የሰዉነት ቢጫ መሆን/ጃዉንዲስ የሚከሰተዉ በሰዉነት ቆዳ ላይ፣ በነጩ የአይናችን ክፍልና በሌሎች ቦታዎች ላይ ሲሆን መንስኤዉ ቢሊሩቢን/bilirubin የሚባለዉ ኬሚካል በደም ዉስጥና በሰዉነት ዉስጥ በሚጨምርበት (ሃይፐርቢሊሩቤኔሚያ በሚከሰትበት) ወቅት ነዉ፡፡ የሰዉነት ቢጫ መሆን በራሱ ህመም ሳይሆን የዉስጣዊ ህመም ስሜቶች መገለጫ ምልክት ነዉ፡፡
ማንኛዉም የቢሊሩቢንን እንቅስቃሴ/ ዝዉዉር ከደም ወደ ጉበትና ከሰዉነት ወደ ዉጪ እንዳይወጣ እክል የሚፈጥሩ ነገሮች ለሰዉነት ቢጫ መሆን ምክንያት ይሆናሉ፡፡ የሰዉነት ቢጫ መሆን በሶስት የተለያዩ ቦታዎች የሚመደብ ሲሆን እነርሱም:-

· ከጉበት በፊት ባለ ችግር የሚከሰት ( Pre-hepatic jaundice)፡- ይህ እንደ ወባ ባሉ ኢንፌክሽንና ሌሎች ከዘር ጋር በተገናኙ የሚመጡ ችግሮች የሚመጣ ሲሆን እነዚህ ችግሮች ቀይ የደም ሴሎች በብዛት እንዲሞቱ እድልን የሚጨምሩ ናቸዉ፡፡

· ጉበት ዉስጥ ባለ ችግር የሚከሰት ( Intra-hepatic jaundice )፡-ይህ በቀጥታ በጉበት ላይ በሚደርስ አደጋ/ጉዳት ምክንያት የሚመጣ ሲሆን ይህን ችግር ከሚያመጡ ህመሞች ዉስጥ የጉበት ቫይረሶች, በአልኮሆል ምክንያት የሚከሰት የጉበት ችግር፣ በመድሃኒቶች፣ የጉበት ካንሰርና ሌሎች የጤና ችግሮች ናቸዉ፡፡

· ከጉበት በኃላ ባለ ችግር የሚከሰት (Post-hepatic jaundice)፡- ይህ የሚከሰተዉ ሀሞትን የሚያስተላልፉ መስመሮች በሚዘጉበት፣ በሚጎዱበትና በሚቆጡበት ወቅት የሚመጣ ሲሆን የሀሞት ጠጠር፣ የቆሽትና የሀሞት ከረጢት ችግሮች መከሰት ዋነኛ መንስኤዎቹ ናቸዉ፡፡

ከዚህ የምንረዳዉ የአይን ቢጫ መሆን የሚመጣዉ በተለምዶ እንደሚባለው በሌሊት ወፍ ምክንያት የሚከሰት የጤና ችግር ሳይሆን በተለያዩ የጤና ችግሮችና እንፌክሽኖች ምክንያት የሚመጣ የጤና ችግር መሆኑን ተገንዝበን የአይን ወይም የቆዳ ቢጫ መሆን ሲከሰትብዎ የተከሰተበትን መሰረታዊ የጤና ችግር ለማወቅና አስፈላጊዉን ህክምናን የጤና ክትትል እንዲደረግልዎ ሳይዘገዩ ባፋጣኝ የህክምና ባለሙያን ማማከር ያስፈልጋል፡፡

ዉድ የሃሎ ዶክተር ፌስ ቦክ ተከታታዮች፣ ከላይ እንዳየነዉ ለአይንም ይሁን ለቆዳ ቢጫ መሆን መንስኤዎቹ ብዙ ሲሆኑ ለዛሬ ግን አንዱ የጤና ችግር ከሆኑት ዉስጥ በሄፓታይትስ ቢ ላይ ትኩረት አድርገን እንወያያለን፡፡

ሄፓታይትስ ቢ (Hepatitis B)
ሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ ጉበትን ከሚያጠቁ አምስቱ የሄታይትስ ቫይረሶች አንዱ ሲሆን እንደ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ በአለማችን እስከ 2 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ የተጠቁ ናቸዉ፡፡ በየዓመቱም 780 000 ሰዎች በሄፓታይትስ ቢ ምክንያት ለህልፈተ ህይወት/ ሞት ይዳረጋሉ፡፡ሄፓታይትስ ቢ በጉበት ላይ ጉዳት የሚያመጣ ሲሆን በዚህ ቫይረስ የተያዙ የተወሰኑ ሰዎች ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ ከሰዉነታቸዉ ዉስጥ ማጥፋት ስለማይችሉ ቫይረሱ ለረጅም ጊዜ በጉበታቸዉ ዉስጥ በመቆየት(chronic hepatitis B) በጉበት ላይ ጉዳት እነዲደርስ ያደርጋል፡፡
ሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ እና ኤችአይቪ ቫይረስ የመተላለፊያ መነገዶቻቸዉ ተመሳሳይ ቢሆንም ሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ ከኤችአይቪ አንፃር ሲታይ ከ50 እስከ 100 ጊዜ እጅግ ተላላፊ ነዉ፡፡

