marriage  የሰርግ ወቅት ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ኩለው የሚድሩበት፣ ጥንዶች የሚሞሸሩበትና ሆቴሎች፣ መናፈሻዎችና መንገዶች በሙሽሮች የሚጨናነቁበት የሰርግ ወቅት፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ተጋቢዎቹ እርስ በርሳቸው ተዋውቀው፣ በጓደኝነት ቆይተውና ጉዳያቸውን ሁሉ በውጪ ጨርሰው ለጋብቻ የሚበቁበት ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት፣ ጥንዶች ጋብቻቸውን የሚፈፅሙት በቤተሰብ ይሁንታና ፈቃድ ነበር፡፡ ሴት ልጅ ለጋብቻ የምትታጨውና የምትመረጠው ባህርይዋ ታይቶም ጭምር ነበር – አንገቷን የደፋች ጨዋ መሆኗ ተመርምሮ፤ ይህንን ጨዋነቷን የምታረጋግጠው ደግሞ ህጓንና ክብሯን ጠብቃ በመገኘት ነው፡፡ ክብረ ንፅህናን እስከ ጋብቻ ዕለት ድረስ ጠብቆ አለማቆየት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እጅግ ነውር ተግባር ተደርጐ ነበር የሚቆጠረው፡፡ በሰርግ ዕለት በሴቷም ሆነ በወንዱ ቤተሰቦች ዘንድ እጅግ በጉጉት ከሚጠበቁት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሙሽራዋ ጨዋነት የሚበሰርበት የጫጉላ ምሽት ነው፡፡ እስቲ አምጣው የደሙን ሸማ እስኪ አምጣው የደሙን ሸማ  እንድንስማማ  ተብሎ የሚቀነቀነውም ለዚሁ ነው፡፡ ይህ የሙሽራዋ ጨዋነት ማረጋገጫ ሰነድ ከሁለቱ ጥንዶች በበለጠ የወላጆችና የቤተሰብ የኩራት ምንጭ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ 
ይኼኛው ከዘመን ጋር እየተቀየረ ሄዶ፣ ጥንዶቹ በራሳቸው ፍላጎትና ምርጫ እየተዋወቁ በመግባባት ጋብቻቸውን በፍቃዳቸው መፈፀም ጀመሩ፡፡ ወላጆችም ለጥንዶቹ ጋብቻ ይሁንታ እንዲሰጡ ጊዜው አስገደዳቸው፡፡   ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ አዲስ ተጋቢዎች ወደ ጋብቻ ሰተት ብለው ከመግባታቸው በፊት የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ የሚገደዱበት ሁኔታ ተከሰተ – የኤችአይቪ/ኤድስ መስፋፋትን ተከትሎ፡፡ 
ወንዱ ልቡ የፈቀዳትን ሴት ለማግባት ወደቤተሰቦቿ ዘንድ አማላጅ ሲልክ የመጀመርያው ጥያቄ፣ ከኤችአይቪ ነፃ መሆኑን የሚያረጋግጥ የሃኪም ማስረጃ አቅርብ የሚል ሆነ፡፡ 
በእርግጥ ይሄኛው ከሙሽራዋ የጨዋነት ማረጋገጫ ጋር ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ ይሄኛው ለጋራ ደህንነት የሚወሰድ ቅድመጥንቃቄ ነው፡፡  ምናልባት የሰርግ ዘፈኖቻችንም  እስኪ አምጣው የደሙን ስሪንጅ  እስኪ አምጣው የደሙን ስሪንጅ  ትዳር ላደራጅ ወደሚሉ ተቀይረው ይሆናል፡፡ 
በአሁኑ ወቅት ግን ጋብቻ ለመፈፀም የኤችአይቪ ምርመራ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የትዳር ህይወት ሊታደጉ የሚችሉ የተለያዩ የጤና ምርመራዎች አሉ፡፡ 
የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አከበረኝ ወርቁ በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን ጠቅሰው እንደሚናገሩት፤ ጋብቻ ለመፈፀም ያቀዱ ጥንዶች ከመጋባታቸው በፊት ማድረግ የሚገባቸው የጤና ምርመራዎች በሁለቱ ተጋቢዎች የወደፊት ህይወት ላይ እጅግ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ በጥንዶች መሀል የተጀመረውን ትዳር በማፍረስ ረገድም እነዚህ ችግሮች ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ጥንዶች ከጋብቻቸው በፊት ሊፈፅሟቸው የሚገቡ የጤና ምርመራዎች መካከል በግብረስጋ ግንኙነት ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች፤ የሔፒታይተስ ቢ እና ሲ ቫይረስ፣ የደም ካንሰርን የሚያመጡ (ሒውማን ቲ ሴል ሊውኮትሮፒክ ቫይረስ)፣ የደም ዓይነት (Blood Type or RH factor) እና በዘር ቅልቅል ወቅት ወደ ልጁ ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ጥንዶቹ ከመጋባታቸው በፊት መመርመር ያለባቸው የጤና ችግሮችን አለመመርመር ጥንዶቹ ወደፊት የሚወልዷቸውን ልጆች በዘር ውርስ ለሚተላለፉ የልብ፣ የካንሰር፣ የስኳር በሽታዎችና መሰል ችግሮች ተጋላጭ ያደርጓቸዋል፡፡ ስለዚህም ጥንዶቹ ከጋብቻቸው ምስረታ በፊት የሚያደርጉት የጤና ምርመራ ጠቀሜታው ለሁለቱ ጥንዶች ብቻ ሳይሆን በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩትም ህፃናት ጭምር ነው፡፡ የሁለቱ ጥንዶች ጥምረት ከዘርመል እና አፈጣጠር አኳያ የተለያየና በልዩ ልዩ ህክምናዎች ሊስተካከል የሚችል ከሆነ ጥንዶቹ አብሮነታቸውን መቀጠል እንደሚችሉ የሚናገሩት ዶ/ሩ፤ ለዚህም እንደምሳሌ የሚያነሱት የደም ዓይነት ልዩነት (Blood Type Factors RH-or RH+መሆንን) ነው፡፡ ይህ ችግር የጤና ችግር ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ባይሆንም የሁለቱ ጥንዶች የደም አይነት መለያየት፣ ጥንዶቹ በትዳር ህይወታቸው የመውለድ ፀጋን እንዳያጣጥሙ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡  ችግሩ በህክምና እርዳታ ሊስተካከል የሚችል ችግር ቢሆንም ለህክምና የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካቶች ችግሩ እንዳለባቸው እንኳን ሳያውቁ ተደጋጋሚ ውርጃን በማስተናገድ ልጅ ወልዶ መሳም ህልም ሆኖባቸው ይቀራል፡፡  ከጋብቻ በፊት በሚደረግ ምርመራ ላይ ተሳታፊ መሆን የሚገባቸው ሁለቱም ጥንዶች ሲሆኑ የምርመራውን ውጤት በተረጋጋ መንፈስና በማስተዋል ለመቀበል ዝግጁ መሆንም ከሁለቱም ጥንዶች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ የምርመራ ውጤት የሁለቱን ጥንዶች የጋብቻ ጉዞ ሊያስቀር የሚችል ቢሆን እንኳን ሁለቱም ውጤቱን በፀጋ ለመቀበል የሚያስችል የስነ-ልቦና ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የምርመራው ውጤት ምንም ይሁን ምን በጋብቻ ሀሳባቸው ላይ ለውጥ ለማስከተል እንደማይችል የተማመኑ ጥንዶች፤ በትዳር ጉዞዋቸው ወቅት የሚደርሱትን ችግሮች ተቋቁሞ ለማለፍ እንደሚችሉ ማመን እንደሚገባቸው ዶ/ር አከበረኝ አበክረው አስገንዝበዋል፡፡  ትዳር ማለት እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ ሊዘልቅ የሚችል የህይወት ጉዞ ነውና በደንብ አስቦበት መግባቱ፣ አንዴ ከገቡ በኋላ ደግሞ ኃላፊነትን ለመሸከም ዝግጁ መሆን ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡   Source- addisadmassnews

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.