በተክለ ቁመናዊ መስህባቸውና በግርማ ሞገሳቸው አንቱታን ካተረፉ የሆሊውድ ዝነኞች መካከል ናአሚ ሀሪስ አንዷ ነች፡፡ ናአሚ ሀሪስ ለኮስሞፖሊቲያን ዘጋቢ ለሆነቸው ሰፊ ጎዳደር ስትናገር የመጀመሪያ ዲግሪዋን በካምበሪጅ ዩኒቨርሲቲ እንዳጠናች እና በቀጣይም ወደ ሆሊውድ በማቅናት ወደ ፊልሙ ዓለም እንደተቀላቀለች ገልፃለች፡፡ ናአሚ ስለ ሆሊውድ ጉዞዋና በፊልሙ ዓለም ስለነበራት ቆይታ ስታወጋ ‹‹ያለኝ ማራኪ ተክለ ቁመና እና ግርማ ሞገስ በራሱ ከፍተኛ የራስ በራስ መተማመን እንዲኖረኝ ከማድረጉ ባሻገር ብዙ አድናቂዎችና ተከታዮች እንዲኖሩኝ አስችሎኛል›› ብላለች፡፡ በተመሳሳይ የእንግሊዙ ኒው ሳይንቲስት መፅሔት የተዋበ ተክለ ቁመና ባለቤት የሆኑ ሴቶች የብዙ ወንዶች ቀልብ ከመሳብ ባሻገር በፈለጉት የህይወት አቅጣጫ በቀላሉ ስኬታማ መሆንና ብዙ ተከታዮች ማፍራት እንደሚችሉ ገልፅዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ሞዴል ሊያ ከበደ ግርማሞገስ ካላቸው ኢትዮጵያውያን ዝነኛ ሰዎች መካከል አንዷ ናት::

እንዲሁም የስነ ልቦና ተመራማሪዎች ይህንን ግርማ ሞገስ ማንኛውም ግለሰብ መላበስ እንደሚችል ያስረዱበትን ስነ ልቦናዊ ትንታኔ ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

ግርማ ሞገስ (Charisma) የማንኛውም ሰው ስሜት ለአፍታም ቢሆን ጨምድዶ የሚይዝ ግሩም ትዕይንት ነው፡፡ ትዕይንቱ የሚንፀባረቅባቸው ሴቶች ክስተቱን በተፈጥሮ የታደሉት አልያም ደግሞ ሆን ብለው ያዳበሩት ሊሆን ይችላል፡፡ ሁነኛው ቁም ነገር ግን ሴቶቹ አብዛኞቻችን ያጣናቸውን ነገር ግን አጥብቀን የምንፈልጋቸውን በራስ የመተማመን፣ ፆታዊ ግፊት፣ ተስፈኝነትና ደስተኝነትን የያዙ ከመሆናቸው ባሻገር እጅግ ማራኪና ስሜት ገዥ ተክለ ቁመና ባለቤትም ናቸው፡፡ እነኚህንም ሳይሰስቱ ከውስጥ ወደ ውጭ ማውጣት መቻላቸው ነው፡፡ ከሌላው በተለየ እንደ ጣኦት ወይም መልአክ የሚታዩትንና የተመልካችን ልብ የማስደንገጥ ብቃት የመጎናፀፋቸው ምስጢርም ይኸው ነው፡፡ የተፈጥሮ ግርማ ሞገሳችን ለመወደድ ወይም ለመፈቀር ማውራት፣ ማጌጥ ወይም ልታይ ልታይ ማለት ላይጠበቅባቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ያያቸው ሁሉ እንዲሁ የሚወዳቸው አንዳች ኃይልን የተጎናፀፉ እድለኞች ናቸው ብለን ልንገልጻቸው እንችላለን፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ በሌሎች ዓይን ብሎም ስሜት ቀጥሎም ልብ ውስጥ ተቀናቃኛቸውን በመቅደም ዘው ብሎ ለመግባት የሚሞክሩና የሚሳካላቸው የባህሪ መግለጫዎችም አሉ፡፡ እነኚህ ታዲያ ለመወደድና ለመፈቀር (ማለትም ግርማ ሞገስን ለመጎናፀፍ) ጥቂትም ቢሆን መስዋዕትነት መክፈልን ይጠይቃሉ፡፡ ውስጥ ድረስ ዘልቆ በመግባት ሁሉን ማወቅ የሚችል የሚመስል እይታን ማዳበር፣ የተጠናና የተስተካከለ ንግግር ማድረግና በአጠቃላይም ብዙሃን የሚመርጡትንና የሚፈልጉትን ባህሪ በመለየት እሱንም አጥንቶ በሚገባ እንዲታይ አድርጎ ከውጭ ማንፀባረቅ መቻል ፈጽሞ ተፈላጊነትን መጎናፀፊያና የግርማ ሞገሳምነት ምስጢር ነው፡፡

