ክረምት መግባቱን ተከትሎ ሀይለኛ ጉንፋን ይዞኛል፣ ሌሎች የቤተሰብ አባላቶቼን ወዲያው ሲተዋቸው እኔን ግን አሁንም ድረስ አፍንጫዬን እንደዘጋኝ አልፎ አልፎም ከባድ የአፍንጫና የጉሮሮ ፈሳሽ ያከታትልብኛል፡፡ ምን ባደረገው ሊተወኝ ይችላል? እባካችሁን መላ በሉኝ፡፡
ዓለም ተስፋ

ውድ ዓለም፡- ጉንፋን ሲያጓድዱት በሽታ ይሆናል- ባያጓድዱትስ? ለነገሩ የት ሊደርስ! ይሁን እንጂ ተጠቂ ለሆነ ግለሰብ የበሽታ ትንሽ የለውም፡፡ ያልተነካ ግልግል ያውቃል እንደሚባለው ላልተነካ ሰው ጉንፋን እንደበሽታ ላይቆጠር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የህመም ቀላል የለምና ጉንፋንም በቀላሉ ሊታይ አይገባም፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በመዲናችን አዲስ አበባ እየታየ ያለው ጉንፋን ከተላላፊነቱና ክብደቱ አንፃር ሲታይ ይሄ ነገር ‹‹ጉንፋን ነው ወይስ በርድ ፍሉ?›› የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ዳድቶናል፡፡ ለማንኛውም መንስኤውንና መፍትሄ ያልነውን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
ጉንፋን ተብሎ የሚጠራው በጥቅሉ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ የላይኛው የመተንፈሻ አካላችን ኢንፌክሽን ሲሆን፣ በዓለማችን በአጠቃላይ በተላላፊ ኢንፌክሽንነትና የዕለት ተዕለት ተግባራችን በብቃት እንዳንወጣ በሚፈጥረው ሳንካ፣ ቁጥር አንድ ተጠቃሽ በሽታ ሆኗል፡፡

እነዚህ ቁጥራቸው ከ200 ያላነሰ የቫይረስ አይነቶች ከብዛታቸው የተነሳ ሰውነታችን ለነዚህ የሚሆን የመከላከያ አይነት አምርቶና አዘጋጅቶ ሙሉ በሙሉ ሊቋቋም አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በዕድሜው በገፋ ቁጥር ከሞላ ጎደል በጉንፋን የመያዝ ዕድሉ እየቀነሰና በጉንፋን ሳቢያ የሚመጡትንም ስሜቶች የመቆጣጠር ሁኔታው እየጨመረ ይሄዳል፡፡


በአጠቃላይ በጉንፋን ቫይረስ ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት ስሜቱን የሚቋቋሙ ሲሆኑ 25 በመቶ ደግሞ የጉንፋን ስሜቶችና ህመሞች የሚጎሉባቸው ናቸው፡፡ በአማካኝ ቤት የሚውሉ ህፃናት ከ6-10 ጊዜ፣ በመዋዕለ ህፃናት የሚውሉ ልጆች ከ10-12 ጊዜ እንዲሁም ወጣቶችና ጎልማሶች ከ2-5 ጊዜ በዓመት የጉንፋን ተጠቂዎች ይሆናሉ፡፡

ይህ የጉንፋን ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን በዋነኛ የሚተላለፍባቸው መንገዶች፣ በጉንፋን የተያዘ ሰው ሲያወራ፣ ሲያስል፣ ወይንም ሲያስነጥስ፣ በአማካኝ ሁለት ሜትር ርቀት አካባቢ ሆነን ቫይረሱ የያዘውን አየር ወደ ውስጥ ስንስብ፣ ጉንፋን የተያዘን ሰው በእጃችን ጨብጠን ወይንም የተጠቀመበትን (በእጁ የያዘውን) ማንኛውም ዕቃ ነክተን አይናችንን አፍንጫችንን ወይንም አፋችንን የያዝን እንደሆነ ነው፡፡


