…በበሬ ክፍተት የገባው የጠዋቱ ብርሃን ስለታም ሰይፉን ወድሮ ከወለሌ ላይ እንደጠገበ ጐረምሣ ተገትሯል፡፡ 
“ውጪ ውጪ” የሚለው ስሜቴን መግረዝ አልቻልኩም!…በደረቴ ተኝቼ የማነበው የአረጋሽ “ያላለቀው ዳንቴል” መጽሐፍ መስጦኛል…፤ ግን በመሀል ይሔ ሐሳብ እንዴት ሊመጣብኝ ቻለ…? አሃ…ይሔ ፍርድ አወቅ ነዋ” መጽሐፉ ውስጥ ያለው አንኳር ገጸባህሪ ነው፡፡ “ዛሬ እጮኛዬ ነሽ…ነገ ደግሞ ሚስቴ” ያላትን በዚህ በሰንበት እረፍቷን አወጀላት (የልቡ ካላንደር ላይ) ቤቱ ውስጥ ጉድ ጉድ እያለ ነው፤ እሷማ እሷ ናት…
የጡት ማስያዣዋን እና ሙታንታዋን ሲያጥብላት…የሆነ የቅናት መንፈስ ውስጤን ሰቀዘው፤ አናወጠችኝ፡፡ እሷ ደግሞ እንዲህ ሲሆን ግማሽ ሴትነቷን የተጋራት እየመሰላት አስታዋሽ እንዳጣ ወተት አልጋው ላይ ተጥዳ ተበጣጥሳለች! አትወደውም…ግን ደግሞ ትወደዋለች…”ንጉሤ” ትለዋለች፤ አልጋ ላይ ሲሆኑ፡፡ ዳንቴልነቷን ይተረትርላትና እንደገና…
“እንደዚህ በላይሽ ላይ ወፍ አትብረር የምለው…ቅናት እንዳይመስልሽ…እረፍትን እንድታጣጥሚልኝ ስለምፈልግ እንጂ…እንደ ድሮ ወንዶች ከስራ ብር ብለሽ መጥተሽ…እቤት ውስጥ ተንደፋድፈሽ ሆዴን እንድትሞይልኝ…የሥጋ ሥሜቴን እንድታረኪልኝ ጠልቼ አይደለም…በሥራ እየባተልሽ ድስትሽ ሲገነፍል…
“ማነሽ ድስቱ ገነፈለ ማለት ቀላል ነው…” ቲቪ ውስጥ ሆኖ የሚተውን ተዋናይ መሠላት…የሌባ ጣቷን ወደፊቱ ቀስራ …“ና” አለችው፣ እሱም መደስኮሩን ትቶ እንደታጠቀ ወታደር በተጠንቀቅ ሄደላት፡፡ 
“እዚህ ላይ ጥብቅ አድርገህ ሳመኝ?” ያተኩሳል። ከተባለው ቦታ ሌላ አንገቷ ስር ሳማት… አይኗን ጨፍና ትስለመለማለች፡፡ 
ወደ ደረቷ እየተንሸራተተ …ይቃኛታል፤ ክራሩ በአግባቡ “ትዝታን” ይደረድራል፡፡ 
ሁለቱም እኩል ያዜማሉ፡፡ ከት ብለው እንደመሳቅም አይነት፡፡ ደስ የሚል ሳቅ… ከተራራ ላይ እንደነጋሪት ሲጐሰም የሚሰማ፡፡ ለምን ሳቅ ከነጋሪት ጋር ተገናኘ የሚለኝ ካለ መብቴ ነው! እንደውም አፄ ምኒልክ አድዋ ይዘውት የዘመቱትን ሰራዊት ይመስላል…አተማመሙ፡፡ እና እንደ አብሪ ጥይት በጥቀርሻ ሰማይ ላይ “ጢው” ብሎ እንደሚጠፋው ማለት አለብኝ?… 
