ደም በመስጠት የሚካሄድ ሕክምና

ደም በመስጠት የሚካሄደው ሕክምና ጉዳት አያስከትልም ማለት አይደለም፡፡ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከነዚህ መካከል፣ ቫይረሶችን፣ባክቴሪያ ወይም ጥገኛ ነፍሳትን ወደ ሌላው ሰው የማስተላለፍ አደጋ አለ፡፡ በተጨማሪም የኩላሊትንና የሳንባን አሠራር የሚያዛባ አለርጂ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በኒሞኒያ፣በኢንፌክሽን፣በልብ ድካምና በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ የመጠቃትን አጋጣሚ ስለሚጨምር አንዳንድ ጊዜ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ በአገራችን ብዙ ሰዎች ደም ፈሷቸው ሲሞቱ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ለማለት ይቻላል ለመዳን የሚችሉ ናቸው፡፡

የደም ባህርይ እና የሚያመጣው ተጽዕኖ

ደም እንደ ኦክስጅን፣አልሚ ምግቦችና በሽታ ተከላካዮች ያሉ ጥሩ ነገሮችን ወደ ሰውነት ሕዋሳት ያደርሳል፡፡ እንዲሁም ቆሻሻን ከሕዋሳት ውስጥ ያስወግዳል፣ከእነዚህም መካከል መርዛማ ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣የተጎዱ እንዲሁም የሞቱ ሕዋሳትና ሌሎች ቆሻሻዎች ይገኙባቸዋል፡፡ደም ቆሻሻን በማስወገድ ረገድ የሚጫወተው ሚና፣ከሰውነት ከወጣ በኋላ መነካቱ አደገኛ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት ለመገንዘብ ይረዳል፡፡ እንዲሁም ለሕመምተኛ ደም ከመሰጠቱ በፊት በውስጡ የሚገኘው ቆሻሻ በሙሉ ተለይቶ ተወግዷል ብሎ ዋስትና መስጠት የሚችል ሰው የለም፡፡

ደም በሰውነታችን ውስጥ 100,000 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ሲሆን በዚህ ጊዜ ደምን የሚያጣሩትንና በትክክል መሥራታቸው በደም ላይ የተመካውን ዋነኞቹን የሰውነት ክፍሎቻችንን ማለትም ልብን፣ኩላሊትን፣ጉበትንና ሳምባዎችን ጨምሮ በእያንዳንዱ የአካል ክፍል ውስጥ ያልፋል ለማለት ይቻላል፡፡

ደም መወሰድ ያለበት መቼ ነው?

ከባድ የመቁሰል አደጋ ሲያጋጥም ካልሆነ በስተቀር ለሕመምተኞች ደም መስጠት በደም ምትክ የሚሰጡ  አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ደም ሥሮችን መተኮስ፣ ደም እንዳይፈስ ለማገድ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎችን ኬሚካል ባለው ለየት ያለ ፋሻ መሸፈንና የደምን መጠን የሚጨምሩ መድኃኒቶችን መስጠት ይገኙበታል፡፡

ደም መስጠት

ደም ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮችን እንደሚያከናውን ምንም አያጠያይቅም፡፡ ደም ለፈሰሳቸው ሕመምተኞች ደም መስጠት በሕክምናው ማኀበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ብዙ ዶክተሮች ደምን እጅግ ዋጋማ ያደረገው በዚህ መንገድ ለሕክምና መዋሉ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሆኖም በሕክምናው ዓለም ነገሮች እየተለዋወጡ ነው፡፡ ቀስ በቀስ አስገራሚ ለውጦች እየተካሄዱ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በርካታ ዶክተሮችና የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እንደበፊቱ ደም ለመስጠት አይቸኩሉም፡፡

