የአደገኛ እጾች መዘዝ 
የልብ በሽታ
የአዕምሮ መዛባት
የእንቅልፍ እጦት
ተስፋ የመቁረጥ ስሜት
ጭንቀትና መደበት
ራስን የማጥፋት ፍላጎት 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሣይኮሎጂ ትምህርት ዘርፍ የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያለ ነው ካናቢስ የተባለውን አደንዛዥ እፅ መጠቀም የጀመረው፡፡ ለከፋ ጉዳትና ውስብስብ ችግር እንደሚዳርገው፣ የልጅነት ህልሙን እንደሚያጨናግፍበትም ፈጽሞ አላሰበም፡፡ 
በትምህርቱ ከሰቃዮቹ ተርታ ሚመደበው ቢኒያም (ስሙ ለዚህ ፅሁፍ የተቀየረ) ፤የቤተሰቦቹና የመምህራኑ ሁሉ ተስፋ ነበር፡፡ ይሄም ሌት ተቀን በትምህርቱ እንዲተጋና የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግብ ጉልበት ሆነው፡፡ የሶስተኛ ዓመት ማጠቃለያ ፈተና ሲቃረብ፣ አንዳንድ የክፍሉ ተማሪዎች “አስጠናን” በሚል ሰበብ እየቀረቡት መጡ፡፡ ጥያቄዎቻቸውን በደስታ እየመለሰ፣ የሚያውቀውን እያስረዳቸውና አብረው እያጠኑ ለጥቂት ጊዜያት  አብሯቸው ዘለቀ፡፡ ይሄኔ ነው ለዛሬ ውድቀቱ መነሻ ወደሆነው ሱስ ይዘውት የገቡት፡፡

b1cc8dc7f28895bcf560deb908a8e901_M
ስፍራው ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ ጀርባ ከሚገኙት መቃሚያ ቤቶች ባንዱ ነው፡፡ ጓደኞቹ የመቃሚያ ቤቱ ፀጥታና ድባብ ለጥናት ምቹ እንደሆነ አሳምነው ነው  ቢኒያምን ወደዚህ  ቤት ያመጡት። እሱ ቀደም ብሎ የማያውቀውና ያለመደው አዲስ ነገር በማየቱ ለጊዜው ስሜቱ ተረባበሸ፡፡ ሆኖም አንድ እንጨት ንከስ እያሉ ከሚሰጡት ጫት ጋር ለመላመድ ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ሁኔታው ተመቸው ወይም በእሱ አማርኛ “ሙዱ ገባው”፡፡ የሶስተኛ ዓመት ትምህርቱን አጠናቆ ወደ አራተኛ ዓመት የተዛወረው በቀድሞው ከፍተኛ ውጤት አልነበረም፡፡ ሆኖም ቢኒያምን ብዙም አላስጨነቀውም፡፡ ዩኒቨርስቲው ለእረፍት ሲዘጋ ከእነዚሁ ጓደኞቹ ጋር እዚያችው ቤት እየተቀጣጠረ አብሮ መዋሉን ቀጠለበት፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ጓደኞቹ አልፎ አልፎ ተደብቀው የሚያጨሱትን ነገር ለማየትና ለመቅመስ፣ ስሜታቸውንም ለመጋራት ጉጉት ያደረበት፡፡ ይቅርብህ ያለው ማንም አልነበረም፡፡ ጓደኞቹ እጿን አቃምሰው ሱሰኛ ሊያደርጉት ወይም በእሱ አማርኛ “ሊከትቡት” ቋምጠው ነበርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የመጀመሪያው ቀን ስሜቱ የተረጋጋ አልነበረም፡፡ እንደ ሲጋራ ተጠቅልሎ የሚጨሰውን ነገር ሰጥተውት አንድ ሁለቴ እንደሳበ፣ ሃይለኛ ሳልና የማስመለስ ስሜት ገጠመው፡፡ አይኑ እንባ አዝሎ ራስ ምታት ለቀቀበት። “ሳብ ሳብ አድርግበት ይተውሃል” አሉት ጓደኞቹ፡፡ እንደተባለው አደረገ፡፡ እውነትም ፍርሃቱና ድብርቱ ከላዩ ላይ ተገፈው ሲሄዱ ታወቀው፡፡ ደስ ደስ የሚል ስሜት ተሰማው፡፡ ጥንካሬና ሁሉን እችላለሁ አይነት ስሜት ሁለመናውን ወረረው፡፡ 


