በውፍረትና ካንሰር በሽታ ተያያዥነት ላይ አንድ የህክምና ባለሙያን አነጋግረናል፣ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ጥያቄ፡- እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በአገራችን ውፍረት የጤና ችግር ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ውፍረት በህክምና እንዴት ይገለፃል?
ዶ/ር፡- ውፍረት ማለት በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው የስብ ክምችት መብዛት ሲሆን ቀጥተኛ መለኪያ
ስለሌለው በተለያዩ ቀጥተኛ ባልሆኑ መለኪያዎች ይለካል፡፡ አንደኛውና ብዙ ጊዜ የምንጠቀመው የውፍረት መለኪያ
(BMI) የምንለው ሲሆን የሰውነት ክብደት (በኪሎ ግራም) ከቁመት (በሜትር) ጋር በማነፃፀር የሚሰላ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ውፍረትን እንደሚከተለው ይከፋፍለዋል፡፡
ከ18.5-24.9 (Normal)
BMI 25-29 ኦቨር ዌይት (Over weight)
30 እና ከ30 በላይ ወፍራም (obese) የሚባለውነው፡፡
ሌሎች የውፍረት መለኪያዎችም አሉ፡፡ ይኸውም ስብ ክምችት በየትኛው ክፍል ላይ እንደሚበዛ ሲሆን ከልብ ችግሮች
ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረት እንዴት ይመጣል?
ዶ/ር፡- በአካባቢያዊ እና በተፈጥሮ /ጄነቲክ/ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል፡፡ ከሁሉም ይልቅ ግን
ከእንቅስቃሴ ነፃ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ፣ ከሚገባው በላይ ካሎሪ መውሰድ፣ ጣፋጭ ነገሮችን መመገብ፣ መድሃኒቶች፣
የሆርሞን ችግሮች፣ ሴቶች ላይ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች እና የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ
በጀነቲክ ምክንያቶች የሚመጣን ውፍረት ማሻሻል ወይም መለወጥ የማይቻል ሲሆን ይህም በራሱ ከ30-50% ድረስ
ያለውን የውፍረት ክስተትን ያመጣል፡፡ እስካሁን በአብዛኛው ለውፍረት መንስኤ የሆነ ጂን በጥናት
አልተደረሰበትም፡፡

ጥያቄ፡- በአገራችን ውፍረት ምን ያህል አሳሳቢ ነው?
ዶ/ር፡- የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ዘገባ እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች
የውፍረት ሰለባ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከ17% በላይ ህፃናቶች ሲሆኑ፣ 30% አዋቂዎች ናቸው ይላል፡፡
በአሁኑ ሰዓት አንድ ሦስተኛው የአሜሪካ ህፃናትና ወጣቶች የውፍረት ሰለባዎች እንደሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
በአገራችንም በተመሳሳይ መልኩ ውፍረት እየበዛ እንደመጣ የሚያሳዩ የተለያዩ ምልክቶች ቢኖሩም በጥናት የተደገፈ
መረጃ ግን የለም፡፡

ጥያቄ፡- የህፃናት ውፍረትስ?
ዶ/ር፡- ህፃናት በቦዲ ማስ ኢንዴክሳቸው (BMI ከዕድሜያቸውና ከፆታቸው አንፃር ተሰልቶ ወፍራም የሚባሉ
ሲሆን፣ በህፃንነት መወፈር አዋቂ ሲሆኑም ወፍራም ለመሆን የሚያበቃቸው አደጋ ከመሆኑም በተጨማሪ ለማንኛውም
ከውፍረት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሞትን አመላካች ነው፡፡ ወፍራም የሆኑ ህፃናት የደም ግፊት፣ ስኳር፣ ኮሌስትሮል
እና የጉበት ምርመራ ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረት ምን ያህል አሳሳቢ ነው?
ዶ/ር፡- ውፍረት በጣም አሳሳቢ የሆነበት ምክንያት ለበሽታዎች መጋለጥ ምክንያት በመሆኑ ሲሆን ከእነዚህም
ውስጥ ለሣንባ በሽታ፣ ለእንቅልፍ መዛባትና ለግፊት ተጋላጭ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአልኮል ውጭ የጉበት
በሽታ፣ የሀሞት ከረጢት በሽታ፣ ስትሮክ፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ የልብ የደም ቧንቧ ጥበት፣ የስኳር በሽታ፣
የኮሌስትሮል መዛባት፣ የደም ግፊት፣ የቆሽት በሽታ፣ ለሪህ በሽታ እና ካንሰር የማጋለጥ ዕድል አለው፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረትና የካንሰር ተጋላጭነትስ?
ዶ/ር፡- የካንሰር በሽታ በየዓመቱ በውፍረት ምክንያት ይመጣል፡፡ ይህም ከ15-20 በመቶ ከካንሰር ጋር
ተያይዞ ለሚመጣ ሞት ምክንያት ይሆናል፡፡