ታሪካዊ ምሳሌዎች
እ.ኤ.አ የ1420ዎቹ ዘመናት ለፈረንሳያውያን ጥሩ ጊዜያት ያልነበሩበት ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ አብዛኛው የፈረንሳይ ምድር በእንግሊዝ እጅ ውስጥ ከመግባቱም ሌላ ንጉስ ቻርልስ 7ኛ በስደት ርቆ እንዲኖር የተገደደበት ጊዜ ነበርና፡፡ በወቅቱ የእንግሊዝን ኃይል መክቶ ፈረንሳይን ለነፃነት የሚታደጋት የቁርጥ ቀን ልጅ ማንም አልነበረም፡፡ ሁሉም ፈረንሳያዊ በጠቅላላ በእንግሊዛውያን ቅኝ ግዛት ስር መሆኑን አምኖ በተቀበለበት ወቅት ነበር ከአንድ የገበሬ ቤተሰብ የተገኘች ማንንም ወንድ በፍቅር ሊያንበረክክ የሚችል ግርማ ሞገስ ያለው የተክለ ቁመና ባለቤት የሆነች የ13 ዓመት ታዳጊ ከዚህ አስተሳሰብ ውጪ በመሆን ብቅ ለማለት የቻለችው፤ ዦን ኦፍ አርክ፡፡

ይህቺም ታዳጊ ፈረንሳይ በምንም ተአምር የእንግሊዝን ቅኝ ተገዥ እንደማትሆን ከተራራ የገዘፈ እጅግ ታላቅ እምነትና አቋም ነበራት፡፡ የዚህችን ታዳጊ ድምጽ የሚሰማ በጊዜው አለመኖሩም የሚጠበቅ ነበር፡፡ ለምን ቢባል ከአንድ የድሃ ገበሬ ቤተሰብ ከመውጣቷ በተጨማሪ ምንም የማታውቅ ህፃን እንዲሁም ሴት ነችና፡፡

