ዳንኤል፣ ጤነኛ፣ ለቅርጫት ኳስ ጨዋታ ተስማሚ ቁመና ያለው፣ በ30ዎቹ የዕድሜ አጋማሽ የሚገኝ ጎልማሳ ነው፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ጓደኞቹ፣ በተሟሟቀ የቅርጫት ኳስ ጨዋታ መኻል በቁልምጫ ዳኒ፣ ”ትከሻህ ላይ ያለው ጥቁር ነገር ምንድነው?” በማለት የጠየቁትን ዳንኤል በፍፁም አይዘነጋውም፡፡ 


ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ያ ጥቁር ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ሲመረመር፣ ሜላኖማ (melanoma) የተባለ ኃይለኛ የቆዳ ካንሰር በሽታ መሆኑ ተነገረው፡፡ ሐኪሞቹ ሞህ (Mohs’) በተባለ ማይክሮግራፊክ ቀዶ ህክምና በካንሰር የተጠቁትን ኅብረ-ህዋሳት (ሴሎች) አስወገዱለት። ነገር ግን ሁለት ወር ያህል እንደቆየ ካንሰሩ በአካሉ ተሰራጭቶ፣ ብብቱ ስር ያበጠ የነጭ ደም ሴሎች ቋጠሮ (እባጭ) አስተዋለ፡፡ ሐኪሞቹ ለበሽታው ኬሞቴራፒ (chemotherapy) የተባለ የካንሰር መድኃኒትና ሌሎች ኬሚካሎች ቢሰጡም፣ በሽታውን ግን መግታት አልቻሉም፡፡ 

እንዲያውም ሐኪሞቹ ለሚሰጡት ህክምና “አሻፈረኝ አልበገርም” ያለው በሽታ ይብስ ተስፋፍቶ ወደ ሳንባው ተዛመተ፡፡ በዚህ ጊዜ ሐኪሞቹ የዳንኤልን የበሽታ መከላከያ አቅም በማነቃቃትና ከፍ በማድረግ የካንሰርን ዕጢ እንዲወጋ ኢንተርፌሮን አልፋ (Interferon-alpha) የተባለ ህክምና ጀመሩለት፡፡ ነገር ግን ዳንኤል ህክምናው በጣም ስለከበደውና ስላመመው ከመጀመሪያ ቀን በኋላ ሌላ ህክምና መቀበል አቃተውና ቆመ፡፡ 


“ዳንኤልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት የካንሰር ህክምናውን ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው። በዚያን ጊዜ የቆዳው ካንሰር ከሳንባው አልፎ ጉበቱንም ጀምሮት ስለነበር፤ በሽታው በፍጥነት እየተባባሰበትና ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ነበር፡፡ የምግብ ፍላጎቱ በጣም ትንሽ ስለነበር ምግብ አይበላም። በዚህ የተነሳ ክብደቱ 16 ኪሎ ያህል ቀንሶ ነበር፡፡ ክብደቱን መሸከም ስላቃተው የሚንቀሳቀሰው እንኳ ከዘራ እተደገፈ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ቅርጫት ኳስ መጫወት ቀርቶ ሥራ እንኳ መሥራት አይችልም” በማለት የዳንኤልን አስገራሚ የፈውስ ታሪክ በፌብሩዋሪ 2014 ዲስከቨሪ መፅሄት ላይ ያቀረቡት በቫይቪሚያ ደሴት የኑትሮን ቴራፒ ተቋም የጨረር ህክምና ባለሙያ ሚ/ር ጀምስ ዌልሽ ናቸው፡፡ 


“አሁን ካንሰሩ ወደ አጥንቱ በመዛመቱ፣ በቀኝ ታፋው ላይ ከፍተኛ ስቃይ ያለው ህመም እየተሰማው ነው፡፡ 
በዚህ ጊዜ ዳንኤል በህይወት የሚኖረው ጥቂት ወራቶች ብቻ ቢሆን ነው ብዬ ስላሰብኩ፣ ስቃዩን ለማስታገስ ያህል በተለይ በታፋው ላይ ብቻ ያነጣጠረ በጣም የአጭር ጊዜ የጨረር ህክምና (ራዲየሽን ትራፒ) ሰጠሁት፡፡ እንደቀዶ ህክምና ሁሉ የጨረር ህክምናም የውስጥ አካል ህክምና ብቻ ነው፡፡ ኬሞቴራፒና ሌሎች በጥንቃቄ የሚሰጡ የመድኃኒትና ኬሚካሎች ህክምናዎች ግን በሽታው በተከሰተበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን በአካባቢውም ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ፡፡ የጨረር ህክምና እንደዚያ አይደለም፡፡ ተፅዕኖ የሚፈጥረው፤ ጨረሩ ባረፈበት የተለየ ስፍራ ላይ ብቻ ነው፡፡ 