በሰፊው መሬት ላይ አንድም ወጣ ገባ በሌለው፣ ደረቱን ለሰማይ አስጥቶ እንደጐረምሳ ደረት በፀጉር እንደታጀበው፣ መሬቱም በለምለም…የሳቀ ሳር አጊጧል፤ የመሬቱን ውበት በለስላሳ ጣቷ ገብታ ሳሩ ውስጥ የምታርመሰምሰዋ ፀሐይ፣ አበሻ ቀሚሷን በጥለት ባጌጠ የሳቅ መቀነት ሸብ አድርጋ ልቧ እስክስታ እየደለቀ ነው፡፡ 
ወድቆ የነበረው የአክሱም ሐውልት ቆሟል፡፡ የሷም የስሜት ቀስት ተወጥሯል፡፡ 
እንኳን የአዳም ፍጥረት ቀርቶ ተፈጥሮም ስትስቅ ለብዙ ዘመን ስንቅ ይሆናል፡፡ እንዲህ በንፁህ ልብ ሸራ ላይ ያልሳሉት ሥዕል መልክ አልባ ይሆናል… የክራሩ ድምጽ ቀነሰ …ሳቋ እርካታን እያለከለከለ…ሰማዩ ደረት ላይ ተዘረረ…ሰማይ ደግሞ ሃበሻ ነው፡፡” 
ይሔን ገጽ መላልሼ አንብቤዋለሁ፡፡ እቺ አረጋሽ የፍቅር አገላለጿ ተመችቶኛል፡፡ የእርካታው መረብ እኔንም ሳያጠምደኝ አልቀረም፣ 
ማናት ሰላም ባለው ፍቅር እማትቀና? ማናት ሳቋ እንደማታዋ ፀሐይ ወርቃማ እንዲሆንላት እማትመኝ? ማናት ነፃነቷን እሚያውጅላት ወንድ ማትሻ…? ማናት መብቷን እስከመገንጠል እንዲዜምላት አብራ እማታዜም ርግብ…?
ማናት ለባሏ አባወራ ሆና፣ እማወራ ባል ማታልም…? ይሄ ሁሉ ነፃነት ለነፃነት ቀለም አጊጦ በጠራ ሰማይ ላይ ያለከልካይ ሲስቅ…አቦ የምር ቀናሁባት፣ ፍርድ አወቅን ብነጥቃት…እቺ ከረፈፍ ተሰጥቷት ምላሹን ንፉግ የሆነች…እንዳንቀላፋች በደንብ አስተኝቼ ውዱን የእኔ ባደርገው ተመኘሁ፡፡ 
ሳስበው…ያጣችውን በሙሉ ሰጥቷታል…ምንም ስለሌላት ለመቀበል አቅሙ አልነበራትም…በባዶ ሜዳ እናቷ እንደሞተችባት ጥጃ ባተለች…
ሸክላ በሸክላ ሠሪው ላይ የማመጽ ምንም መብት የለውም! ሲፈልግ መልሶ መላልሶ…ያቦካካዋል…ጥሩ የአበባ ማስቀመጫን ጀበና በማድረግ፡፡ ”ደከመኝ” ስትለው ከበር ጀምሮ እቅፍ ያደርግና መኝታ ቤት አስገብቶ…ልብሶቿን ቀይሮ፣ እግሯን ለብ ባለ ውሃ አጥቦ…እየኮረኮራት ያስተኛታል…አስቆ፡፡ እሷ ግን ከመተኛቷ በፊት ምንም አይነት ጣዕም ሳታቀምሰው ማንኮራፋቷን ትጀምራለች፡፡ እንዳይበርዳት ግልጽነቱን “በፍቅር ጋቢ ጀቡኖ ያለብሳትና ሥትነሳ ለምትጐርሰው ይሯሯጣል፡፡” እና ፍርድ አወቅን ብወደው አይደለም ባፈቅረው ቅር የሚሰኝ አለ…?
