የሪህ ነገር! መንስኤው፤ መከላከያውና ሕክምናው – (ከህክምና ባለሙያ ጋር የተደረገ ልዩ ውይይት)

ዩሪክ አሲድም እና ካልሼም የሚባሉ ንጥረ ነገሮች ለሰውነታችን እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሰውነት ውስጥ ከሚፈለገው መጠን በላይ ሲሆኑ ሰውነታችን ሊያስወግዳቸው አቅም ያጣል፡፡ በዚህን ጊዜ ካልሼም ፎስፊት ወደሚባል ጠጣር ንጥረ ነገርነት ተቀይረው ወደ መገጣጠሚያ ቦታዎች ይሰበሰባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከመገጣጠሚያ በሽታዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ሪህ በሽታ ይከሰታል፡፡ ለመሆኑ የሪህ በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች ምንድናቸው? በተለየ ሁኔታ ለሪህ በሽታ የሚጋለጡ እነማን ናቸው? የሪህ በሽታ መፍትሄ ምንድን ነው? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ዶክተር አነጋግረንልዎታል፡፡

 

ጥያቄ፡- የሪህ በሽታ መንስኤ ምንድን ነው?
ዶክተር፡- ለሪህ የጤና ችግር በመንስኤነት የሚገለፁ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዋና ዋና የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡

– የዕድሜ መጨመር

– በሰውነት ውስጥ ከሚፈለገው በላይ የንጥረ ነገሮች መፈጠርና መከማቸት

– በሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝ /infection/

– ከቤተሰብ መካከል የጤና ችግሩ ካለ በዘር የመተላለፍ ዕድል ይኖረዋል

– ምክንያታቸው በውል የማይታወቅ ጉዳዮች /idiopathic/

– በተፈጥሮ ዩሪክ አሲድን ለማስወጣት የማይችሉ ሰዎች ለሪህ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ለሪህ የሚያጋልጡ ሌሎች ምክንያቶች ካሉ ቢገልፁልኝ?

ዶክተር፡- ለሪህ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአመጋገብ ስርዓታችን ውስጥ ቀይ ሥጋ፣ ጉበት ኩላሊትና የጭንቅላት ስጋን አዘውትሮ መመገብ እንዲሁም አልኮል መጠጣት ለሪህ በሽታ ተጋላጭ የመሆን ዕድልን ያሰፋሉ፡፡ ከላይ ከተገለፁት በተጨማሪ ሰውነት ክብደት መጨመር፣ በቁጥጥር ስር ያልዋለ ደም ግፊት፣ ውሃ በብዛት ያለመጠጣት፣ የኩላሊት በሽታና ለተለያዩ በሽታዎች የሚሰጡ መድሃኒቶች ለሪህ በሽታ ተጋላጭ ያደርጋሉ፡፡

ጥያቄ፡- የሪህ በሽታ ሲከሰት የሚያሳያቸው ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?

ዶክተር፡- ህመሙ  በሚከሰትበት ወቅት ከሚታዩ ህመም ነክ ምልክቶች መካከል የሚከተሉት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

– ከትንሽ የጣት ጫፍ እስከ ትላልቆቹ የሰውነት ክፍሎች አካባቢያሉ መገጣጠሚያ ቦታዎች ያብጣሉ

– የሰውነት ትኩሳት መከሰት

– ከቁርጥማት ጀምሮ መላ መገጣጠሚያ ቦታዎችን በመንካት እስከሚቸግር ድረስ ህመም

– ከፍተኛ ስቃይ ያለው ህመም

– መገጣጠሚያ አካባቢዎች በተለይ መልኩ መቅላት

– በመገጣጠሚያ አካባቢዎች የማቃጠል ሁኔታ ይከሰታል

– የጡንቻ መዛል በተለይ ጠዋት ጠዋት እጅና እግርን ለማንቀሳቀስ መቸገር ይኖራል

– የጤና ችግሩ ከሁለት ሳምንት በላይ ከቆየ በመገጣጠሚያ ቦታዎች ጠጣርየሆኑ ነገሮች ይፈጠራሉ

– በዓይን፣ በቆዳ፣ በልብና በሌሎችም  አካባቢዎች የህመም ስሜቶች ይከሰታሉ

– ቁርጥማት

– በዓይን፣ በቆዳ፣ በልብና በሌሎችም አካባቢዎች የህመም ስሜቶች ይከሰታሉ፡፡

ጥያቄ፡- ሪህ በሽታ በወቅቱ ካልታከመ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው?

