ኮሌስትሮል በሰውነታችን ውስጥ ስላለው ጥቅምና ጉዳት ከመነጋገራችን አስቀድሞ ስለምንነቱ የተወሰነ ነገር እናንሳ፡፡

cholestorlኮሌስትሮል ቅባታማ ተፈጥሮ ያለው፣ ከሰው ልጆች በተጨማሪ በሁሉም እንስሳት ሰውነት ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር ነው፡፡ ይህ ንጥረ ነገር በሰውነታችን ውስጥ ላሉት የተለያዩ ሴሎችና ሆርሞኖች የተፈጥሮ አካላቸው ነው፡፡ ኮሌስትሮል በተፈጥሮ ቅባታማ ስለሆነ ከደም ጋር በቀላሉ ተዋህዶ መዘዋወር አይችልም፡፡ ስለዚህ በደማችን ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ኮሌስትሮል ተሸካሚ የሚባሉትን ይጠቀማል፡፡ በእነዚህ ተሸካሚዎች አማካኝነት የሚዘዋወረው፣ ኮሌስትሮል መጠን ጤናማ ከሚባለው በላይ ሲሆን በተለያዩ የደም ስሮች ውስጥ በመጠራቀም፣ በልባችንና በደም ቧንቧዎቻችን ብሎም በአጠቃላይ ጤንነታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡

በሰውነታችን የኮሌስትሮል ተሸካሚ በመሆን በብዛት የሚታወቁት Low Density Lipoprotein (LDL) እና High Density Lipoprotein (HDL) ናቸው፡፡ LDL የሚባሉት ኮሌስትሮልን ይዘው ደም ውስጥ የሚዘዋወሩ ሲሆኑ፣ HDL ደግሞ ኮሌስትሮልን ወደ ጉበታችን የሚመልሰው ነው፡፡ እናም በሰውነታችን ውስጥ ያለው ኮሌስትሮል ሁሉም ጎጂ ነው ብሎ ማሰቡ የተሳሳተ ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ ካየናቸው ውስጥ HDL የተባለው የኮሌስትሮል አይነት፣ ሰውነታችንን ለልብና ደም ቧንቧዎች በሽታ ተጋላጭነት የሚቀንስ/ተከላካይ ኮሌስትሮል ሲሆን፣ LDL ግን በተቃራኒው ለተለያዩ በሽታዎች አጋላጭ ወይም አምጪ የኮሌስትሮል አይነት ነው፡፡ ስለዚህ LDL ጎጂ ኮሌስትሮል በመባል ይታወቃል፡፡

ኮሌስትሮል ለሰውነታችን ጥቅም አለው?

ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው ኮሌስትሮል ሙሉ ለሙሉ ለሰውነታችን አላስፈላጊ ሳይሆን በጤናማው መጠን አስፈላጊ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለተለያዩ ሆርሞኖች፣ ቫይታሚን ዲ እንዲሁም ምግብ እንዲፈጭ የሚያግዙ ኢንዛይሞችን ለመስራት እንደሚያገለግል መረዳት ነው፡፡

ነገር ግን መጠኑ ከፍ ባለ በደም ቧንቧዎቻችን በመከማቸትና፣ አቴሮስከለሮስስ እንዲፈጠር በማድረግ የደም ዝውውርን ያዛባል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደ ልብ፣ አንጎልና ኩላሊት የመሳሰሉት የሰውነት ክፍሎቻችን የሚያስፈልጋቸውን የደም መጠን ካለማግኘታቸው የተነሳ ጤናማ አሰራራቸው ይስተጓጎላል፤  በዚህም ምክንያት፡-

– በልባችን ላይ የኮረናሪ ደም ቧንቧ በሽታ

– ስትሮክ (የግማሽ ሰውነት መድከም ወይም ፓራላይዝድ መሆን)

– የኩላሊት መድከም (Renal Failure) እና የመሳሰሉትን ሊያመጣ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የኮሌስትሮል መጠን መጨመር ለሽንት ቧንቧ ዕጢ ካንሰር (prostactic cancer) የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል፡፡

ሰውነታችን የማይፈለግ የኮሌስትሮል መጠን የሚጨምረው እንዴት ነው?

1. የምንበላው ምግብ፡- አላስፈላጊ ኮሌስትሮሎችን LDL ሊያበዙ የሚችሉ ምግቦች የሚባሉት እና ኮሌስትሮል ናቸው፡፡ እነዚህ ሳቹሬትድ ፋትና ኮሌስትሮል በብዛት የሚገኙት ደግሞ የእንስሳት ተዋፅኦ በሆኑ እንደ ስጋ፣ ዕንቁላል፣ ወተትና አይብ በመሳሰሉ ምግቦች ውስጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡

2. የሰውነት ክብደት፡- ከመጠን ያለፈ ክብደት በሰውነታችን ውስጥ አደገኛ የሆኑ ኮሌስትሮሎችን ያበዛል፡፡ የክብደት ጤናማነት የሚለካው በቦዲ ማስ ኢንዴክስ ሲሆን ክብደታችንን ለቁመታችን ስኩዬር በማካፈል ማወቅ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፡- 1 ሜትር ከ70 ሴ.ሜ እና 70 ኪ.ግራም የሆነ ሰው ቦዲ ማስ ኢንዴክሱ

