ከ50-60 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወንዶች የማረጥ እጣ ፋንታ ሊገጥማቸው ይችላል 
በ40ኛው ዓመት እድሜ ማጠናቀቂያ ላይ የወሲብ ፍላጎት ማጣት፣ የስሜት መዋዠቅና ድብርት ይከሰታል 

ሴቶች በህይወት ዘመናቸው በአብዛኛው አጥብቀው ከሚፈሯቸውና ከሚሸሿቸው ጉዳዮች አንዱ ማረጥ ነው፡፡ ይህን ተፈጥሮአዊ ሂደት ተከትሎ የሚከሰቱ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ለውጦችን መቀበልና እንደአመጣጣቸው ማስተናገዱም የብዙ ሴቶች ፈተና ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከ45-49 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች ትውልድ ለመቀጠል (ለመውለድ) የሚያስችላቸውን የዘር እንቁላል ማምረት ሙሉ በሙሉ እንደሚያቆሙ ቀደም ያሉ ሳይንሳዊ መረጃዎች ቢጠቁሙም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ ሳይንሳዊ መረጃዎች ይህንን የማረጫ ዕድሜ ወደታች አውርደውት ከ35 ዓመት ዕድሜ ክልል በላይ ያሉ ሴቶች በማንኛውም ጊዜ እንደሚያርጡ ይጠቁማሉ፡፡ 

1a27199b47d7abcaeec0ecc4269f55e6_XL
በእንግሊዛውያን ተመራማሪዎች የተደረገና ባለፈው ጥር ወር ይፋ የሆነ አንድ ጥናት በበኩሉ፤ ከ50-60 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወንዶችም ይኸው የማረጥ እጣ ፈንታ ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቁሞ፤ ከ70ኛ ዓመት እድሜያቸው መጠናቀቂያ በኋላ በሰውነታቸው ውስጥ የሚኖረው የቴስቶስትሮን መጠን በግማሽ እንደሚቀንስ አመልክቷል፡፡ 


አርባኛው የዕድሜ ክልል መጠናቀቂያ የአብዛኛው ወንዶች ወሲባዊ ስሜት መቀዛቀዣ ጊዜ መሆኑን የጠቀሰው መረጃው፤ በዚህ ዕድሜ ክልል ብልት እንደቀድሞው ፈጥኖ ለመንቃትና ለመቆም እንደሚቸገርም ጠቅሷል፡፡ በሴቶች ስነተዋልዶአዊ አካላት ላይ ተፈጥሮአዊ ለውጥ የሚያስከትለው ኤስትሮጂን ሆርሞን የሚፈጥረውን ዓይነት ለውጥ ቴስቶስትሮን የተባለው ሆርሞን በወንዶች ላይ እንደሚፈጥር ያመለከተው ይኸው መረጃ፤ ሆርሞኑ ወንዶች ዘር ለመተካት የሚያስችላቸውን በቂ ስፐርም ከማምረት እንደሚያግዳቸውና የብልት መልፈስፈስ እንደሚያስከትል ጠቁሟል፡፡ 
ቴስቶስትሮን የተባለው ሆርሞን፤ ወንዶች በጉርምስና ዕድሜያቸው (ለአቅመ አዳም ሲደርሱ) የወንድነት መለያ የሆኑ ለውጦች ለምሣሌ የጢም ማብቀል፣ የድምፅ መጎርነን፣ የጡንቻ መዳበር እንዲፈጠርና በብብትና በስነ ተዋልዶ አካላት ዙሪያ ፀጉር እንዲበቅል ለማድረግ የሚያስችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሆርሞኑ ወንዶች በጉርምስና ጊዜያቸው የወሲብ ፍላጎት እንዲኖራቸው፣ የብልት መነሳሳት እንዲፈጠርና በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ስሜት ያለውና የተሳካ ወሲብ እንዲፈፅሙ ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡ ይህ ሆርሞን ወንዱ በሚገኝበት የዕድሜ ደረጃ መሠረት መጠኑ እንደሚወሰን የገለፀው መረጃው፤ ዕድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር በወንዶች ሰውነት ውስጥ የሚመረተው የቴስቶስትሮን መጠን እንደሚቀንስ ጠቁሞ በ70ዎቹ ዕድሜ ዘመን በግማሽ ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ በዚህ ወቅትም ወንዶች የብልት መልፈስፈስ፣ ድብርት፣ የስሜት መዋዠቅ፣ የወሲብ ፍላጎት ማጣት፣ ወሲብ የማድረግ ብቃት ማነስ፣ ብልት እንደቆመ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት አለመቻል፣ ዘር ሲረጭ ግፊቱ ጠንካራ አለመሆን፣ ዘርን ሲረጩ አለማወቅ፣ የዘር ፍሬዎች መሰብሰብና ከረጢታቸውም ከወትሮው ማነስ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚከሰተው በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ በቀስ እንደሆነና የወንዶች የወሲብ አካል ከወሲብ ግንኙነት በራቀና ወሲብ መፈፀም ባቆመ ቁጥር የደም ስሮቹ በመጨራመትና የዘር ማቀፊያዎቹም በመውደቅ ለመውለድ (ዘር ለመተካት) ያለውን ዕድል በእጅጉ እንደሚቀንሱት መረጃው አመልክቷል፡፡ 