ከዚህ ስሜትና ደስታ ርቆ የቆየባቸውን ዓመታት በከንቱ እንደባከኑ ቆጥሮ ተፀፀተ፡፡ ቀስ በቀስ በሱሱ ተጠመደ፡፡ ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል ሁሉ ተሳነው፡፡ ምግብ መብላትና ራሱን መጠበቅ እርግፍ አድርጐ ተወ፡፡  ሰውነቱ ከእለት ወደ እለት እየሳሳና እየመነመነ ሄደ በሽተኛ መምሰል ጀመረ፡፡ ቤተሰቦቹ ሁኔታው እጅግ አስደነገጣቸው፤ ሁኔታውን በድብቅ ለመከታተል ሞክረው ደረሱበት፡፡ በልጃቸው ላይ የደረሰው ችግር እጅግ ያሳሰባቸው ወላጆቹ፤ ልጃቸውን በቁጣም፣ በምክርም በልመናም ከገባበት ለማውጣት ብዙ ጣሩ፡፡ ሆኖም አልተሳካላቸውም። “በእኔ ህይወት ውስጥ ማንም አያገባውም” የሚል ሆነ ምላሹ፡፡ የቀድሞ ውጤቱን የሚያውቁ አንዳንድ መምህራን፤ የቢኒያምን  የውጤት ማሽቆልቆል እያዩ ማለፍ አልቻሉም፡፡ ቀስ እያሉ በምክር ለመመለስ ሞከሩ፡፡ ምክሩ ግን  ቢኒያምን የበለጠ እንዲሸሽ አደረገው፡፡ “ምን እየሆንክ ነው?” የሚለው የመምህራኑ ጥያቄ ከትምህርት ገበታው ላይ አራቀው፡፡ ወደ ዩንቨርስቲው መሄዱን ከእነአካቴው ተወው፡፡ 
የአራተኛ አመት ትምህርቱን ከሁለት ሴሚስተር በላይ መዝለቅ አልሆነለትም፤ ከዩኒቨርስቲው ተባረረ። መባረሩ ቢኒያምን ባያስደነግጠውም ቤተሰቦቹ ግን በጣም አዘኑ፡፡ ይባስ ብሎ ሰውነቱ መንዘፍዘፍና አንዳንዴም ራሱን መሳት ጀመረ፡፡ በህይወት የመቆየቱ ጉዳይ ያሳሰባቸው ወላጆቹ፤የስነልቡና ባለሙያዎች እንዲያዩትና የጤና ክትትል እንዲያደርጉለት አማኑኤል ሆስፒታል አስገቡት፡፡ ወራትን በፈጀ ተከታታይ ህክምና፣ ቢኒያም ወደ ቀድሞ ጤንነቱ እየተመለሰ ይገኛል። በአደገኛ እፅ ሱሰኝነት ሳቢያ የደረሰበትን ችግር ያጫወተኝም የእፅ ሱሰኛ በነበረበት ወቅት ምግብ በአግባቡ ባለመመገቡ ምክንያት በጨጓራውና በአንጀቱ ላይ የደረሰውን የጤና ችግር ለመታከም ኢትዮ – ጠቢብ ሆስፒታል አግኝቼው ነው፡፡