ልጅቷ ግን ይህን ሁሉ ከጉዳይ ሳትጥፍ መላ ፈረንሳውያንን ማነቃቃትና የእንግሊዝን ኃይል እንዲመክቱ ፍፁም ከ13 ዓመት ልጅ በማይጠበቅ አኳኋን የጥሪ ማስተጋባት ዘመቻዋን ቀጠለችበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በስደት የሚኖረውን የፈረንሳይ አልጋ ወራሽ ቻርልስ 7ኛን ወደ ዙፋኑ ለመመለስ እንደምትታገልም ትናገር ገባች፡፡ ይህንንም ለመፈፀም ቻርልስ ወደ ተሰደደበት አገር በማቅናትና ለጊዜው ከአልጋ ወራሹ ጋርም በመነጋገር እንግሊዝን ለመውጋት የጦርነት እቅድ ለመንደፍ ከእጅ ወደ መዳፍ ከማይሞሉ የእምነቷ ተቀባዮችና ተከታዮች ጋር በመሆን እጅግ አድካሚ የእግር ጉዞ አደረገች፡፡ የ13 ዓመቷ ታዳጊ ቀስ በቀስ በፈረንሳውያን ብቻም ሳይሆን በእንግሊዛውያንም ሳይቀር ዝናዋ እያየለ መጣ፡፡ ከንጉስ ቻርልስ ጀምሮ ጠቅላላ በመላው ፈረንሳውያን ዘንድ የወጣቷ መንፈስ ጠንካራነት ታላቅ መነቃቃትን ፈጠረ፡፡ በጠላት ክንድ ስር ለመዋል እርግጠኛ የነበረው ፈረንሳዊ ወጣት በሙሉ ‹‹ዕድሜ ለ13 ዓመቷ ጉብል›› ይበልና ጦሩን ወደ እንግሊዝ አነጣጥሮ ለመወርወር ዝግጁ ሆነ፡፡ ይህን ሁኔታ የተረዳችው እንግሊዝም ሞቶ የተነሳውን የፈረንሳውያንን ወኔ ለመሸርሸር እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረግ ግድ ብሏ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ፈረንሳይ በመጨረሻ በእንግሊዝ እግር ስር መውደቋ ባይቀርም፡፡ በአስደናቂዋ፣ ቆራጧና መንፈሰ ጠንካራዋ ታዳጊ ጆን ኦፍ አርክ ምክንያት የእንግሊዝ ጦር ሙሉ በሙሉ ለመመታት ከጫፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡

‹‹ፈጣሪ በቅዱስ ሚካኤል…››
በወቅቱ የ13 ዓመት ዕድሜ ብቻ የነበራት ታዳጊዋ ጆን ኦፍ አርክ ‹‹ፈጣሪ በቅዱስ ሚካኤል መልዕክት አድርሶኛል፡፡ መልእክቱም ፈረንሳይ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዥ አትሆንም፣ ንጉስ ቻርልስም ዙፋኑን ይወርሳል…›› የሚል መንፈሳዊነትን የተላበሰ ባህሪን በመግለፅ የዚህን እውነትም ተግባራዊነት ለማሳየት ቆርጣ በመነሳት እጅግ ለቁጥር የሚያታክቱ ተከታዮቿን ከማፍራቷም በላይ በፈረንሳይ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አስደናቂ የሚባል ተግባርን አከናውናለች፡፡ ዛሬ ‹‹ጆን ኦፍ አርክን አላውቃትም›› የሚል ፈረንሳዊ ካለ እሱ ፈረንሳዊ አይደለም፡፡ እናም እንደ ጆን ኦፍ አርክ ከእውነት ወይም ከመሬት ተነስቶ ነቢይ ነኝ ማለት ቢያንስ ጥቂት ተከታዮችን አያሳጣም፡፡ ‹‹የዚህች ሴት እውነት ምን ይሆን?›› ብሎ ለመመራመር የሚጓጓውም ብዙ ነውና ሽንጧን ገትራ ላመነችበት ጉዳይ በፍፁም እምነትና ቆራጥነት መስበክ የቀጠለች ግርማ ሞገስን መጎናፀፍ ትችላለች፡፡

እንደ ኤልቪስ ፕሪስሊም በራስ መተማመንና የውስጥና እምቅ ኃይል ማውጣት መቻልም ደርባባነትን የሚያጎናፅፍ ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ መድረክ ላይ ከወጣ ሙዚቃና ሙዚቃን ብቻ የሚተነፍሰው ፕሪስሊ ሁሉ ነገሩን በሚወደው ነገር ማድረግ መቻሉ ከውስጥ ያለውን እምቅ ችሎታ አውጥቶ እንዲጠቀምበት ስለረዳው በድምፁም እንቅስቃሴው ያስደሰታቸው በሞላ መልሰው በራሱ የፍቅር ዜማ አንጎራጉረውለታል፡፡