“ወድቃ የተገኘች ልጅ ናት… ምስኪን መሀን አሮጊት …ከገንዳ ውስጥ አውጥተውኝ ከጉንዳን ቀምተው ማድቤት ውስጥ አመድ ልሰው አሳደጓት፡፡ 
ፍርድ አወቅ ያገኛት…ጨርቅ እና እንትኗን የቀደደችለት ጐረምሣ…ሠርክ እየሰከረ እንትኗን የቀደደበት የጌሾ ጫካ ውስጥ ያለ ርህራሄ እንትን ካረጋት በኋላ…አይንሽን ለጌሾ ብሏት የጠፋ ጊዜ ነበር፤ ያውቀዋል ጐረምሣውን…እሷንም ጠንቅቆ። ታዲያ ለምን ውሃ ላኝክ? አጥሚት ልቆርጥም ያሰኛታል?”
ተመልሼ መቶ አስራ አንደኛው ገጽ ላይ ያነበብኩት ነው፡፡ እቺን እርጥብ ነው የወደደው…
“የህሊናዬን ለውጥ የማየው ውስጤን ሳፀዳው ነው፡፡ አሁን የገባኝ መንፃት፣ ዓይኔ ላይ የተጋረደው ሩቅ አለመመልከት…ማንም የለጠፈብኝ አይደለም፤ እኔ መግፈፍ ስላልቻልኩ እንጂ እኔ ውስጥ እነዛ የወለዱኝ ነበሩ…እነሱ ሳያንሱ ራሴን ጠልፎ ለመጣል እሮጥ ነበር…ይመጣል ብዬ ስጠብቅ አልሄድኩምና ቀረ…”
ተስገብግቤ የመጨረሻውን ምዕራፍ ሳነበው ነበር የዋህነቷን ሞኝነቷ ጠልፎ እንደጣለባት ያወቅሁት፡፡ የሆነ ተስፋ ተሰማኝ … ፍርድ አወቅን ፈልጐ ለማግኘት…ያወቅሁትን እንዳላወቅሁ አስቤ ተመለስኩ ወደ ንባቤ…
“የሰማዩ ስፋት የሚታይህ ባጠበብከው የአይንህ መጠን ነው…አዕምሮህም ርቆ የሚሄደው አንተ በለካኸው ተበጣሽ ክር እንጂ በብርሃን ልኬትህ መጠን አይደለም፤ አርዝመን ካሰብን ሰፊ መሰብሰብ እንችላለን… ራሳችንን ለመደሰት ካላዘጋጀነው ጉልበታችንን አቅፈን ቁጭት እናዜማለን፣ ፍርድ አወቅ እንደዛ አይደለም፣ 
እስክስታ እሚመታ ሳቅ ካማረህ በፍርድ አወቅ የዋህነት መጠለል ይኖርብሃል፤ ለእውነተኛ ፍቅር ተንበርክኮ መገዛት ካሰኘህ ፍርድ አወቅን መሲህ አድርገው፤ ፍርድ አወቅ ሲወድ የምሩን ነው፡፡ ሲሰጥ አይሰስትም፡፡ 
ሲስቅ ህዝባቸው ላይ ቂም የፀነሱ መንግስታት ካዩት ይቅርታ ይጠይቃሉ፤ የበደሉትን ህዝብ፡፡ ፍቅር ሲሰራ…ስልጣን ላይ ችክ ያለን ገዢ ያላንዳች ማንገራገር 
“በቃኝ”ን ያስመኛል፡፡ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ቢሰሙት በዘር፣ በሀይማኖት፣ በመሬት … መሻኮት ከንቱነት መሆኑን ይረዳሉ…ብቻ ፍርድ አወቅ ጋ ሳቅ…በጥለት ያጌጠ የሀገር ልብስ ነው፡፡”
