ከአጋፔ
attract-300x211በዘመናችን ስለ ፍቅር ያለው ግንዛቤ እጅጉን የተዛባ ነው። ብዙዎቻችን ስለ ፍቅር ልናውቅና ልንማር የምንሞክረው ከልብ ወለድ ታሪኮችና ከፊልሞች ከመሆኑ የተነሳ ስለ ፍቅር ያለን ግንዛቤ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል። ፍቅር ለታይታ የሚደረግ፣ እንደ ዛር ለተወሰነ ጊዜ አንዘፍዝፎ የሚለቅ፣ ያለበለዚያም በብልጣብልጥነት እየተሸነጋገልን የምንኖርበት የኑሮ ስልት አይደለም። ስለ እውነተኛው ፍቅር ለመረዳት ብዙዎቻችን “ፍቅር” ብለን የምንጠራቸው ነገር ግን ፍቅር ያልሆኑትን ሁለት ነገሮች እንመልከት።

1. ስሜት
በልብ ወለድ መጻሕፍት የምናነበው፣ በፊልሞች የምንመለከተው በተለይም በተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚፈጠር አንዳንድ ጊዜ እራስን እንኳን ለመቆጣጠር የሚያስቸግር ስሜት አለ። ብዙ ሰዎች በወጣትነት ዘመናቸው ወደተቃራኒ ፆታ እንዲሳቡ የሚያደርጋቸው ይህ ስሜት ነው። የወደዱትን ሰው ገጽታ ወይም ድምፅ በተደጋጋሚ ማየት መስማት ያስደስታቸዋል። የወደዱትን ሰው በልባቸው አንግሰው ከዚያ ሰው ውጪ መኖር እንደማይችሉ ወይም ሊኖሩም ቢሞክሩ ሕይወታቸው ጐዶሎ እንደሚሆን ይሰማቸዋል። የወደዱትን ሰው ላለማጣት ቢያስፈልግ የሕይወት መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደሚችሉ እራሳቸውን ለማሳመን ስለሚጥሩ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ይላሉ። ከወደዱት ሰው ሊለያቸው የሚችል ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ህግ ቢኖር እንኳ ኃሳባቸውን መመለስ ይሳናቸዋል። ስሜቱ እየፀና ሲሄድ የእለት ተግባራቸውን በሚገባ ማከናወን መብላትና መጠጣት ጭምር ሊያቅጣቸው ይችላል። በማንኛውም አጋጣሚ የሚያዩትንና የሚሰሙትን ጥሩ ምግባር ሁሉ ከወደዱት ሰው ጋር እያቆራኙ ስለሚመለከቱ የወደዱት ሰው እንከን የሌለበት ነው ብለው እራሳቸውን ያሳምናሉ። ይህ ስሜት /ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም/ መስዋዕትነት ለመክፈል ሊያደርስ ይችላል። በእርግጥም ይህ ዓይነት ስሜት ለጊዜው ጥቅም ፈላጊ አይመስልም።

እውነታው ግን ከዚህ ስሜት ጀርባ ያለው “ጥቅም” ነው ግለሰቡን ለመስዋዕትነት የሚያዘጋጀው። ለዚህ አፈቀርኩ የሚለው ሰው እራሱ እንኳን በግልጽ ለማይረዳው ጥቅም ሲል “የፍቅረኛውን” ነፃነትና መብት ይጋፋል እንጂ አይሆንም ቢባል እንኳ መተው አይችልም። ይህ ስሜት ፍቅር ያለመሆኑን ማረጋገጥ እና ስሜት ውስጥ በገባው ሰው ጥቅም ላይ የተመሰረተ አልፎ ተርፎም ሰይጣናዊ ሊሆን እንደሚችል መረዳት የሚቻለው የመጨረሻው እርምጃ እራስን ወይም አፈቀርኩ የሚሉትን ሰው እስከ ማጥፋት የሚያሳስብ መሆኑ ነው። ይህ ስሜት ብዙዎችን በወጣትነት ዘመን የሚይዛቸው በመሆኑ ፍቅር ያዘን ብለው ሲንገላቱበት ይታያል። ከዚህ ስሜት የተነሳም የብዙ ወጣቶች ሕይወት ሲበላሽ ይታያል። በዚህ ስሜት ውስጥ ያሉ ሁለት ወጣቶች ሲገናኙ የዚህን ስሜት እሳት እያራገቡ ለተወሰነ ጊዜ ሲሟሟቁ ይቆያሉ። አልፎ ተርፎም ትምህርታቸውን፣ ቤተሰባቸውን ወይም ሥራቸውን እስከመተው ይደርሳሉ። እየቆዩ ሲሄዱ ግን እራሳቸው አራግበው ያነደዱት የስሜት እሳት እየከሰመ ይሄዳል። ከዚያም ለመለያየት እርስ በእርሳቸው ሰበብ ይፈላለጋሉ። በተለይም ይህንን የስሜት ረመጥ ሲያራግቡ ወደ ቅድመ ጋብቻ ወሲብ ከተሸጋገሩ ስሜታቸው ውሃ የተደፋበት ያህል ወዲያው መቀዝቀዝ

