“ፕሌይ ቦይ” ተብሎ በሚጠራው የፍትወት መቀስቀሻ መጽሔት ውስጥ ሴቶችን ትንሽ ደስ የምትል ለመጫወቻ የምትሆን ዓይነት እንስሳ አድርጎ ነው የሚያቀርባቸው

 ፕሌይ ቦይ ተብሎ በሚጠራው የፍትወት መቀስቀሻ መጽሔት ውስጥ ሴቶችን ትንሽ ደስ የምትል ለመጫወቻ የምትሆን ዓይነት እንስሳ አድርጎ ነው የሚያቀርባቸው “ፔንት ሀውስ” የሚባለው መጽሔት ደግሞ ሴቶችን ለቤት ውስጥ መጫወቻና መዝናኛ የሚሆኑ ልክ እንደ ድመትና እንደውሻ (እንደ ቤት ውስጥ እንስሳ) አድርጎ ነው የሚቆጥራቸው። ወይንም እንደ አንድ የሰው አካል አንድ ክፍል ብቻ አድርጎ ነው የሚቆጥራቸው። አንዳንድ የልቅ ፍትወት ፊልሞች ላይ ሴቶች ፊታቸው ሳይታይ ኃፍረተ ሥጋቸው ብቻ እንዲታይ በማድረግ ያቀርቧቸዋል። ይህን የሚያደርጉት ምን ዓይነት አስተሳሰብ ለማራመድ መሰላችሁ? ሴቶች ሰብዐዊ ናቸው ሆኖም ለስሜት ማርኪያና መጫወቻ አሻንጉሊት ሆነው ብቻ የተፈጠሩ ናቸው የሚለውን አስተሳሰብ በሰው ህሊና ውስጥ ለመቅረጽ ነው።

አንዳንድ የስፖርት መጽሔቶች የመዋኛ ልብስ ላይ ብቻ የሚያተኩር ዕትም አላቸው። ይህም በቀላሉ የሚያሳየው ሴቶች ሰብዓውያን ሳይሆኑ በቃ ልክ እንደ አንድ የስፖርት ዓይነት እንደሚታዩ ነው። ልቅ የፍትወት ፍልስፍና ወሲብን እንደ ስፖርት ውድድር አድርጎ ያሳያል፤ በውድድርም አሸናፊና ተሸናፊ እንደሚኖር ሁሉ ወንዱ ራሱን አሸናፊ መሆኑንና አለመሆኑን እንዲመዝንበትና አሸናፊነቱን እንዲኩራራበት ያደፋፍረዋል። ስለዚህ ወንዱ ከስንት ሴት ጋር እንደተኛ፣ ከተኛቸውም ሴቶች ጋር ያደረጋቸውን ነውሮች በማሰላሰል እንዲመሰጥና ራሱን ለዚህ ልቅ ለሆነ ልምምድ እንዲያስገዛ ለማድረግ ታስቦ ነው የተዘጋጀው። ወንዶች ማንነታቸውን የሚፈትኑትና የሚመዝኑት ስንት ሴቶችን ድል በማድረግ ወሲብን በመፈጸማቸው ይሆናል።

በተለይም የፖርኖግራፊ ማስታወቂያ ዕቃን ለማሻሻጥ በሚያስደንቅ ሁኔታ የሴትን ስብዕና ከማጉደፍም አልፎ ቃላት በማይገኝበት ሁኔታ በማቅረብ በዚህ ንግድ ለተሰማሩ ጥቂት ግለሰቦች የሃብት ምንጭ ሆኗል። ይኸው የረከሰ አመለካከት ነው ድንበርና አየር ሳይገድበው አልፎ ተርፎ መጥቶ ዛሬም በየሃገሩ በዝሙት አዳሪነት የተሰማሩትን ሴቶች ወንዶች እንደ ሸቀጥ ገንዘብ ከፍለው በመውሰድ ከሰብዐዊነት ውጭ ሊጠቀሙባቸው የሚፈልጉት። ለምን ቢባል እንደማንኛውም ሸቀጥ ዋጋ ተከፍሎባቸዋል።

በፖርኖግራፊ ገበያ አይነ ግቡ የሆነ የሰውነት ቅርጽ የሌላት ሴት ትናቃለች፣ ትጠላለች። እንደነዚህ ዓይነት ሴቶችን ውሾች፣ ዓሣነባሪዎች፥ አሣማዎችና ከዛም የባሰ ስም ይሰጧቸዋል። ምክንያቱም ለልቅ ወሲብ ፊልም ንግድ እነርሱ ያወጡትን የውበት መመዘኛ ለማሟላት ስላልቻሉ ብቻ ነው እንዲህ ተብለው የሚጠሩት። ልቅ ፍትወት ስለሴቶች ክብረህሊናና ስብዕና ምንም ግድ የለውም፤ የሚፈልገው ጥሩ ገበያ ይኖረዋል ብሎ የሚያስበው ገላዋን ብቻ ነው።

