diaper-rashበሽንት ጨርቅ ምክንያት የሚመጣ ሽፍታ (Diaper rash) በማንኛውም በሽንት ጨርቅ በተሸፈነ ቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ነው፡፡ይኼ ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ የሚችል ቢሆንም አብዛኛውን ግዜ የተለመደው ምክንያት ግን በሽንት እና በሰገራ የቆሸሸ የሽንት ጨርቅ ከቆዳ ጋር የሚኖረው ፍትግትግ ነው፡፡

ይህ የቆዳ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ በህጻናት ላይ የሚወጣ ተደርጎ ቢታሰብም ማንኛውም ሽንት ጨርቅ (ዳይፐር)ተጠቃሚ ሰውን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ብዙውን ጊዜ ከ9 እስከ 12 ወር እድሜ ያላቸውን ህፃናት ቢያጠቃም እስከ አንድ ሳምንት እድሜ ያላቸውን ህፃናትን እንኳ ሊያጠቃ ይችላል፡፡

በሽንት ጨርቅ ምክንያት የሚመጣ ሽፍታን የሚያመጡ የተለመዱ ነገሮች ምንድ ን ናቸው?

ይህንን በሽታን የሚያመጡ ምክንያቶችን በተለያዩ ምድቦች እንመድባቸዋለን፡፡ የመጀመሪያውና በአብዛኛው የሚታየው የሽንት ጨርቅ ከቆዳ ጋር በሚኖረው ፍትግትግ ይከሰታል፡፡ሽንት ጨርቅ ብቻ ሳይሆን ምንም አይነት በሽንት እና በሰገራ የቆሸሸ ጨርቅ ይህን ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ልጅሽ በቆሸሸ ሽንት ጨርቅ ተጠቅልሎ የሚቆይበት ጊዜ በጨመረ ቁጥር ለዚህ ችግረ የመጋለጥ እድሉም እየጨመረ ይኼዳል፡፡የልጅሽ ቆዳ በቀላሉ ከመቅላት ጀምሮ እስከመላላጥ እና መቁሰል ሊደርስ ይችላል፡፡ ከሌሎቹ በተለየ በዚህ ምክንያት የሚመጣ የቆዳ ችግር በሚታጠፉ የቆዳ ክፍሎች ወይም ለሽንት ጨርቁ ቀጥተኛ ተጋላጭነት በሌላቸው ክፍሎች አይታይም፡፡

በመቀጠል ደግሞ የቆዳ ኢንፌክሽኖች ይገኛሉ፡፡ ባክቴሪያና ፈንገስ በመጀመሪያው መደዳ ይመደባሉ፡፡ልጆች የሚጠቁት በሽታ የመከላከል ሀይላቸው ሲቀንስ ሲሆን በሽታዎቹ የተለያየ መገለጫ አላቸው፡፡ በሽንት ጨርቅ የተሸፈነውን አካባቢ ላይ በባክቴሪያ ምክንያት ኢንፈክሽን ሲኖር ቆዳ ላይ አበጥ አበጥ ብለው በውሀ መሰል ፈሳሽ ወይም በመግል የሚሞሉ ትንንሽ(1-2ሚ.ሜ) እብጠቶች በየቦታው ይታያሉ፡፡ አንዳንዴም ይፈነዱና ይቆስላሉ፡፡

በፈንገስ የሚመጣው ደግሞ የራሱ የሆነ ምልክት አለው፡፡ ቂጣቸው እና ሌላም በሽንት ጨርቁ የሚሸፈን አካላቸው በጣም ቀይ ሆኖ ጥግ ጥጉን እራሳቸውን በቻሉ ሌሎች አነስ ያሉ ቀይ ቦታዎች ይከበባል፡፡ ከጨርቅ ጋር ባለው ፍትግትግ ከሚመጣው ሽፍታ ጋር ቢመሳሰልም በታጠፉ ቆዳዎች መካከል መገኘቱ እንዲሁም በፊንጢንጣ ዙሪያ መገኘቱ ይለያቸዋል፡፡ በኢንፌክሽን የሚመጣው ሽፍታ ባለሙያዎች በአይን አይተው ቢለይዋቸውም ካስፈለገ ደግሞ ከላያቸው ላይ የተወሰደ ናሙናን በላብራቶሪ ማጣራት ይቻላል፡፡