እቺ አረጋሽ እንዴት አባቷ ነው እምትገልፀው! እርግጠኛ ነኝ ፍርድ አወቅ ላይ ፎንቃ ገብቶላታል…እናቷንና! እሷ ነሁልላ እኔንም አነሆለለችኝ እኮ…፡፡
“ወድቀሽ ስለተገኘሽ ክብር አይገባሽም አላልኩሽም፣ ሴት ልጅ ፈቅዳና ወዳ ክብሯን ካልጣለች በቀር…አክሊል ናት፤ ግን ሳታውቀው ይሁን አውቃው ምቾት አደናቅፎ ይጥላታል፣…ያኔ እንኳን ራሷን ችላ ለመቆም ቀርቶ ተረባርበው ቢያነሷት እንኳ ፈቅዳ ወድቃለች እና ውዱቅ ናት። ማናችንም ስንወለድ እማናውቀው ሰው እጅ ላይ እንወድቃለን…ከዛ በኋላ ነው…ህይወት ራሷ ብቅልና ጌሾ ሰብስባ…” ጌሾ ሲል ልቧ በረገገች…እፍ የተባለ ገለባ ይመስል…አይኖቿ እየጠበቡ መጡ…ሀይል እንዳጠረው አምፖል፡፡ 
“እሚጥምም … እሚጐመዝዝም ‘ህይወት’ የምትጠነስሰው፡፡ በመንገዳችን ላይ ራሳችን ደንቃራ እንሆናለን … ለራሳችን …” እሱ የመኝታ ቤቱ ምንጣፍ ላይ ዝርፍጥ ብሎ ተቀምጦ … እሷ ያማረ የአልጋ ልብስ በከፊል ደርባ አልጋው ላይ ናት … እንዲህ ቁም ነገር እያወራ ተኛች … እያንኮራፋች …፣ እንዲበርዳት አልፈለገም … የተለመደ ደግነቱን አልነፈጋትም። አልብሷት ትራሱን አመቻችቶ …ወጣ፣… ሥትነሣ እምትቀምሠው ለመሥራት፡፡” 
አሁን ሙሉ በሙሉ ቤቴን ጐረምሳው ብርሃን ተቆጣጠረው … ለረጅም ሠዓት በደረቴ ስለተኛሁ ነው መሠለኝ ጡቶቼን የህመም ሥሜት ተሠማኝ … “ውጪ! ውጪ!” የሚለኝ ስሜት በመጠኑም ቢሆን ትዕግሥት ያገኘ ይመስላል … “ያላለቀው ዳንቴል”ን ይዤ ተነሳሁና የቤቴን መስኮት ከፈትኩ … ነፋስ ጐበኘኝ … ጐረምሣው ‘እፎይ’ ብሎ ተደላደለ። እኔም ውስጤን የሆነ ነገር ተሠማኝ … ‘ውጪና አግኚው…’ ደግሞ ቁርስ መብላት አማረኝ፤ የቀረኝን … ተስገብግቤ መጨረሻውን ባነበውም … ትንሽ ገፅ ነው …፣ ማቋረጥ ፍርድ አወቅን መበደል መሠለኝ … ያቺ ከረፈፍ እማ ወየውላት …!
ተመለስኩ … በልቤ እየሳቅሁና እያፏጨሁ … ወደ ንባቤ … ትራሴን አመቻችቼ ካቆምኩበት ቀጠልኩ … የጣፈጠኝን አገላለፅ ደጋግሜ አጣጥሜዋለሁ፡፡
“ቢያንስ ያዘዝኩሽን ደስተኛ ሆነሽ መፈፀም ነበረብሽ …” 
“ረሳሁት!” ትዕቢት ልቧን ነፍቷታል፡፡ በጭቃ አለም እሚረገጥ ድንጋይ ሲገኝ ማን ያላቁጣል! 
