S-legsእኔ ባለትዳርና የልጆች አባት ነኝ፡፡ የምወዳትና የምትወደኝ ባለቤትም አለኝ፡፡ ከባለቤቴ ጋር ከጅምሩ አንስቶ የሞቀ ፍቅር ውስጥ ሆነን ቆይተን ልጆችም ወልደን በደስታ ኖረናል፡፡ በቅርርባችን ውስጥ ችግር አልነበረም፡፡ የወሲብ ህይወታችንም ግሩም ነበር፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ተለውጦ የወሲብ ህይወታችን በጣም ተቀዛቅዟል፡፡ እኔ ወሲብ ለመፈፀም ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረኝም በእርሷ በኩል ግን ከፍተኛ መቀዛቀዝ ይታያል፡፡ ስለ ሁኔታው ለመወያየትም ፍቃደኝነት አይታይባትም፡፡ እኔ በዚህ የጉልምስና ዕድሜዬ ሌላ ሴት ጋር ለወሲብ ብዬ መሄድን ጭንቅላቴም አይፈቅደውም፡፡ እንደ አንድ የትዳር ቅመም ወሲብ አስፈላጊ እንደመሆኑ የዚህ መጉደል ትዳራችንን አደጋ ላይ እንዳይጥለው እየፈራሁ ነው፡፡ ምን ትመክሩኛላችሁ? መልሳችሁን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡

ወንድማችሁ ቢ ነኝ   ውድ ቢ ጥያቄህ በአብዛኛው ባለትዳሮች ዘንድ የሚከሰት በመሆኑ ጉዳይህን እንደ ጉዳያችን አድርገን ችግርህን ልንጋራና መፍትሄ ልናበጅለት ቅድሚያ ሰጥተነዋል፡፡

ባለትዳሮች ከሁለት የተለያየ ቤተሰብ የኑሮ ሁኔታ፣ ባህልና ማህበራዊ ዳራ በመምጣት በጋብቻ አንድ መሆናቸው የችግራቸው አይነት ይብዛም ይነስም በጋብቻ ውስጥ ግጭትና አለመግባባት መፈጠሩ በብዛት የተለመደ ነገር ነው፡፡ ከዚህ ላይ ልናጤነው የሚገባው ለምን ተፈጠረ ሳይሆን የተከሰተውን ችግር እንዴት ልንወጣው እንደምንችል በግልፅ መነጋገሩና ስምምነት ላይ መድረሱ ትዳርን በጠንካራ አለት ላይ እንድንገባ ያስችለናል፡፡
ምንም እንኳ ጥያቄህ ያተኮረው በባለቤትህ ላይ በተከሰተው ለአነስተኛ የወሲብ ፍላጎት መፍትሄ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ቢሆንም ለአንተና መሰል ችግር ለገጠማቸው ጥንዶች መንስኤዎቹን መመልከቱ ተገቢ ነው ብለን ስላሰብን በቅድሚያ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

አነስተኛ የወሲብ ፍላጎት ምንድን ነው? እንዴትስ ይከሰታል?

የወሲብ ፍላጎት ማነስ በህክምናው ቋንቋ (Hypoactive sexual desire disorder) የሚባለው ለወሲብ ግንኙነት ፍላጎት ማጣትን ሲያመለክት በተለያየ ዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ በአብዛኛው ሰዎች ዘንድ የሚገጥም የወሲብ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በአካላዊና አዕምሮአዊ ተፅዕኖዎች ስለሚከሰት በቀላሉ መድሃኒት በመዋጥ ብቻ ሊስተካከል እንደማይችል የተለያዩ ጠበብት ይናገራሉ፡፡ የሚከተሉትንም ነጥቦች ለችግሩ መከሰት እንደምክንያት ያስቀምጣሉ፡፡

