tena“ፅንብ ማቋረጥ የወሊድ መከላከያ ተደርጐ ሊታሰብ አይገባም”

እንዲያው እግር ጥሎት አልያም ጉዳይ ኖሮት ፒያሳ ካቴድራል ትምህርት ቤት አካባቢ ወደሚገኘው ሠፈር ብቅ ያለ ይታዘበው፣ ይገረምበት ነገር አያጣም፡፡ በለጋ የወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች በአካባቢው በብዛት ውር ውር ሲሉ መመልከቱም አይቀርም። ወጣቶቹ በሥፍራው በብዛት የሚታዩት ለአንድ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ጉዳያቸውን የሚፈጽሙት ደግሞ በምስጢር ነው፡፡ በተለይ ከቤተሰቦቻቸው አባላት አንዱ ወይም አንዷ ምስጢራቸውን እንዲያውቁባቸው ስለማይፈልጉ፣ወደ ሥፍራው የሚመጡት ብቻቸውን አሊያም ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋ ነው፡፡

ገና የቸርችልን ጐዳና ተገንጥለው ወደ ካቴድራል የሚወስደውን መንገድ ይዘው አንድ አስር እርምጃ እንደተጓዙ በድለላ ተግባር ላይ በተሰማሩ ወጣቶች እጅ ላይ ይወድቃሉ። ወጣቶቹ እነሱ ለሚፈልጉት ዓላማና ተግባር የሚመጡትን ሴቶች ለመለየት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በቂያቸው ነው፡፡ በተለሳለሰ ቃላትና በጓደኝነት ስሜት ለማግባባት ይሞክራሉ፡፡ የፈለጉትን አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ፣ ክፍያው አነስተኛ እንደሆነ፣ ህመም እንደማይሰማዎና ንፅህናውን የጠበቀ አገልግሎት እንደሚያገኙ ለማሳመን በመሞከር በጄ ካሉ፣ በከተማዋ ለዚሁ ተግባር ከተከፈቱ ክሊኒኮች ወደ አንዱ ይዘዎት እብስ ይላሉ፡፡
ታዲያ በእነዚህ ክሊኒኮች በሚሰጠው የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡና ለጤና ችግር የተዳረጉ ወጣቶችን ቤት ይቁጠራቸው። ፒያሳ እጅግ የተለመደና የታወቀ ሥፍራ በመሆኑ በምሣሌነት አነሳሁት እንጂ፣ የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎቱ በከተማዋ ትላልቅ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች እንዲሁም በበርካታ ክሊኒኮች የሚሰጥና እጅግ ብዙዎች የሚጠቀሙበት አገልግሎት ነው። አገልግሎቱ በሙያው በሰለጠኑ ባለሙያዎችና ንጽህናውን በጠበቀ ሁኔታ የሚሰጥባቸው ቦታዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ያለባለሙያ እርዳታና ድጋፍ በልምድ ብቻ በሚሰሩና ንጽህናቸው እጅግ አሳሳቢ በሆኑ ሥፍራዎችም ይሰጣል፡፡ ለአገልግሎቱ የሚጠየቀውን ክፍያ የመክፈል አቅም የሌላቸው ወጣት ሴቶች፤ በአነስተኛ ክፍያ አገልግሎቱ ወደሚሰጥባቸው ቦታዎች ለማምራት ይገደዳሉ፡፡ እነዚህ ቦታዎች ደግሞ በየጥጋጥጉና በየመንደሩ ያሉና በቀላሉ ሊደረስባቸው የማይችሉ በመሆናቸው ደላሎች ያስፈልጓቸዋል፡፡ ይህንን የድለላ ተግባር የሚያከናውኑ በርካታ ወጣቶች እንደ ሜሪስቶፕስ ባሉ የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት በስፋት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች እየተዟዟሩ አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ሥፍራው የሚመጡትን ወጣቶች እየጠለፉ ይወስዳሉ፡፡
በእነዚህ አፈ ጮሌ ደላሎች ተደልለው ሄደው አገልግሎቱን ካገኙ ወጣቶች መካከል አብዛኛዎቹ እጅግ ለከፋ የጤና ችግርና ለሞት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ዛሬ ያለምክንያት አላነሳሁትም፡፡ በአገራችን ውርጃን /ፅንስ ማቋረጥን/ ሙሉ በሙሉ የሚፈቅድ ህግ ባይደነገግም፣ ሁሉም ሃይማኖቶች ስለውርጃ ያላቸው አቋም ተመሳሳይና ፈጽሞ የማይቀበሉት ቢሆንም፣ ፅንስ ማቋረጥ ዛሬም በአገራችን በግልጽና በስፋት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከተለያዩ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው፤በአለማችን ጽንስ ማቋረጥን ህጋዊ መብት አድርገው በመደንገግ ድርጊቱ ያለ እገዳ በግልጽ እንዲከናወን የፈቀዱ አገራት ሲኖሩ፣60 በመቶ የሚሆነው የአለማችን ህዝብ የሚኖረው ፅንስ ማቋረጥ ያለ እገዳ በሚፈፀምባቸው አገራት ውስጥ ነው፡፡