ይጀምራል። መናናቅ ወይም መተቻቸት ይጀምራሉ። ለምሳሌ እርግዝና ቢከሰት እርስ በእርሳቸው መወቃቀስ ይጀምራሉ። ምናልባትም ተደናግጠው ለመጋባት ቢወስኑ እንኳን ያላሰቡትና ያልተዘጋጁበት ውሳኔ ስለሚሆን ዘላቂነቱ አጠራጣሪ ይሆናል። ይልቁንም የዚህ ዓይነቱ ክስተት በመንፈሳዊ ወጣቶች መካከል ሲከሰት የተማሩትና ሊጠብቁት ይመኙት የነበረውን ሕገ እግዚአብሔርን መጣሳቸውን ሲገነዘቡ ተስፋ በመቁረጥ በኃጢአተኝነት ስሜት እራሳቸውን ሲወቅሱ ይገኛሉ። ከነበራቸው መንፈሳዊ አገልግሎትና ዓላማም ይለያሉ። እነዚህ ወጣቶች ሲያንገላታቸው የነበረው ስሜት እንጂ ፍቅር ያለመሆኑን የሚገነዘቡት ስሜቱ ሲበርድ በመሆኑ ስለ ፍቅር ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ሆኖ ሊቀር ይችላል። አንዳንድ ጊዜም በህይወት ዘመናቸው ሁሉ ስለ ተቃራኒ ፆታና ስለ ፍቅር ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ሆኖ የሚዘልቅበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል።

2. ጓደኝነት
ሰዎች ጓደኝነት የሚመሰርቱት ወይም የጀመሩትን ጓደኝነት የሚያፀኑት በአብዛኛው ስሜታቸውን የሚረዳና በጋራ የሚያስማማቸው ነገር ሲኖር ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ አንዳቸው የራሳቸውን አስተሳሰብና ጠባይ እየተው የጓደኛቸውን ይከተላሉ። ቀድመው ይጠሉት የነበረውን ነገር በጓደኛቸው ምክንያት እየወደዱት ቀድሞ የያዙትን ምግባር ትተው የጓደኛቸውን ምግባር ይከተላሉ።
በአጠቃላይ በክፉም ሆነ በደግ መጽሐፍ “ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከክፉ ጋር ክፉ ሆነህ ትገኛለህ” እንዲል ባልጀራቸውን ይመስላሉ። ለዚህ ነው ፈረንጆቹም “ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ” የሚሉት።

በጓደኝነት ለብዙ ዓመታት መቆየት ያቀራርባል። በጋራ የሚስማሙበት ነገር እየበዛ ስለሚሄድ ምስጢር መጋራት፣ በሀዘንና በደስታ መረዳዳት ይኖራል። ብዙ ገጠመኞችን መጋራ ማሳለፍ ስለሚኖርም እስከ ህይወት ፍፃሜ የማይረሱ ትዝታዎችን ማፍራት ይቻላል። ሆኖም ግን ይህ ግንኙነት በፈተናዎች ውስጥ አብሮ ለመዝለቅ አስተማማኝ አይደለም። ከሁለቱ ጓደኛማቾች የአንዱ የህይወት ፍልስፍና ሲቀየርም ያስተሳሰራቸው የጓደኝነት ክር እየላላ ይመጣና ሁለቱም የየራሳቸውን መንገድ መከተል ይጀምራሉ። ሁለቱም ከሃሳባቸውና ካሉበት ሁኔታ ጋር የሚስማማ አዲስ ጓደኛ አፍርተው ይኖራሉ። ይህ ዓይነቱ ጓደኝነት በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ጊዜን ለማሳለፍ እንጂ ከዚያ ያለፈ ግብ ስለማይኖረው ማንኛቸውን ጓደኝነቱን ለማጽናት የሚያስፈልግ መስዋዕትነት ቢኖር ለመክፈል አይገደዱም። በጓደኝነት ውስጥ መዋደድ ሊኖር ይችላል። ፍቅር ተብሎ ለመጠራት ግን ሚዛን አይደፋም።

Source- Zehabesha.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.