ምንም እንኳን በጣም ጥቂት ቢሆኑም በአለርጂ ምክንያት የሚመጡም አሉ፡፡ ልጅዎት ለተለያዩ ነገሮች አለርጂክ ሊሆን ይችላል፡፡ ቅባቶች፣ የሚጠቀሙት ሽንት ጨርቅ (ዳይፐር)፣ ሶፍት፣ሽቶ የመሳሰሉት የተለመዱ ናቸው፡፡ አለርጂክ የሆኑት ነገር የሚነካቸው ቦታ ላይ መቅላት፣ በውሀ መሰል ፈሳሽ የተሞላ እብጠት እንዲሁም መቁሰል ሊኖር ይችላል፡፡

መድሃኒቱ ምንድን ነው?

ልጅሽ ሽፍታ ከታየበት በለስላሳ ጨርቅ እና ንፁህ ውሃ እጠቢው፡፡ ይሄ በሽታውን ከማዳን ይልቅ ለልጅሽ ከማቃጠሉ እና ከማሳከኩ ስሜት እረፍት ይሰጣል፡፡ ቫስሊን መቀባት (አለርጂ ካልሆነ) ከሽንት ጨርቅ ጋር የሚኖረውን ፍትግትግ ስለሚቀንስ ህመሙን ይቀንሳል፡፡ ከዛ ባለፈም ልጅሽን ሽንት ጨርቅ ሳታለብሺ ቆዳው አየር እንዲያገኝ ማድረጉ በጣም ቀላሉ እና ተመራጩ መንገድ ነው፡፡

እነዚህ መንገዶች በሁለት ወይም ሶስት ቀን ልጅሽን ካላዳኑ ሽፍታው በኢንፌክሽን ምክንያት የመሆኑ እድል ከፍተኛ ነው እና ሀኪም ጋር መሄድ ተገቢ ነው፡፡ መድሃኒቶቹም በቀላሉ የሚገኙ እና ሙሉ በሙሉ የሚያድኑ ስለሆኑ ብዙም አትጨነቂ፡፡ በአለርጂ የመጣ ከሆነ ደግሞ አለርጂክ የሆነበትን ነገር ከመጠቀም መቆጠብ አለብሽ፡፡

መከላከያ መንገዶቹ ምንድን ናቸው?

በመጀመሪያ ልጆት ሳይታመም በፊት በሽታውን መከላከል ወሳኝነት አለው፡፡ ሽንት ጨርቁን ቶሎ ቶሎ መቀየር ሽንት እና ሰገራ ከቆዳ ጋር ያላቸውን ንክኪ ስለሚቀንስ ፍትግትጉን ይቀንሳል፡፡ በዚህን ጊዜ ባክቴሪያ ወይም ፈንገስ ቆዳቸው ውስጥ የሚገቡበት ዘዴ ስለሌለ በኢንፌክሸን የሚመጣውን አይነት ሽፍታንም የመከላከል አቅም አለው፡፡ ከዚህ ባለፈ አንዳንዴ ሽንት ጨርቅ ሳያደርጉ ቆዳቸውን ማናፈስ እና በንፁህ ውሃ ማጠብ ሽፍታን የመከላከል ብቃት አላቸው፡፡

ኪንታሮት

ኪንታሮት ምንድን ነው?

