በባዶ እግር የመሄድ ጠቀሜታዎች – በ መስከረም አያሌው

Closeup of a man’s bare feet walking at a beach at sunset, with a wave’s edge foaming gently beneath them, toned colors

ዘመን እና ስልጣኔ ከቀየሯቸው ነገሮች አንዱ የሰው ልጅ በባዶ እግር ከመጓዝ ተላቆ በጫማ መሄድ ነው። የሰው ልጅ ለእግሩ ጫማ ከማበጀት አንስቶ የተለያየ የጥራት ደረጃ ያላቸው እና የኑሮ ደረጃ መለኪያ የሆኑ መጫሚያዎችን እስከማማረጥ ደርሷል። በእኛ አስተሳሰብ ለእግሮቻችን መጫሚያዎችን በማበጀታችን እግሮቻችንን ከችግር እና ከአደጋዎች መጠበቃችንን እንደ ትልቅ ጠቀሜታ እንቆጥረዋለን። ነገር ግን በእግራችንና በምንረግጠው መሬት መካከል ጫማን በማጥለቃችን ልናገኛቸው የሚገቡ ነገር ግን ልናገኛቸው ያልቻልናቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውን አናስተውልም። ከአፈር፣ ከሣር እና ከአሸዋ የሚገኙ ተፈጥሮአዊ ነገሮች ደግሞ በባዶ እግር መሄድን ጠቃሚ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ተጠቃሾቹ ናቸው። በዘርፉ ምርምሮችን ያደረጉ ባለሙያዎች ግን በዚህ ድርጊት ብዙ ነገሮችን ማጣታችንን ደርሰንበታል ይላሉ። በጀማይካ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ተመራማሪዎችም በቅርቡ ባወጡት መረጃም ጠቀሜታውን ዘርዝረዋል።

በባዶ እግራችን በምንሄድበት ወቅት እግራችን በቀጥታ ከመሬት ጋር ንክኪ ስለሚኖረው በመሬት ውስጥ የሚገኙት አሉታዊ (ኔጋቲቭ) ኤሌክትሮኖች ወደ ሰውነታችን የመግባት እድል ያገኛሉ። እነዚህ አሉታዊ ኤሌክትሮኖችም በሰውነታችን ውስጥ የሚኖረው ባዮ ኤሌክትሪክ ሥርዓት የተመጣጠነ እንዲሆን ያግዘዋል። እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ፤ ያለ ምንም ተጨማሪ ነገሮች በየዕለት እንቅስቃሴያችን ውስጥ ለአምስት ደቂቃዎች በባዶ እግሮቻችን መሄድ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። በተለይ በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን የምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች ሁሉ ኤሌክትሮኒክሶች በመሆናቸው ይሄንን ነገር ማመጣጠን የምንችለው ከመሬት ጋር ቀጥተኛ ንክኪን በመፍጠር ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ። እየተገለገልንባቸው ያሉት እንደ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ላፕቶፕ፣ ቴሌቪዥን፣ የኤሌክትሪክ ማሞቂያዎች እና የተለያዩ ኮምፒውተሮች ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ (ፖዘቲቭ) ኤሌክትሮኖችን የሚያመነጩ ነገሮች ናቸው። ከእነዚህ ቁሳቁሶች የሚመነጩት ፖዘቲቭ ኤሌክትሮኖችን ወደ ሰውነታችን ውስጥ በመግባት ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት መቋቋም ያስችለን ዘንድም ኔጋቲቭ ኤሌክትሮኖችን ከመሬት ላይ በመውሰድ ሁለቱን ኤሌክትሮኖች እንድናመጣጥን ባለሙያዎቹ ይመክራሉ። ጠቅለል ባለ መልኩም በባዶ እግር መሄድ የሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች የሚከተሉት ናቸው።

እንቅልፍን ያስተካክላል

በሰውነታችን ውስጥ ያሉት ፖዘቲቭ ኤሌክትሮኖች በመሬት ላይ ካሉት ኔጋቲቭ ኤሌክትሮኖች ጋር በሚነካኩበት ወቅት ኔጌቲቭ ኤሌክትሮኖቹ ወደ ሰውነታችን ስለሚገቡ ቦታ ይለቅለታል። እነዚህ ኔጋቲቭ ኤሌክትሮኒክሶች ደግሞ በባህሪያቸው ሰውነት ዘና እንዲል ስለሚያደርጉ የተስተካከለ እንቅልፍ እንድንተኛ ያደርገናል። በሰውነት ውስጥ ለስርዓተ እንቅልፍ ጠቃሚ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የተስተካከሉ እንዲሆኑ በማድረግ በቂ እና ጥራት ያለው እንቅልፍን እንድንተኛ ያደርገናል።

በሽታ የመቋቋም አቅምን ይጨምራል

በአካባቢ እና ማኅበረሰብ ጤና ጆርናል ላይ ታትሞ የወጣው የዩኒቨርሲቲው የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው ደግሞ በባዶ እግራቸው የመሄድ ልማድ ያላቸው ሰዎች ሰውነታቸው በሽታን ለመቋቋም የሚያግዘውን ኃይል በቀላሉ ማዳበር ይችላሉ። ይሄም የሚሆነው እነዚህ ኔጋቲቭ ኤሌክትሮኖች በሰውነት ውስጥ የሚመረተው የነጭ ደም ሴሎች መጠን እንዲቀንስ በአንፃሩም የቀይ ደም ሴሎች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ነው። በመሆኑም እነዚህ ቀይ የደም ሴሎች ሰውነት በሽታን ለመቋቋም የሚኖረው አቅም እንዲዳብር ያግዙታል።

