ስሜ ስምረት ይባላል፡፡  እንድታማክሩኝ የምፈልገው መልከ ጥፉ የምባል ሰው ነኝ፡፡ ከሌሎች ሴቶች ጋር መልኬን ሳወዳድርና እራሴን በመስተዋት ስመለከት በተፈጥሮዬ እናደዳለሁ፡፡ ብቸኛዋ አስቀያሚ ሴት እንደሆንኩ አድርጌ ስለማስብ ሁሌም እበሳጫለሁ፡፡ እርግጥ በትምህርቴ እጅግ ውጤታማ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል አንዷ ነኝ፡፡ ነገር ግን በህይወቴ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ሁሉንም ጓደኞቼን ስመለከት የለበሱት ሁሉ ያምርባቸዋል፡፡ ሁሉም ነገራቸው የተስተካከለ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሁሉም የፍቅር ጓደኞች አላቸው፡፡ ታዲያ ከፍቅረኞቻቸው ጋር ስላለፉት ጊዜ ሲተርኩልኝ እኔስ መቼ ነው ይህንን ነገር የማየው እያልኩ እከፋለሁ፡፡ እንደዚህ አድርጎ የፈጠረኝን አምላኬንም አማርረዋለሁ፡፡ ወንዶች ጓደኞቼ ላይ ይረባረባሉ እንጂ እኔን አይመለከቱኝም፡፡ ይሄ ነገር ደግሞ እራሴን እንድጠላ እያደረገኝ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በሚታሰበው በላይ ተጨንቄያለሁ፡፡ እንደው ምን ባደርግ ይሻለኛል? በአፋጣኝ ምክርህን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡

ስምረት ነኝ

ውድ ስምረት በቅድሚያ እንደዚህ አይነቱ ችግር የአንቺ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ሴቶች ችግር እንደሆነ ማወቅ አለብሽ፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ የተለያየ ነው፡፡ አንቺም እራስሽን ከሌሎች ሴቶች ጋር ስለምታወዳድሪ ለባሰ ጭንቀት ያጋልጥሻል፡፡

ውድ ስምረት የስነ ልቦና ባለሞያዎች መሰል በተፈጥሮ የተገኘ የእራስን አካላዊና የፊት ገጽታ አለመቀበል እና ደስተኛ አለመሆን እና አስቀያሚ ነኝ እያሉ በተደጋጋሚ የማሰብ ችግር ‹‹ቦዲ ዳይሰሞርፊከ ዲስኦርደር›› በማለት ይጠሩታል፡፡ ይህ ችግር ቀላል የአዕምሮ ችግር ተብለው ከሚታወቁት የአዕምሮ ህመም አይነቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ዋነኛ መገለጫውም በተፈጥሮ በተገኘ አካላዊ ገጽታ ደስተኛ አለመሆን እና በተደጋጋሚ የሚያንሰኝ ነገር አለ ብሎ ማሰብ ነው፡፡

ውድ ስምረት ይህ አይነት ችግር ያለበት ሰው አንድ የሰውነት ክፍሉን ወይንም ሁሉንም የሰውነት ክፍሉን ሊጠላ እና በተፈጥሮው ሊከፋ ይችላል፡፡ ይህ መከፋት ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜትን በመሸርሸር ከሰው ጋር ለመግባባት መቸገርን እና ስራን በአግባቡ መስራት እንዳንችል ሊያደርገን ይችላል፡፡ ይህ ችግር በተለያየ ምክንያት ሊከሰት የሚችል ሲሆን የግለሰቡ ያለፈ ወይንም የአሁን ተፈጥሯዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ግን ችግሩን በማባባስ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአእምሮ፣ በአካል እንዲሁም በስሜት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ይህንን መሰል ችግር ያስከትላሉ፡፡ በአጠቃላይ ይህ አይነቱ በራስ ተፈጥሯዊ ውበት ደስተኛ ያለመሆን ችግር ሶስት የአካል ክፍሎች ላይ በብዛት ይንፀባረቃል፡፡ በፀጉር ርዝመት እንዲሁም ተፈጥሮ፣ በቆዳ ቀለም እና በአፍንጫ አቀማመጥ እና ተፈጥሮ ላይ ደስተኛ አለመሆን፡፡

