ሴትን ወደህ በሴቷ አለመወደድ የተለመደ ነገር ነው። ሴትም ወንዱን ወዳ በወንዱ አለመወደድ ተደጋግሞ የሚከሰት ነው። አንዳንዴ “ከዛሬ ነገ ሐሳቧን ትቀይር ይሆናል” እያልክ እሷን ለማግኘት ብዙ ትለፋለህ። አማላጅ ትልካለህ፣ ታስለምናለህ። ትጃጃላለህ። እሷ ግን ወይ ፍንክች!

ተስፋ ሳትቆርጥ ብዙ ትጥራለህ። ለውጥ የለም። በሁኔታው ትበሳጫለህ። ራስህን ትጠላለህ። በመጨረሻም እሷን ወይም የሄዋንን ዘር ሁሉ ለመበቀል ከራስህ ጋር ቃል ትገባለህ። ይሄ ሁሉ አላስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ካልፈለገችህ፣ አልፈለገችህም! ያለህ አማራጭ ራስህን ከሷ ማራቅ፤ ሌላ ፍቅረኛ መፈለግ። እሷ ስለቀረች የመሬት መንቀጥቀጥ አይነሳም፤ ዘጠነኛው ሺህ አይቃረብም። እንደውም በሷ ምትክ፣ ሌሎች ከሷ የተሻሉ ታገኝ ይሆናል። እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረስህ በፊት ግን ገና ከልጅቷ ጋር ስትተዋወቅ፣ እሷ የምትሰጥህን ምልክቶች በአግባቡ ማንበብ ብትችል ኖሮ፣ ራስህን ከዚህ ሁሉ ጣጣ ባዳንክ ነበር።

አንድ ሴት ለአንድ ወንድ የአልፈልግህም ምልክቶችን የምትሰጠው ለግንኙነት እንደማትፈልገው በግልጽ መናገር ስለሚከብዳትና ጓደኝነቱን ማጣት ስለማትሻ ሊሆን ይችላል። “አታስቸግረኝ፣ እኔ እንደሆንኩ ለፍቅር ግንኙነት አልፈልግህም፣ ለፍቅር የማስብህ ሰው አይደለህም” ከማለት ይልቅ በምልክት መልዕክቷን ማስተላለፍ ሊቀላት ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ አንተን ለመፈተን ስትልም፣ የማትፈልግህ መስላ ልትተውን ትችላለች። መታደን፣ መለመን ከሚያስደስታቸው ሴቶች መካከል አንዷ ልትሆን ትችላለች።

ያለምንም ውጣ ውረድ ከሚወዱት ጋር የፍቅር ግንኙነትን የሚመሰርቱ ሴቶች እንዳሉ ሁሉ፣ በእምቢታ ጀምረው “እሺ” ማለትን የሚመርጡ ጥቂት አይደሉም። አንዳንድ ሴቶች ለሚወዱት ወንድ፣ ፍቅራቸውን ወዲያው መግለጽ ሊከብዳቸው ይችላል። አፍቃሪህ “እወድሃለው ስለው ቢኮራብኝስ?” በማለት ስሜቷን ሳትገልጽ፣ አምቃ ልትይዝ ትችላለች። ስለዚህ አንተን ለመፈታተን ምልክቶችን ትሰጥህ ይሆናል። ስሜቷን ወይም የምትሰጥህን ምልክቶች በሚገባ ተረድተህ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ደግሞ ያንተ ፋንታ ነው።