“እንዴት ሰው ለራሱ የራሱን ጉዳይ ይረሳል…?” በዓይኑ እውነት ረጨላት፡፡ 
“ውይ ፍርድ አወቅ አትጨቅጭቀኝ!… ለምን መጣሽ ከሆነ እሄድልሃለሁ…” አተኩሮ ተመለከታት … ሔዳስ …? የት ነው ማረፍያዋ? … ዛፉ እሱ ብቻ ነበር … የትም አትሔድም ብሎ አልነበረም የወደዳት … ከልቡ ጥላ ያስጠለላት፡፡ ለራሷ ብሎ ነበር፡፡ 
“የቀረብሽ አንቺው ነሽ …” እየተመናቀረች ወደ መኝታ ቤት ገባች … ጫማዋን ሳታወልቅ … እግሯ መሬት እንዳለ በጀርባዋ ተጋደመች … ቀስ ብሎ ተከትሎ ሲቃኛት … ፊቷን በከፊል በሻርፕ ሸፍና ተደብቃለች … ከማን? ከህሊና…? ወይስ ካፈጠጠባት እውነት …? ተመልሶ ለብ ያለ ውሃ ይዞ መጣ … እግሯን ካጠባት በኋላ በፎጣ እያደራረቀ … እቅፍ አድርጐ በብርሃን መሠላል … እየተረማመደ ቀሚሷን ገፎ ጣለ … ሽቅብ አመራ … ዳገቱ ብዙም አስቸጋሪ አልነበረም … ዋናው የተራራው አናት ላይ ሲደርስ ትንፋሹ ይፋጅ ነበር … ዝቅ ሲል … የብርሃኑ መሠላል ከቦታው አልነበረም፡፡ 
የገዛ አንድ ቋሚ መሠላሉን (ካስማ) ዘረጋና የሆነ አቃፊ ሥፍራ ውስጥ በአደራ ዶለው፡፡” 
ለምንድነው እንዲህ የሚያቁነጠንጠኝ …? ምናለ ይሔን ሁሉ ነገር ከእኔ ጋር አድርጐት ቢሆን … ሰው ግን ስስታምነቱ ነው እንዴ ቀድሞ የተፈጠረለት…!? ለምንድነው በጥሩ ወንድ እና በጥሩ ምግብ እኛ ሴቶች የምንቋምጠው? … ልጅቷ የምር እያበገነችኝ ነው፡፡ እኔ ብሆን መታጠቢያ ቤት ወስጄ ለሰስ ባለ ሙቅ ውኃ አብረን ከታጠብን በኋላ ፍቅር እየዘመርኩለት፣ ሳቅ እንደ አበባ እየበተንኩለት … ቀኝ እጁን እንደ ሙሽራ እየጐተትኩ … መኝታ ቤት ወስጄ … ወይኔ…!
“ሁለቱም ጭድ እንደሌለው የጭቃ ቤት በርጥበት ተፈነጋገሉ … እሱ ግራ እጁን አንተርሷታል … እሷ ጀርባዋን ሰጥታው … ግድግዳው ላይ አፍጥጣለች …” ፈጣጣ…! ምናባቷ ዞራ ጥምጥም አርጋ አታቅፈውም! “ግራ እጁ ላይ ደሙ የረጋ መሠለው … የመደንዘዝ ሥሜት ወረረው…” እኔን ይደንዝዘኝ! “በከፊል የተራቆተ ገላዋን በጥለት ባጌጠ የአልጋ ልብስ ሸፈነላት፡፡ ራቁት ማየት አይወድም… ጀርባዋን ስለሠጠችው ሌላ አላሠበም … እንዳይበርዳትና እንዳትራቆት ተጨንቋል …”
የምር ደም የምታፈላ ሴት ናት! ከየት አባቷ የመጣች ፋራ ናት በጌታ … ቱ…!፡፡ አራት ገፅ ቀርቶኛል … ከአራቱ ግማሹን አውቀዋለሁ … መጨረሻውን እያወቅነው እንዳላወቅን መሆን አይደል ህይወት … ፍርድ አወቅን ማግኘት አማረኝ … አማረኝ ብቻም ሳይሆን ሰውነቴ በሙሉ በመፈለግ ሞረድ ተሞርዶ ስል ሆኗል፡፡ …
***
“የጠበቅሁትን ባላገኝ ግድ አይሠጠኝም … ለራሴ ታማኝ ነኝ…” 
“እኔ እኮ በቁንጅናም በስርዓትም እበልጣታለሁ…” 
“ያላት ይበቃኛል!” 
