በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትና ኤችአይቪ/ኤድስ

 

በዚህ ሰሞን ከሚከበሩ ቀናት ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚያሳስበው የ16 ቀን ዘመቻና የዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን ይገኙበታል፡፡

Printየሁለቱ የመታሰቢያ ጊዜ ከመቀራረብ ባለፈ ሁለቱን የሚያገናኛቸው ነገር አለ፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ኤድስን በሚመለከተው አካል (UNAIDS) በ2010 የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ኤችአይቪ በተለየ ሴቶችን የሚያጠቃ መሆኑን ነው፡፡ ከ24.5 ሚሊዮን ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ካለባቸው ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ያሉ ከሰሐራ በታች የአፍሪካ አገሮች 59 በመቶ (13.2 ሚሊዮን) የሚሆነው አኀዝ ሴቶች ናቸው፡፡ የጾታ ሚዛን ማጣቱ በተለይ ከ15 እስከ 24 በሚሆነው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚጨምር ሲሆን፣ 74 በመቶ ሴቶች ናቸው፡፡ በአገራችንም ሰፋ ያለ ጥናት ባይገኝም እ.ኤ.አ. በ2005 በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ስርጭት 2.4 በመቶ የደረሰ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን፣ ይህ መጠን በሴቶች በ2.9 በመቶ ይጨምራል፡፡

ለሴቶች በኤችአይቪ የበለጠ ተጠቂ መሆን የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቀሱም፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃትና ኤችአይቪ ያላቸው የሁለትዮሽ ቁርኝት በሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችም ሆነ በጤና ባለሙያዎች ተጠቃሽ ወሳኝ ምክንያት መሆኑ አልቀረም፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሴቶችን በኤችአይቪ የመያዝ አጋጣሚ የሚጨመር ሲሆን፣ በተቃራኒውም ሴቶች ከኤችአይቪ ጋር አብረው መኖራቸው ከወንዶች በተለየ ለጾታዊ ጥቃት እንደሚያጋልጣቸው ይታመናል፡፡ በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ የሁለቱን ግንኙነት በመቃኘት ሴቶችን ለኤችአይቪ የሚያጋልጡ ጥቃቶችንና በሕግ ሴቶች ያላቸውን ጥበቃ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ምልከታ

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማንኛውም ዓይነት መድሎን ለማስወገድ የተፈረመው ስምምነት (CEDAW) በአንቀጽ 1 በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት (Gender Based Violence) ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ የሚፈጸሙባቸው ወይም ከኅብረተሰቡ ሴቶችን በተለየ የሚመለከት ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡ ጥቃቱ አካላዊ፣ አእምሮዓዊና ወሲባዊ ጥቃትን የሚያጠቃልል ሲሆን ሴቶችን የሚያስፈራራ፣ የሚያስገድድና ነፃነታቸውን የሚነፍግ ድርጊት ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1993 በተባበሩት መንግሥታት የተዘጋጀው መግለጫ (The UN Declaration on the Elimination of Violence Against Women) በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በዝርዝር ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ መግለጫው ጥቃቱ የሚከተሉትን እንደሚጨምር ይገልጻል፡፡

(a)    Physical, sexual, psychological violence occurring in the family, including battering, sexual abuse of female children in the household, dowry related violence, marital rape, female genital mutilation and other traditional practices harmful to women, non-spousal violence and violence related to exploitation.
(b)    Physical, sexual and psychological violence occurring within the general community, including rape, sexual abuse, sexual harassment and intimidation at work, in educational institutions and elsewhere, trafficking in women and forced prostitution.

በዚህ መግለጫ መሠረት ማንኛውም አካላዊ፣ ወሲባዊና ሥነ ልቦናዊ በቤተሰብና በማኅበረሰብ የሚፈጸም መደፈር፣ መደብደብ፣ መጠለፍ፣ መገረዝ፣ ወሲባዊ ትንኮሳ ወዘተ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሊባል ይችላል፡፡

በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትና ኤችአይቪ/ኤድስ ያላቸው ቁርኝት በተባበሩት መንግሥታት በጥሞና የታየው እ.ኤ.አ. በ2001 ነው፡፡ በዚህ ጉባዔ የሴቶችን እኩልነት ማረጋገጥና በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ የሴቶችን የኤችአይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት እንደሚቀንስ ታምኗል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሰብዓዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች ትርጉም ባለው መልኩ መረጋገጥ የኤችአይቪ/ኤድስን አደጋ ለማስወገድ ቀዳሚ ዓለም አቀፋዊ መልስ ነው፡፡ ከዚህ ጉባዔ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት (UNHCHR and UNAIDS) እ.ኤ.አ. በ2006 የሴቶች ሰብዓዊ መብቶችና የኤችአይቪ አደጋ ያላቸውን ግንኙነት የሚዘረዝር መመርያ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ መመርያ እንደተገለጸው የሴቶች በቤት ውስጥና በኅብረተሰቡ የሚሰጣቸው የዝቅተኛነት ቦታ በሽታው በሴቶች ላይ በፍጥነት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 በUNAIDS የወጣው ሪፖርት የሴቶች እኩል አለመሆንና ኤችአይቪ/ኤድስ ያላቸውን ቁርኝት በአጽንኦት ገልጿል፡፡ ይህንኑ ሪፖርቱ ሲገልጽ እንዲህ ብሎታል፡፡

“The increased vulnerability of women and girls to HIV infection stems from biology and social, economic, legal and cultural factors such as entrenched gender roles, unbalanced power relations, disproportionate burden of AIDS related care and the occurrence and societies’ acceptance of, violence against women, including sexual coercion”

በዚህም የሴቶችና የልጃገረዶች ለኤችአይቪ ያላቸው ተጋላጭነት ከተፈጥሮና ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከሕጋዊና ከባህላዊ ምክንያቶች እንደሚመነጭ ዓለም አቀፋዊ መግባባት መኖሩን አሳይቷል፡፡ በተለይ ሴቶች በጾታቸው ምክንያት የሚሰጣቸው ድርሻ፣ የተዛባ የቤተሰብ የሥልጣን ግንኙነት፣ ኤድስን የመሰሉ በሽታዎችን የመንከባከብ ግዴታ በብዛት ሴቶች ላይ መጣሉና ጾታዊ ጥቃት ተጋላጭነታቸውን አስፍቶታል፡፡

ጾታዊ ጥቃት ተጋላጭነትን እንደሚጨምር

ከላይ የተገለጹትን ነጥቦች በስፋት ለማብራራት እንሞክር፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የሴቶችን የኤችአይቪ ተጋላጭነት ይጨምራሉ፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የተፈጥሮዓዊ ቀጥተኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሴቶች በተፈጥሮ የሥነ ተዋልዶ አካሎቻቸው ከወንዶች በበለጠ ለበሽታው እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡ የሴቶች የመራቢያ አካል በግንኙነት ጊዜ ለቫይረሱ የተጋለጠ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ስለመሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች በዝርዝር ያትታሉ፡፡ ቫይረሱ ባለበት ሰው የሚፈጸም የመደፈር አጋጣሚ ደግሞ የበለጠ ሴቶችን ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌላው ምክንያት ማኅበራዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የሴቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ከወንዶች ጋር በእኩልነት አለመታየት (Gender Inequality) እና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጠቃሽ ማኅበራዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ጥናቶች ሴቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ተገቢው የእኩልነት ቦታ የማይሰጣቸው መሆኑ የበሽታው ተጠቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በUNAIDS እ.ኤ.አ. በ2008 የወጣው ሪፖርትም ወሲባዊ ጥቃት ሴቶችን ከወንዶች በሦስት እጥፍ ተጠቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ሪፖርቱ የአፍሪካን አገሮች መነሻ በማድረግ ባሰፈረው መደምደሚያ፣ “In several African countries like Tanzania, Rwanda, and South Africa, the risk of HIV among women who have experienced gender based violence may be upto three times higher than among other women” በማለት ገልጿታል፡፡

በህንድ የተደረገ ጥናትም በትዳር ውሰጥ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሴቶች ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡ የዓለም አቀፍ ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር የሚኖሩ ማኅበረሰብ (ICW) በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትና ኤችአይቪ ያላቸውን ቁርኝት በጥናት አረጋግጧል፡፡ በጥናቱ መሠረት በልጃገረዶች ላይ የሚፈጸም ድብደባና መደፈር ኤችአይቪን ያሰራጫል፤ ጥቃቱም ሴቶች ጉዳዩን በግልጽ እንዳይወያዩ አድርጓል፤ ስለ ኤችአይቪ የሚነገሩ መላምቶችም በሽታውን አስፋፍተውታል፡፡ ለምሳሌ ከልጃገረዶች ጋር ግንኙነት መፈጸም ኤችአይቪን ያስወግዳል በሚል ብዙ ሴቶች እንደሚደፈሩ ጥናቱ ገልጿል፡፡ ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ከተፈጥሮዓዊ ምክንያቱ በበለጠ ሴቶችን ለበሽታው የሚያጋልጠው በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መሆናቸውን ነው፡፡