የፖርኖግራፊ ዝግጅት ፍልስፍና ሴቶች “እምቢ” ማለታቸው በተዘዋዋሪ መንገድ “እሺ” ማለታቸው ነው ብሎ ነው የሚደመድመው፤ በዚህ የፊልም ዝግጅታቸው ውስጥ ሴቶች ሲደበደቡና ሲደፈሩ፣ በሚያሰቅቅ ሁኔታ ሥቃይ ሲቀበሉ ያሳያሉ፤ በመጨረሻ እነዚያው ሴቶች ያለፉበትን ሁኔታ ሁሉ ልክ እንደወደዱት አድርገው እንዲተውኑ ያደርጓቸዋል። ስለዚህ ይህ አሰራር ወንዶችን ለማዝናናትና ርካታን እንዲያገኙ ለማድረግ ሴቶችን ማሰቃየትና እንደፈለጉ ቢያደርጓቸው ምንም አይደለም የሚል መልዕክት ያለው ነው።

ልቅ ፍትወት ፊልም በሴቶች ላይ የተደረገ ጥላቻና ንቀትን የታጀለ ንግግር የሞላበት ነው። በፊልሞቹ ውስጥ ሴቶች ስቃይ ይቀበላሉ፣ በንቀት ይተፋባቸዋል። በመቶ በሚቆጠሩ ዘግናኝ መንገዶች ክብራቸውን በሚገፍፍ ሁኔታ ይሰቃያሉ። የሚያሳዝነው ግን ይህን ሥቃይ የሚቀበሉ ሴቶች የበለጠ እንዲያሰቃይዋቸውና እነዲያጎሳቁሏቸው ሲለምኑና ይህንን ጉስቁልና እንደሚወዱት አድርገው እንዲተውኑ ያስገድዷቸዋል። ይህን ሁሉ ነገር የተመለከተ ወንድ ምን ያህል ለሴቶች ክብር ይኖረዋል? ሴቶችን ከልቡ ማፍቀርስ እንዴት ይችላል?

የልቅ ፍትወት ትልቁ ገበያ የሚያተኩረው ሴቶች “ሕጻናትን” ተመስለው የሚፈጽሙት ልቅ ወሲብ ነው። ትልቅ ሴት ነች፣ እንደ ህጻን ሴት እንድትለብስና የህጻን ዓይነት ጫማ እንድታደርግ፣ ጸጉሯን እንደ ህጻን ሴት እንድትሰራና የህጻናት የጸጉር ጌጥ ጸጉሯ ላይ እንድትሰካ፣ አሻንጉሊት እንድትይዝ ይደረግና፣ ልቅ የፍትወት ፊልም እንድትተውን ትደረጋለች። ይህ ምን መልዕክት የሚያስተላልፍ ይመስላችኋል? አዋቂዎች ህጻናትን ለልቅ ፍትወት ቢጠቀሙባቸው ምንም አይደለም የሚል አይደለም? ይህ አካሄድ እነዚህ የልቅ ፍተወት ፊልም አዘጋጆች ህጻናትንም ገና ከጠዋቱ ለዚህ ገበያቸው እያዘጋጇቸው እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

ልቅ የፍትወት ፊልም ዝግጅት ሥራቸውን ይበልጥ የሚስብና በሱሷቸው የተጠመዱትን የበለጠ ለማስገበር ሲፈልጉ አብዛኛው የተውኔታቸው ታሪክ የሚያጠነጥነው ሕገወጥ ተግባርና ወንጀልን አስታክከው በመስራት ነው። ይህ ማለት ፍትወትን ማጣጣምና የበለጠ መርካት የሚቻለው በደንቡና በአግባቡ ስትፈጽመው ሳይሆን ሕገወጥ በሆነ መንገድና ከወንጀል ጋር ስትፈጽመው ነው የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ።

ልቅ የፍትወት ፊልም የዝሙት አዳሪነትን አስከፊና አስነዋሪ ገጽታ በሚያብረቀርቅ ቀለማት እየቀባባው ሌሎችን እያሳተ ወደዚህ አስነዋሪ ተግባር እንዲገቡ እያደፋፈረ ነው። ሐቁ ግን ፊልም ቀባብቶ እንደሚያቀርባቸው ዓይነት አይደለም፤ ብዙዎች እንደሸቀጥ ከየአገሮች ተገዝተው በባርነት ሥርዐት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የሚያውቅ የለም

በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው በልቅ ፊልም ዝግጅት ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነው የሚታዩት ሴቶቸ አብዛኛዎቹ በቅርብ ዘመዶቻቸውና በጎረቤቶቻቸው የመደፈር ዕጣ የደረሰባቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በግብረሥጋ ግንኙነት የተነሳ ተላላፊ በሆኑ በማይድኑ በሽታዎች የተያዙ፣ አንዳንዶቹም በያዛቸው የግብረሥጋ ግንኙነት በሽታ የተነሳ በወጣትነታቸው ሕይወታቸው ያለፈ፣ ብዙዎቹ የሚያልፉበትን አስጨናቂና አስቀያሚ ልምምድ ለመርሳት ሲሉ በኃይለኛ አደንዛዥ ዕጽ ሱሶች የተለከፉ ናቸው።

ይቀጥላል….

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.