“ከሷ በላይ እወድኃለሁ!”
“የሷን ያህል አላፈቅርሽም!”
“ወደኸኛል ማለት ነው?”
“ሰው ጠልቼ አላውቅም”
“እኔ ራሴን ችዬ የምኖር ሰው ነኝ፡፡ ለሠጡኝ መመለስ አያቅተኝም …” 
“እሷ በእኔ የመፈለግ ከረጢት ውስጥ የታሠረች ውዴ ናት …”
አይን አይኑን እያየሁ ይበልጥ ወደድኩት … ሳላስበው እንባዬ ሊያመልጠኝ ነበር … ታገልኩ … ጥርሴን ነከስኩ … በሠፊው ወደ ውስጤ ትንፋሽ ሳብኩ …
“በጊዜ ስለምትመጣ በር ከፍቼ ልጠብቃት…” 
“እኔ ሐሳቤን መች ጨረስኩልህ…?” መለማመጥ እንዳይመስልብኝ ፈርቻለሁ … እርግጥ ሐሳብን መናገር … ፍቅርን መግለፅ … ለትምክህተኞች ካልሆነ በቀር … መለማመጥ አይደለም፡፡ 
“ልንጠቅህ አልኩ እንዴ…?”
“እኔ አልቆብኛል…!” የሆነ ነገር ከእኔ እየጠበቀ ነው፡፡ 
“ስሟን አልነገርከኝም…?” 
“ልቤ ያውቃታል፡፡” ሳቅሁ … ሙሉነቱ ይመስጣል … እየኮራ እንዳልሆነ አውቃለሁ … ቢኮራም ደግሞ መብቱ ነው!፡፡
“የምሬን ነው … ስሟን አ.ል.ነ.ገ.ር.ከኝ.ም…” ሳይገረም አይቀርም፡፡ 
“ስምረት” 
ምን ማለት ነው…? ለራሴ የጠየኩት ጥያቄ … ምንም የሠመረ ነገር አይታይባትም … መልኳም መልክ የለውም … ፀባይዋም እንደተናቆረ ህዝብና መንግስት ያኮረፈ ነው፡፡ ያስታውቅብኛል … ድብን አድርጌ ቀንቻለሁ፡፡ 
“ያንቺን አልነገርሽኝም…” አቤት እንዴት ደስ እንዳለኝ … 
“ሶስና …” ፊቱ ላይ ደስ የሚል ፈገግታ ተስሏል … እሚያምረው መልኩ፣ ሲስቅ የሚረጨው ብርሃን በቀስታ ደመና የተለጠፈ ነው … ታድሎ … ባነንኩ፣ ቤት ነኝ … “ያላለቀው ዳንቴል”ን አርቄ አስቀምጬዋለሁ … 
የምር ፍቅር ይዞኛል… ውድድድድድ አድርጌዋለሁ … እንዲህ እስክነሆልል ድረስ… ዋልጌ የሚለኝ አይጠፋም… ማን በመታመን እና በቅንንት የታሸን ወንድ ይጠላል… ጅል ሴት ካልሆነች በስተቀር እሚወደድን መውደድ ነው፡፡ ማን ጐንበስ ብሎ ቀና የሚያደርግን ያጥላላል…? ማንም! ጥሩውን መጥፎ የምናደርገው ራሳችን ነን፡፡ 
የእኔ የዘቀጠ አስተሳሰብ ጥሩውን ካዛባ ይለውሰዋል … ወይ መተላለፍ…!
ለምንድን ነው ፍርድ አወቅን የወደድኩት…? ብዙ መሳጭ ታሪክ አለው … ወድቆ ሰው እንዲወድቅ አይጥርም… በጠንካራው ስብዕናዬ… ገርበብ ብሎ በተከፈተው ልቤ ሠተት ብሎ ገብቷል፤ ባፈቀራት ሴት ገላ ውስጥ እኔ ተኛሁለት፡፡ 
ወይ “ያላለቀው ዳንቴል…”!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.