በአገራችን ተጠቃሽ ጥቃቶች

በአገራችን በስፋት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለኤችአይቪ ሴቶችን ተጋላጭ ያደርጉዋቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የተወሰኑትን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ቀዳሚው ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሲሆን፣ በብዙ የአገራችን ክፍል በስፋት የሚፈጸም ጥቃት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በተዘጋጀ ማኑዋል እንደተገለጸው፣ ከ15 አስከ 24 ዕድሜ ባላቸው ወጣቶች ውስጥ የሴቶች ለበሽታው ተጋላጭነት 10 በመቶ ሲሆን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ በተንሰራፋበት የአማራ ክልል እርጉዝ የሆኑ ሴቶች የኤችአይቪ ተጠቂነት እንደሚጨምር ተገልጿል። የመደፈር ወንጀልና የቤት ውስጥ ጥቃትም በብዛት የሚስተዋልና ለበሽታው ምክንያት የሆኑ ጥቃቶች ናቸው፡፡ በባህል መነሻነት የሚፈጸሙ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የውርስ ጋብቻ፣ ብዙ የማግባት ሥርዓትም በአገራችን የሴቶችን ለኤችአይቪ ተጋላጭነት የሚጨምሩ ናቸው፡፡ ግርዛት በስፋት መገኘቱ፣ ገራዦቹ በአንድ መሣሪያ ብዙ እንስትን የመግረዝ ልማዳቸው፣ ኤችአይቪ በደሙ ውስጥ ያለበትን የቅርብ ዘመድ ሳይቀር በጋብቻ የመውረስ ባህል፣ ብዙ ሚስት ባገቡ ወንዶች ያለጥንቃቄ የሚደረግ ግንኙነት ወዘተ. በአገራችን ሊጠቀሱ የሚችሉ የሴቶችን ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሚያደርጉ ጥቃቶች ናቸው፡፡ ሴቶች ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው መኖሩ ከተረጋገጠም በኋላ ለጥቃት እንደሚጋለጡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሴቶች በኅብረተሰቡ ይገለላሉ፣ በሽታውን ያመጡ ናቸው በሚል ውግዘት ይደርስባቸዋል፣ በቤተሰብ አባላት ይደበደባሉ፣ ይሰደባሉ፣ ንብረትም እንዳይወርሱ የሚደረጉም አሉ፡፡

የአገራችን የሕግ ማዕቀፍ

አገራችን የሴቶችን መብት ለማክበር፣ ለመጠበቅና ለማሟላት ዓለም አቀፋዊና ብሔራዊ ግዴታ አለባት፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን የሴቶችን መብቶች ዕውቅና የሚሰጡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን ፈርማለች፡፡ ሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ፣ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ቃልኪዳን ስምምነትና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማንኛውም ዓይነት መድልኦ ለማስወገድ የተደረገው ስምምነት በአገራችን ተፈርሟል፡፡ በእነዚህ ሰነዶች የሴቶች የእኩልነት፣ የአካል ደኅንነት፣ የጤንነት፣ በሕይወት የመኖር፣ የነፃነት፣ የጋብቻ ወዘተ. መብቶች የተረጋገጡ በመሆኑ ሴቶችን ከጥቃትና ጥቃቱ ከሚያስከትለው ኤችአይቪ ለመከላከል ጠቃሚ የሕግ መሠረት ይጥላሉ፡፡

ብሔራዊ ሕግጋትንም በተመለከተ መንግሥት ላይ ግዴታ የሚጥሉ ሕግጋት በአገራችን አሉ፡፡ ቀዳሚው ሕገ መንግሥቱ ሲሆን ይህ ሰነድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን የአገሪቱ ሕግ አካል ከማድረግ ባለፈ ለሴቶች ዝርዝር የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ቀርጿል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35 የሴቶችን የእኩልነት መብት ዋስትና የሰጠ ሲሆን ሴቶችን ለጥቃት የሚያጋልጡ ልማዳዊ ድርጊቶች ተፈጻሚ እንደማይሆኑ፤ መንግሥትም ሴቶችን ለጥቃት ከሚያጋልጡ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ይገልጻል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ለማናቸውም ሰው የተጠበቁለት የአካል ደኅንነት፣ በሕይወት የመኖር፣ የነፃነት፣ የእኩልነት ወዘተ. መብቶች ለሴቶችም ተፈጻሚ ስለሚሆኑ ሴቶችን መታደጋቸው አይቀርም፡፡