ጥያቄ፡- ምን አይነት ካንሰሮች በውፍረት ይመጣሉ?
ዶ/ር፡- የጡት ካንሰር፣ የማህፀን ካንሰር፣ የማህፀን በር ካንሰር፣ የትልቁ አንጀት ካንሰር፣ የጉሮሮ
ካንሰር፣ የቆሽት ካንሰር፣ የኩላሊት ካንሰር፣ የፕሮስቴት ካንሰር፣ የጉበት ካንሰር የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- በውፍረትና ካንሰር ትስስር ላይ የተሰሩ ጥናቶች አሉ?
ዶ/ር፡- ባለፉት ዓመታት የውፍረትና የካንሰር ግንኙነት የሚያሳዩ የተለያዩ ጥናቶች የተሰሩ ሲሆን አሁንም
በመሰራት ላይ ያሉ በርካታ ጥናቶች የተሰሩ ሲሆን አሁንም በመሰራት ላይ ያሉ በርካታ ጥናቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ውፍረት ለተለያዩ አይነት ካንሰሮች የመጠቃት ዕድልን ይጨምራል፡፡ በተጨማሪም ውፍረት
ከካንሰር ባገገሙ ሰዎች ላይ ተጓዳኝ በሽታዎች እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ፡- የልብ ህመም፣ ስትሮክ፣ ስኳር
እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረት ለካንሰር በማጋለጥ ከሌሎች ምክንያቶች አንፃር እንዴት ይታያል?
ዶ/ር፡- ውፍረት ከሲጋራ ባልተናነሰ የካንሰር ሪስክ የሚጨምር ሲሆን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣
ውፍረት በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልንና ተያይዞ የሚመጣ የሞት አደጋን በ33% ይጨምራል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት
BMI ከ35 kg/m2 በላይ ያላቸው ወንዶችና ከ30 kg/m2 በላይ ያላቸው ሴቶች ከትልቁ አንጀት ካንሰር ጋር
የተያያዘ የከፋ ውጤት አላቸው፡፡ ስለዚህ ውፍረት ለከፋና ለተዛመተ (advanced) የፕሮስቴት ካንሰር
ያጋልጣል፡፡ ለካንሰር ህክምናም ያለውን ምላሽ ይቀንሳል እንዲሁም እየተመላለሰ (Recurrence) እንዲመጣ
ከማድረጉ ባሻገር የመሞት አደጋን ይጨምራል፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረትን የሚያመጡ አመጋገቦችና የኑሮ ዘይቤዎች ምን ምን ናቸው?
ዶ/ር፡- ከላይ ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት፣ ውፍረትን የሚያመጡ አመጋገቦችንና የኑሮ ዘይቤዎች ህብረተሰቡ
በደንብ አውቋቸው ሊከላከላቸው የሚገባ ሲሆን እነዚህም፡-