ኪንታሮት የሚለውን ቃል ለብዙ አይነት በቆዳ ላየ ለሚታዩ ቁስሎችን ለመግለፅ እንጠቀማለን፡፡ አሁን ግን ለማውራት የፈለግነው በአብዛኛውን ጊዜ በህፃናት ላይ ስለሚታየው የቆዳ ችግር ነው፡፡ ኪንታሮት ፖክስ ቫይረስ (pox virus, molluscum contagiosum) በሚባል ቫይረስ የሚመጣ የቆዳ በሽታ ነው፡፡ በዛ ብለው የተበታተኑ ትንንሽ የቆዳ ቀለም ያላቸውና መሃላቸው ላይ ወደ ውስጥ ገባ የሚሉ በቆዳ ላይ የሚወጡ እብጠቶች ይፈጥራል፡፡

ኪንታሮት አንድ ብቻ ሆኖ ወይም በብዛት ሊወጣ ይችላል፡፡ ኪንታሮት ፊት፣አንገት፣ እጅ፣ እግር፣ ደረት እና የመሳሰሉየቆዳ ክፍሎች ላይ ይወጣል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በውስጥ እጆች እና እግሮች ላይ አይወጣም፡፡ ምንም እንኳ በሁሉም አካል ላይ የሚወጣ ቢሆንም የመከላከያ አቅም ያነሰበት ሰው ላይ ካልሆነ በስተቀር በአንድ ጊዜ ሁሉንም ሰውነት አያጠቃም፡፡ ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን የሚያጠቃው ይሄ በሽታ በቆዳ ላይ ከሚታይ እብጠት በተጨማሪ ሊያሳክክ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌሎች የውስጥ አካላቶችን አያጠቃም፡፡

ከአንድ የአካል ክፍል ወደ ሌላ መተላለፍ ይችላል፡፡ በጣም በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል፡፡ በቆዳ ንክኪ፣ ፎጣዎችን እና ልብስ አብሮ በመጠቀም፣ የመታጠቢያ እቅዎችን በመጠቀም፣ የዋና ቦታ እና በመሳሰሉት ቀላል ንክኪዎች ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ምንም እንኳን ሲታይ ደስ ባይልም ምንም የከፋ ችግር አያስከትልም፡፡

ኪንታሮት ህፃናት ላይ ለምን ይወጣል?

በጎልማሳ ሰዎች ላይ በሽታን የመከላከል አቅማቸው ሲቀንስ የሚወጣ ቢሆንም ጤናማ ህፃናት ላይ ግን ይወጣል፡፡ የህፃናት የበሽታ የመከላከል አቅማቸው ገና በደንብ ስላላደገ እንደዚህ አይነት በሽታ ያጠቃቸዋል፡፡ በህፃናት መቆያ የሚውሉ ህፃናት ላይ በብዛት ይታያል፡፡ በነዚህ መቆያዎች ብዙ ህፃናት ስለሚኖሩ ልጆቾ የኪንታሮት በሽታ ካለባቸው ህፃናቶች ጋር የመገናኘት አቅማቸው ይጨምራል፡፡

የኪንታሮት መድሃኒት ምንድን ነው?

ኪንታሮት ከወራት እስከ አመታት ቆይቶ በራሱ ጊዜ ይጠፋል፡፡ አሊያም ሆስፒታሎች ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ሊጠፋ ይችላል፡፡ በብዛት የምንጠቀመው መንገድ ግን በፈሳሽ ናይትሮጅ ማቀዝቀዝ ወይም ማቃጠል (Cryotherapy) ነው፡፡

ኪንታሮትን መከላከያ መንገዶች

ዋናውና የመከላከያ መንገድ ንፅህናን መጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኪንታሮት ካላቸው ሰዎች እና ልጆች ጋር ያላቸውን ንክኪ መቀነስ ሞክሩ፡፡ ሌሎቹን የኪንታሮት መተላለፊያ መንገዶች ለምሳሌ ፎጣ አብሮ መጠቀምን መተው አለባችሁ፡፡.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here