የሄፓታይትስ ቢ የህመም ምልክቶች
በሄፓታይትስ ቢ እንፌክሽን ምክንያት የሚታዩ ምልክቶች የሚታዩት ኢንፌክሽኑ ከተከሰተ ከ3 ወራት በኃላ ሲሆን ምልክቶቹ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ከነዚህ ምልክቶች ዉስጥ ጥቂቶቹ፡-
· የሆድ ህመም
· ጠቆር ያለ የዉሃ ሽንት
· የሰዉነት ትኩሳት
· የመገጣጣሚያ ላይ ህመም
· የምግብ ፍላጎት መቀነስ
· ማቅለሽለሽና ማስታወክ
· የድካም ስሜት
· የቆዳና የአይን ነጩ ክፍል ቢጫ መሆን ናቸዉ፡፡
ነገር ግን በሄፓታይትስ ቢ የተያዙ ህፃናትና የተወሰኑ አዋቂዎች ምንም አይነት የህመም ምልክቶች ላያሳዩም ይችላሉ፡፡

ለሄታይትስ ቢ ቫይረስ እንፌክሽን የሚያጋልጡ ነገሮች
· ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ
· ያለ ጥንቃቄ ሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ ከተያዘ/ች ሰዉ ጋር የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ
· እንደ ጨብጥና ከርክር ባሉ የአባለዘር በሽታዎች ተይዘሁ ከሆነ
· መርፌ፣የጥርስ ብሩሾችንና ሌሎች ነገሮችን በጋራ የሚጠቀሙ ከሆነ
· ለሄፓታትስ ቢ ሊያጋልጦት የሚችል ስራዎች፡-የጤና ባለሙያዎች፣ የእሳት አደጋ ሰራተኞች
· ዲያሊስስ(የኩላሊት ዕጥበት) የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡

የሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ መተላለፊያ መንገዶች
· ልቅ በሆነ የግብረስጋ ግንኙነት
· ከእናት ወደ ልጅ
· በደምና ደም ንኪኪ(ጤንነቱን ያልጠበቀ የሌላ ሰዉ ደም በመዉሰድ፣ጤንነቱን ያልጠበቀ መርፌ መወጋት፣አደንዛዥ ዕፅ ለሚጠቀሙ መርፌ በጋራ መጠቀም)
· ሄፓታይትስ ቢ ከተያዘ ሰዉ ጋር በጣም የቀረበ ግንኙነት መኖር (intimate contact)
የሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ መከላከያ መንገዶች
· የሄፓታይትስ ቢ ክትባት መዉሰድ
· ጥንቃቄ ያለዉ የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ
· ማንኛዉንም ደም የነካቸዉን ነገሮች በጋራ ያለመጠቀም(መርፌ፣ምላጭ፣የጥርስ መቦረሻ፣የፂም መላጫ)
· እናቶች በእርግዝና ወቅት ለሄፓታይትስ ቢ ምርመራ ማድረግ
· ደም ለሌላ ሰዉ ከመሰጠቱ በፊት ለሄፓታይትስ ቢ መመርመር

ሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ እና ክትባቱ (HBV vaccine)
ሄፓታይትስ ቢ ቫየረስን ለመከላከል ከሚረዱ ነገሮች ዉስጥ አንዱ የሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ ክትባትን መከተብ ሲሆን ማንኛዉም ሰዉ ከላይ በተገለፀዉ መሰረት ተጋላጭነት ካለዉ ተመርምሮ በሄፓታይትስ ቢ ያልተያዘ መሆኑ ከተረጋገጠ የሄፓታትስ ቢ ቫይረስን ለመከላከል ክትባት መዉሰድ የሚችል ሲሆን ክትባቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲሰራ ሶስት ጊዜ መከተብ ያስፈልጋል፡፡ሄፓታይትስ ቢ ቫይረስ ቫክሲንን ሙሉ ለሙሉ የተከተቡ ከ95% በላይ የሚሆኑ ህፃናትና አዋቂዎች በሽታዉን የሚከላከሉ አንቲቦዲዎችን(Antibodies) የሚያዘጋጁ ሲሆን ክትባቱ ቢያነስ ለ 20 ዓመታትና ምናልበትም እስከ እድሜ ልክ በሽታዉን ሊከላከል ይችላል፡፡
የሄታይትስ ቢ እንፌክሽን ያላቸዉ ሰዎች የህክምና ክትትል ማድረግና ሊደረጉ የሚገባቸዉን ጥንቃቄዎች መዉሰድ ያስፈልጋቸዋል፡፡

10989135_450781938419365_3113410645329733277_n

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.