አንቺም በደብዳቤሽ ላይ በየትኛው የአካል ክፍልሽ ደስተኛ እንዳልሆንሽ በግልፅ ባታስቀምጪም ከእነዚህ የአካል ክፍሎችሽ ውስጥ ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን፡፡ በቅርቡ በጀርመን አገር የተደረገ አንድ ጥናት እንደጠቆመው ይህን አይነት አስተሳሰብ ይዘው ወደ ባለሞያ ከሚቀርቡ በርከት ያሉ ሰዎች ውስጥ ብዙዎቹ እነሱ እንደሚያስቡት አስቀያሚ እንዳልሆኑ ይጠቁማል፡፡ ስለዚህ አንቺም፣ አንቺ እንደምታስቢው አስቀያሚ እንዳልሆንሽ እገምታለሁ፡፡ አስቀያሚ ነኝ እያልሽ ማሰብ ማቆም አለብሽ፣ ችግርሽ እንዲባባስ የሚያደርገው ደግሞ በተደጋጋሚ አስቀያሚ ነኝ ብለሽ ለራስሽ የምትነግሪው እምነትሽ ነው፡፡

ውድ ስምረት ሁሉም ሰው ቆንጆ እና ተፈላጊ መሆንን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ቆንጆ አይደለሁም ብሎ ስላሰበ ብቻ ‹‹የቦዲ ዳይስሞርፊክ ዲስኦርደር›› ችግር አለበት ማለት አንችልም፡፡ አንድ ሰው የቦዲ ዳይስሞርፊክ ዲስኦርደር ተጠቂ ነው ብሎ በትክክል ለመደምደም እና ወደ ህክምናው ለመሄድ የሚከተሉት ምልክቶች መንፀባረቅ አለባቸው፡፡ ስለዚህ አንቺም ከዚህ ቀጥለው ከተዘረዘሩት የቦዲ ዳይስሞርፊክ ዲስኦርደር ምልክቶች በአንቺ ላይ የሚታየውን በትክክል መለየት ይኖርብሻል፡፡

– የፊቴ ወይንም የአካሌ ገጽታ እጅግ የተበላሸ ነው ብሎ ያለማቋረጥ ማሰብ

– ተፈጥሯዊ ውበቴ አስጠሊታ ነው ብሎ ማሰብ ተከትሎ እራስን ከማህበራዊ፣ ቤተሰባዊ እንዲሁም ከሌሎች መሰል ተግባራት ማራቅ እና በተደጋጋሚ እራስን ስለማጥፋት ማሰብ ወይንም የማጥፋት ሙከራ ማድረግ

– ስለውበት እና ቁንጅና ሲነሳ በድንገት መደንገጥ እና መፍራት፣ በተደጋጋሚ የአስቀያሚነት ጥሩ ምሳሌ ነኝ እኮ ብሎ ማሰብ

– ለራስ አነስተኛ ግምት መስጠት እንዲሁም ከሰዎች ጋር ስንሆን የሀፍረት ስሜትን ማስተናገድ

– ከቤትም ሆነ ከዶርም አካባቢ ሰዎች ስለእኔ ሊያወሩ ይችላሉ በሚል ስጋት ከቤት አለመውጣት ስራንም በሚያስፈልገው የትኩረት መጠን መስራት አለመቻል፡፡

ስምረት እንግዲህ እነዚህ ምልክቶች የሚታዩበሽ ከሆነ የቦዲ ዳይስሞርፊክ ዲስኦርደር ችግር አለብሽ ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል ለመጠቆም እንደሞከርነው እንደ አንቺ ያላቸውን ተፈጥሯዊ የፊት እና አካላዊ ገጽታ የማይቀበሉ ሰዎች እንደሚያስቡት አስቀያሚ አይደሉም፡፡ እንደውም በሌላ ሰው እይታ ሲታዩ ቆንጆ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ እነሱ ግን እያንዳንዷን ግድፈት አጋነው ስለሚያስቡ ወይንም ግድፈት እንኳን ባይኖር አይናቸውን ወይንም አፍንጫቸውን ወይንም ከንፈራቸውን አሊያም ሌላ የሰውነት ክፍላቸው ለእሱ በሆነ ምክንያት አስቀያሚ መስሎ ይታያቸዋል፡፡