እንደ ቢኒያም አይነት ታሪክ ያላቸው በርካታ ወጣቶች፣ ከትምህርት ገበታቸውና ከሥራቸው  በአደገኛ እፅ ሱሰኝነት ተፈናቅለው፣ የወደፊት ተስፋቸውና ህልማቸው ተጨናግፎ ማየት ዛሬ ዛሬ የተለመደ ይመስላል፡፡ በየትምህርት ቤቶች በራፍ ላይ፣ እንዲሁም  በየመንደሩና በየጉራንጉሩ ውስጥ ቤታቸውን ለአደገኛ እፆች መጠቀሚያነት ያዋሉ በርካቶች የብዙዎችን ህይወት እያጨለሙ ነው፡፡ 
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ወቅቶች እነዚህን በድብቅ አደገኛ እፆችን ያስጨሳሉ የሚባሉትን ቦታዎች በድንገተኛ ፍተሻና አሰሳ ሲዘጋና ባለቤቶቹንም ሲያስቀጣ  መቆየቱ የሚታወቅ ቢሆንም ከአሰሳው የተረፉት ወይም ሊደርስባቸው ያልቻሉት ቤቶች፣ ዛሬም ብዘዎችን ለከፋ ሱሰኝነትና የጤና ጠንቅ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ መልኮች እየተጠቀለሉ የሚጨሱ አደገኛ እፆች በየትምህርት ቤቶች ደጃፍ፣ በየመዝናኛ ስፍራዎች፣ በመቃሚያ ቤቶችና በናይት ክለቦች በግልፅ ይሸጣሉ፡፡ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ እሪ በከንቱና ዶሮ ማነቂያ፣ አውቶቡስ ተራ፣ ጐጃም በረንዳ፣ ጣሊያን ሰፈርና ዳትሰን ሰፈር አደንዛዥ እፆቹ ያለከልካይ በአደባባይ የሚሸጡባቸው ስፍራዎች ናቸው፡፡
የአደንዛዥ እፆችና የህገወጥ መድሃኒቶችን ዝውውርና አጠቃቀም በተመለከተ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች፣ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማሉ፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ያወጣው መረጃ  እንደሚያመለክተው፣ ህገወጥ የአደገኛ እፆች ዝውውር በየዓመቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ከአራት መቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሲሆን ከአንድ መቶ አርባ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችም  እጅግ አደገኛ የሆኑ እፆች ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት በ2012 ዓ.ም ላይ ይፋ ያደረገውና The African Drug Nexus የተሰኘ  ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ አደገኛ እፅ ተጠቃሚዎች ያሉባት ሀገር ነች፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት በዚህ ጥናት ውስጥ ካካተታቸው አስር የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቁሞ፣ ከአገሪቱ ህዝብ 1.6 በመቶ በላይ የሚሆነው የአልኮልና አነቃቂ መድሃኒቶች ተጠቃሚ ናቸው ብሏል፡፡ ከእፅ ተጠቃሚ ዜጎች መካከል ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዙት የጐዳና ተዳዳሪዎች እንደሆኑ የገለፀው ሪፖርቱ፤ 85 በመቶ ያህሉ  የጐዳና ልጆች ቢያንስ የአንድ አይነት አነቃቂ እፅ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡


ይኸው የአደገኛ እፆች ዝውውርና አጠቃቀም በተለይ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ እየጨመረ እንደሄደም ይኸው ጥናት አመላክቷል፡፡ በተለይ አምራች ሃይል የሆነውና ተስፋ የሚጣልበት ወጣቱ ትውልድ፤የእነዚህ መድሃኒቶችና እፆች ዋንኛ ተጠቃሚ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይሄ አስጊ ሁኔታ  በአጭሩ  መቀጨት  እንዳለበት የገለፀው ጥናቱ፤ ካልሆነ ግን  ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማስከተሉ አይቀሬ ነው ብሏል፡፡

በአገራችን በህገወጥ መንገድ በስፋት እየተመረተ ለገበያ የሚቀርበው እፀፋሪስ ከሚባለው ተክል የሚገኘውና ካናቢስ የተሰኘው አደንዛዥ እፅ ሲሆን በአገሪቱ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውልና ከሌሎች አደንዛዥ እፆች ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ዋጋ ያለው እፅ ነው፡፡ ተክሉ በአገራችን በተለይም በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል እየተመረተ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን ካናቢስ እየተባለ የሚጠራው ከደረቀው አፀፋሪስ ቅጠልና አበባ የሚገኘው ክፍል ነው፡፡ እፁ አዕምሮን የማዛባትና የማሳት ባህርይ እንዳለው የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከተክሉ ግንድ የሚገኘውና ሬዚን እየባለ የሚጠራው እፅ ደግሞ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ገበያ ላይ የሚገኝና በአገራችን አብዛኛዎቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚጠቀሙት እፅ ነው፡፡ ይህ እፅ የአዕምሮ መዛባት፣የማመዛዘን ችሎታን ማጣትና የሳንባ ካንሰርን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከካናቢስ ሌላ በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገራችን ጥቅም ላይ ከሚውሉ የአደንዛዥ እፅ አይነቶች መካከል ሄሮይን፣ አምፊታሚንስ፣ ኮኬይን፣ ሞርፊን፣ ፔቲዲን፣ ማታደንና ከዴይን የሚባሉት ይገኙበታል፡፡ እፆቹ በመርፌ፣ በእንክብል፣ በሲጋራና በሱረት መልክ በጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በአገራችን አነዚህን አደንዛዥ እፆች መጠቀም፣ ማዘዋዋር፣ ማምረትና ለተጠቃሚ ማድረስ በህግ የሚያስጠይቁ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ሆኖም ቁጥጥሩ የላላ እንደሆነ አንዳንድ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ 


