pregnancy

 

በውድቅት ሌሊት “ዎክ” ማድረግ ያምረኝ ነበር 
የሚዳቋ ጥብስ አምሮኝ ከየት ይምጣ?!

“እርግዝናው የመጀመሪያዬ ነው፡፡ በፊት በፊት ሴቶች ሲያረግዙ የማይሆን ነገር ያምራቸዋል ሲባል ስሰማ ሲሞላቀቁ ነው  
እያልኩ አስብ ነበር፡፡ ግን ተሳስቻለሁ፡፡ ከእርግዝናዬ 3 ወራት በኋላ ውስጤ የሚፈልገውና የሚያምረኝ ሁሉ ግራ  የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ደግሞ የፈለግሁትን ካላገኘሁ ፈጽሞ ጤና አይኖረኝም፡፡ ባለቤቴ ፍላጎቴንና አምሮቴን ለማሟላት  ከፍተኛ ጥረት በያደርግም አንዳንዴ አማረኝ የምለው ነገር እንኳን ለእሱ ለእኔም ግራ ይሆንብኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን  የጠየቅሁትን ፈልጎ ከማምጣት አይቦዝንም፡፡  

“በቅርቡ ያጋጠመኝን ልንገርሽ፡፡ ጠዋት ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ የሚዳቋ ሥጋ ጥብስ አማረኝ አልኩት፡፡ የሚዳቋ ሥጋ  ከየት ይገኛል የበግ ወይ የፍየል ሥጋ ይገዛና ይጠበስልሽ አለኝ። በፍፁም አልፈልግም አልኩት፡፡ ለአንድ ጓደኛው ደወለና  ሲያማክረው ቻይና ሬስቶራንት ይዘሃት ሒድ አለው። ይዞኝ ሄደ፡፡ እኔ እራሴ በህይወቴ ሚዳቋ የምትባል ፍጡር አይቼ  አላውቅም፡፡ ምግቡ መኖሩን ስንጠይቅ አለ ተባልንና አዘዝን። የቀረበልኝን ምግብ አይነቱንም ሆነ አቀራረቡን ከዚህ ቀደም አይቼው አላውቅም፡፡ ግን ጥርግ አድርጌ ነው የበላሁት። በጣም የገረመኝ ነገር ደግሞ ለቀረበልን አንድ የምግብ  የከፈልነው ከ800 ብር በላይ መሆኑ ነው፡፡

ይህ ምግብ ዳግም እንዳያምርኝ ፀሎቴ ነው፡፡”  በጳውሎስ ሆስፒታል ለእርግዝና ክትትል መጥተው ካገኘኋቸው ነፍሰጡር ሴቶች መካከል የስምንት ወር ነፍሰጡሯ  ሰናይት ታከለ ነበረች ከላይ የቀረበውን ታሪክ የነበረችኝ፡፡ በሆስፒታሉ አግኝቼ ካነጋገርኳቸው ነፍሰጡር ሴቶች መካከል  አብዛኛዎቹ በእርግዝና ወቅት የተለያዩ ነገሮች አምሮት በተለያየ ጊዜ እንደሚያጋጥማቸውና ያማረቸውን ነገር ካላገኙ  ወይም ካልበሉ ጤናቸው እንደሚጓደል ይገልፃሉ፡፡ 


አንድ ልጅ ወልዳ ሁለተኛውን ለመውለድ እየተጠባበቀች የምትገኘው ሠላም ፍቃዱ፤  በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው  አምሮት ጉዳይ ከመጀመሪያ እርግዝናዋ በኋላ እንዳላስቸገራት ትናገራለች፡፡ “የመጀመሪያ ልጄን እርጉዝ ሆኜ የብዙ ነገሮች  አምሮት ያሰቃየኝ ነበር፡፡ እኔ በአብዛኛው የሚያምረኝ የሚበሉ ወይም የሚጠጡ ነገሮች አልነበረም፡፡ በውድቅት ሌሊት  ተነስቼ በባዶ እግሬ ወክ ማድረግ በጣም ያምረኝ ነበር፡፡ ባለቤቴ ደግሞ ይሄንን አይፈቅድልኝም፡፡ የሲጋራ ጭስና  የተበላሹ ምግቦች ሽታም ወልጄ እስክገላገል ድረስ በየዕለቱ ውል እያሉ ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ይህ አምሮቴ ባለቤቴ የአጫሽ  ጓደኛውን በሲጋራ ጭስ የታጠነ የአንገት ሻርፕ ለማምጣት እስኪገደድ አድርሶት ነበር፡፡ 