ከ25 በመቶ በላይ የሚሆነው የአለማችን ህዝብ ደግሞ ጽንስ ማቋረጥ ሙሉ በሙሉ በማይፈቀድባቸው አገራት ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ እነዚህ ጽንስ ማቋረጥን ህጋዊ መብት አድርገው የፈቀዱ አገራት ለዚህ ተግባራቸው የሚሰጧቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሏቸው፡፡ ከእነዚህ መካከልም፡-
የእናቲቱን ህይወት ለመታደግ
ፅንሱ በተዛባ ሁኔታ ካለና እናትየዋ የምትጐዳ ወይም ለሞት የምትዳረግ ከሆነ፤
2. አዕምሮአዊና አካላዊ የጤና ሁኔታ
እናትየዋ አዕምሮአዊም ሆነ አካላዊ የጤና ችግር ካለባትና የወለደችውን ልጅ ተንከባክቦ የማሳደግ አቅም የላትም ተብሎ የሚታመን ከሆነ፤
3. ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች
የእናትየዋ ኢኮኖሚ አነስተኛ መሆንና የሚወለደውን ልጅ ለማሳደግ አቅም ማጣት፣ በበርካታ አገሮች የጽንስ ማቋረጥ ተግባርን ህጋዊ ለማድረግ የሚጠየቁ መስፈርቶች ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጽንስ ማቋረጥ ተግባርን አስመልክታ፣ከዚህ ቀደም የፀደቀውን የወንጀል ህግ በማሻሻል በ1998 ዓ.ም ጥንቃቄ የተሞላበት ህጋዊ ውርጃን የተመለከተ መመሪያ አጽድቃለች፡፡
በዚህ መመሪያ መሠረትም የፅንስ ማቋረጥ በስድስት መሠረታዊ መስፈርቶች ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል፡፡ እነዚህ መስፈርቶችም፡-
ፅንሱ የተገኘው በአስገድዶ መደፈር አማካኝነት በተፈጠረ የግብረሥጋ ግንኙነት ከሆነ፤
በዘመዳሞች መካከል በተከናወነ የግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት የተፈጠረ ጽንስ ከሆነ፤
ፅንሱ ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር/ጉድለት ካለበት፤
እናቲቱ የአካልና የአዕምሮ ችግር ካለባት፤
የእናቲቱ ወይም የፅንሱ ህይወት አደጋ ላይ ከሆነና ይህም በእናቲቱ ጤና ላይ አደገኛ ችግር ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ከታሰበ፣
እናቲቱ ሕፃኑን ለማሳደግ በአካልም በአዕምሮም ብቁ አይደለችም ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ፡፡
እነዚህ ስድስት ነጥቦች ፅንሱን በህጋዊ መንገድ ለማቋረጥ እንዲቻል ፈቃድ ያሰጣሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ችግር ያለባት ሴት ፅንሱ እንዲቋረጥ በምትፈልግበት ወቅት እንዲቋረጥላት መጠየቅ ትችላለች፡፡ ለጽንስ ማቋረጥ ተግባሩ በሴቷ የሚሰጠው መረጃ ብቻ በቂ እንደሆነና የህክምና ባለሙያው ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ መጠየቅ እንደማይችልም ህጉ ይደነግጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ማንኛውም ጽንስ ማቋረጥን የፈለገች ሴት በፈለገችበት ጊዜና ሁኔታ ጽንሱን ለማቋረጥ እንድትችል ስለሚያደርጋት፣ ዛሬ ዛሬ ፅንስ ማቋረጥ እንደወሊድ መቆጣጠሪያ ከሚታይበት ደረጃ ላይ መድረሱን የማህፀንና የጽንስ ሃኪም የሆኑት ዶ/ር ፋሲል ተገኘ ይናገራሉ፡፡ “መንግስት ጽንስ ማቋረጡ ያለምንም ገደብና ክልከላ ህጋዊ እንዲሆን ከመፍቀድ ይልቅ ስለመከላከያውና ጽንስ ከመፈጠሩ በፊት ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች አብዝቶ በማስተማር ሴቶችን ሊያነቃ ይገባል፡፡ ጽንስ የማቋረጥ ሂደት ተያያዥ ችግሮችና ጉዳቶች እንዳሉትም ሊታወቅ ይገባል፡፡ ጽንስ ማቋረጥ በምንም ዓይነት ሁኔታ የወሊድ መከላከያ (መቆጣጠሪያ) ተደርጐ ሊታሰብ አይገባም፡፡” ይላሉ፡፡ ድርጊቱ ሙያው ባላቸው የጤና ባለሙያዎችና አዋላጅ ነርሶች አማካኝነት ሊከናወን እንደሚገባውም ዶ/ር ፋሲል ያሰምሩበታል፡፡