ዶክተር፡- ሪህ አጣዳፊ እና አብሮ ኗሪ የሚባሉ ሁለት ደረጃዎች አሉት፣ አጣዳፊ የሚባለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ህመም ወይም ስቃይን ያመጣል፡፡ አብሮ ኗሪ የሚባለው በወራት እና በዓመታት የሚዘልቅ የበሽታ አይነት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሰዎች መገጣጠሚያዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ሊያጡት ይችላሉ፡፡ ይህም ማለት መንቀሳቀስ የሚገባቸው የሰውነት ክፍሎች በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጭ ይሆናሉ፡፡ ሌላው ኩላሊት እና ልብ ላይ ጠጠር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ዩሪክ አሲድ በከፍተኛ መጠን በሰውነት ውስጥ በመፈጠሩ ሳቢያ ሀይፕርዩራሲኒያ በሚባል በሽታ ይጋለጣል፡፡

ጥያቄ፡- በሽታው በትክክል መከሰቱን ለማወቅ የሚደረጉ ምርመራዎችን ቢገልፁልን?

ዶክተር፡- በመጀመሪያ የሚደረገው ከበሽታው ጋር በመነጋገር ስለበሽታው ሁኔታና ደረጃ ለመረዳት ጥረት ይደረጋል፡፡ ከበሽተኛው ጋር በሚደረግ ውይይት የሚገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ካበጠው የመገጣጠሚያ ቦታዎች ላይ ፈሳሽ በመውሰድ በፈሳሹ ውስጥ ምን ያህል ጠጣር ነገሮች እንዳሉ ለማረጋገጥ የላብራቶሪ ምርመራ ይካሄዳል፡፡ የሪህ በሽታ በረጅም ጊዜ በመገጣጠሚያ ቦታዎች ላይ ያስከተለውን ጉዳት ለመለየት የራጅ (ኤክስሬ) ምርመራ ይካሄዳል፡፡ በደም ውስጥ ያለውን Uric acid መጠን የመለካት እና በሽንት ምርመራ Ureat Crystal የተባሉትን ንጥረ ነገሮች የመለየት ምርመራ እናካሂዳለን፡፡ በዚህ የምርመራ ሂደት በሽታው በትክክል መከሰቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ጥያቄ፡- የጠቀሷቸው የምርመራ አይነቶች በአገራችን ይሰራሉ?

ዶክተር፡- ካበጠው መገጣጠሚያ ላይ ፈሳሽ በመውሰድ የሚሰራውን የላብራቶሪ ምርመራ ብዙ ብዙዎቹ ሐኪሞች ስለማይጠቀሙት የምርመራ ዘዴው በሀገራችን ብዙ የተለመደ አይደለም፡፡ ሌሎች የምርመራ አይነቶች ግን በሀገራችን ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- መፍትሄው ምንድን ነው?

ዶክተር፡- አንድ ሰው ለመጀመሪያ ወይም በተደጋጋሚ ጊዜ የሪህ በሽታ ከተከሰተበት ከፍተኛ ስቃይ ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው የህክምና ስቃዩን ለማስታገስ የሚያስችል መድሃኒቶች ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ረገድ Non-Steroid Anti-Inflamaty drugs /Nsaids/ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ መድሃኒቶች ለውጥ ካልመጣ Corticoid Steroids የሚባሉ መድሃኒቶችን በመርፌ ወይም በሚዋጥ መልክ እንሰጣለን፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች የህመም ስቃይን ከማቃለል በተጨማሪ መገጣጠሚያው ከጥቅም ውጭ እንዳይሆን ለጊዜው ፋታ ይሰጣሉ፡፡ ሌላው የመድሃኒት አይነት Colchicines tablet ይባላል፡፡ ይህ መድሃኒት በሳምንት ሶት ቀን የሚሰጥ ሲሆን ያም ሪህ የተባለው በሽታ ሙሉ በሙሉ እንዲድን ከማድረጉ ባሻገር ወደፊትም  እንዳይከሰት የመከላከል ብቃት አለው፡፡ ሌላኛው የህክምና ዘዴ Unic acid ከሰውነት ውስጥ እንዲቀንስ ማድረግ ነው፡፡

Unic acid ለመቀነስ ከሚያስከትሉ መድሃኒቶች ውስጥ በአሁኑ ሰዓት የተሻሉ ሆነው የተገኙ Allpurinol እና Zyopruinol የሚባሉ ናቸው፡፡ በእዚህ መድሃኒቶች ለማከም ጥረት ይደረጋል፡፡ እጅና እግር መንቀሳቀስ ካቆመ በቀዶ ህክምና እንዲስተካከል ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአማራጭ የህክምና ዘዴዎች እናክማለን፡፡

ጥያቄ፡- አማራጭ ህክምና ሲባል ምን ማለት ነው? በዚህ የህክምና ዘዴ እንዴት ነው ሪህ በሽታ የሚታከመው

ዶክተር፡- አማራጭ ህክምና ማለት የኤሽዥያዎች ህክምና ነው፡፡ በዚህ የህክምና አይነት ሪህን ጨምሮ በርካታ የህመም አይነቶችን ማዳን ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የሪህ በሽታን ተከትሎ የሚመጣን የአካል መጉደል በተመለከተ በአማራጭ የህክምና ዘዴ ማለትም ዘመናዊ ዋግምት፣ ደረቅ መርፌ፣ ዘመናዊ ጭስ፣ ንዝረት፣ ባሮ ቴራፒ፣ ፔዳልና አጁቫን ቴራፒ በሚባሉ አማራጭ የህክምና አይነቶች ሪህን ማከም ይቻላል፡፡ ሪህ በአጭር ጊዜ የሚታከም ሳይሆን የረዥም ጊዜ ክትትል ይጠይቃል፡፡

ጥያቄ፡- እንዴት እንከላከለው?