1. ማረጥ (Menopause):- ይህ የእድሜ ወቅት ሴቶች በአብዛኛው የወር አበባ ማየት የሚያቆሙበት በመሆኑ በወሲብ ፍላጎታቸው ላይ በተለያየ መንገድ ተፅዕኖ ያመጣባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ሴቷ እድሜዋ እየገፋ በመጣ ቁጥር ለወሲብ ለመነቃቃትና ስሜት ውስጥ ቶሎ ለመግባት ረጅም ጊዜ ይወስድበታል፡፡ በዚህ ጊዜ የሴቷ እንቁላሎች Estrogen የተባለ ሆርሞን ማመንጨት ስለሚያቆሙ በብልቷ አካባቢ ድርቀትን በማስከተል ወሲብን በቀላሉ እንዳይመች ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ሆርሞን እጥረት መኖር የብልቷ ግድግዳዎች ስስ እንዲሆን ስለሚያደርግ በግንኙነት ወቅትና ከዛም በኋላ እንዲቆስል ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን ዕድሜ ሁል ጊዜ እየጨመረ ስለሄደ ፍላጎት ይቀንሳል ማለት እንዳልሆን ልናጤነው ይገባል፡፡

2. እርግዝና፡- ሴቶች በእርግዝና ወቅት በሰውነታቸው ላይ የሆርሞን (hormone) ለውጥ ስለሚታይ በወሲብ ህይወታቸው ላይ መጠነኛ ተፅዕኖ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ይህ ነገር በአብዛኛው የሚከሰተው በመጀመሪያዎቹ 3 ወራትና በመጨረሻዎቹ የእርግዝና ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ይህ ክስተት ከሰው ሰው ስለሚለያይ እንደ ዋና ምክንያት አድርገን ልንወስድ አንችልም፡፡ ነገር ግን ሴቶች በወሊድ ጊዜ ከምጥ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ጭንቀትና ስቃይ እንዲሁም ከላይ እንደጠቀስነው የሚከሰተው የሆርሞን ደረጃ መዛባት የወሲብ ፍላጎታቸው እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉትም በማህፀናቸው ላለ ህፃን ጽንስም በማሰብ ይጎዳል ብለው በመፍራት ወሲብ ማድረግን የሚፈሩ አሉ፡፡

3. በግንኙነት ወቅት ያለ የብልት ህመም፡-
ሴቶች በግንኙነት ወቅት ህመም የሚሰማቸው/የሚያማቸው ከሆነ ለወሲብ ያላቸው ስሜት በጣም የቀዘቀዘ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የestrogen እጥረት መኖር በብልቷ አካባቢ ድርቀትን ሲያስከትል፣ በአንድ ወቅት ደግሞ በነበረ የመደፈር/ ወሲባዊ ጥቃት አጋጣሚ የታችኛው ብልት ጡንቻዎች ስብስብ (contract) በማለት ህመምን ይፈጥራሉ፤ አንዳንድ ጊዜ እንደውም የወንዱ ብልት ገና ወደ ውስጥ መግባት ሲጀምር ከፍተኛ ህመም ስለሚሰማቸውና ብልታቸውን ስለሚቆጠቁጣቸው ወሲብ ማሰብ እንዳይችሉ ይሆናሉ፡፡

4. ህመም/በሽታ (Illness)፡- በተከታታይ ህመም/በሽታ የሚበዛበት ማንኛውም ሰው ለወሲብ ያለው ፍላጎቱ ይቀንሳል፡፡ ወሲብን ለማሰብ እንኳን የሚቸገርበት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ይሁንና በበርካታ አጋጣሚዎች ከበሽታው ይልቅ በሽታውን ለማዳን የምንወስዳቸው መድሃኒቶች ለወሲብ ያላቸውን ፍላጎት እንዲቀንሱ ያደርጋሉ፡፡
ለምሳሌ አርትራይስ (Arthritis) ያለባቸው ሰዎች በመገጣጠሚያቸው አካባቢ ህመምና እብጠት ስለሚያጋጥማቸው መንቀሳቀስና ወሲብ ማድረግ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ የዚህ ህመም አይነቶች ሴቶች በብልታቸው አካባቢ እርጥበት እንዳይኖራቸው ስለሚያደርግ በግንኙነት ወቅት እርካታን ያሳጣቸዋል፣ ከፍተኛ ህመምም እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ የኩላሊትም በሽታ ያለባት ሴት ለተለያዩ የብልት ቁስለቶች ስለምትጋለጥ በግንኙነት ወቅት ለከፍተኛ የህመም ችግር ያጋልጣል፡፡

