ትኩሳት

10396281_474483126049246_6347311085644792939_nትኩሳት ጊዜያዊ የሆነ የሰዉነት ሙቀት መጨመር ችግር ሲሆን ብዙዉን ጊዜ የሚከሰተዉ በህመም ምክንያት ነዉ፡፡ የትኩሳት መከሰት/መኖር የሚያሳየዉ የሆነ ትክክል ያልሆነ ነገር በሰዉነትዎ ዉስጥ እየተካሄደ መሆኑን ማሳያ ነዉ፡፡ በአዋቂዎች ላይ የትኩሳት መከሰት ምቾት እንዳይሰማዎ ቢያደርግም የትኩሳትዎ መጠን 39.4 ዲግሪና ከዚያን በላይ ካልሆነ በቀር ብዙም ላያሳስብዎ ይችላል፡፡ ነገር ግን በጨቅላና ታዳጊ ህፃናት ላይ የሰዉነት ሙቀት በትንሽ መጠን መጨመር መኖር እንኳ ካለ አሳሳቢ የሆነ ኢንፌክሽን ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡
ባጠቃላይ ሲታይ ትኩሳት ከጥቂት ቀናት በኃላ የሚጠፋ ነዉ፡፡ የተለያዩ ያለሀኪም ትእዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ መድሃኒቶች ቢኖሩም አንዳንድ ጊዜ መድሃኒት ሳይወስዱ መቆየት ተመራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንቱም ትኩሳት የሰዉነት የበሽታ መከላከያ ዘዴዎች የተለያዩ እንፌክሽኖችን እንዲዋጉ ስለሚረዳ ነዉ፡፡

ምልክቶች
ትኩሳት የሚከሰተዉ የሰዉነት ሙቀት ከተለመደዉ/ከኖርማል በላይ ከፍ ሲል/ሲጨምር ነዉ፡፡ ለርስዎ የተለመደዉ/ኖርማል የሆነዉ የሰዉነት ሙቀት ከሌላ ሰዎ ጋር ሲነፃፀር ከኖርማል የሰዉነት ሙቀት (37°C) በተወሰነ መጠን ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ትኩሳቱን እንዳመጣብዎ ምክንያቶች የተለያዩ ተጨማሪ የህመም ምልክቶች ሊታዩ የሚችሉ ሲሆን ከእነዚህም ዉስጥ፡-
• ማላብ
• የራስ ምታት
• የምግብ ፍላጎት መቀነስ
• መደካከም
• ብርድ ብርድ ማለት
• የጡንቻ ላይ ህመምና
• የሰዉነት መጠዉለግ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
የትኩሳትዎ መጠን በጣም ከፍተኛ (ከ39.4°C እስከ 41.1°C) ከሆነ የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡ እነርሱም
• ቅዠት
• መነጫነጭ
• የሰዉነት መጠዉለግ መባባስ
• መዘባረቅ
• እንደ የሚጥለዉ ሰዉ ማንቀጥቀጥ መከሰት ናቸዉ፡፡

የትኩሳት ምክንያቶች
ትኩሳት የሚከሰተዉ በአዕምሮችን ዉስጥ ያለና የሰዉነትን ሙቀት የሚቆጣጠረዉ አካል ወይም ሀይፖታላመስ/ቴርሞስታት ሴንተር የሰዉነትን ሙቀት ከተለመደዉ/ከኖርማሉ በላይ ከፍ እንዲል ሲደርገዉ ሲሆን ይህ ሲከሰት ሰዉነትዎን ብርድ ብርድ ስለሚልዎ ተጨማሪ ልብስ እንዲደርቡ አሊም ተጨማሪ ሙቀት ለማመንጨት ሰዉነትዎ መንዘፍዘፍ/መንቀትቀጥ እንዲጀምር ያደርጋል፡፡ በዚህ ሂደት ዉስጥ የሰዉነት ሙቀትዎ ከኖርማሉ በላይ ይጨምራል፡፡
የሰዉነትዎ ሙቀት በቀን ዉስጥ በተለያዩ ሰዓታት ሊለያይ ይችላል፡፡ ስለሆነም ጧት ጧት የሰዉነትዎ ሙቀት የሚቀንስ ሲሆን ወደ አመሻሽና ማታ ላይ ደግሞ ከፍ ይላል፡፡ ምንም እንኳ የብዙ ሰዎች ኖርማል የሰዉነት ሙቀት መጠን 37°C መሆኑን ቢረዱም ኖርማል የሰዉነት ሙቀት መጠን ከ36.1°C እስከ 37.2°C ሊሆን ይችላል፡፡
ትኩሳት ወይም የሰዉነት ሙቀት መጨመር በሚከተሉት ምክንያቶች ይከሰታል፡፡ እነርሱም
• የቫይረስ ኢንፌክሽን
• የባክቴሪያል እንፌክሽን
• በከፍተኛ ሙቀት፣ የፀሃይ ቃጠሎ
• የተወሰኑ የሰዉነት መቆጣት ህመሞች/ inflammatory conditions
• የተለያዩ እጢዎች
• የተወሰኑ መድሃኒቶች
• የተወሰኑ ክትባቶችና የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡
በትኩሳት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶች/ Complications
• ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የሰዉነት ድርቀት/ severe dehydration
• መቃዠት/ Hallucinations
• ከትኩሳት ጋር ተያይዞ የሚመጣ እንደሚጥለዉ ሰዉ ማንቀጠቀጥ፡- ይህ በአብዛኛዉ ከ6 ወራት እስከ 5 ዓመታት ድረስ ባሉ ህፃናት ላይ ይታያል፡፡
ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች
ለእርስዎም ይሁን ለልጅዎ ትኩሳት በሚኖርበት ወቅት ምቾት እነዲሰማዎ
• በቂ ፈሳሽ መዉሰድ፡- ትኩሳት የሰዉነትዎ ፈሳሽ እንዲቀንስና ለሰዉነት መጠዉለግ ስለሚያጋልጥዎ በቂ ዉሃ፣ ጅዉስ/ጭማቂ ወይም ሁለቱንም መዉሰድ ይገባል፡፡ እድሜያቸዉ ከአንድ አመት በታች ላሉ ህፃናት ኦ አር ኤስ (ORS) መጠቀም ይችላሉ፡፡
• በቂ እረፍት ማግኘት፡- ዕረፍት ማድረግ ትኩሳት እንዲቀንስ ይረዳል
• ተትኩሳትዎ እንዲቀንስ ቀለል ያሉ አልባሳትን መልበስ፣ የክፍሉን ሙቀት እንዲቀንስና ቀዝቀዝ እንዲል ማድረግ፤ እንዲሁም በሚተኙበት ወቅት አንሶላ ብቻ ወይም ስስ ብርድልብስ መልበስ
መድሃኒቶች
የትኩሳትዎ መጠን መጠነኛ ከሆነ የትኩሳት ማስታገሻ መድሃኒቶችን መዉሰድ ብዙም አይመከርም፡፡ ምክንያቱም ይህን ማድረግ የህመሙ ጊዜ እንዲራዘም አሊያም ህመሙን ያመጣዉ ምን እንደሆነ ለመለየት ሊያዳግት ይችላል፡፡
ያለሃኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ መድሃኖቶች፡- እንደ አሴታሚኖፌን (ፓራስታሞል)፣ አስፒሪን( ለአዋቂዎች ብቻ) መዉሰድ፡- መድሃኒቶቹን ሲወስዱ ከመጠን ማለፍ የለብዎትም፡፡ አጠቃቀሙን ከህክምና ባለሙያዎ/ ፋርማሲስት መጠየቅ ይገባል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.