ግርማ ሞገስን ለመጎናፀፍ እጅግ በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ በጣም የሚደንቀው ነገር ግን እንደነ ኤልቪስ ፕሪስሊ እጅግ ተወዳጅ ለመሆን ከእነኚህ መንገዶች አንዱን ብቻ መጠቀም ሊበቃ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ጆን ኦፍ አርክ የተጠቀመችው ውበትን በቅድስና፣ ፕሪስሊ ደግሞ ረቂቅነትን ወይም የአላማ ሰው ሆኖ መገኘትን ሊሆን ይችላል፡፡ ከአስር ከማያንሱት እጅግ አስፈላጊ የግርማ ሞስነት ወይም ደርባባነትና ተፈላጊነት መጎናፀፊያ መንገዶች ቢያንስ አንዱን እንኳን የሙጥኝ ማለት በሌሎች ዘንድ ሙጥኝ መባልን ያለተቀናቃኝ ያስገኛል፡፡ ግን ከአስሩ ብልሃቶች እርስዎ ከየትኛው እንደሆኑ ይመርምሩ፤ ከአንዱ ካልሆኑም ለእርስዎ ቅርብ የሆነውን በማጥናት ይጠቀሙበት፡፡

1. ማራኪነት፡- ውበት እንደተመልካቹ ነው ቢባልም አንዳንዴ በብዙዎች ዓይን በፍጥነት የሚገባ ማራኪ ወይም አስደሳች ገፅታ ያላቸው ሴቶች መኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ አንዳንድ ሴቶችም የዚህን የደስ ደስ ያለው ገጽታ መገለጫዎች ባለቤት ይሆኑና ያሻቸውን በሙሉ ሊያፈዙ ይችላሉ፡፡ ውስጣቸው ምንም ይሁን ምን እነዚህ አይነት ሴቶች በአፍታ እይታ በፍቅር የሚጦዙ አስደናቂ ፍጥረታት ናቸው፡፡

2. የአላማ ሰውነት፡- የአላማ ሰው ከሆንሽም አላማሽ ምንም ይሁን ምን ሰዎች ይከተሉሻል፡፡ የሚከተሉሽ አንቺን ብለው ሳይሆን የአላማሽን ምስጢር ለማወቅና እነሱም ሊጠቀሙበት ነው፤ መንገድ ላይ ሳያስቡት ግን በአንቺ ፍቅር ይነደፋሉ፡፡ እናም ሩቅ አላሚ ተስፈኛ ከመሆን ለአፍታም ቢሆን አትቦዝኚ፡፡

3. ረቂቅነት፡ ውስጥ በብዙ ነገሮች የተሞላና ሰዎች ሊረዱት የማይችሉት አይነት ይሁን፡፡ ሀበሻ ‹‹ልቧ አይገኝም›› እንደሚለው ማለት ነው፡፡ ረቂቅነት በሌሎች መንገዶችም ይገለፃል፡፡ ለምሳሌ የአረመኔነት፣ የሆዳምነት፣ የነጭናጫነት፣ ወይም የየዋህነት ህብር ማለት ነው፡፡ ወይ እንደ ሲግመን ፍሩድ እየቀረብሽ እንደገና የምትርቂ ወስላታ ለመሆን ሞክሪ፡፡ አልያም ሳቂታና አኩራፊ ሁኚ ወይም ደግሞ ጨካኝና የዋህ ሁኚ፡፡ በቃ በአጭሩ ባህሪሽ ሊጨበጥ የማይችል ሲሆን በበርካቶች ዘንድ የመወደድ እድልን ያስገኝልሻል፡፡