ይህ ቫይረስ በአብዛኛው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው ጉንፋን በተያዘ በመጀመሪያው ከሁለት እስከ ሶስት ባሉት ቀናት ውስጥ ሲሆን በጥቅሉ ግን እስከ ሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥም ሊተላለፍ የሚችልበት አጋጣሚ አለ፡፡
ጉንፋን በአብዛኛው በክረምት (በብርድና ዝናባማ ወቅት) በዝቶ ሚታይበት ምክንያት በተለምዶ እንደሚባለው፣ ብርድ መትቶን፣ በቅዝቃዜ ወቅት ልብስ ሳንደርብ ወጥተን፣ ድራፍት መትቶን ወይንም በቅዝቃዜ በእርጥብ ፀጉር ከቤት ወጥተን ሳይሆን፣ የጉንፋ ቫይረሶች ቀዝቃዛ አየር ለመራባት አመቺ ስለሚሆንላቸውና እንዲሁም በክረምት ወቅት ከቤት ያለመውጣትና ቤት ውስጥ አብሮ የመቀመጥ ሁኔታ የጉንፋንን የመተላለፍ እድል ስለሚጨምረው ነው፡፡


በጉንፋን የመያዝ ምልክቶችስ ምን ምን ናቸው?
የጉንፋን ቫይረስ እንደ ብዛቱ ሁሉ ሰዎች ላይ የሚያስከትለው ስሜትም የተለያየ ቢሆንም፣ በላንቃችንና በጉሮሮአችን አካባቢ የመከርከር ስሜት ብሎም በሚወጡበት ጊዜ የህመም ስሜት መሰማት፣ የአፍንጫችን መደፈንና ከአፍንጫ የሚወጣው ቀጭንም ሆነ ወፍራም ፈሳሽ መብዛት፣ ማስነጠስ፣ ማሳል፣ የራስ ህመም መሰማት፣ በትንሹ የትኩሳት ስሜት መሰማት፣ ድካም ድካም ማለት፣ ቁርጥማት መሰማት፣ እንዲሁም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ከሞላ ጎደል ይጠቀሳሉ፡፡ አንድ ሰው በጉንፋን ቫይረስ ከተያዘ በኋላ ከሁለት እስከ ሶስት ቀናቶች ባሉት ጊዜ ውስጥ የጉንፋን ስሜት ሊጀምረው ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው የጉንፋን ስሜት ያለው ሰው በአማካኝ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሊሻለው ቢችልም እስከ ሶስት ሳምንታት ያክል የሚቆይበት አጋጣሚ አለ፡፡


በጉንፋን ላለመያዝ የመከላከል እርምጃ
በጉንፋን ከተያዘ ሰው በተቻለ መጠን መራቅ፣ እጅ አለመጨበጥ፣ ምክንያቱም ጉንፋን የተያዙ ሰዎችን መጨበጥ በጉንፋን የመያዝ ዕድልን በ70 በመቶ ስለሚጨምር ነው፡፡
ነገር ግን ጉንፋን የተያዘን ሰው ከጨበጡ ወይንም የነካውን ዕቃ ከያዙ በቶሎ ከ15 ሰከንድ ባላነሰ ጊዜ ውስጥ እጅዎን በውሃና በሳሙና መታጠብ ይኖርበታል፡፡ በህዝብ አገልግሎት መስጫዎች ወይንም ጉንፋን የያዘው ሰው ባለበት አካባቢ ለዕጅ ማድረቂያ ከፎጣ ይልቅ ሶፍት መጠቀም ጥሩ ነው፡፡


ጉንፋን የያዘው ሰው የተጠቀመበትን ብርጭቆ ወይንም የመመገቢያ ማንኪያና ሹካ አለመጠቀምና ጤነኛ አመጋገብና የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ የሰውነትን ህመም መከላከያ አቅም መገንባት ትልቅ የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡


በተጨማሪም እርስዎ ጉንፋን በሚይዝዎት ጊዜ በተቻለ መጠን ቤት መቀመጥና ወደ ሰው ላለማስተላለፍ መጠንቀቅ፣ የሚጠቀሙበትን ሶፍት ቶሎ ቶሎ (ወዲያው ወዲያው) ማስወገድና በተገቢው ቦታ መጣል፣ እንዲሁም በመሀረብ ከመጠቀም ይልቅ በተቀያሪ ሶፍት መጠቀም፡፡