ስለዚህ በተቻለን መጠን የመጀመሪያ ምርጫችን ሊሆን የሚገባው ያለንን ተፈጥሯዊ የፊት ገጽታ እና አካላዊ ተፈጥሮ አምነን መቀበል ነው እንጂ መለወጥ በማንችለው ተፈጥሯችን መጨነቅ እና መረበሽ አይኖርብንም፡፡ ይህ ማለት ለምሳሌ የሚያስጨንቀን የቁመታችን ማጠር፣ የቆዳችን ቀለም መጥቆር ወይንም ሌላ ከሆነ ይህንን ተፈጥሯችንን መቀየር ስለማንችል ያለንን ተፈጥሮ መቀበል ነው ያለን የመጀመሪያ አማራጭ፡፡ እንደውም እኛ እንዳስጠላ ያደረገኝ ይሄ ተፈጥሮዬነው ብለን የምናስበውን ግድ ፊታችንን እንደ መገለጫችን አድርገን ነው መውሰድ የለብንም፡፡ ቁመታችንን መጨመር አንችልም የቆዳችንን ቀለም እንደዚያው መቀየር አንችልም፡፡ ስለዚህ ያለንን ቁመት እንዲሁም ያለንን የቆዳ ቀለም ተቀብለን ያለን ተፈጥሮ ውስጥ ስላለው

ውበት ነው ማሰብ የሚገባን፡፡

ሌላው አንቺ ስለውበት ያለሽ ግንዛቤ ትንሽ የተዛባ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አንቺ ውበትን በውጫዊ ውበት ብቻ ነው የለካሽው፡፡ ነገር ግን ውበት የተስተካከለ የፊት እና አካላዊ ገጽታ መኖር ብቻ ሳይሆን የተስተካከለ ፐርሰናሊቲ መኖርም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ አንቺም በትምህርትሽ ውጤታማ መሆንሽ በራሱ እንደ አንድ ውበት ልትመለከቺው ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ እራስሽን በፍፁም ከሌሎች ሰዎች ጋር አታነፃፅሪ፡፡

በዚህ ጉዳይ ተረብሸሽ ከትምህርትሽም ሆነ ከሌላ ህይወትሽ ብትስተጓጎዬ እራስሽ ነሽ የምትጎጂው ስለዚህ ከዚህ ሀሳብ እራስሽን አርቂ፡፡ እርግጥነው በዩኒቨርሲቲ ህይወት ውስጥ የግድ መደረግ አለባቸው ተብለው የሚታሰቡ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህ ነገሮች አንዱ የተቃራኒ ጾታ ጓደኛ መያዝ ነው፡፡ በመጀመሪያ ይሄ ነገር ግድ ነው፡፡ ከሄድኩበት አላማስ አያስተጓጉለኝም ወይ? ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ እንደማያስተጓጉለን እርግጠኛ ከሆንን ደግሞ የወንድ/ፍቅረኛ እንዴት እንደሚያዝ እና ወንዶች እንዲቀርቡን ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል፡፡

ፍቅረኛ እንዲኖረን የምንፈልግ ከሆነ እና ጥሩ የሚባሉ ወንዶች እንዲቀርቡን የምንፈልግ ከሆነ በቅድሚያ የሚከተሉትን ነገሮች እንገንዘብ፡፡

– እንዲኖርሽ የምትፈልጊውን የወንድ ጓደኛ አይነት ለይተሽ እወቂ፤ ምን አይነት ወንድ ነው የምትፈልጊው? ጥሩ ቁመና ያለው፣ አዋቂ የሆነ፣ ተጫዋች እና ቀልድ አዋቂ የሆነ እራሱንም ሆነ ሌሎችን የሚያከብር እያልን እንዘርዝራቸው

– ከዚያ አንቺ እንደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪነትሽ የምትፈልጊውን አይነት ወንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዴት እና የት ነው የማገኘው ብለሽ አስቢ፡፡ ላይብረሪ የመጀመሪያ ምርጫሽ ሊሆን ይችላል፡፡

– ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚዘወተርባቸው ቦታዎች ላይ መገኘት ጥሩ አማራጭ ነው

– አሁን ደግሞ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው፡፡ ፌስቡክን የመሳሰሉ የማህበራዊ ድህረ ገፆችም የፍቅር አጋርን የምናገኝበት ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥንቃቄ ማድረግ ቢኖርብንም፡፡

Source- Zehabesha.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.