አለም አቀፍ እፅ አዘዋዋሪዎች ኢትዮጵያን እንደመተላለፍያ ስፍራ የሚጠቀሙባትም ቁጥጥሩና ክትትሉ አነስተኛ በመሆኑ እንደሆነ እነዚሁ ወገኖች ይገልፃሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከኮሎምቢያና ከሜክሲኮ ወደሌሎች አገራት ለማዘዋወር ታስቦ በሰው ሆድ ዕቃ ውስጥ ወደ አገራችን የገባ ሔሮይን የተባለ አደንዛዥ እፅ፣ በእፅ አመላላሹ ሶማሊያዊ  ሆድ ዕቃ ላይ በደረሰ ጉዳት ሳቢያ ችግሩ ታውቆ፣ በቀዶ ጥገና  ከሰወየው ሆድ ውስጥ የወጣለት ቢሆንም የሰውየው ህይወት አልፏል፡፡ በርካታ አገራት በእፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወስዱት እርምጃና ቅጣት እጅግ ከፍተኛ ሲሆን  በአንዳንድ አገራት ቅጣቱ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡


አደንዛዥ እጽ  በግለሰብ፣ በቤተሰብ ብሎም በአገር ላይ ከሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በተጨማሪ በተጠቃሚዎቹ  ላይ የሚያስከትለው የጤና ቀውስም ቀላል አይደለም፡፡ የስነ አዕምሮ ሀኪሙ ዶክተር አሳየኸኝ መንግሥቱ ይህንን  አስመልክተው ሲናገሩ፣ አደገኛ እፆች የምግብ ፍላጐትን ማሳጣት፣ የልብ በሽታን፣ የአዕምሮ መዛባትን፣ የማመዛዘን ችሎታን ማሳጣት፣ የአዕምሮ መናወጥ፣ የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን፣ የአተነፋፈስ ስርአትን ማዛባት፣ የእንቅልፍ እጦት፣ ተስፋ የመቁረጥ ስሜትን፣ ጭንቀትና መደበትን፣ እንዲሁም ራስን ለማጥፋት የመፈለግ ስሜትን ያሳድራሉ፡፡ የሰውነት መንዘፍዘፍ፣ ራስን መሳትና ድንገተኛ ሞትም የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች እጣ ፈንታዎች ናቸው ብለዋል፡፡ የእፁ ተጠቃሚዎች አዕምሮአቸውን እንደልብ ማዘዝ ስለማይችሉ  አመፅ፣ አስገድዶ መድፈርና መሰል ከባድ ወንጀሎችን እንዲፈፅሙ ይገፋፋሉ ሲሉም ገልፀዋል፡፡ በአብዛኛው አደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች እፁን በጋራ በሚጠቀሙባቸው መርፌዎች የሚወስዱ በመሆኑ፣ አችአይቪን ጨምሮ በደም ንክኪ ለሚተላለፉ በሽታዎች እንደሚጋለጡም ዶክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች በማንኛውም ጊዜና ወቅት ከሱሳቸው መላቀቅ እንደሚችሉ የተናገሩት ዶክተሩ፤ሱሰኞቹ ረዘም ያለ የስነልቡና ክትትልና ህክምና በማድረግ፣ ወደ ቀድሞው ህይወታቸው መመለስ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡


በአለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉት አደንዛዥ እፆች መካከል ሄሮይን የተባለው ከፍተኛ ስቃይን በማስታገስ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ጊዜያዊ የደስታ ስሜትንም ይፈጥራል፡፡ ኮኬይን የተባለው አደንዛዥ እፅ ደግሞ በአንዳንድ አገራት ከአንገት በላይ ማለትም ለአፍ፣ ለአፍንጫ፣ ለጆሮና ለጉሮሮ ቀዶ ህክምና ማደንዘዣ በመሆን ያገለግላል፡፡    

Source; addisadmassnews

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.