ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ የመጣውን የተማሪዎች ዝሙት አዳሪነት ለመከላከል ከተማሪዎች ካውንስል፣ ከመምህራን፣ ከተለያዩ ክበባት፣ ከዩኒቨርስቲው ሠራተኞች እና ከሆቴል አስተዳደሮች የተዋቀረ ልዩ ኮሚቴ አቋቋመ። ይኸው ኮሚቴ የዩኒቨርስቲውን ዲን የበላይ ጠባቂው አድርጎ ሥራውን ጀምሯል።

የኮሚቴው ዋነኛ ሥራ በዝሙት ተግባር በተሰማሩ ሴት ተማሪዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ነው። የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ምንጮች ለሪፖርተራችን እንደገለጹት ከኾነ ከአሁን በኋላ ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ያለበቂ ምክንያት በምሽት የሚወጡ እና የሚያድሩ ሴት ተማሪዎች ስማቸው እንደሚመዘገብ እና በዝሙት አዳሪነት የሚያስጠረጥር ተግባር ሲያከናውኑ ከተገኙ ያለ ምንም ምኅረት ከዩኒቨርስቲው እንደሚባረሩ የሚገልጽ አዲስ ሕግና መመሪያ ወጥቷል።

“በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የገንዘብ ችግር ያለባቸው የዩኒቨርስቲው ሴት ተማሪዎች በደላሎች አማካኝነት በድብቅ የዝሙት አዳሪነት ተግባር ያከናውኑ ነበር” ሲል የገለጸው የሦስተኛ ዓመት የሕግ ተማሪ እና የኮሚቴው አባል (ስሙ እና ዲፓርትመንቱ እንዲጠቀስ አልፈለገም) ጉዳዩ እየባሰበት መምጣቱን ተናግሯል። “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በርካታ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በትላልቅ ደላሎች አማካኝነት እየተመለመሉ የውጭ አገር እና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች በሚስተናገዱባቸው ሆቴሎች ውስጥ ፎቷቸውንና አድራሻዎቻቸውን በድብቅ ማኑዋል (ሜኑ) ላይ በማኖር በቋሚነት የተወሰኑ ሰዓታት የወሲብ አገልግሎትና በሣምንት ለሁለት እና ለሦስት ቀናት ደግሞ አዳር እስከ መሥራት ደርሰዋል” ብሏል።

እንደ ተማሪው ገለጻ ዩኒቨርስቲው ይህን መሰል አዲስ የሥነ ሥርዐት ሕግ እና መመሪያ በአስቸኳይ ለማውጣት የተገደደው ከወር በፊት በዩኒቨርስቲውመሥተዳደርና በተማሪ ካውንስሉ በተደረገ የህቡዕ (የድብቅ) ጥናት ላይ በመመሥረት ነው። ዩኒቨርሰቲው በተመረጡ ሆቴሎች የፔንሲዮን አሠራር ሂደትላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት የበርካታ ሴት ተማሪዎችን አድራሻና ፎቶዎች በማንዋሉ (ሜኑው) ላይ በማግኘቱ እና በተጨባጭ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት በመመልከት በማረጋገጡ ጭምር ነው።

ዩኒቨርስቲው ድርጊቱን በተደጋጋሚ ሲያከናውኑ ነበር ያላቸውን ሴት ተማሪዎች በተናጠል በማነጋገር የምክር አገልግሎት ሰጥቷቸዋል። ለችግሩ ምክንያት ተደርገው የቀረቡት ደግሞ የገንዘብ ችግር (የኪስ ገንዘብ እጥረት)፣ የሞራል መውደቅ፣ የዕድሜ እኩዮች እና የጓደኛ ጫና፣ የሱስ ተገዢመኾን፣ መረን የለቀቀ የመዝናናት ፍላጎት፣ የሆቴል መስተንግዶ ደላሎች አማላይ የገንዘብ አቅርቦት እና ከዚህ በፊት ከዩኒቨርስቲው የተባረሩ ሴትተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ከመመለስ ይልቅ ትምህርት ላይ ያሉ ለማስመሰል በቆይታ ከዚህ ተግባር ባለድርሻዎች ጋራ የመሠረቱት ጥብቅ ግንኙነት ተማሪዎችን ለዝሙት አዳሪነት እንዲጋለጡ እንዳደረጋቸው ምንጮቻችን አስረድተዋል።

“ለምሳሌ እኔ ውስጥ የተፈጠረ አንድ የኅሊና ውዝግብ ልንገርህ” ያለን የጋዜጠኝነት እና የኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ (ስሙእንዲጠቀስ አልፈለገም) “በወቅቱ ከዩኒቨርስቲው ለዳሰሳ ጥናት በወጣንበት ሰዓት የጓደኛዬ እጮኛ በአንድ ሆቴል ውስጥ ከአንድ ፈረንጅ ጋራ አልጋ ይዛ እንደነበር አረጋግጠናል፤ ነገር ግን ይህን ለጓደኛዬ ማሳወቅ አለብኝ ወይስ የለብኝም የሚለው አእምሮዬን እና ልቡናዬን እየበጠበጠኝ ነው” ብሏል።

ከዓመታት በፊት በአንዳንድ የዩኒቨርስቲው የሶሻል ሣይንስ ተማሪዎች ተርም ፔፐር እና የመመረቂያ ጽሑፎች ላይ ይህ ችግር መኖሩን ተጠቋቁሞ ነበር። ይኸው ችግር መኖሩ ከታወቀ ወዲህ በቂ ትኩረት በዩኒቨርስቲው መስተዳደር አልተሰጠውም ያለው ይኸው ተማሪ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኤች አይ ቪ ኤድስ እና በሥነ ፆታ ላይ የሚሠሩ ክበባት እና ድርጅቶች የችግሩን ጥልቀት እንዲመረምሩት አስገድዷቸዋል። ባገኙት ውጤት ላይ በመመሥረትም አመሻሹ ላይ ከካምፓስ ዶርም ወጥተው በሆቴሎች የሚያመሹ እና የሚያድሩ ሴት ተማሪዎች በመበራከታቸው ዩኒቨርስቲው ይህን ኮሚቴ ለማዋቀርና ጠበቅ ያለ የሥነሥርዓት ሕግ ለማውጣት ተገዷል ሲል ተናግሯል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.