የጽንስ ማቋረጥ ተግባር ህጋዊ ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል ከሚሉ ድርጅቶች መካከል አንዱ “Ipas Ethiopia” የተባለው ድርጅት ነው፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት መመሪያውን አጽድቆ ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ ድርጅቱ ህጉ ተግባራዊ እንዲሆንና ህብረተሰቡም በመብቱ እንዲጠቀም የተለያዩ የቅስቀሳ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ከአመታት በፊት በውርጃ/ጽንስን በማቋረጥ ዙሪያ ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለማወቅ ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡ ጥናቱ ሲጠናቀቅ በተገኘው ውጤት መሠረትም አዲስ አበባ፣ ጐንደርና መቀሌ እንደቀደም ተከተላቸው ከፍተኛ ውርጃ/ጽንስ ማቋረጥ የተመዘገበባቸው ከተሞች ሆነዋል፡፡ ጥናቱ በቅርብ አመታት ውስጥ ቢከናወን ምናልባትም ይህ ሁኔታ ሊቀየርና ሌሎች ከተሞችም በጽንስ ማቋረጡ ተግባር ላይ ተሳታፊነታቸው ጐልቶ ሊወጣ ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን አብዛኛዎቹ ከተሞች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚፈፀሙ ድርጊቶች ሁኔታው ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ አመላካቾች ናቸው፡፡ በለጋ የወጣትነት ዕድሜያቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው፣ በየክልል ከተሞቹ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሚሄዱ ወጣት ሴቶች፣ ጥንቃቄ በጐደለው ወሲባዊ ግንኙነት አማካኝነት የሚፈጠረውን ያልተፈለገ ጽንስ ለማቋረጥና ውርጃን ለመፈፀም ዛሬም በየአካባቢው የሚገኙ ክሊኒኮችንና የልምድ አዋላጆችን ሲያስሱ ይገኛሉ፡፡
ወጣቶቹ “ለማስፈንጠር” በሄዱባቸው ቦታዎች የእነሱ ህይወትና ተስፋ ተስፈንጥሮ ለሞትና ለዕድሜ ልክ የአካል ጉዳት የተዳረጉትን ቤት ይቁጠራቸው። የወጣት ሴቶችን ህይወት ለመታደግና ያለአግባብ የሚሞቱትን ሴቶች ቁጥር ለመቀነስ፣ ውርጃን ህጋዊ ማድረግ የሚደገፍ ሃሳብ እንደሆነ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፤ “ያለጊዜውና ያለዕቅድ የተፈጠረው ያልተፈለገ እርግዝና ወጣቶቹን ከትምህርታቸው ሊያግዳቸውና ህልማቸውን ሊያሰናክልባቸው ስለሚችል፣ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማድረግ ህልማቸውን እንዲያሳኩ ማገዝ ይቻላል፤ያደጉትአገራትም ጽንስ ማቋረጥን ህጋዊ በማድረጋቸው ያጡት ነገር የለም። ዜጐቻቸው ያለአግባብ እንዳይሞቱ ከማድረግ ውጪ” ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ ይህንን ሃሳብ አጥብቀው የሚቃወሙ ወገኖች ደግሞ “ውርጃን ህጋዊ ማድረጉ በየትኛውም ሃይማኖትና ባህል ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ውርጃ ህጋዊ ሆነም አልሆነ በውርጃ ሳቢያ የሚሞቱ ዜጐችን ቁጥር ሊቀንስ አይችልም፡፡ ያደጉት አገራት ውርጃን ህጋዊ ቢያደርጉ ከባህላቸው፣ ከአኗኗራቸውና ከህብረተሰቡ የግንዛቤ አቅም ጋር አስተሳስረው ነው፡፡
ስለዚህም በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ውርጃ በህግ ሊደገፍና ሊፈቀድ አይገባም፡፡ ውርጃን ህጋዊ ማድረግ ማለት ሴቶች በሌሎች የእርግዝና መከላከያ መንገዶች እንዳይጠቀሙ ማዘናጋት ማለት ነው” ሲሉ መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ውርጃ ዛሬ በአገራችን ህጋዊ ማዕቀፍ ኖሮት በህግ የተደገፈ ተግባር ባይሆንም፣ በህግ የተከለከለም ተግባር አለመሆኑ ድርጊቱ በየቦታው በግልጽና በገሃድ እንዲፈፀም አድርጐታል፡፡
ለዓመታት በሁለት ወገን ከፍሎ ሲያጨቃጭቅ የነበረው የጽንስ ማቋረጥ ህጋዊነት ዛሬም መቋጫ ሣያገኝ አከራካሪነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡
ውርጃ በሀገሪቱ ህግና ደንብ ፀድቆ ማንኛዋም ሴት በፈለገችና በጠየቀች ጊዜ ሁሉ ውርጃን መፈፀም ትችላለች የሚል ህግ ወጥቶ የምናይበት ጊዜ ሩቅ ባይመስልም፣አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሴቷ ለጽንስ ማቋረጡ የምትሰጠው ምክንያት ብቻ ብቁ ሆኖ፣ ያለምንም ተጨማሪ ጥያቄ የጽንስ ማቋረጡ ሊከናወንላት ይገባል በሚለው ህግ ሥር ነን፡፡ ስለዚህም የጽንስ ማቋረጥ አዋጁ በአትኩሮት ሊጤንና ሊመረመር ይገባዋል፡፡
 
Source- Addis Admas

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.