ሆኖም ሙሉ ደምና የደም ክፍሎች የተገኙት ከሰው ደም በመሆኑ እንደ ቫይረስ ያሉ በሽታ አስተላላፊ ሕዋሳትን ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ደም ለጋሾችን በጥንቃቄ መምረጥም ሆነ የላብራቶሪ ምርመራዎች ማድረግ አደጋውን አያስወግዱትም፡፡

በደም አያያዝ ረገድ የሚሠሩት ስህተቶችና የተወሰደው ደም ከሰውነት በሽታ መከላከያ ጋር ሊጋጭ መቻሉ ናቸው፡፡ የሌላን ሰው ደም የሚወስዱ ሰዎች፣የሌላ ሰው አካል የተተካላቸው ግለሰቦች ለሚያጋጥማቸው ዓይነት አደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡ የሰው በሽታን የመቋቋም ተፈጥሯዊ ኃይል ባዕዱን አካል ላይቀበል ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደም መውሰድ በሽታ የመቋቋም ተፈጥሯዊ አቅምን ሊያሳጣ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ሕመምተኛው ከቀዶ ሕክምና በኋላ ለበሽታ እንዲዳረግና ቀደም ሲል በሰውነቱ ውስጥ ቢኖሩም ጉዳት የማያስከትሉበት በነበሩ ቫይረሶች እንዲጠቃ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ቁጥራቸውእያደገ የመጣው እንዲህ ያለ እውቀት ያላቸው የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች፣ ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምናን በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄና ማስተዋል የተሞላበት ግምገማ እያደረጉ ነው፡፡

ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚከናወን ሕክምና በርካታ አደጋዎች ቢኖሩትም፣ በተለይ ደግሞ ሌሎች አማራጮች እያሉ አሁንም በስፋት ጥቅም ላይ የሚውልበት ምክንያት

አንዱ በርካታ ሐኪሞች የሕክምና ዘዴዎችን ለመለወጥ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ወይም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ያለደም የሚደረጉ አማራጭ ሕክምናዎች መኖራቸውን ባለማወቃቸው ነው፡፡ ሐኪሞች ደም ለመስጠት የሚወስኑት ቀደም ሲል ባገኙት ትምህርት፣ ከሌሎች ሐኪሞች በወረሱት እውቀትና በምርመራ ውጤት ላይ ተመሥርተው ነው፡፡ በተጨማሪም የቀዶ ሕክምና ዶክተሩ ችሎታ በሕክምናው ወቅት በሚፈሰው የደም መጠን ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ፡፡ በሕክምና ወቅት የሚፈሰው ደም ቀዶ ሕክምናውን እንደሚያከናውነው ባለሙያ በእጅጉ ይለያያል፣በመሆኑም በቀዶ ሕክምና ወቅት የደም መፍሰስን ማስቆም የሚቻልባቸውን ዘዴዎች በተመለከተ ለቀዶ ሐኪሞች በቂ ማሠልጠኛ የመስጠቱ አስፈላጊነት እየጨመረ ሄዷል፡፡ ሌሎች ደግሞ ደም ከመውሰድ ውጪ ያሉት አማራጭ ዘዴዎች ዋጋቸው በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፣ ሆኖም ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሁኔታው ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡

ከሙሉው ደም ውስጥ ከ38-48 በመቶ የሚሆኑት ቀይ የደም ሕዋሳት ናቸው፡፡ እነዚህ ሕዋሳት ሕብረሕዋስ ውስጥ ኦክስጅንን ያስገባሉ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ደግሞ ያስወጣሉ፡፡ በዚህ መንገድ ሕብረ ሕዋሱ በሕይወት እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡

ለጋሾች የሚሰጡት ይህ ሙሉውን ደም ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን ኘላዝም ብቻ ይለግሳሉ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ሙሉው ደም ለታካሚዎች ቢሰጥም ደሙ ከመመርመሩና ለሕመምተኞች ደም በመስጠት ለማከናወን ሕክምና ከመዋሉ በፊት በዋና ዋና ክፍሎች መከፋፈልም በጣም የተለመደ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.