የስነ-ወሲብና የስነ-ልቦና ባለሙያው ዶክተር አስናቀ ይሄይስ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ ወንዶች በተፈጥሮአቸው ጤናማ የሆነ የወሲብ ፍላጎትና ለወሲባዊ ግንኙነት ብቁ የሆነ አካላዊ ተፈጥሮ እንዲኖራቸው የሚያደርገው ቴስቶስትሮን የተባለው ሆርሞን፤ በአብዛኛው በወንዶች የጉርምስና ወቅት ተፈጥሮ የወንዶቹ ወንድነት መለያ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያስችላል፡፡ ወንዶች በጉርምስና መጀመሪያ ዕድሜያቸው ላይ ድምፃቸው እንዲጎረንን፣ ጡንቻዎቻቸው እንዲዳብሩና ከሴቶች የተለየ አካላዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው የሚያደርገውም ይኸው ሆርሞን ነው፡፡ ሆርሞኑ በጉርምስና የዕድሜ ዘመን በመጠን በርከት ብሎ የሚመረት ሲሆን ወንዱ በፈለገው ጊዜና ሁኔታ የወሲብ ፍላጎቱ እንዲነሳሳ፣ ብልቱ እንደልቡ እንዲቆምና በግንኙነት ወቅት ጠንከር ያለ ግፊት ያለው የዘር ርጭት እንዲኖረው ለማድረግ ያስችላል፡፡ ዕድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር ግን ሰውነታችን ይህን ሆርሞን የሚያመርትበት መጠን ቀስ በቀስ እየቀነሰ ይሄዳል። ይህም በወንዶች ወሲባዊ ህይወት ላይ ለውጥ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ለውጡ ቀስ እያለ የሚከሰት እንጂ እንደሴቶቹ በአንድ ጊዜ የሚፈጠር ባለመሆኑ የወንዶች ዘር የመተካት (የመውለድ) ብቃት ማነስ እምብዛም ጎልቶ እንዲታይ አላደረገውም፡፡ ይሁን እንጂ ወንዶች የ50 ዓመት ዕድሜያቸውን ከዘለሉ በኋላ የወሲብ ፍላጎታቸውም ሆነ አፈፃፀማቸው እንደቀድሞው ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ በመውለድ ብቃታቸው ላይ የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ 


በተለይ ወንዱ ጤናማ ካልሆነና ሌላ ተጨማሪ ችግሮች እንደ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ የሣንባ በሽታና መሰል የጤና ችግሮች ካሉበት ልጅ የማግኘት ዕድሉ የመነመነ ነው ብለዋል፡፡ 
በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ወንዶች የወሲብ ፍላጎት ማጣት ወይም የብልት መልፈስፈስ አሊያም እንደልብ አልቆም ማለት ሲያጋጥማቸው ቪያግራን የመሳሰሉ መድሃኒቶችን መጠቀም እንደሚያዘወትሩ የጠቀሱት ባለሙያው፤ እነዚህ ነገሮች ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ችግሩን እንደሚያባብሱትና ሰዎችን የመድሃኒት ሱሰኛ በማድረግ፣ ለከፋ የጤና እክል እንደሚዳርጋቸው ገልፀዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር የገጠማቸው ሰዎች ወደ ህክምና ባለሙያዎች በመሄድ ችግራቸውን ቢያማክሩ፣ መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚችሉና ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ችግር ለማከም እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡  

Source- .addisadmassnews

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.