“አሁን ሁለተኛ ልጄን ሳረግዝ ግን ያ ሁሉ ስሜትና ፍላጎት ጠፍቷል፡፡ ምንም ችግር ሳያምረኝ ነው ዘጠኝ ወሬን  የጨረስኩት፡፡ አሁን ለመውለድ የቀረኝ ጥቂት ቀናት ነው፡፡ በዚህ ጊዜም የተለየ አምሮት ያጋጥመኛል ብዬ አላስብም”  ብላለች፡፡ 


“ባለቤቴ በነፍሰጡርነት ያሳለፈቻቸው ጊዜያት ለእኔ የፈተናና የሥቃይ ወራት ነበሩ፡፡ የባህርይዋ መለዋወጥ፣ የፍላጎቷ  መብዛት፤ ተነጫናጭነቱ ምርር አድርገውኝ ነበር፡፡ “ምነው ባይወለድ ቢቀርስ” እስክል ድረስ ነው የተማረርኩት፡፡ ሌሊት እንቅልፍ የሚባል ነገር የላትም፡፡ የበላችው ነገር ፈፅሞ አይረጋላትም፡፡ አንዳንዴ ስቃይዋ በጣም ያሣዝነኝ ነበር፡፡  ፍላጐቷን ለማሟላትና የምትጠይቀኝን ሁሉ ለመፈፀም ጥረት ባደርግም ደስተኛ አትሆንም። ይህ ደግሞ እኔን በጣም  ያናድደኝ ነበር፤ ኡይ ያ የፈተና ወቅት ነበር፡፡ አማረኛ ያለችውን ነገር ለማግኘት ብዙ መከራ አይቼ ፈልጌ ሳመጣላት  “አሁን አምሮቴ አለፈልኝ፣ አልፈልገውም” ብላ ወሽመጤን ብጥስ ታደርገዋለች፡፡ አንድ ጊዜ የኔ ቢጤ ፍርፋሪ  ከነመያዣው (አቁማዳ ነው መሰለኝ የሚባለው) አማረኝ ብላ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ሄጄ፣ ከኔ ብጤዎች ላይ ገዝቼ  ሳመጣላት፣ “አሁን አለፈልኝ አልፈልግም” አለችኝ፤ እኔ እሱን ለማግኘት የከፈልኩት መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም፡፡ ግን ምን ታደርጊዋለሽ፡፡ የሚስቶች የእርግዝና ወቅት የባሎች የፈተና ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በድጋሚ እንድታረግዝ  አልፈልግም፡፡”

በሚስቱ የነፍሰጡርነት አምሮት የተማረረ አባወራ ያጫወተኝ ነበር፡፡ ነፍሰጡርነት ለሔዋኖች ብቻ የተሰጠ፣ ዘርን የመተካት ተፈጥሮአዊ ሒደትና ፀጋ ነው፡፡ እርግዝና ከ15-45 የዕድሜ ክልል  ውስጥ ባሉ ሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን በአማካይ የሰው ልጅ የእርግዝና ወቅት 40 ሣምንታት ወይም 280 ቀናትን  ይፈጃል። በእርግዝና ወራት ሰውነት የተለያዩ ለውጦችን ያስተናግዳል፡፡ 


ነፍሰጡር ሴት በእርግዝናዋ ሳቢያ የተለያዩ ሆርሞኖች በሰውነቷ ውስጥ ይፈጠራሉ፡፡ እነዚህ ሆርሞኖችም በሰውነቷ  የተለያዩ ክፍሎች ላይ የሚታዩ ለውጦችን ያስከትላሉ፡፡ በባህርይዋ፣ በአተነፋፈሷ፣ በልብ ምቷ ና በምግብ ፍላጎቷ ላይ  ለውጥ ይከተላል፡፡