4. ቅዱስነት፡ እንደ ጆን ኦፍ አርክ የምታምነውን ነገር አንፀበርቀው፤ እንደ አልበርት አንስታይን ለማታምኚበት ነገር ፍንክች አለማለትንና በራስሽ ዓለም ብቻ መኖርን ተማሪ፡፡ በመተማመንና በመግባባት ማመን የለብሽም፡፡ የራስሽ እምነት የራስህ ነው፤ ደግሞም ትክክል ነው፡፡ ይህንንም ያለመታከት ሌሎች እንዲሰሙህና እንዲከተሉሽ ታደርጊያለሽ፤ ነገር ግን እነሱ የሚሉትን ካዳመጥሽና ከአንቺ እምነት ጋር ልታቀናጂው ካሰብሽ የቅዱስነት መገለጫን ማግኘት አትችዪም፡፡ እናም በዚህ መንገድ ግርማ ሞስን አታገኚም፡፡

5. አንደበተ ርቱዕነት፡- ቃላት ስሜትን ለመቆጣጠር ኃይላቸው ከፍተኛ ነው፤ እናም ጥሩ ተናጋሪ በመሆን የሌሎችን ስሜት ለመያዝ ትችያለሽ፡፡ ለምታወሪው ነገርም ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ይኑርሽ፤ በዚህ ሁኔታም ግርማ ሞስን ትቀዳጃለሽ፡፡

6. አስመሳይነት፡ ራስሽን ሰዎች በሚወዱት መንገድ ቀርፀሸ ቅረቢ፣ እንደ እውነት የውሸት አልቅሺ፤ እንደ እውነት የውሸት ሳቂ፣ እንደ እውነት የውሸት ተናገሪ፡፡ ቁም ነገሩ የአለቀስሽው የሳቅሺውና የተናገርሽው እውነት ከመሆኑ ላይ ሳይሆን በሚያስደስት አኳኋን ወይም ልብን በሚበላ መንገድ መከናወኑ ነው የግርማ ሞገስን ካባ ሊያስደርብሽ የሚችለው፡፡

7. ግድ የለሽነት፡ ለዓለም ወይም ለሁኔታዎች የሚኖር እይታ የተዛባና ግድ የለሽነት የሚንፀባረቅበት ሲሆን በሌሎች ዘንድ መወደድን ያስገኛል፡፡ በተለይ ደግሞ ሰዎችን ችላ ማለት የመፈቀሪያ መንገድ መሆኑን ልብ በይ፡፡ ለአጠቃላይ ሁለንተናሽ ግድ የለሽ ሆነሽ ስትታይ ሰዎች አንቺን የመቅረብና የማወቅ ፍላጎታቸው ይንራል፡፡ በዚህ አካሄድ ታዲያ በፍቅርሽ ስር መዋላቸው አይቀርም፡፡

8. ደካማነት፡- አንድ ደካማ ጎን ሲኖርሽ ያንን ደካማ ጎንሽ ለመጠቀም ወይም ለማሰተካከልና የህሊና እርካታ ያገኙ ዘንድ ይጠጉሻል፤ ከዚያም ይወዱሻል ማለት ነው፡፡ በተለይ ደካማ ጎንሽ ተፈጥሯዊ ሲሆንና ልታስተካክይው ያልቻልሽው ሲሆን ጥሩ ነው፡፡ አቤት በዚያች ቀዳዳ መግባት የሚፈልገው ብዛቱ! ደካማ ጎንሽን ከማሳይ አትቦዝኚ፡፡

9. ጀብደኝነት፡- በሰዎች ፊት ጀብደኛ ሁን፤ ራስሽን በአደገኛ አካባቢዎች አስገቢ፡፡ በቃ በአንድ ነገር ዝነኛ ሁኚ፤ አድናቂዎችሽ ብሎም ፈላጊዎችሽ ይበዛሉና፡፡ ጆን ኦፍ ኬኔዲን ለሞት የዳረገው ያለጠባቂ በነፃ መዘዋወር የመውደድ ጀብደኝነቱ ቢሆንም በዚህ ባህሪው ግን በርካቶች ይወዱታል ያደንቁታል፡፡ ፈረንሳዊው ቻርለስ ደጎልም የህዝብን አመፅ ፊት ለፊት የሚጋፈጡ ጀብደኛ መሪ ነበሩ፡፡ ታዲያ ዛሬ እንኳን ፈረንሳውያን እኛስ ለደጎል አገር ሰጥተው የለ!? ‹‹ደጎል አደባባይ››