=70Kg (1.7m)2= 24.2 ይሆናል

ጤናማ የሚባለው ከ18.5 እስከ 24.9 ያለው ሲሆን፣ በ24.9 በላይ ጤናማ ያልሆነ ክብደት ነው፡፡ እንደተለያዩ ጥናቶችና የዓለም የጤና ድርጅት አገላለፅ፣ የአንድን ሰው ክብደትና አላስፈላጊ ቅባቶች ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል ችግር አመላካች ቦርጭ ነው፡፡ እናም የአንድን ሰው የሆድ ውፍረት ጤናማነት ለመለካት፣ የወገብን ስፋት ብቻውን ወይም የወገብ ስፋትን ለዳሌ ስፋት ብቻውን ወይም የወገብ ስፋትን ለዳሌ ስፋት አካፍለን መለካት እንችላለን፡፡ ይህ ልኬት በተለይ በሴቶች ላይ ከላይ ካስቀመጥነው BMI ይልቅ በተሻለ ሁኔታ ችግር አምጪ የውፍረት መጠን ሊጠቁም ይችላል ተብሏል፡፡ የሆ ውፍረት ልኬት በፆታና በዕድሜ እንዲሁም በዘር (ማለትም በተለያዩ አህጉራት ባሉት ህዝቦች) ሊለያይ ሲችል እኛ መጠቀም የምንችለው፡-

– የወገብ ስፋት ጤናማ አይደለም የምንለው ለወንድ ከ102 ሴ.ሜ በላይ ከሆነና ለሴት ከ88 ሴ.ሜ በላይ ከሆነ

– የወገብ ስፋትን ለዳሌ ስፋት ስናካፍል ጤናማ አይደለም የምንለው ደግሞ ለወንድ ከ0.9 በላይ ከሆነና ለሴት ከ0.85 በላይ ከሆነ ነው፡፡

3. የሰውነት እንቅስቃሴ መጠን፡- መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ክብደታችንና ብሎም ጎጂ ኮሌስትሮሎችን ከሰውነታችን ውስጥ ይቀንሳል፡፡

4. ከቤተሰብና በዘር የሚወረስ፡- ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ከቤተሰብና በዘር ሊተላለፍ እንደሚችል ነው፡፡ በዚህ መንገድ የኮሌስትሮል መብዛት ያጋጠመው ሰው፣ ከተወለደ በኋላ ችግሩ ከተከሰተበት ሰው ይልቅ ቀደም ባለ /በለጋ/ ዕድሜ ለልብ ችግር ሊጋለጥ ይችላል፡፡

5. ዕድሜና ፆታ፡- ዕድሜ በጨመረ መጠን፣ በሰውነታችን ውስጥ የጎጂ ኮሌስትሮል መጠንም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ታዲያ ሴቶች በወጣትነታቸው ከወንዶች ያነሰ ጎጂ ኮሌስትሮል ቢኖራቸውም፣ ከ55 ዕድሜያቸው በኋላ የጎጂ ኮሌስትሮል መጠናቸው እንደሚበዛ ነው፡፡

በሰውነታችን የኮሌስትሮል መብዛት እንዴት እናውቃለን?

በሰውነታችን ውስጥ የኮሌስትሮል መብዛት በራሱ ምንም ምልክት አያሳይም፡፡ ስለዚህ ማንም ዕድሜው ከ20 በላይ የሆነ ሰው፣ ቢያንስ በዓመት አንዴ የደም ውስጥ ኮሌስትሮልን መጠኑን መለካት አለበት፡፡

እንደ ሲዲሲ በአሜሪካ ዕድሜያቸው፣ ከ20 ዓመት በላይ ከሆኑ ሰዎች ሃያ በመቶ /20 በመቶ/ የሚሆኑት ከፍተኛ የደም ውስጥ ኮሌስትሮል መጠን አላቸው፡፡ ከእነዚህም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከ65 እስከ 74 ዕድሜ ያላቸው ሴቶች ናቸው፡፡

የተለያዩ የኮሌስትሮል ዓይነቶች በሰውነታችን ውስጥ ያላቸውን ጤናማ መጠን ስናይ

– አጠቃላይ ኮሌስትሮል ከ200 mg/dl (decilitre) ያነሰ፤

– LDL (ጎጂ) የሚባለው ኮሌስትሮል ከ100 mg/dle ያነሰ

– HDL (ጠቃሚ) ኮሌስትሮል ከ40 mg/dle የበለጠ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

ኮሌስትሮል ብዛት ያለበት ሰው ምን ማድረግ አለበት

– ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት መከተል- የሰውነት ክብደት መቀነስ

– መደበኛ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ

– በሐኪም ትዕዛዝ ኮሌስትሮልን የሚቀንሱ መድሃኒቶችን መጠቀም ቀዳሚዎቹ መፍትሄዎች ናቸው፡፡

Source  =Zehabesha

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.