በሚስሉበት ወይንም በሚያስነጥሱበት ወቅት እጅዎን በአፍዎና በአፍንጫዎ ላይ መሸፈንና እጅን ተጠንቅቆ መታጠብ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡


ከዚህ ሁሉ በፊት ጉንፋን ቢይዝዎትስ?
ጉንፋን በእርግጥ መድሃኒት የሌለውና በሂደትም በራሱ የሚጠፋ ወይም የሚድን ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ሰው በጉንፋን ከተያዘ በኋላ ስሜቶቹን ለማቅለል የህመሙን የቆይታ ጊዜ ለማሳጠርና እንግልቱን ለመቀነስ የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወን ይችላል፡፡


– ውሃና ሌሎች ፈሳሾችን በብዛት መውሰድ ከሰውነታችን በአፍንጫ ፈሳሽና በላብ መልክ የሚወጣውን ፈሳሽ በመተካት የሰውነታችንን የውሃ ድርቀት ከመከላከሉም በላይ፣ ለአፍንጫችን መደፈንና ለሚከተለው የራስ ህመም ምክንያት የሆነውን ወፍራም ፈሳሽ በማቅጠን ስሜቶቹን ይገታል፡፡ ጉሮሮን ለብ ባለ ውሃና ጨው በመጉመጥመጥ የጉሮሮ መከርከርንና ተጓዳኝ ስሜቶች መቀነስ፣ ውሃ አፍልተን እንፋሎቱን በመታጠን የመተንፈሻ አካላችን እንዳይደርቅ መከላከል፡፡ ውሃ መታጠን ወይም እንደ ‹‹ስቲም ባዝ›› መጠቀምም በድርቀት ሳቢያ ለሚመጡ ስሜቶች መፍትሄ ከመሆንም አልፎ ለቫይረሱ መራቢያ ምቹ የሆነውን የደረቅ አየር ሁኔታ ይቀይራል፡፡


ሰውነታችንን በማሳረፍ የሰውነታችንን የመከላከያ ብቃት መገንባትና ማር በመብላት ለሰውነታችን ኃይል መስጠት፣ እንደ ብርቱካንና ሎሚ የመሳሰሉትን የቫይታሚን ሲ ምንጮችን በመውሰድ ሰውነታችን ትግሉን እንዲያበረታ ማገዝ፣ ከዶሮ የተሰራ ሾርባ መጠጣት የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ብቃት ሊያጎለብት በተጨማሪም ትኩስ፣ ኃይል ሰጪና፣ ፈሳሽ እንደመሆኑ መጠን ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት ያከናውናል፡፡ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን በአማራጭነት መጠቀምዎም እንደ ራስ ምታትና መሰል የሰውነት ህመሞችን ይገታሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ግን ስሜቱ የበረታ እንደሆነና ጊዜው የረዘመ ከሆነ፣ የትንፋሽ ማጠርና የደረት ውጋት ከጀመረ፣ የአክታ መብዛት፣ ሀይለኛ ትኩሳት፣ ማስመለስ፣ እንዲሁም የጉሮሮ ህመም በርትቶ አላስውጥ ያለ እንደሆነ ወደ ሐኪምዎ በመሄድ መፍትሄ ማግኘት እንደልብዎ አይዘንጉ፡፡


ውድ አንባብያን ዓለም ላይ የተጠቀሱትን መፍትሄ ያልናቸውን መንገዶች በመጠቀም ችግር ለመቅረፍ መሞከር መልካም ነው፡፡ እናም በሂደት ያለውን ለውጥ ማየት ነው፡፡ ሁኔታው በዛው ከቀጠለ ግን ሌላም ተያያዥ ችግር ሊኖር ስለሚችል ወደ ሐኪም መሄድ ያዋጣል ነው የእኛ ምክር፡፡ ሰላምና ጤና ለሁላችን ይሁን፡

Source- Zehabesha.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.