“ዳንኤልን ህመሙ ካልተሻለው እንደገና ለመታየት ከሳምንት በኋላ እንዲመጣ ወይም በስልክ ብቻ እንደማናግረው ቀጠሮ ሰጥቼ ሸኘሁት፡፡ ዳንኤል በቀጠሮው መሰረት ሲመጣ የታፋው ስቃይ በጣም ተሽሎት ነበር፡፡ የጨረር ህክምናው ሰራ ማለት ነው። ይሁን እንጂ መራመድ ካልቻለ በዚያው ይቀራል እንጂ ወደዚህ ክሊኒክ አይመጣም በሚል እሳቤ፣ ከሶስት ወር በኋላ እንዲመጣ ቀጠርኩት፡፡ 
“የታፋው ስቃይና ህመም በመጥፋቱ በጣም ብደሰትና ብገረምም በተለያየ ሞገድ የካንሰር ሴሎቹን ለመግደል የተደረገለት የራዲዮ ቴራፒ ህክምና ህመሙን ቢያስታግስለት እንጂ በሽታውን ከስሩ መንግሎ እንደማያጠፋና ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ሳስበው ድካሙ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ተሰማኝ፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል፤ ዳንኤልን ዳግመኛ አየዋለሁ ብዬ አልጠበኩም ነበር፡፡   
“ነገር ግን፣ ከሶስት ወር በኋላ ዳንኤል መጥቶ ሳየው በጣም ተገረምኩ፤ በጣም ተደሰትኩ፡፡ የታፋ ህመሙ በፍፁም በመጥፋቱ የሚወስዳቸውን የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች አቁሟል፡፡ ፊቱ ላይ የበሽተኝነትና የመገርጣት ሳይሆን የጤንነት ስሜት ይነበብ ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በጣም የገረጣውና የኮሰመነው የበሽተኛ ሰውነቱ አገግሞ አራት ተኩል ያህል ኪሎ ጨምሯል፡፡ በአጠቃላይ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረበት ሁኔታ በጣም ተሽሎታል፡፡ 


liver“የዚያኑ ‘ለታ፣ ሲቲ ስካን እንዲነሳ ፕሮግራም ያዝኩለት፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት አዲስ በሽታ ቢገኝበት ምንም ማድረግ እንደማይቻልና አዲስ ህክምና እንደማይደረግለት አስጠነቀቅሁት፡፡ እንደዚያም ብለው ዳንኤል ግን ሲቲ ስካኑን መነሳት ፈለገ፡፡ ወደ ራዲዮሎጂ ክፍል ወሰድኩትና ፊልሙን ከተነሳ በኋላ አብረን እንድናየውና እንድንነጋገርበት ወደ እኔ ክፍል ጠራሁት፡፡ 
“ይኼኔ ነው እንግዲህ ነገሮች ድንገት የበለጠ አስደሳች መሆን የጀመሩት፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ ዳንኤል የተነሳውን ለማየት ወደ ራዲዮሎጂው ክፍል ሄድኩ፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ በሳንባውም ሆነ በጉበቱ ላይ ካንሰር እንደነበረ የሚሳይ አንዳችም ምልክት አጣሁበት፡፡ አጥንቶቹ ኖርማል ናቸው፤ ብብቱ ስርም ምንም ያበጠ ነገር (ዕጢ) አይታይም። ይህ ፊልም በፍፁም የዳንኤል ሊሆን አይችልም፤ ምልክት ሲደረግባቸው ተደበላልቀው ይሆናል፤ ስለዚህ የተሳሳተ ነው የሚል ስሜት ተሰማኝ። ነገር ግን በጣም አቅርቤ ስመለከተው፣ በአንድ ወቅት ካንሰሩ በነበረበት ስፍራ፣ የጨረር ህክምና (ራዲዬሽን) ሲደረግለት የተፈጠረ በጣም ትንሽ “የራዲዮግራፊክ ጭረት” አየሁ፡፡ ነገር ግን አንዳችም የካንሰር ዕጢ በቦታው አልነበረም፡፡ ታፋ ላይ የተደረገ የጨረር ህክምና በጣም ሩቅ በሆኑት ሳንባ፣ ጉበትና ብብት ላይ ተፅዕኖ ስለማይፈጥር፣ የስካኑን ፊልም ወደ ቢሮዬ አምጥቼ ለዳንኤል አሳየሁ፤ ሌላ ህክምና አድርጎ እንደሆነም ጠየቅሁት፡፡ እሱም የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶቹን ከማቆሙ በስተቀር አንዳችም ህክምና እንዳላደረገ ነገረኝ፡፡ 


