ምላሳችን የተለያዩ ምግቦና መጠጦችን በማጣጣም ተጠምዶ ስለሚውል የምግቦቹን መልክ ለጥቂት ደቂቃዎች ይዞ ቢቆይ ቸግር የለበትም፡፡ ይሁንና ጠዋት ምንም አይነት ምግብ ሳይወስዱ ምላስዎ ቢጫ፣ ነጭ ወይም ብርቱካንማ ነገር ተጋግሮበት ሲታይ የሆነ ውስጥ ችግር እንዳለ ሊያመለክት ይችላል ይላሉ፣ ሐሳባቸውን ለፕሪቬንሽን መጽሔት የሚያካፍሉት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር ሎውረን ፔጅ፡፡ ባለሞያዋ እንደሚሉት፣ ይህ ዓይነት ችግር የሚከሰተው አሲድ ሪፍለክስ የተባለው የጨጓራ አሲድን ወደ ጉሮሮ የመርጨት ህመም ሲኖር ነው፡፡ በተፈጥሮ ጉሮሮ መጨረሻ ላይ የተገጠመው ቫልቭ፣ የሆድ ውስጥ ፈሳሾችም ይሁኑ ሌሎች ይዘቶች ወደ ጉሮሮ እንዳይወጡ አግዶ ይይዛቸዋል፡፡ አሲድ ሪፍለክስ የሚባለው ችግር ሲኖር ግን የጨጓራ አሲዶች ከጨጓራ ወደ ምግብ ቧንቧ እና ጉሮሮ እንዲሁም ምላስ ላይ እየወጡ ይጋገራሉ፡፡ ጠዋት ላይም አፍ መጥፎ ጠረን እንዲይዝ ያደርጋሉ፡፡ ይህ በተለምዶ ቃር የምንለው ችግር በጊዜው መፍትሄ ካልተሰጠው ከበድ ያለ የጨጓራ ህመም በማስከተል ጉዳቱ ከፋል፡፡ ስለዚህ ቀድሞ በቀላሉ ከፋርማሲ በባለሞያ ምክር በሚወሰዱ መድሃኒቶች ማከምን ባለሞያዋ መክረዋል፡፡ ስለሆም ምላስዎን ጠዋት ቼክ ያድርጉ፣ ይህ ችግር ካለ ፈጣን እርምጃ ይውሰዱ፡፡

ጥፍራችሁንም ተመልከቱ

ጥፍራችሁ ላይ ቢጫ፣ ቡናማ ወይም ነጫጭ ስትራይፖች ወይም ሰረዞችን ተራ ምልክቶች አድርጋችሁ አትውሰዷቸው ይላሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች የቆዳ ካንሰር እየመጣ መሆኑን ሊያመለክቱ ችላሉ፡፡ 95 ከመቶ የሚሆኑት የቆዳ ካንሰሮች በጊዜ ከተገኙ በቂ ህክምና የሚሰጣቸው ቢሆንም ብዙ ሰዎች በጊዜ ህክምና ጋር ስለማይደርሱ ብዙ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ቀለም ያላቸው የጥፍር ላይ ስትራይፕ ምልክቶች ሲገኙና የጥፍር ቀለምም እየተለወጠ ሲሄድ፣ ምልክቱ በቀላሉ መታለፍ የለበትም የሚሉት ባለሞያዋ ሐኪም ጋር ቀርቦ ጉዳዩን መታየት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

ፀጉር ሲሳሳ እና ፎረፎር ራስ ቅልን ሲቆጣጠር

ፀጉርዎን ጠዋት ሲያበጥሩ ከማበጠሪያው ጋር አብሮ የሚወልቀው የፀጉር ዘለላ በየጊዜው እየበረከተ ሲሄድ፣ ሐሳብ ሊገባዎት እንደሚገባ ባለሞያዎች ያሳስባሉ፡፡ የፀጉር መሳሳትና መርገፍ ከሆርሞን መዛባት በተለይ የታይሮይድ ሆሞን ጋር የመያያዝ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ የታይሮይድ ሆርሞን አጠቃላይ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ ከማሳደር በተጨማሪ የወሲብ ህይወትንም ያስተጓጉላል፡፡

ሐኪም ጋር ቢቀርቡ በተገቢ ሆርሞን ህክምና ችግሩ ሊሻሻል ይችላል፡፡ ነገር ግን የፀጉር መሳሳትና መሰባበር ሌላ ከቆዳ ጋር የተያያዘ ምክንያት ይኖው እንደሆነ ማጣራቱ ይቀድማል ይላሉ ባለሞያዎቹ፡፡

የፀጉር መሳሳቱ ብቻ ሳይሆን ፎረፎርም ትኩረት የሚሻ እና ጠዋት ሲነሱ በአስተውሎት ሊመለከቱት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ዶ/ር ሎረን ይናገራሉ፡፡ ከፀጉርና ማበጠሪያው አልፎ ፎረፎር፣ ጥቁር ሸሚዝ እና ኮትዎ ላይ እየተነጠፈ የሚያሳቅቅዎት ከሆነ በእርግጥም አሳሳቢ ነው፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን? ለዚህ ባለሞያዋ አስገራሚ ምላሽን ይሰጣሉ፡፡ ከመጠን ያለፈ መጨነቅና ውጥረት የበሽታ መከላከል አቅምን ከማዳከም አልፎ፣ የራስ ቅልን ወዝ የመምጠጥና የማድረቅ ተፅዕኖም እንዳለው ተደርሶበታል፡፡ ስለዚህ ፎረፎር ሲበዛብዎት የየዕለት ውሎ እና ኑሮዎትን መመርመሩን ይበርቱበት ይላሉ ዶ/ር ሎረን፡፡ ውጥረት ፎረፎርም ያመጣል፡፡

የዓይን ቀለም እና ዙሪያ ገባው እክሎች

ከድሮ ጀምሮ የዓይን ቢጫ ቀለም መያዝ ከቢጫ ወባ ጋር መያያዙን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ በተለምዶ ቢጫ ወባ የምንለው የጉበት በሽታ ነውና ዓይንዎ ቀለም መቀየሩን፣ በተለይም ቢጫ መሆኑን ጠዋት ከመስተዋት ፊት ቆመው ካስተዋሉ፣ ቸል ሳይሉ ፈጣን የባለሞያ እርዳታ እንዲሹ ይመከራል፡፡

የዓይን ቀለምን የሚቀይረው የጉበት በሽታ ብቻ አይደለም፤ የዓይን መቅላትም ከዓይን ነርቮች ጉዳት ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ከመጠን ላለፈ የፀሐይ ብርሃን መጋለጥም በዓይን ቀለም እና የውስጡ ነርቮች ጉዳት የማድረስ አጋጣሚው ከፍ ያለ ነው፡፡ በዓይን ውስጥ ብቻ ሳይሆን የዓይን ዙሪያ ቆዳ ላይም ክብ መሰል ጥቁረት ሊታይ ይችላል፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ ፊታችንን ከምንቀባቸው ቅባቶች ወይም መነፅር አለርጂ ጋር እንደሚያያዝ ባለሞያዋ ይጠቁማሉ፡፡ ስለሆነም የትኛውም ለየት ያለ ምልክት ጠዋት ላይ ቼክ ተደርጎ፣ አስፈላጊውን እርምጃ ራስ ወይም ባለሞያ መፍትሄ እንዲሰጠው ማድረግ ላይ ባለሞያዎቹ አጠንክረው ይመክራሉ፡፡

ይህ ጽሑፍ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.