ጥፍረ መጥምጥ/ Nail fungus

ጥፍረ-መጥምጥ ነጭ ወይም ቢጫ ነጠብ በመሆን በእጅና እግር ጣቶች ጫፍ ላይ የሚጀምርና በብዛት የሚከሰት የጤና ችግር ነዉ፡፡ ጥፍረ መጥምጥ በፈንገስ የሚከሰት እንፌክሽን ሲሆን እየቆየና ወደ ዉስጥ እየገባ ሲመጣ ጥፍርዎ መልኩን እንዲቀይር፣እንዲወፍርና ጫፉ እንዲጨባበጥ ያደርጋል፡፡ይህ የጤና ችግር በአንድ ጊዜ ብዙ ጥፍሮችን ሊያጠቃ ቢችልም ሁሉንም ጥፍሮች ግን በአንድ ጊዜ ሊይዝ አይችልም፡፡
የህመሙ ምልክቶች
የጥፍር ፈንገስ ካለዎ የሚከተሉት ምልክቶችን በጥፈርዎ ላይ ሊያዩ ይችላሉ፡፡
• የጥፍር መወፈር
• የጥፍር መቀላሉ መሰባበር፣ መጨባበጥ፣መነቀል
• የጥፍር ቅርፅ መበላሸት
• አንዳንዴ ህመምና የተወሰነ መጥፎ ጠረን መከሰት
• የጥፍር መልክ መቀየር ( መጥቆር/መፍዘዝ) የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡
ጥፍረ መጥምጥ እንዴት ይመጣል፡-
• ጥፍረመጥምጥ አብዛኛዉን ጊዜ ደርማቶፋይት በሚባሉ የፈንገስ አይነቶች የሚመጣ ሲሆን አንዳንዴ በይስት/ Yeasts እና ሻጋታ/molds አማካይነት ሊመጣ ይችላል፡፡
የጥፍር ፈንገስ ከእጅ ጣቶች ይልቅ በእግር ጣቶች ላይ በብዛት ይከሰታል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የእግር ጣት ጥፍሮች በብዛት ተሸፍነዉ ስለሚቆዩ ( ሞቃት፣ ብርሃን የማያገኝና እርጥበታማ) ለፈንገስ ማደግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ሌለኛዉ የእግር ጣቶች ከእጅ ጣቶች አንፃር ሲታይ የሚኖራቸዉ የደም ዝዉዉር አነስተኛ ስለሆነ የበሽታ መከላከያ ዘዴዎች በጊዜዉ እንፌክሽኑን ለይተዉ ማስቆም ስለማይችሉ/ስለሚያዳግታቸዉ ነዉ፡፡
ለጥፍረ መጥምጥ ተጋላጭነትዎን የሚጨምሩ ነገሮች
• በእድሜ መግፋት
• ወንድ መሆን
• እርጥበታማ ወይም እምቅ አየር በሚበዛበት ቦታ መስራት ወይም ለረጅም ጊዜ እጅዎ እርጥብ ሆኖ የሚቆይበት የስራ ባህሪይ ካለዎ / ፅዳት
• እርጥበትን የማይመጡና የአየር ዝዉዉርን የሚቀንሱ/የሚያግዱ ካልሲዎች/ጫማዎችን የሚዘወትሩ ከሆነ
• የጥፍረ መጥምጥ ችግር ካለዉ ሰዉ ጋር የሚኖሩ ከሆነ/መጫሚያዎቹን የሚጠቀሙ ከሆነ
• ህዝብ በብዛት በሚገለገልበት እርጥበታማ ቦታዎች፣ መዋኛ ስፍራዎች፣ ጂምና ሻወር ቤቶች በባዱ እግርዎ መሄድ
• የእግር ፈንገስ ካለዎ
• መጠነኛ የሆነ የቆዳ ወይም የጥፍር ላይ አደጋ አጋጥምዎት ከነበረ
• ህፃናት ላይ፣ የስኳርና የደም ዝዉዉር ችግር ካለዎ፣ የበሽታ መከላከል አቅምዎ የተዳከመ ከሆነ
ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች
ጥፍረ መጥምጥ በፈንገስ ምክንያት የሚመጣ ስለሆነ በአፍ ሊወሰዱ የሚችሉና ፍቱን የሆኑ የፈንገስ መድሃኒቶች ስላሉ የህክምና ባለሙያዎን በማማከር ተገቢዉን ህክምና እንዲወስዱ/እንዲከታተሉ እንመክርዎታለን፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች ቀስ በቀስ በፈንገስ የተጎዳዉን በአዲስ ጥፍር በመተካት እንዲስተካከል ያደርጋሉ፡፡
ጥፍረ መጥምጥን መከላከል
የሚከተሉት ልምዶች/ባህሪያት ጥፍረመጥምጥ እንዳይይዝዎ ወይም በድጋሚ እንዳይመጣ ለመከላከል ሊረዳዎ ይችላል፡፡
• ሁሌ/ መደበኛ በሆነ መልኩ እጅና እግርዎን መታጠብ፤ እንዲሁም ሁሌ ጥፍርዎን ማሳጠርና እርጥበት እንዳይኖረዉ ማድረግ፡- እጅና እግርዎን በሳሙናና ዉሃ በደንብ መታጠብ፣ በጣትና ጣት መሃከል ሳይቀር በደንብ ማደራረቅ
• ላብን ሊያመጡ የሚችሉ ካልሲዎችን መጠቀም፡- ከሱፍ፣ ከናይለንና ፖሊስተር የተሰሩ ካልሲዎች እርጥበትን የመምጠጥ ባህሪ ስላላቸዉ እነርሱን መጠቀም፡፡ በተጨማሪም በተለይ እግርዎን የሚያልብዎ ከሆነ ካልሲዎን ቶሎ ቶሎ መቀያየር
• እርጥበትን ሊቀንሱ የሚችሉ ጫማዎችን መጠቀም፡- አንዳንዴ ክፍት ጫማ ማድረግ
• ከተቻለ አሮጌ ጫማዎችን ማስወገድ፡- አሮጌ ጫማ በዉስጣቸዉ ፈንገስን ስለሚይዙ/ ስለሚያድግባቸዉና ለድጋሚ እንፌክሽን ስለሚያጋልጥዎ ለማስወገድ መሞከር፤ አለበለዚያ በዲስእንፌክታንት ወይም አንታይፈንጋል ፓዉደር ማፅዳት
• ህዝብ በብዛት በሚገኝበት ቦታ በባዶ እግርዎ ያለመሆን፡- በመዋኛ ቦታዎች፣ ሻወር ክፍሎች ዉስጥ ነጣላ ጫማ ማድረግ
• በቁንጅና ሳሎን ዉስጥ የሚጠቀሙበትን የጥፍር መዋቢያ እቃዎች በትክክል መፅዳታቸዉን/መቀቀላቸዉን ማረጋገጥ
• ጥፍረ መጥምጥ ካለዎ የጥፍር ቀለም ወይም አርቴፊሻል ጥፍር ያለመጠቀም፡- ይህ እርጥበትን ሊይይዝና ኢንፌክሽኑን ሊያባብሰዉ ስለሚችል ኢንፌክሽኑ እስኪድን ድረስ ያለመጠቀም
• ኢንፌክሽን ያለዉን ጥፍር ከነኩ በኃላ እጅዎን መታጠብ፡- የጥፍር ፈንገስ ከጥፍር ወደ ጥፍር ሊተላለፍ ይችላል፡፡

 

11167980_496489673848591_2732502752972794782_n

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.