የሴት ጓደኛህ ለፍቅር ግንኙነት እንደማትፈልግህ ለመግለጽ የምታስተላልፋቸውን ምልክቶች በዚህ ጽሁፍ ለመዳሰስ እንሞክራለን።

የከነፍክላት ልጅ ለፍቅር ግንኙነት የማትፈልግህ ከሆነ፦

1) የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ዝግጁ እንዳልሆነች ትነግርሃለች።
አንተን በፍቅረኛ ዓይን አታይህም። ብዙ ሴቶች ያልጠበቁት ሰው ለፍቅር ጓደኝነት ሲጠይቃቸው፣ በቅድሚያ ዝግጁ አለመሆናቸውን ይገልጻሉ። በሌላ አነጋገር “ላፈቅርህ አልችልም” ማለታቸው ነው። “ላስብበት፣ ጊዜ ስጠኝ” ካለችህ፣ የፍቅር ጥያቄ ታቀርባለህ ብላ አስባ እንደማታውቅ ያሳያል። በጣም የምትግባቡ ጓደኞች ብትሆኑም፣ በፍቅረኛ ዓይን ላታይህ ትችላለች። ለዚህም ይሆናል የማሰብያ ጊዜ የጠየቀችህ። ስለዚህ ታስብበት። ጊዜ ስጣት። በሰጠሃት በቂ የጊዜ ገደብ ምላሽ ካላገኘህ፣ አፈግፍግ። ጥሩ ጓደኞች ልትሆኑ ትችላላችሁ፤ ፍቅረኞች ግን ልትሆኑ አትችሉም። የጓደኝነትንና የፍቅረኝነትን ድንበር ጠንቅቀህ ማወቅ ይኖርብሃል።

“እንዴት እንደዚህ ታስባለህ? የማይሆን ነገር ነው!” ካለችህ፣ የጓደኝነትን ትርጉም ባለመረዳትህ፣ በጓደኝነትና በፍቅረኛነት መካከል ያለውን ድንበር ባለማወቅህ ወይም አውቀህ በመጣስህ አልተደሰተችም ማለት ነው። “ጓደኛዬ” ብላ ብዙ ነገሮችን ስትነግርህ፣ ሚስጥሯን ስታካፍልህ፣ አንተ በሌላ ነገር ትተረጉመዋለህ ብላ አልነበረም። ሴቶች ለጓደኝነት ከብዙ ነገር የበለጠ ክብርና ዋጋ ይሰጣሉ። ፍቅረኛ መሆን ደግሞ አለመግባባት ሲፈጠር ጓደኝነትን ሊያሳጣ ይችላል። ስለዚህ ጓደኝነት ወደ ፍቅረኝነት እንዲሸጋገር የማይፈልጉ ሴቶች አሉ።

2) ሁል ጊዜ ደዋዩ አንተ ብቻ ነህ። እሷ ስትደውልላትም አታነሳም።

ለዚህ ምክንያቱ :-

a) ልታናግርህ አትፈልግም። ደጋግመህ መደወልህ አሰልችቷታል። ድምፅህን መስማት አትፈልግም።

b) ትዝ አትላትም። መደወልህን ብታውቅም፣ መልሳ የደወልችልህ መስሏት ረስታሃለች።

አንድ ጊዜ ደውለህ ሳታነሳ ስትቀር መልሰህ ደውልላት። ተፈላጊነቷን ከፍ ለማድረግ አውቃ ዝም ትልህ ይሆናል። ነገር ግን ከሁለተኛም ድወላ በኋላ ካላናገረችህ፣ መልሰህ እንዳትደውል። ከሁለት “ሚስድ ኮል” በላይ መተው የለብህም። እንደማትፈልግህ በግልጽ እየነገረችህ፣ ለምን ያንተን ጊዜና የሷን ትዕግስት ታቃጥላለህ? ከፈለገችህ ራሷ መልሳ ትደውላለች። ስሜትህን ተቆጣጠር።

ደጋግመህ ስለደወልክላትና ትዕግስት ስላስጨረስካት የምትሸነፍልህ ከመሰለህ ተሳስተሃል። ደጋግሞ እየደወለ ከሚያስቸግር ሰው በላይ የሚያበሳጭ ነገር የለም። ስለዚህ ይበልጥ እንድትጠላህና እንድትሰለችህ ተጨማሪ ምክንያት አትስጣት። በስልክ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችም አትነዝንዛት።

3) ዓይን ዓይንህን አታይም። ከአንተ ጋር ንኪኪም አትፈጥርም። ብዙ ወንዶች ይህን ምልክት አያስተውሉትም። አንድ ሴት ከወደደችህ ዓይኖቿን ከዓይኖችህ አትነቅልም። አጠገብህም መሆን በጣም ያስደስታታል። በርግጥ አንዳንዴ ሴቶች ለሚወዱትም ወንድ ቅርብ ሆነው መገኘት አይፈልጉም። ብዙ መቀራረብ ሊያስፈራቸው ይችላል። እንደገና ደግሞ በጣም ቀረበችኝ ዓይን ዓይኔን አየችኝ ብለህ፣ የተሳሳተ ግምት ውስጥ እንዳትገባ። አንዳንድ ሴቶች በተፈጥሯቸው ከወንድ ጋር ተቀራርበው ማውራትና መሳሳቅ ይወዳሉ። የመዳራት ዓይነት ባህሪም ሊያሳዩ ይችላሉ። ይህ ማለት ግን ያን ወንድ በፍቅር ዓይን ያዩታል ማለት አይደለም። ስለማትፈራህና እንደ አንድ ጓደኛ ስለምታምንህ ሊሆን ይችላል በግልጽነት እንደፈለገች የምትሆነው። ስለዚህ የተሳሳተ ግምት ወስደህ ፍቅረኛ እንድትሆንህ ከመጠየቅህ በፊት ትክክለኛ ፍላጎቷን በደንብ ለማወቅ ሞክር። እየወደደችህ ዓይን ዓይንህን የማታይህ ከሆነ ደግሞ ሲውል ሲያደር መቀየሯ አይቀርም። ዓይን ዓይንህን ባታይም፣ ባትተሻሽህም፣ ሌሎች “የእወድሃለው” ምልክቶችን በማሳየት ፍቅሯን ልትገልጽልህ ትችላለች።