– በቂ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ ለምሳሌ ለረጅም ሰዓት ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን ማየት፣ ከሚፈለገው ካሎሪ
/የኃይል መጠን/ በላይ መመገብ፣ ያለቀላቸው የካርቦ ሃይድሬት ውጤቶችና ስብ የበዛባቸው ምግቦች መመገብ፣ በተለይ
ሳቹሬትድ የሆነ የስብ ዓይነት በብዛት መመገብ ለምሳሌ የድንች ውጤቶች ችፕስ እና የመሳሰሉት፣ ጣፋጭ ለስላሳ
መጠጦች፣ ኬክ፣ ኩኪስ፣ አይስክሬም፣ የሥጋ ተዋፅኦዎች፣ ቅቤ፣ የሚረጋ ዘይት እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረትና ኮሌስትሮል ያላቸው ግንኙነትስ?
ዶ/ር፡- ውፍረት ከኮሌስትሮልና ስኳር መጨመር ጋር የሚያያዝ ሲሆን ይህም የሚሆነው የኮሌስትሮል ምርትን
በመጨመር ነው፡፡ ውፍረት በስኳር የመያዝን ሪስክ ይጨምራል፡፡ ይህም በዋናነት ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን
በሴሎቻችን ላይ በሚገኙት ኢንሱሊን ተቀባዮች (receptors) ላይ እንዳይሰራ ማድረግ ሲሆን በተጨማሪም
በደማችን ውስጥ የሚዘዋወሩ ነፃ የስብ መጠን በመጨመር፣ ለጉበታችን ስኳር ማምረቻ ግብአትነት ያገለግላሉ፡፡
እንዲሁም በደም ውስጥ የሚዘዋወረው ነፃ የስብ መጠን መብዛት፣ በቀጥተኛ መንገድ ጣፊያ ውስጥ የሚገኙ ኢንሱሊን
አምራች ሴሎችን በመጉዳት ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ውፍረት አይነት 2 የተባለውን ስኳር ህመም እንዲጨምር
ያደርጋል፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረትና ኮሌስትሮል ያላቸው ግንኙነት ምን ይመስላል?
ዶ/ር፡- ውፍረት ለተለያዩ የልብ ችግር የሚያጋልጥ ሲሆን ከሚያመጣቸው የልብ ችግሮች መካከል የልብ የደም
ቧንቧ ጥበትና የልብ ድካም ናቸው፡፡ ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ የሚመጣ የሚመጣ ሞትን ይጨምራል፡፡ ከዚህም
በተጨማሪ ወፍራም ሰዎች ለልብ ምት መዛባት ተጋላጭ ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረትና የደም ግፊት ግንኙነት አላቸው?
ዶ/ር፡- ወፍራም ሰዎች ለደም ግፊት መጨመር ተጋላጭ ናቸው፡፡ ይህም በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙትን
ካቴኮላሚንስ የተሰኙ ቅመሞችን በመጨመርና ኩላሊት ጨውን (Sodium) መልሶ ወደ ሰውነታችን እንዲያስገባ
በማድረግና የደም ቧንቧ መኮማተርን በመጨመር ነው፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረትን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ዶ/ር፡- ዋነኛው ውፍረትን መከላከያ መንገድ የአኗኗር ዘይቤን መቀየር ሲሆን እነሱም፡-

– የካርቦ ሃይድሬትና የስብ መጠንን መቀነስ፤
– የተመጣጠነ እና የካሎሪ መጠኑ የተመጠነ አመጋገብ መከተል፤
– ፋይበር ያላቸውን ምግቦች መጠን መጨመር፤
– በሳምንት ከ150-300 ደቂቃ የሚሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር
የሚፈለገው ለውጥ ካልመጣ፣ ውፍረትን የሚቀነሱ መድሃኒቶች መጠቀም ነው፡፡

ጥያቄ፡- ውፍረት መቀነስ ከካንሰር ለመጠበቅ ዋስትና ይሆናል?
ዶ/ር፡- ሙሉ በሙሉ ዋስትና አይሆንም፤ ምክንያቱም ካንሰር በብዙ መንስኤዎች መስተጋብር የሚመጣ ስለሆነ
ነው፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ክብደትን መቀነስ የካንሰር ተጋላጭነትን ይቀንሳል፡፡

ጥያቄ፡- ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?
ዶ/ር፡- ውፍረት በአብዛኛው ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጉድለትና ከአመጋገብ ችግር የሚመጣ እንደመሆኑ እና
ለተለያዩ በሽታዎች ምክንያት በመሆኑ፣ ሁሉም ሰው ይህን ተገንዝቦ የአኗኗር ዘይቤውን በማስተካከል ሊከላከለው
የሚገባ በዓለማችን በፍጥነት እየጨመረ የሚገኝ ችግር ሲሆን ውፍረት ከሚያመጣቸው ዘርፈ ብዙ ቀውሶች መትረፍ
የሚቻለው ቀውሶችን ከማከም ይልቅ ቀድሞ ሜዲካል ቼክ አፕ በማድረግና ከላይ የተጠቀሱ መከላከያዎችን ተግባር ላይ
በማዋል ነው፡፡ በዚህ ረገድ በውፍረት፣ በልብና የደም ስር በሽታዎች እንዲሁም የስኳር ህመሞች ጋር በተያያዘ
በገዙንድ ህክምና ማዕከል ከማከም ባሻገር ለእነዚህ ህመሞች የሚጠቅሙ የሜዲካል ቼክ አፕ አገልግሎት እና ቀጣይ
እርምታዊና ሙያዊ እገዛዎችን ጭምር በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡

ጥያቄ፡- እናመሰግናለን
ዶ/ርት፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.