የሽንት ቧንቧ እንፌክሽን

 

የሽንት ቧንቧ እንፌክን ማለት በሽንት መተላለፊ ስርዓት በየትኛዉም ቦታ ላይ ባለዉ የሽንት መተላለፊያ መስመር (በኩላሊት፤ ፊኛ፤ በዩሬተርና ዩሬትራ) ላይ የሚከሰት የኢንፎክሽን አይነት ሲሆን ይህ የጤና ችግር በአብዛኛዉ የሚከሰተዉ ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ነዉ፡፡ የሽንት ቧንቧ እንፌክን ከአንድ ጊዜ በላይ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህ ማለት ሴቶች በአመት ከአንድ ጊዜ በላይ የሽንት ቧንቧ እንፌክሽን ሊያጋጥማቸዉ የሚችል ስለሆነ ምልክቱ በታየበት ጊዜ ሁሉ ተገቢዉን ምርመራ በማድረግ ህክምና ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ እንፌክሽን የሚከሰትበት ዋነኛ ምክንያት ሽንትን ከፊኛ ወደ ዉጪ የሚያጓጉዘዉ የሽንት መተላለፊያ ቱቦ (ዩሬትራ) በሴቶች ላይ አጭር መሆኑ ነዉ፡፡ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖች የሚከሰቱት ኢንፌክሽኑን እንዲከሰት የሚያደርጉት ባክቴሪያዎች ከዉጭኛዉ የብልት ክፍል ወደ ሽንት መተላለፊያ ቱቦ ገብተዉ ሲራቡና ወደ ላይኛዎቹ የሽንት መተላለፊያ መስመሮች ( ፊኛና ኩላሊት) በሚሄዱበት/በሚዛመቱበት ወቅት ነዉ፡፡

ለሽንት ቧንቧ እንፌክሽን የሚያጋልጡ ነገሮች
· ሴት መሆን
· የግብረስጋ ግንኙነት መፈፀም
· የተወሰኑ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም (ዳያፈፍራም)
· ሴቶች በሚያርጡበት ወቅት (menopause)

· የሽንት መተላለፊያ መስመሮች በሚዘጉበት ወቅት ለምሳሌ የሽንት ቧንቧ ውስጥ ጠጠሮች ሲኖሩ)
· የበሽታ መከላከል አቅም ሲቀንስ
· ሽንት ለመሽናት የሽንት ማሽኛ ካቴተር መጠቀምና የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰዉ የሽንት ቧንቧ እንፌክሽን በወንዶች ላይ በብዛት ስለማይከሰት የበሽታዉ ምልክቶች ከሌሉ በስተቀር ምርመራና ህክምና አያስፈልጋቸዉም፡፡ በተጨማሪም የሽንት ቧንቧ እንፌክሽን በግብረ ስጋ ግንኙነት የማይተላለፍ ስለሆነ ሴት ወይም ወንዱ ቢያዙ አንዱ ወደ ሌላዉ ኢንፌክሽኑን ሊያስተላልፉ አይችሉም፡፡

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክቶች
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሁል ጊዜ ምልክት ይኖሩታል ተብሎ ባይገመትም ምልክቶቹ ከተከሰቱ የሚከተሉትን ሊያጠቃልል ይችላል፡፡
· የሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት/ማጣደፍ
· ሽንት በሚሸኑበት ወቅት የማቃጠል ስሜት መከሰት
· ቶሎ ቶሎ/ በተደጋጋሚ ግን ትንሽ መጠን ያለዉ ሽንት መሽናት/መዉጣት
· ጠንከር ያለ የሽንት ሽታ መከሰት
· የሽንት መልክ መቀየር ( ጉም የመሰለ )
· የሽንት መቅላት፣ደማቅ ሀምራዊ ወይም ኮካ ኮላ መምሰል በሽንት ዉስጥ ደም መኖሩን ያሳያል፡፡
· በሴቶች ላይ የዳሌ ዉስጥ ህመም
· በወንዶች የፊንጢጣ ዉስጥ ህመም የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡

ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሊደረጉልዎ የሚችሉ ምርመራዎች

· በላበራቶር የሽንት ምርመራ ማድረግ
· የሽንት ካልቸር መስራት
· እንደ ራጅ፣ አልትራሳዉንድና ሲቲ ስካን ያሉትን እንደየአስፈላጊነቱ ማድረግ
· ሲስቶስኮፕ፡- በተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ እንፌክሽን የሚያስቸግርዎ ከሆነ ሊታዘዝልዎ ይችላል፡፡

ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሲኖር ችግሩን ያመጡትን ባክቴሪያዎች ለማከም መድሃኒቶች ይታዘዛሉ፡፡ ሊታዘዙ የሚችሉት መድሃኒቶች የሚወሰኑት እንደ ህመምዎ ደረጃና ኢንፌክሽኑን እንዳመጣዉ የባክቴሪያ አይነት ነው፡፡

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኑ ቀላል ከሆነ
ለቀላል ኢንፌክሽን ሊሰጡ የሚችሉ መድሃኒቶች የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡፡

· ትራይሜቶፕሪም-ሰልፋሜቶክሳዞል (ባክትሪም)

· አሞክሳሲሊን

· ናይትሮፉራንቶይን

· ሲፕሮፍሎክሳሲልን/ ኖርፍሎክሳሲሊን

· ሌቮፍሎክሳሲልንና የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡

ብዙዉን ጊዜ መድሃኒቱን ከጀመሩ በኃላ የህመሙ ምልክቶች በጥቂት ቀናት ዉስጥ የሚሻሻል ሲሆን የህመሙ ምልክቶች ቢቀንሱም/ ቢጠፉም መድሃኒትዎን የህክምና ባለሙያዎ ለሰጠዎ እርዝማኔ በአግባቡ ወስደዉ መጨረስ ይገባል፡፡

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኑ ከፍ ያለ ከሆነ
የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኑ ከፍ ያለ ከሆነ ህክምናዎ በደም ስር ሊሰጥ ስለሚችል ሆስፒታል መተኛት ሊስፈልግዎ ይችላል፡፡

የሽንት ቧንቧ እንፌክሽንን እንዴት መከላከል ይቻላል?
· ንፅህና/ Hygiene/ መጠበቅ
ሴቶች ሽንታቸዉን ከተፀዳዱ በኃላ ማደራረቅ/መጥረግ ያለባቸዉ ከፊት ወደኃላ መሆን አለበት፡፡ ከኃላ ወደፊት መጥረግ ጀርሞችን ከፊንጢጣ ወደ ሽንት ቱቦ በሶፍትና እጅዎ እንዲመጣ ስለሚያደርግ ለሽንት ቧንቧ እንፌክሽን ያጋልጣል፡፡ ሰገራም ከወጡ በኃላ መደረግ ያለበት ከፊት ወደ ኃላ ሲሆን በአንድ ሶፍት ከአንዴ በላይ እየደጋገሙ መጥረግ አያስፈልግም፡፡
· አለባበስ
በጣም ጥብቅ ያሉና አየር በቀላሉ እንዳይዘዋወር የሚከለክሉ የዉስጥ ሱሪዎችን መልበስ እርጥበት ስለሚጠራቀም ለቆዳ መላላጥና ባክቴሪያ እንዲራባ ያደርገዋል፡፡
· አመጋገብ
ፈሳሽ በበቂ መጠን መዉሰድ ያስፈልጋል፡፡የሽንትዎ ቀለም እየቀላ ከመጣ በቂ ፈሳሽ እየወሰዱ አለመሆኑን ስለሚያሳይ ፈሳሽ በበቂ መጠን መዉሰድ ይገባዎታል፡፡
· እንቅስቃሴ
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ሽንት ፊኛዎ ዉስጥ አለመኖሩን ያረጋግጡ፡፡ በእንቅስቃሴ ወቅት በቂ ፈሳሽ መዉሰድ ይገባል፡፡
· የግብረስጋ ግንኙነት ባክቴሪያ ወደ ሽንት መተላለፊያ ቱቦዎች እንዲገባ ስለሚያደርግ ግንኙነት ከፈፀሙ በኃላ ሽንት መሽናትና መታጠብ እንዲሁም ሁለት ብርጭቆ ዉሃ መጠጣት የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን ለመቀነስ ይረዳል፡፡

11025802_454429414721284_1934728859877216169_n

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.