4) ሌሎች ወንዶች ምን ያህል ቆንጆ እንደሆኑ ትነግርሃለች። ይህን የምታደርገው አንተን ለማስቀናት አይደለም። የድሮ ፍቅረኛህ ብቻ ነች አንተን ለማስቀናት ስለሌሎች ወንዶች ውበት የምትናገረው። አዲስ የተዋወቅካት ሴት ወይም ጓደኛህ ስለሌሎች ወንዶች ቆንጆነት በፊትህ የምታወራ ከሆነ አንተን በፍቅረኛ ዓይን ሳይሆን በጓደኛ ዓይን ነው የምታይህ። ለሴት ጓደኞቿ ሐሳቧን ሳትፈራ እንደምትገልጽ ሁሉ ላንተም የተሰማትን ታዋራሃለች—ለፍቅረኛነት ያስበኛል ብላ ስለማትጠብቅ።

5) አንተ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት እንድትጀምር ሁኔታዎችን ታመቻቻለች። እንደዚህ ማድረጓ 1) እላይ እንደተጠቀሰው በጓደኛነት ዓይን ነው የምታይህ። ስለዚህ ፍቅረኛሞች እንሆናለን የሚል ሐሳብ በአዕምሮዋ ውስጥ የለም። 2) ጠጋ፣ ጠጋ ማለትህ ካስፈራትና ጓደኛነታችሁን ማጣት ካልፈለገች፣ ማድረግ ያለባት አንተን ከሌላ ሴት ጋር ማስተዋወቅ ነው። በሁለቱም መንገድ ካየነው መልዕክቷ ግልፅ ነው፤ አንተን በፍቅረኛነት አትፈልግህም።

6) ቀልድህ አያስቃትም። አንተ እሷን አስቃለሁ ብለህ መከራህን ስትበላ፣ የምትናገረው ነገር አይደለም ጥርሷን ማስገልፈጥ ፊቷን እንኳ አያስፈግግም። መሳሳቅና መቀላለድ የድሪያ አንዱ መንገድ ነው። ካንተ ጋር መዳራት የሚያስደስታት ሴት፤ በሚያስቀውም፣ በማያስቀውም ትደሰታለች። ካልፈለገችህ ግን አይደለም በማያስቀው ልትስቅ፣ ቀልድህ ራሱ አይገባትም። ጓደኞች ከሆናችሁ ግን ይሉኝታ ይዟት ወይም ቀልዱ ከምር የሚያስቅ ሆኖ ሲገኝ ትስቅልህ ይሆናል።

7) ሁሌም እቅድ ማውጣት ላይ ታቅማማለች። አንተ ለምታቅደው ነገር መሰናክል ትሆናለች። ቀጠሮ አታከብርም። እንደማይመቻት ነግራህ አትመጣም። በየጊዜው ለሁለታችሁ ብለህ ያቀድከውን እንድትሰርዝ ታደርግሃለች። መስሎህ ነው እንጂ እቺ ልጅ ላንተ አይደለችም። ጊዜህን አታባክን። ከወደደችህ ለምን ታቅማማለች? ለምን እቅድህን ታሰርዝሃለች?