ለልብ ህመም መጋለጥን ይቀንሳል

ኔጋቲቭ ኤሌክትሮኖች በሰውነት ውስጥ የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥር እንዲጨምር የማድረግ ጠቀሜታ አላቸው። በመሆኑም ደም በደም ሥሮች ውስጥ እንዳይታጨቅ እና ከሚፈለገው መጠን በላይ ውፍረት እንዳይኖረው ለማድረግ ያግዛል። በመሆኑም ደም እንደልቡ ስለሚዘዋወር እና የሚፈለገውን ያህል የውፍረት መጠን እንዲኖረው ስለሚያደርገው ለልብ ህመም እና ለድንገተኛ የልብ መድከም መጋለጥን ይከላከላል።

የነርቭ ሥርዓትን ያስተካክላል፤ ጭንቀትን ይቀንሳል

በሰውነታችን ውስጥ ያሉት ፖዘቲቭ ኤሌክትሮኖች በመሬት ውስጥ ካሉት ኔጋቲቭ ኤሌክትሮኖች ጋር በቀጥታ በሚገናኙበት ወቅት በሰውነት ውስጥ ያለው ውጥረት እንዲቀንስ ያደርጉታል። በዚህ ጊዜ ሰውነት ያመነጫቸው የነበሩና ለጭንቀት አጋላጭ የሆኑ ሆርሞኖች እንዲወገዱ በማድረግ ሰውነት ለጭንቀት እና ለውጥረት እንዳይጋለጥ ያደርገዋል። እነዚህ የጭንቀት ፈጣሪ ሆርሞኖች ባለመመረታቸው በሰውነት ውስጥ የሚገኙ ነርቮች ሥርዓታቸው የተስተካከለ እና ተግባራቸውም በተለመደው መልኩ የሚከናወን እንዲሆን ያግዘዋል። በተጨማሪም ከጊዜ በኋላ የሚመጡ የጡንቻ መዛሎችን፣ ለረጅም ጊዜ በአንድ የስራ አይነት ላይ ከመቆየት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጡንቻ ድካሞችን እና መሸማቀቆችን ለመከላከል ከሚያግዙ ተፈጥሮአዊ ዘዴዎች አንዱ በባዶ እግር መሄድ ነው።

ራስ ምታትን ያስወግዳል

ከላይ እንደተጠቀሰው የሰውነት ፖዘቲቭ ኤሌክትሮኖች እና የመሬት ኔጋቲቭ ኤሌክትሮኖች በሚገናኙበት ወቅት ሰውነት የተመጣጠኑ ኤሌክትሮኖችን ያገኛል። በተጨማሪም እነዚህ ኔጋቲቭ ኤሌክትሮኖች በሰውነት ውስጥ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉትን ፍሪ ራዲካልስ አቅም የማዳከም አቅም አላቸው። በመሆኑም እንደ ማይግሪን ያሉ የራስምታት ችግር ተጠቂዎች በባዶ እግራቸው በሚሄዱበት ወቅት እነዚህን ፍሪ ራዲካልስ በቀላሉ ማስወገድ ስለሚችሉ ለራስ ምታት ያላቸውን ተጋላጭነት ለማስወገድ ያግዛቸዋል።

በወር አበባ ጊዜ የሚኖረውን ህመም ይቀንሳል

ኔጋቲቭ ኤሌክትሮን በሰውነት ውስጥ ያለውን የጭንቀት ስሜት የማስወገድ ባህሪይ ስላለው በወር አበባ ወቅት ያለውን ህመም ለማስታገስ ያገለግላል። ህመሙ የሚጀምረው በአንጐል ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ጭንቀትና ተያያዥ ተፅዕኖዎችን በማስወገድ በዚህ ወቅት ያለው የህመም ስሜት እንዲቀንስ ያደርገዋል።

የተስተካከለ አጠቃላይ ቅርፅ እንዲኖር ያደርጋል

በእግሮቻችን ጫፎች ላይ ስሜት ተቀባዮች እና የነርቭ ጫፎች አሉ። እነዚህ የሰውነት ክፍሎች በጫማ ውስጥ በሚቀመጡበት ወቅት እንደልባቸው ዘና ለማለት እና በተመቻቸ መልኩ ለመንቀሳቀስ ያቅታቸዋል። በተጨማሪም እግር መስራት ያለበትን ነገር ጫማው እንዲሰራ ስለምናደርገው እግራችን መያዝ የሚገባውን ጥንካሬ እና ቅርፅ እንዳይዝ ያደርገዋል። እግራችን የተስተካከለ ቅርፅ እንዳይኖረው ሆነ ማለት ደግሞ ለጀርባ ህመም፣ ለአንገት ህመም እንዲሁም ለጉልበት ህመም የመጋለጥ እድላችን እንዲጨምር ያደርገዋል። እነዚህ ሁሉ ተደማምረውም ሰውነት የተስተካከለ ቅርፅ እንዳይኖረው ያደርገዋል። ነገር ግን በእግራችን በምንሄድበት ወቅት እግር ተፈጥሮ በሰራው መልኩ እንቅስቃሴዎችን ስለሚያከናውን ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንዳይከሰቱ በማድረግ የሰውነት ቅርፅ እንዲስተካከል ያደርገዋል።

 

በቀን ውስጥ ለአምስት ደቂቃዎች በባዶ እግር በመሄድ ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህልም የደም ግፊትን ለማስተካከል እና የደም ዝውውርን ለማስተካከል፣ ስር ለሰደዱ ህመሞች ያለውን ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ ለሰውነት መመርቀዝ ያለውን ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ የኩላሊት እና ተያያዥ ጤንነትን ለመጠበቅ እንዲሁም ማንኮራፋትን ለመከላከል ያግዛል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.