5. የስነ ልቦና ችግር፡- ጭንቀት፣ ፍርሃት፣ መረበሽና ድብርት የአንድን ሰው የወሲብ ፍላጎት ከሚቀንሱ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ያለመረጋጋት ሁኔታ፣ የኑሮ ውድነት፣ ከቤተሰብ ጋር መልካም ያልሆነ ግንኙነት፣ ባለቤትን በወሲብ ወቅት ለማርካት እንዲሁም ከአሁን በፊት ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባት ከሆነ እንድትፈራና ወንድን እንዳታምን ስለሚያደርግ በስተመጨረሻ ወሲብን ከአዕምሯቸው ውስጥ ለማስወገድ ይጥራሉ፡፡

6. ግልፅ ያለመሆን፡- ምንም እንኳን የተለያዩ ምክንያቶች ለወሲብ ያለንን ፍላጎት የሚቀንሱ መሆናቸውን ከላይ ብናይም በባለትዳሮች መካከል ያለ ግልፅነት የጎደለው ግንኙነት ለችግሩ ቁንጮ የሆነውን ቦታ ይይዛል፡፡ ይህ ችግር በአልጋ ውስጥም ሆነ ከአልጋ ውጭ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ባሏ በቀን ተቀን ህይወቷ ለሚያስጨንቃት ለምትወደውና ለምትጠላው ነገር ትኩረት የሚሰጥ (responsive) ካልሆነ ይህ ችግር ወደ አልጋ ላይ ሊሻገር ይችላል፡፡ ብዙ ሴቶቻችን ደግሞ ስለወሲብ ህይወታቸውና ፍላጎታቸው በግልፅ የማውራት ችግርና ሀፍረት ስላለባቸው ይህንንም ማጤኑ ተገቢ ይመስለናል፡፡

ውድ ጠያቂያችን ከላይ የጠቀስናቸውን መንስኤዎች በደንብ ከተረዳህ መፍትሄው ብዙ የሚያዳግትህ አይመስለንም፡፡ በቅድሚያ ግን እነዚህን ጥያቄዎች ለሁለታችሁም ማንሳት ተገቢ ነው እንላለን፡፡
– ሁል ጊዜ ወደ ቤት ስትገቡ ይደክማችኋል?
– ወሲብ ማድረግ ስታስቡ የንዴትና ጥፋተኝነት ስሜት ይሰማችኋል?
– በቅርብ ወይም ባለፉት ዓመታት አስጨናቂ ህይወት አሳልፋችኋል? ለምሳሌ፤ ስራ ማጣት፣ የገንዘብ ችግር፣ ቦታ የመቀየር፣ ያለዕቅድ ልጅ የመውለድ፣ የምትወዱትን የማጣት?
– ፀጥታ የሰፈነበት የሚረብሽና አመቺ የሆነ ወሲብ የምታደርጉበት ቦታ የላችሁም?
– በአንተና በባለቤትህ መካከል ጤናማ የሆነ የግንኙነት ችግር አለን?
ከነዚህ ጥያቄዎች መካከል አንዱን ወይም ሌላውን አዎ ካሉ ለወሲብ ፍላጎትዎ መቀነስ ምክንያት ስለሚሆኑ ነገሮችን እንደገና በማጤን በቀላሉ ከትዳር አጋርዎ ጋር ግልፅ በሆነ ውይይት በመነጋገርና አስፈላጊውን ምክር ደግሞ ከዚህ በታች ከጠቀስኳቸው ባለሙያዎች በማግኘት ችግሩን በማስተካከል መፍታት ይቻላል፡፡

ምን አይነት መፍትሄዎች ይኖራሉ?
ችግርዎን ለመፍታት የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን የሚገባው ሐኪም ማማከር ነው፡፡ ይህም ችግር ከህክምና ጋር መሆኑንና አለመሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡ ድርቀት የሆርሞን መዛባትና የቫይታሚን እጥረት ከተለያዩ የህክምና ችግሮች ስለሚፈጠሩ መፍትሄያቸውን ለማግኘት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ የህክምና ችግር ካልሆነ ደግሞ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን ለምሳሌ፣ ሳይካትሪስት፣ ሳይኮሎጂስት፣ ሶሻል ወርከር፣ የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪዎችን መጎብኘት ብልህነት መሆኑን እንገልፃለን፡፡
ስለዚህ መንስኤዎቹን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚከተሉትን ነጥቦች በህይወታችሁ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ብትለማመዱ ችግራችሁን መቅረፍ ትችላላችሁ እንላለን፡፡