8) በሐሳቧ የምትስለው ወንድ አንተን አይመስልም። ሰውየው መልኩ፣ ቁመናው፣ አስተሳሰቡ፣ አነጋገሩ፣ አበላሉ፣ አጠጣጡ፣ አደናነሱ፣ አለባበሱ፣ ሁለመናው ሆሊውድ ለገበያ የሚያቀርባቸውን የፊልም ተዋንያንን እንጂ አንተን በጭራሽ አይመስልም። በሌላ አነጋገር፣ አንተ የእሷ ፍቅረኛ ልትሆን አትችልም። እንደማትችል በግልጽ ቋንቋ እየነገረችህ ነው። የሆሊውዶቹን ወንዶች ለመምሰል ጊዜህንም ሆነ ጉልበትህን አታባክን። ባጠቃላይ፣ የምትወዳት ልጅ ካንተ ጋር ስትሆን ስለሌሎች ወንዶች ማውራት ካዘወተረች፣ አትኩሮቷ ካንተ ይልቅ ሌሎች ወንዶች ላይ ከሆነ፣ አንተን ለፍቅር ጓደኝነት አላሰበችህም ማለት ነው። አንተን ወይ እንደ ጥሩ፣ አማካሪ ጓደኛዋ ነው የምታይህ፤ ያ ካልሆነ ደግሞ የሚመቻትን፣ በፍቅር የሚያከንፋትን ወንድ እስክታገኝ ድረስ የጊዜ ማሳለፊያዋ ነህ። በርግጥ አንዳንድ ሰዎች ፍቅር ሳይዛቸው ፍቅር ውስጥ ይገቡና፣ ፍቅሩ ከተጀመረ በኋላ አፍቃሪያቸውን በጊዜ ሂደት ሊወዱት ይችላሉ። ይሄ ግን የሚከሰተው አልፎ፣ አልፎ ነው። አንዳንድ ወንዶች ደግሞ “በድቼ ልጅ ካስወለድኳት፣ አማራጭ ስለማይኖራት፣ እየወደደችኝ ትመጣለች” ብለው ያስባሉ። እንደዚህ ዓይነቱ ከንቱ አስተሳሰብ አደገኛ ብቻም ሳይሆን ከራስ ወዳድነት የመነጨ ክፋት ነው። በዚህ አድራጎትህ የተነሳ፣ እድሜ ልክህን እየረገመችህ ልትኖር ትችላለች።

9) ያለጓደኞቿ ካንተ ጋር አትገናኝም። ቀጠሮ ስትይዙም ሆነ ለመዝናናት ስትወጡ ብቻዋን አትመጣም። ብቻዋን ብትመጣ እንኳ፣ ብዙ ላትቆይ ወይም “ወደ ቤት እንመለስ” ልትል ትችላለች። ብቻዋን ሆና ከአንተ ጋር መገናኘት ካልፈለገች፣ አብራችሁ ስትሆኑም እንደድሮው ነጻ ሆና ካላወራችና የመጨናነቅ ስሜት ከታየባት፣ የሆነ ችግር አለ ማለት ነው። ቅርርባችሁ ከጓደኝነት ያለፈ ትርጉም እንዲኖረው እንደማትሻ እየነገረችህ ነው። ለፍቅር ጓደኛነት አትፈልግህም። ጓደኞቿን አስከትላ የምትመጣበትም ምክንያት ፍቅር-ነክ ወሬ ወይም ጥያቄ ካንተ ላለመስማት ነው።

ለፍቅር ያሰብካት ልጅ፣ ከተጠቀሱት ምልክቶች ቢያንስ ሶስቱን ካሳየችህ፣ ለፍቅር እንደማታስብህ ተገንዘብ። ከሶስት በላይ ምልክቶችን ካሳየችህ ደግሞ ግንኙነቱን ብትጀምሩ እንኳ ዘላቂነት ላይኖረው ይችላል። እያወቅክ ራስህን ረመጥ ውስጥ መክተት ነው። በርግጥ የወደደ እውር ነው ይባላል። ነገር ግን እያወቁ መታወር ጅልነት ነው። ወደህ የማትወደድ መሆንህን እያወቅክ፣ ለልጅቷ ያለህን ስሜት በጅምሩ መቅጨት ስትችል፣ ለምን ራስን ስቃይ ውስጥ ትከታለህ? እሷ ላይ ጊዜህን ከምታቃጥል፣ ሌሎች ቆነጃጅትን ተዋወቅ። ላንተ የምትሆን አትጠፋም።

(እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው፣ ሴቶች ለወንዶች የሚያሳይዋቸው “የአልፈልግህም” ምልክቶች፣ ወንዶችም ለሴቶች የሚያሳይዋቸው “የአልፈልግሽም” ምልክቶች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። “አንቺ ትወጂዋለሽ እሱ ግን …” የሚለውን ጽሑፍ ይመልከቱ።)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.