary Syphilis)

ሁለተኛው የቂጥኝ ደረጃ ከአንድ እስከ ሶስት ወራት ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህ ደረጃ በአብዛኛው ከቆዳ የተያያዘ ነው፡፡ ሮዝ ቀለም ያላቸው ሽፍታዎች በመዳፍ፣ በውስጥ እግር እና በተለያዩ የቆዳ ክፍሎች ላይ ይወጣሉ፡፡ እነዚህም በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የፀጉር መሳሳት፣ የጉሮሮ ቁስለት፣ በአፍና በአፍንጫ የሚወጡ ነጭ ልጣፊዎች፣ ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና የክብደት መቀነስ ያሉትን ምልክቶች ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ ልክ እንደ መጀመሪያው ደረጃ ሁሉ ሁለተኛውም ያለ ሕክምና ሊሰወር ይችላል፡፡ከዚህ ቀጥሎ የበሽታው የድብቅ ደረጃ (Latent Stage) ላይ ይገባል፡፡ ከሁለተኛው ወደ ሶስተኛው ደረጃ እንደ መሸጋገሪያነት የሚያገለግል ነው፡፡ ይህ ደረጃ ያለ ምንም ምልክት ለአመታት ይቆያል፡፡ ከዚህ በኋላ ቂጥኝ  ወደ ሶስተኛውና አደገኛው ደረጃ ይሸጋገራል፡፡

ደረጃ 3 – ሶስተኛው (Teritiary Syphilis)

ያለ ሕክምና ከቆዩ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ተጠቂዎች ወደ ሶስተኛው ደረጃ ያመራሉ፡፡ ሶስተኛው እና የመጨረሻው ደረጃ ከመጀመሪያው ኢንፌክሽን ከ 3 እስከ 15 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ በሽታው ተላላፊ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ባክቴሪያው ደም ውስጥ ዘልቆ ስለገባ በልብ፣ በአንጎል፣ እና በነርቮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ይህ ሲሆን ዝም ብሎ መከታተል ለአይነ-ስውርነት፣ ለድንቁርና፣ ለፓራላይሲስ (Paralysis) አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡

ዋናው ጤና

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.