“ዳንኤል በጥቂት ወራት ውስጥ እንዲመለስ ቀጥሬው በትልቅ ፈገግታ ወደቤቱ ተመለሰ፡፡ በዚያች ቀን በምድር ላይ እጅግ ደስተኛ ሰው እንደሆንኩ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ተሳስቼያለሁ፡፡ እኔ በህይወት ያለሁ ሁለተኛው ደስተኛ ሰው ነበርኩ፡፡ በቀጠሮው መሰረት ዳንኤል ከሶስት ወር በኋላ ሲመለስ፣ አዲስ ሰው መስሎ ነበር የመጣው፡፡ ከበፊቱ ሁለት ኪሎ ተኩል ያህል ክብደት ጨምሮ ጡንቻዎቹ ስለፈረጠሙ ወደ ስራ ከመመለሱም በላይ ከረዥም ጊዜ ቆይታ በኋላ ቅርጫት ኳስ ትንሽ ትንሽ መጫወት ጀምሮ ነበር፡፡ ለሁለት ዓመት ተከታታይ ምርመራ ካደረገና የሲቲ ስካኑ ውጤትም ንፁህ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የሚሰራው ሥራና የሚመራው ህይወት ስላለው፣ ሌላ ቀጠሮ ሳልሰጠው ቀረሁ። ይሆናል ተብሎ የተፈራውን ግምት ሁሉ አሸንፎ እነሆ ዳንኤል ከያዘው የካንሰር ህመም ተፈውሷል። ይህ የሆነው የዛሬ 12 ዓመት ገደማ ነበር፡፡ ዳንኤል በምን ሁኔታ ተፈወሰ? ማለታችሁ አይቀርም። የጨረር ህክምና ባለሙያውም ሆኑ ሌሎች ሐኪሞችና ተመራማሪዎች እንዴት እንደተፈወሰ በፍፁም አያውቁም፡፡ ጀምስ ዌልሽ የፈውሱን ምስጢር ባያውቁም፣ “እውነቴን ነው የምላችሁ፤ የዳንኤልን ተአምራዊ ፈውስ አምኜ ተቀብያለሁ። ነገር ግን የፈጠረብኝ ግራ መጋባት አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው” ብለዋል፡፡ ምክንያቱም የዳንኤል ፈውስ የመጀመሪያ ገጠመኝ ከመሆኑም በላይ እጅግ አስገራሚ ክስተት ነው፡፡ ከአካባቢው ርቆ የሚገኝ የካንሰር በሽታን ማዳን፣ አልፎ አልፎ የሚያጋጥምና ለማብራራት የሚያዳግት ለማብራራት የሚያዳግት ግልፅ ያልሆነ (abscopal phenomenon) ክስተት ነው ብለዋል-ዌልሽ፡፡ 


“ዕድሜ ልክ ለሚያሰቃዩ ሰዎች የዚህ ዓይነት ህክምና ለመስጠት ውጤቱን አንዴ ማየት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ የእኔም ሙከራ፣ በትክክል ዳንኤል ላይ የተፈጠረውን ዓይነት ፈውስ መፍጠር ስለሆነ፤ በሌሎች በሽተኞችም ላይ ቢሞከር ምናልባት ሊሰራ ይችል ይሆናል፡፡ 


አብስኮፓል የሚለው ከላቲንና ከግሪክ ቃላት የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም “ከእይታ፣ ከግብ ወይም ከዓላማ የራቀ” ማለት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ1953፣ በአንድ የውስጥ አካል ላይ የተደረገ የጨረር ህክምና ከዚያ ርቆ በሚገኝ የአካል ክፍል ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ተገንዝበው ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙት አር ኤች ሞል (R.H mole) የተባሉት ሐኪም ናቸው፡፡
ይህ ፈውስ አብዛኛውን ጊዜ ከራዲዮቴራፒ ጋር የተሳሰረ ቢሆንም በሌሎች cryotherapy፣ hyperthermia በተባሉ የውስጥ አካል ካንሰር ህክምናዎች ላይ እንደሚሰራ ተስተውሏል፡፡ ህክምናው እንዴት እንደሚያድን ግን በፍፁም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡       

Source; addisadmassnews

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.