ዶክተር፡- ለሪህ በሽታ ከተጋለጡ በኋላ በህክምና ጊዜንም ሆነ ገንዘብን ከማባከን ችግሩን አስቀድሞ መከላከል ተመራጭ ነው፡፡ ይህን የጤና ችግር ለመከላከል የሚከተሉትን ጉዳዮች ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያ በብዛት የምንመገበው ምግብ በአብዛኛው በከፍተኛ መጠን Purina Purina የሚባል ፕሮቲን አለው፡፡ Purina በሰውነታችን በብዛት ካለ ወደ ዩሪክ አሲድነት ይቀየራል፡፡ ዩሪክ አሲዱ ደግሞ ወደ ዩሪክ ክርስቲያልነት በመቀየር በሪህ በሽታ መከሰት መንስኤ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆን ህብረተሰቡ በከፍተኛ ደረጃ ውሃ የመጠጣት ልማድን ቢያዳብር ዩሪክ አሲድ በሽንት መልክ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአልኮል መጠንን መቀነስ ወይም ማቆም፣ የምንጠጣው አልኮል በሙሉ ወደ ሽንትነት እንዲቀየርና በሰውነታችን ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ሽንት እንዲፈጠር ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ ዩሪክ አሲድን ይዞ ይወጣል የተባለውን ውሃ እንዲሁ ያለምንም ጥቅም ከሰውነታችን ውስጥ እንዲወጣ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም አልኮል በ Purina  metabolism ላይ የእራሱ የሆነ በጎ ያልሆነ ተፅዕኖን ያስከትላል፡፡ በዚህ ሳቢያ ዩሪክ አሲዱ ከሰውነት ውስጥ ሳይወጣ እንዲቆይና ወደ ጠጣርነት እንዲቀየር ያደርገዋል፡፡

ስለሆነም አልኮል መጠጣትን ቢቀንሱ ወይም ቢያቆሙ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂዎች አይሆኑም፡፡ በሌላም በኩል የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፣ እኛ ሀገር የምንወስደው ምግብ Purina የተባለ ፕሮቲን በብዛት አለው፡፡ ለምሳሌ ዓሳና ዓሳ ነክ ምግቦች፣ የእንስሳት ተዋፅኦዎች (በተለይም ጉበት፣ ኩላሊት፣ ጭንቅላት እና ቀይ ሥጋ) እነዚህ ምግቦች የፕሮቲን መጠናቸው ከፍተኛ በመሆኑ በተለይ የሪህ በሽታ ትንሽም ቢሆን ምልክት ያለባቸው ሰዎች ባይመገቧቸው ይመረጣል፡፡ ከዓሳና የዓሳነክ ምግቦች እንዲሁም ከእንስሳት ተዋፅኦዎች ከመመገብ ይልቅ የወተት ተዋፅኦዎችን ቢመገቡ የተሻለ ነው፡፡ ለምሳሌ ትልቅ ጮማ ከመብላት ትንሽ ቅቤ ጣል አድርጎ መመገብ የተሻለ ተመራጭ ነው፡፡

ከወተት ተዋፅኦዎች በተጨማሪ ጥራጥሬ ነክ ምግቦችን (ለምሳሌ አተር፣ ባቄላ፣ አደንጓሬ ወዘተ…) ማዘውተር ተገቢነት ይኖዋል፡፡ ምክንያቱም የወተት ተዋፅኦዎችና ጥራጥሬ ምግቦች Purina የሚባለው የፕሮቲን አይነት በጭራሽ የሌላቸው በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የአመጋገብ ስርዓታችንን በአስተካከልን ቁጥር በሽታውን መከላከል ይቻላል፡፡ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደትን መቀነስ ሰዎች አላስፈላጊ የሰውነትን ክብደት በሚቀንሱበት ጊዜ አንድም ሪህ በሽታ እንዳይከሰት መከላከል ይቻላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ችግሩ ደግሞ ደጋግሞ እንዳይከሰት ያደርገዋል፡፡ ሰውነት እንዴት ይቀንሳል ቢባል 1ኛ ስብ ነክ የሆኑ ምግቦችን መቀነስ፣ 2ኛ በቀን ውስጥ የምንወስደውን የካሎሪን መጠን መቀነስ (ለምሳሌ ዳቦና ሌሎች ኃይል ሰጭ ምግቦች) 3ኛ ኤሮቢክ የሚባለውን የስፖርት አይነት መስራት፡፡ ይሄን ስፖርት አዘውትሮ መስራት በሰውነት ውስጥ የተከማቸን የስብ መጠን ለማጥፋት ያስችላል፡፡

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.