10. መግነጢሳዊነት፡- የሰዎችን ትኩረት የሚወስድ አንዳች ኃይልን ተለማመጂ፡፡ ለምሳሌ ሰዎችን አትኩረሽ ተመልከቻቸውና ዘወር በይ ቀጥለው እነሱ ያፈጡብሻል፡፡ ከዚህ በኋላ ማረፍ የማይወደው ቀላዋጭ አይናቸው (ስሜታቸው) ይከተልሻል፡፡ ቤኒቶ ሙስሎኒ ቁጣውን የሚያሳየው በዓይኑ ነበር፡፡ ቃላት ከመናገሩ በፊት ዓይኑን በዙሪያው ካሉት ሰዎች ላይ በማፍጠጥ ያለ ንግግር ሃሳባቸውን ያስቀይራል፡፡ በፍቅርም እንደዚያው ነው፡፡ ለምሳሌ ፍቅረኞች እርስ በእርስ የሚተያዩበት ሁኔታ የስበት ኃይሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንንም መንገድ በመከተል በአንቺና በምርኮኛሽ መካከል የሚኖረውን የስበት ኃይል ጨምረሽ ተወዳጅነትን አግኚበት፡፡

አደገኛ ክስተቶች
‹‹erotic fatigus›› ወሲብ ከተፈፀመ በኋላ የሚኖር ቅፀበታዊ ድካምና ፀፀት ነው፡፡ ግርማ ሞገሳሞቹም በዚህ መሳዩ ክስተት የመጠቃታቸው ዕድል የሰፋ ነው፡፡ የወደዱትን ያህል የመጠላት አጋጣሚ ይጠነክርባቸዋል፡፡ በአስገራሚ ሁኔታ ፍቅራቸው ሙሉ በሙሉ ወደ ጥላቻ ይቀየራል፡፡ ለዚህ አይነቱ መጥፎ ሁኔታ መፈጠር ምክንያቱ ደግሞ ሰለባቸው ምን ጊዜም በእንከን አልባነታቸው እንዲዘልቁ ከመሻቱ የተነሳና ይህም አልሆን ብሎ በፍቅር ያነሆልል የነበረው ባህሪያቸው ፍፁም ተቀይሮ ለፍቅር ተጠቂያቸው አልመች ሲል ነው፡፡ በአንድ ወቅት አፈቅርሃለሁ ብላ ልጅና ትዳሩን ያፋታችው ኮዳ እንደ ምላሷ ሳይሆን እንደ እውነቱ ልጆች እናትና ባለትዳር መሆኗን ያወቀው የፍቅር ምርኮኛዋ ጎረምሳ እስከ ወዲያኛው እንዲያሸልብ አድርጋዋለች፡፡

ምልክታቸው
ግርማ ሞሳሞቹ በፋኖስ ይመሰላሉ፤ ጨለማን ከመቅጽበት ወደ ብርሃንነት የሚቀይር የፋኖስ መብራት እንዲሁ ስንመለከተው ላያስገርመን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጋዝ በጨርቅ ድልድይነት ተሸጋግሮ ከዚያም ወደ ብርሃንነት በመቀየር ሊያሞቀንና ሊያደምቀን መቻሉ አስደናቂ ትዕይንት ነው፡፡ ግርማ ሞገሳሞቹም በአካላቶቻቸው ድልድይነት የውስጣቸውን ግፊት እንዳለ አውጥቶ በማንፀባረቅ ለራሳቸውም ለሌላውም ብርሃን ይሆናሉ፡፡ አዎ ፋኖስ ናቸው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.