ከሕገ መንግሥቱ በተጨማሪ ሌሎች ዝርዝር ሕግጋትም ሴቶችን ለኤችአይቪ ተጋላጭ ከሚያደርጋቸው ጥቃት የሚከላከሉ ድንጋጌዎች አሉዋቸው፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሹ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 514 ማንም ሰው አስቦ በሰው ላይ ተላላፊ በሽታ ያሰራጨ ወይም ያስተላለፈ እንደሆነ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል ግን በጥላቻ፣ በቂመኝነት፣ በክፋት ወይም በወራዳነት መንፈስ ወይም እነዚህ ሐሳብ ባይኖሩበትም በሌላ ሰው ላይ ከባድ ጉዳትን ወይም ሞትን የሚያስከትል በሽታ ያሰራጨ ወይም ያስተላለፈ እንደሆነ ከሃያ ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት፣ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል፡፡

የወንጀል ሕጉ በሌሎች ድንጋጌዎችም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በወንጀልነት በመፈረጅ ከፍ ያለ ቅጣት ደንግጓል፡፡ ለአብነት የተወሰኑትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ታስቦ የሚፈጸም ከባድ የአካል ጉዳት (555)፣ የእጅ እልፊት (560)፣ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች (561-570) በተለይ በትዳር ጓደኛ ላይ ጥቃት ማድረስ (564)፣ ሴትን መግረዝ (565)፣ ሴትን መጥለፍ (587)፣ አስገድዶ መድፈር (620)፣ አስገድዶ መድፈር በሽታው እንዳለበት አውቆ በፈጸመው ላይ እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ (628)

ከወንጀል ሕጉ ሌላ የቤተሰብ ሕጉም ሴቶችን ከጥቃት የሚከላከሉ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡ በቤተሰብ ሕጉ፣ የጋብቻ ዕድሜ 18 ሆኖ የተወሰነ ሲሆን ሴቶችም ያለፈቃዳቸው ወደ ጋብቻ እንደማይገቡ፣ ከገቡም ጋብቻውም እንደሚፈርስ ተደንግጓል፡፡

እንደማጠቃለያ

በዚህ ጽሑፍ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ኤችአይቪ/ኤድስ ያላቸውን ቁርኝነት ተመልክተናል፡፡ ጥቃቶቹ ሴቶችን ለኤችአይቪ እንደሚያጋልጡና ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሴቶችም  የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው መገንዘብ እንችላለን፡፡ አገራችን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈረም፣ በሕገ መንግሥቷም በሚካተትና ዝርዝር ሕግጋትንም በማውጣት ሴቶችን ከጥቃትና ከኤችአይቪ/ኤድስ ለመታደግ ቁርጠኝነት ብታሳይም አታገባበሩ አመርቂ አይደለም፡፡ በአፈጻጸም ሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት እንደሚደርስባቸው፣ እንደሚደፈሩ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መድልኦ አሁንም በሴቶች ላይ እንደሚፈጸሙ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ በፍጥነት መስፋፋትም ሴቶችን እየጎዳ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አብዛኛው ሴት በተለይ በገጠር አካባቢ የሥነ ተዋልዶ መብት ተጠቃሚ ባለመሆናቸው የእናቶችና የሴቶች ሞት በብዛት ይታያል፡፡

የሴቶችን መብቶች የማስፈጸም ግዴታ በዋናነት የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት የሴቶችን ጥቃት ቸል የሚል ከሆነ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል ካለማስተዳደር ጋር እኩል ነው፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በሕይወታቸውና በጤንነታቸው ሰፊ ጉዳት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ ጥቃቱ ሲፈጸም በፍርድ ቤት መፍትሔ ለማግኘት የማስረጃ ችግር መኖሩም አሌ የማይባል ነው፡፡ ይህን ክፍተት ለመሙላት መንግሥት በሴቶች ስም የሚኒስቴር መሥርያ ቤት ያቋቋመውን ያህል ለሴቶች ሁለንተናዊ ጥቅም ‘የኢትዮጵያ ሴቶች ሆስፒታል’ ቢያቋቁም ምን ይለዋል፡፡

ሆስፒታሉ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ሕክምና ይሰጣል፤ ለፍርድ ቤት የሚረዳ ጠቃሚ ማስረጃ በወቅቱ ያዘጋጃል፤ ሴቶች የሥነ ተዋልዶ መብቶች ተጠቃሚ ይሆኑበታል፤ የሥነ ልቦናም ምክር ያገኙበታል፡፡ በኬንያ የናይሮቢ የሴቶች ሆስፒታል በሴቶች ጩኸት፣ በመንግሥታቸው ፖለቲካ ቁርጠኝነት ተቋቁሞ የሴቶችን ጥቃት በመቀነስ ረገድ ሰፊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ መልካም አርዓያነታቸውን ብንከተል ምን ይለናል? የሴቶች ጥቃት አሁን ባለው መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ግን ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡን የሚጎዳ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭቱም መስፋቱን አይቀንስም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.