1. ከባለቤትዎ ጋር በግልፅ ስለ ወሲባዊ ህይወትዎ ይነጋገሩ፣ ሲወያዩም ለችግሩ መነሻ ምክንያቶች ናቸው የሚሏቸውን ስሜቶች ለምሳሌ ጥፋት፣ ፍርሃት፣ ህመም፣ ማጣትን ይለዩአቸው፣ ማስተካከያም ሳይዘገዩ ያድርጉባቸው፡፡ ለትዳር አጋርዎም እንዴት ትኩረት መስጠት እንደሚገባዎም ይማሩ፡፡ ልክ እንደማንኛውም ሌላ ችግር በግልፅ ተወያዩባቸው፡፡

2. ሚስት ጊዜ ወስዳ የሰውነት አካላቶችዎን የትኛው ክፍል በእውነት ስሜቷን እንደሚያነሳሳት ትወቅ፡፡ ይህን አንዴ ካወቀች በኋላ ባሏን የትኛውን የአካል ክፍሏን ሲነካ ሊያስደስታት እንደሚችል ልትመራውና ልትነግረው ይገባታል፡፡

3. ከማረጥ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው የብልት ውስጥ ፈሳሽ መድረቅና ለቁስል መዳረግ የተለያዩ ማርጠቢያ ቅባቶች (Lubricants) ለምሳሌ K-Y Jelly or Replents, Estrogen, Ogen (estron), Estrace (Estradio) የተሰኙ ክሬሞች ሐኪም አማክረው በመጠቀም ሴቶችን ብልት ግድግዳዎች መገንባትና እርጥበትን ማሻሻል ስለሚቻል ወሲብን የበለጠ ምቹ ማድረግ ይቻላል፡፡

4. ባል ለሚስቱ ሚስትም ለባሏ ፍፁም ግልፅ ይሁኑ፡፡ አዳምና ሔዋን እራቁታቸውን እንደነበሩ አንዱ ለሌላው እንዲሁ ይሁን፡፡ ስለዚህም የትዳር አጋርህ እንድትናገር ለማደፋፈር ከፈለግህ አንተም ደግሞ ተናጋሪ ብቻ ሳትሆን ጥሩ አድማጭም ሁን፡፡

5. መልካምን ነገር እናስብ፡- ስለ ትዳር አጋራችን መልካም የሆኑ ነገሮችን ማሰብና አንዳችን ስለሌላኛው ምን ምን እንደምንወድላት/ለት በድፍረት መነጋገር ተገቢ መሆኑን ማወቅ፡፡ ማንኛውንም ሰው ቢሆን ምስጋናን መስማት ይወዳልና ለሚደረግልን ሁሉ ብናመሰግን ግንኙነታችንን ስለሚያዳብር በህይወታችን ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ችግሮቻችንን ከሚቀርፉልን መንገዶች ዋናዎቹ ሊሆኑልን ይችላሉ፡፡

ዶ/ር ማይልስ (Dr.Myles Munroe) “The purpose and power of Love Marriage” በተሰኘ መፅሐፋቸው የወሲብ ፍላጎት ከእግዚአብሔር ተሰጠ (God given) በትክክለኛ ጊዜና ቦታ ደግሞ መልካም እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በተለያዩ ሌሎች መንፈሳዊ መፅሐፍትም ባል ለሚስቱ የሚገባትን እንዲያደርግ እንዲሁ ደግሞ ሚስት ለባሏ ማድረግ የሚገባትን እንድትፈፅም ከመግለፃቸው ባሻገር ለፀሎት ይተጉ ዘንድ ተስማምተው ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር እርስ በርሳቸው እንዳይከላከሉ ያዛል፡፡ ስለዚህ በጥያቄህ ላይ በግልፅ እንዳስቀመጥከው በትዳር ውስጥ ወሲብ መፈለግህ በምድርም በሰማይም ስለሚፈቅድልህ ሁለታችሁም ይህን በመተግበር ደስተኛ የወሲብ ህይወት ማግኘት ትችላለሁ፡፡

እንግዲህ ወንድማችን የተለያዩ መፃህፍት፣ ምሁራን እኛም የዚህ አምድ አዘጋጆች ከላይ የመከርነውን ነጥቦች ተግባራዊ ብታደርጉ ችግራችሁ ይቀረፋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተረፈ ሁሉን የሚችለው አምላክ ይርዳህ! ቸር እንሰንብት፡፡

Soure- zehabesha.com

 

 

Leave a Reply to Anonymous Cancel reply

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.