የባሎች ትዕግስትና የፍቅራቸው ልክ ከሚፈተኑባቸው አጋጣሚዎች መካከል የሚስቶቻቸው የእርግዝና ወቅት ተጠቃሽ  ነው። በእርግዝናዋ የመጀመሪያ 3 ወራት ማስመለስና ማቅለሽለሽ በብዛት ሊያጋጥማት ይችላል፡፡ የምግብ ፍላጎቷና  ምርጫዋ የተለየ ሊሆንም ይችላል፡፡ ነፍሰጡር ሴቶች በእርግዝና ወቅት የተለያዩ ነገሮች እንዲሚያምሯቸው ሲናገሩ  ይሰማል:- አፈር፣ የመኪና ወይም የሲጋራ ጭስ፣ የቤንዝን ወይም የተበላሸ ምግብ ሽታ፣ ሣሙና፣ ሊጥ፣ ትርፍራፊ  ምግቦች፣ የኮመጠጡ መጠጦች፣ ያምረናል ከሚሏቸው ነገሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በእርግዝና ወቅት ለሚከሰት የተለየ የምግብ አምሮት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች እንዳሉ  የሚናገሩት የማህፀንና ፅንስ ሃኪሙ ዶክተር አክሊሉ ወንድሙ፤ ከእነዚህ አንዱ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የብረት  ማዕድን እጥረት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ 
በዚህ ማዕድን እጥረት የተነሳ የደም ማነስ የሚፈጠርባቸው ነፍሰጡር ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት የማይበሉ ነገሮችና  ለመብላት የመፈለግ ባህርይ ሊያሣዩ ይችላሉ፡፡ እንደአገራችን ባሉ ታዳጊ አገራት ከ48 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሴቶች  የብረት ማዕድን እጥረት ይታይባቸዋል ያሉት ዶክተሩ፤ “ለዚህም ምክንያቱ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና፣ አከታትሎ  መውለድና በወሊድ ወቅት የሚያጋጥም የደም መፍሰስ ሊሆኑ ይችላሉ። በእነዚህ ምክንያቶች የብረት ማዕድን እጥረት  የገጠማት ሴት በእርግዝናዋ ወቅት እንደ አፈር፣ ሣሙና፣ ትርፍራፊ ምግቦችና መሰል ያልተለመዱ ነገሮችን የመብላት  ፍላጐትና አምሮት ይኖራታል፤ እነዚህ የማይበሉ ነገሮች ደግሞ ንፅህና የሌላቸውና ለምግብነት የሚዘጋጁ ባለመሆናቸው  በነፍሰጡሯ ላይ እጅግ አደገኛ የሆኑ የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉባት ይችላሉ” ሲሉ አስረድተዋል። የማይበሉ ነገሮች  የሚያምራቸውና የሚበሉ ነፍሰጡር ሴቶች፤ ምናልባትም የሥነ አዕምሮ ችግር ያለባቸው ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል –  ዶክተር አክሊሉ። ሌላው ጤናማ የሚባለውና እርግዝናን ተከትሎ በሴቷ ሰውነት ላይ በሚፈጠር የሆርሞን ለውጥ ሣቢያ  በበርካታ ሴቶች ላይ የሚከሰት አምሮት ነው። የሆርሞን ለውጡ ከነርቭ ሥርዓት ሒደት ጋር በተያያዘ የምግብ ፍላጐትና  ምርጫ ላይ ለውጥ ይፈጥራል፡፡ ነፍሰጡሯ ሴት የምትመገበው ምግብ፣ በሆዷ ለያዘችው ፅንስ ጭምር በመሆኑ ምግቡን  የሚጋራት አካል በውስጧ ስለአለ ሰውነቷ የምግብ እጥረት ያጋጥመዋል፡፡ በዚህ ወቅትም በአንድ የተለየ ወይም የተወሰነ  ምግብ ላይ ትኩረት እንድታደርግ ያስገድዳታል፡፡ 


“ይህ ጤናማ የእርግዝና አምሮት ሊባል ይችላል” ያሉት ዶክተር አክሊሉ፤ ነፍሰጡሯ ምንም ያህል ፍላጐትና አምሮት  ቢኖራት ንጽህናቸው ያልተጠበቁ ምግቦችን ወይም ለምግብነት የማይውሉ ነገሮችን በምንም ዓይነት ሁኔታ መመገብ  እንደሌለባት አበክረው አስገንዝበዋል፡፡ በእርግዝና ወቅት የሲጋራ ወይንም የቤንዝን ሽታ አማረኝ የሚሉ ሴቶች ወይንም  አምሮቱ የሚያጋጥማቸው ነፍሰጡሮች በተቻላቸው መጠን አምሮታቸውን ለመርሳትና በሌሎች ነገሮች ለመለወጥ ጥረት  ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን በማድረጋቸው ምክንያትም በእነሱም ሆነ በማህፀናቸው ባለው ፅንስ ላይ የሚፈጠር  ችግር አይኖርም ሲሉም ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡ በአምሮት ሰበብ ለእናቲቱም ሆነ ለጽንሱ እጅግ አደገኛ የሆኑ ነገሮችን  ከማድረግም መቆጠብ እንደሚገባ ዶክተር አክሊሉ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ጤናማና ንቁ ልጅ ወልዶ ለመሳምና የእርግዝና  ወራትን በሰላም ለማጠናቀቅ፣ ይቻል ዘንድ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥሙትን የተለያዩ አዕምሮቶችን በብልሃትና  በጥንቃቄ ማለፍ እንዳለባቸው ነፍሰጡር ሴቶች ሁሉ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ 

Source – .addisadmassnews

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.